ዘመነ ክረምት – ክፍል አምስት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ነሐሴ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል አራት ዝግጅታችን ከነሐሴ ፲ እስከ ፳፯ ቀን (ከማኅበር እስከ አብርሃም) ድረስ ያለው ሦስተኛው የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ (ንዑስ ክፍል) ‹ዕጕለ ቋዓት፣ ደሰያት፣ ዓይነ ኵሉ› እንደሚባል፤ ይኸውም የሰው ልጅ ብቻ ሳይኾን የሰማይ አዕዋፍ፣ የምድር አራዊትና እንስሳትም ጭምር እግዚአብሔርን አምነው በተስፋ መኖራቸው የሚዘከርበት፣ ደሴቶች በልምላሜ ማሸብረቃቸው የሚነገርበት ክፍለ ክረምት እንደ ኾነ፤ በቤተ ክርስቲያን የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔርም በእነዚህ ምሥጢራት ላይ እንደሚያተኩር አስታውሰን፣ በተለይ ዕጕለ ቋዓትን መነሻ አድርገን ወቅቱን የሚመለከት ትምህርት አቅርበን ነበር፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ደግሞ ባለፈ ካረፍንበት እንቀጥላለን፡፡ መልካም ንባብ! 

ደሰያት

በውኃ የተከበበ የብስ መሬት ‹ደሴት› ይባላል፤ ‹ደሰያት› ደግሞ ብዙ ቍጥርን አመላካች ቃል ነው፡፡ በዚህ ወቅት ስለ ደሴቶች በስፋት ይነገራል፡፡ ወቅቱ በድርቅ ብዛት የተጎዱ ደሴቶች በውኃ ብዛት የሚለመልሙበት፤ በውስጣቸው የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ሳይኾኑ እንስሳትም አዕዋፍም ጭምር በሚበቅለው እኽልና በሚያገኙት ምግብ የሚደሰቱበት ጊዜ ነው፡፡ ደሴቶች በውኃ የተከበቡ የመሬት ክፍሎች እንደ መኾናቸው በዚህ ወቅት በልምላሜ ቢያጌጡም በማዕበልና በሞገድ መቸገራቸውም አይቀርም፡፡ ይህም የቤተ ክርስቲያን (የምእመናን ሕይወት) እና የዓለም ምሳሌ ነው፡፡ ደሴቶች በውኃ መከበባቸው ቤተ ክርስቲያን (የምእመናን ሕይወት) በክርስቶስ ደም የተመሠረተች፤ በቃለ እግዚአብሔር የታነጸች ለመኾኗ፤ ደሴቶች በማዕበልና በሞገድ መናወጣቸው ደግሞ በዓለም ውስጥ የሚከሠቱ ረኃብ፣ ጥላቻ፣ ጦርነት፣ ወዘተ የመሳሰሉ ችግሮች፤ በተለይ ሰይጣን የሚያመጣቸው ልዩ ልዩ ኅብረ ኃጢአት (የኀጢአት ዓይነቶች) የቤተ ክርስቲያንን (የምእመናንን) ህልውና የሚፈታተኑ መሰናክሎች መኾናቸውን ያጠይቃል፡፡

ይህቺ ዓለም፣ በውኃ የምትመሰል፣ ሞገድና ማዕበል የበዛባት ሥፍራ ናት፤ የክርስትና ሕይወት ደግሞ በውኃ የተከበበ መሬት፡፡ ውኃ በሞገድ፣ በማዕበል እንደሚናወጥ ዅሉ፣ ዓለምም በተፈጥሮም ይኹን በሰው ስሕተት በሚመጣ ኑፋቄ፣ ክህደት፣ መከራ፣ ችግር፣ ረኃብ፣ ጦርነት ትናወጣለች፤ ትንገላታለች፤ ትሰቃያለች፤ ትፈተናለች፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ እየተፈጸመ ያለው ሰይጣናዊ ድርጊት ዅሉ ለዚህ ማስረጃ ነው፡፡ ዓለም ፈተና ላይ ናት፡፡ አልጠግብ ባይነት፣ ትምክህተኝነት፣ እኔ እበልጥ ባይነት፣ ፍቅር አልባነት (ጥላቻ)፣ ትዕቢት፣ ክህደት፣ ጥርጥር፣ ወዘተ የመሳሰሉ ችግሮች በነዋሪዎቿ ዘንድ እየተስፋፉ በመምጣታቸው ዓለም በፈተና ሞገድ እየተናወጠች ነው፡፡ እርሱ በቸርነቱ ሞገዱና ማዕበሉ ጸጥ እንዲል ካላደረገ የሰው ጥበብና ጥረት ብቻ ከዚህ ፈተና ዓለምን ሊያወጣት አይችልም፡፡ በውኃ የተከበበ መሬት ሞገድ፣ ማዕበልና ስጥመት እንደሚያጋጥመው ዅሉ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም (የክርስትና ሕይወትም) በልዩ ልዩ መከራና ፈተና የታጀበ ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያኖች የምንኖረው ፈተና በሚያናውጣት ዓለም ወይም ውጣ ውረድ በበዛባት ምድር ላይ ነውና፡፡ ይኸውም ኀጢአት፣ ስደት፣ ኀዘን፣ ረኃብ፣ በሽታ፣ ጦርነት፣ ወዘተ. የመሳሰሉትን ምድራዊ ችግሮች ዅሉ ያካትታል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹እንዲህም ያለ መከራ በዓለም ባሉ ወንድሞቻችሁ ዅሉ እንደሚፈጸም ዕወቁ›› በማለት እንዳስተማረው (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፱) በመላው ዓለም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ዛሬ በመከራ ውስጥ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል የዓለም የኑሮ ሸክም ከብዷቸው ይሰቃያሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአሕዛብና በአረማውያን ዛቻና ማስፈራሪያ ይጨነቃሉ፡፡ የክርስትና ትርጕም የገባቸውም በፈቃዳቸው በሰማዕትነት ይሞታሉ፡፡ ይህን ዅሉ ፈተና ተቋቁሞ በክርስትና ሃይማኖት ጸንቶ፣ በምግባር በርትቶ፣ በጸሎት ተግቶ የሚኖር ምእመን እርሱ ብፁዕ ነው፡፡ በሰማያዊው የእግዚአብሔር መንግሥት ለጻድቃን የተዘጋጀውን ሰላማዊና ዘለዓለማዊ ማረፊያ ይወርሳልና፡፡ እንግዲህ እኛም ሞገዱና ማዕበሉ ማለትም ምድራዊ ውጣ ውረዱና ፈተናው ቢያንገላታንም በዚህ ዓለም የሚጎድልብንን ሥጋዊው ጥቅምና የሚደርስብንን ጊዜያዊ መከራ ሳይኾን በእውነተኛው አገራችን በሰማይ የምንወርሰውን ዘለዓለማዊ መንግሥት ተስፋ በማድረግ ዅሉንም በጸጋ እንቀበል፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም ሃይማኖታችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ከልዩ ልዩ ፈተና ይጠብቅልን ዘንድም በፍጹም ሃይማኖት ኾነን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹ከስጥመት አድነን?›› እያልን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው፡፡ እርሱ በባሕር፣ በሞገድ፣ በማዕበልና በነፋስ የሚመሰለውን የዓለምን ውጣ ውረድና መከራ መገሠፅ፤ ሁከቱንም ጸጥ ማድረግ የሚቻለው አምላክ ነውና (ማቴ. ፰፥፳፫-፳፯)፡፡ ከዓቅማችን በላይ የኾነ ችግር ሲያጋጥመን ደግሞ የሚያስጨንቀንን ጉዳይ ዅሉ ለእርሱ ለፈጣሪያችን እንስጠው፡፡ ይህን ለመወሰን እንዲቻለንም የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይለ ቃል እናስተውል፤ ‹‹እንግዲህ በጐበኛችሁ ጊዜ ከፍ ከፍ ያደርጋችሁ ዘንድ ከጸናችው ከእግዚአብሔር ክንድ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፡፡ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ዅሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፡፡ እንግዲህ ዐዋቂዎች ኹኑ፤ ትጉም፡፡ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ፣ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፡፡ እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፤ እንዲህም ያለ መከራ በዓለም ባሉ ወንድሞቻችሁ ዅሉ እንደሚፈጸም ዕወቁ፡፡ ፍቅርንም አጽንታችሁ ያዙአት፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ዅሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ልባሞችም ያደርጋችኋል፤›› (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፮-፲)፡፡

ዓይነ ኵሉ

‹ዓይነ ኵሉ› ትርጕሙ በግእዝ ቋንቋ ‹የዅሉም ዓይን› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ያለፈው (በበጋ የነበረው) እኽል ከሪቅ፣ ከጎተራ ያለቀበት፤ የተዘራውም ያላፈራበት ገና የተክል ጊዜ ነው፡፡ ፍጥረታት በሙሉ የፍሬውን ሰዓት በተስፋ የሚጠባበቁበት ክፍለ ክረምት ስለ ኾነ ወቅቱ ‹ዓይነ ኵሉ› ተብሏል፡፡ ይኸውም ፍጥረታት ዅሉ ወደ ፈጣሪያቸው ወደ እግዚአብሔር በማንጋጠጥ የዕለት ጕርስ፣ የዓመት ልብስ እንዳይከለክላቸው እንደሚማጸኑና ዘወትር የእርሱን መግቦት ተስፋ አድርገው እንደሚኖሩ የሚያስረዳ ቃል ነው፡፡ ‹‹ዐይነ ኵሉ ነፍስ ይሴፎ ኪያከ አንተ ትሁቦሙ ሲሳዮሙ በጊዜሁ ትሰፍሕ የማነከ ወታጸግብ ለኵሉ እንስሳ ዘበሥርዓትከ፤ የሰው ዅሉ ዓይን አንተን ተስፋ ያደርጋል፤ አንተም ምግባቸውን በየጊዜው ትሰጣቸዋለህ፡፡ ቀኝ እጅህን ትዘረጋለህ፤ በሥርዓትህ ለሚኖሩ እንስሳት ዅሉ ታጠግባለህ፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት (መዝ. ፻፵፬፥፲፭-፲፮)፡፡ ይኸውም የሰው ልጅ ዅሉ (ዓይን የተባለ ሰውነት ነው) እግዚአብሔርን ተስፋ አድርጎ እንደሚኖር፤ እርሱም በዘር ጊዜ ዘሩን፣ በመከር ጊዜ መከሩን፣ በበልግ ጊዜ በልጉን እያዘጋጀ በየጊዜው ምግባቸውን እንደሚሰጣቸው፤ እንደዚሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ብቻ ሳይኾን በሰፊው እጁ (በማያልቅ ቸርነቱ) በሥርዓቱ ጸንተው ለሚኖሩ ለእንስሳት ጭምር ምግባቸውን እየሰጠ ደስ እንደሚያሰኛቸው የሚያስረዳ ኃይለ ቃል ነው፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን መተርጕማን እንደሚያትቱት ከሰው ልጅ በቀር ከእግዚአብሔር ሥርዓት የወጣ እንስሳ የለም፤ ማለትም ሰው እንጂ እንስሳት ሕገ እግዚአብሔርን አልተላለፉም፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ አምላክነትን ተመኝቶ ‹‹አትብላ›› የተባለውን ዕፅ በመብላት ሕጉን፣ ትእዛዙን ተላልፏል፡፡ እግዚአብሔርም ይቅር ባይ አምላክ ነውና የሰውን ልጅ (የአዳምን) ንስሐ ተመልክቶ፣ ኀጢአቱን ይቅር ብሎ ሞቱን በሞቱ ሽሮ አድኖታል፡፡ እግዚአብሔር አምላችን በፍጡራኑ የማይጨክን፤ የለመኑትን የማይነሳ፤ የነገሩትንም የማይረሳ አምላክ መኾኑን በማስተዋልና ቸርነቱን ተስፋ በማድረግ በምድር በረከቱን እንዲሰጠን፤ ቅዱስ ሥጋውን ለመብላት፣ ክቡር ደሙን ለመጠጣ እንዲያበቃን፤ በሰማይም ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እንዲያወርሰን እኛም በንጹሕ ልብ ኾነን ዘወትር ልንማጸነው ይገባናል፡፡ በሰው ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር መታመን ይበልጣልና (መዝ. ፻፲፯፥፰)፡፡ ደግሞም ‹‹አንተን ተስፋ የሚያደርጉ አያፍሩም›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፳፬፥፫) እግዚአብሔርን ተስፋ ማድረግ አያሳፍርምና፡፡

ይቆየን