ዘመነ ክረምት – ክፍል ሦስት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፳፭ ቀን ፳፻፱ .

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል ሁለት ዝግጅታችን ዘርዕ እና ደመናን መነሻ በማድረግ ወቅቱን የሚመለከት ትምህርት ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ ዛሬ ደግሞ ቀጣዩን ክፍል ይዘን ቀርበናል፡፡ ትምህርቱን እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡

፪. መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል

ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፱ ቀን ድረስ ያለው ሁለተኛው ክፍለ ክረምት ‹መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል› በመባል ይታወቃል፡፡ ይኸውም የመብረቅና የነጐድጓድ ድምፅ በብዛት የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይልበት፤ የምድር ልምላሜ የሚጨምርበት ወቅት ነው፡፡ ዘመነ ክረምት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ልምላሜ ቢኖርም በዚህ ክፍለ ክረምት በስፋት ይነገራል፡፡ በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያን በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱ፣ በቅዳሴው የሚቀርበው ትምህርትም የእግዚአብሔርን አምላካዊ ጥበብ የሚያስረዳ እና የወቅቱን ተፈጥሯዊ ሥርዓት የሚዳስስ ነው፡፡ በዚህ ወቅት በስፋት የሚወሱትን የሁለተኛውን ክፍለ ክረምት ስያሜዎችም እንደሚከተለው ለማብራራት እንሞክራለን፤

መብረቅ እና ነጐድጓድ

‹‹ወገብረ መብረቀ ለጊዜ ዝናም፤ መብረቅን ለዝናም ምልክት አደረገ፤›› (መዝ. ፻፴፬፥፯) በማለት ቅዱስ ዳዊት እንደ ገለጸው መብረቅ በዝናም ጊዜ የሚገኝ ፍጥረት ነው፡፡ የሚፈጠረውም ውኃ በደመና ተቋጥሮ ወደ ላይ ከተወሰደ በኋላ በነፋስ ኃይል ወደ ምድር ሲወርድ በደመና እና በደመና መካከል በሚከሠት ግጭት አማካይነት ነው፡፡ ነጐድጓድ ደግሞ መብረቅ በሚፈጠርበት ጊዜ የሚሰማው አስፈሪ ድምፅ ነው (ራእ. ፬፥፭)፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የመብረቅ አፈጣጠርን በቅቤ እና በዐረቄ አወጣጥ ይመስሉታል፡፡ ወተት ሲገፋ ቅቤ ይወጣል፤ ልዩ ልዩ የእኽል ዓይነት ከውኃ ጋር ተዋሕዶ በእሳት ሲሞቅ ዐረቄ ይገኛል፡፡ ልክ እንደዚሁ ዅሉ ደመና እና ደመና ሲጋጩም መብረቅ ይፈጠራልና፡፡ የምድር ጠቢባንም ሞቃት እና ቀዝቃዛ አየር ሲጋጩ መብረቅ እንደሚፈጠር ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ላይ ዘመናዊው ትምህርት ከመምጣቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መብረቅ አፈጣጠር አስቀድሞ ማስተማሩን ልብ ይሏል፡፡

የእነዚህን ፍጥረታት ምሳሌነት ለማስታወስ ያህል መብረቅ እና ነጐድጓድ በእግዚአብሔር መቅሠፍት (ቍጣ) አንድም በቃለ እግዚአብሔር ይመሰላሉ፡፡ መብረቅ ብልጭታውና ድምፁ (ነጐድጓዱ) እንደሚያስደነግጥና እንደሚስፈራ ዅሉ፣ እግዚአብሔር አምላክ መቅሠፍት ሲልክ ወይም ሲቈጣ የሰው ልጅ ይጨነቃል፤ ይረበሻልና፡፡ ‹‹ቃለ ነጐድጓድከ በሠረገላት አስተርአየ መባርቅቲሁ ለዓለም ርዕደት ወአድለቅለቀት ምድር፤ የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፡፡ መብረቆች ለዓለም አበሩ፡፡ ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት (መዝ. ፸፮፥፲፰)፡፡ ይህ የነቢዩ ዝማሬ ግብጻውያን እስራኤላውያንን ከባርነት አንለቅም በማለታቸው የደረሰባቸውን ልዩ ልዩ መቅሠፍትና መዓት የሚመለክት ምሥጢራዊ ትርጕም አለው፡፡ እንደዚሁም እስራኤላውያን የኤርትራን ባሕር በተሻገሩ ጊዜ ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ›› እያሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረባቸውንም ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ እግዚአብሔር አብ ከሰማይ ኾኖ ‹‹የምወደውና የማፈቅረው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱንም ስሙት፤›› በማለት ስለ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅነት መመስከሩንና ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት (ቃለ እግዚአብሔር) በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በሰብዓ አርድእት፣ በአበው ሊቃውንት አማካይነት በመላው ዓለም መሰበኩን ያጠይቃል፡፡

ደመና እና ደመና ተጋጭተው መብረቅን እንደሚፈጥሩ፣ የሰው ልጅ ባሕርያተ ሥጋ እርስበርስ ሲጋጩና አልስማማ ሲሉም ልዩ ልዩ ስሜት ማለት ቍጣ፣ ብስጭት፣ ቅንዓት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የጠባይዕ ለውጦች ይከሠቱና ኀጢአት ለመሥራት ምክንያት ይኾናሉ፡፡ የመብረቅና የነጐድጓድ ድምፅ እንደሚያስፈራው ዅሉ፣ በሥጋዊ ባሕርይ አለመስማማት የተነሣ የሚፈጠሩ የኀጢአት ዘሮችም ፍርሃትንና መታወክን በሰው አእምሮ ውስጥ እንዲመላለስ ያደርጋሉ፡፡ ከዅሉም በላይ በምድርም በሰማይም ቅጣትን ያስከትላሉ፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል፤›› ሲል ጠቢቡ ሰሎሞን በኀጢአት ምክንያት ስለሚመጣ ፍርሃት የተናገረው (ምሳ. ፳፰፥፩)፡፡ እንግዲህ እኛ የሰው ልጆችም ራሳችንን ከክፉ ዐሳብና ምኞት በመጠበቅ አእምሯችንን ለክርስቲያናዊ ምግባር እና ለመልካም አመለካከት እናስገዛ፡፡ እንዲህ ብናደርግ በምድር በሰላም ለመኖር እንችላለን፤ በሰማይ ደግሞ ዘለዓለማዊ መንግሥቱን ለመውረስ እንበቃለን፡፡ ስለኾነም ባሕርያተ ሥጋችን ተስማምተውልን በጽድቅ ሥራ እንድንኖር ይረዳን ዘንድ እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው፡፡

እንደ ሌሎቹ ፍጥረታት ዅሉ መብረቅ እና ነጐድጓድም አስገኛቸውን፤ ፈጣሪያቸውን ልዑል እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ ‹‹ይሴብሕዎ ሰማያት ወምድር ባሕርኒ ወኵሉ ዘይትሐወስ ውስቴታ፤ ሰማይና ምድር ባሕርም በእርስዋም የሚንቀሳቀስ ፍጥረት ዅሉ ያመሰግኑታል፤›› እንዲል (መዝ. ፷፰፥፴፬)፡፡ ሠለስቱ ደቂቅም ሰማዩም፣ ምድሩም፣ ባሕሩም፣ ወንዙም በአጠቃላይ ፍጥረታት ዅሉ እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግን ሲያስረዱ እንዲህ በማለት ዘምረዋል፤ ‹‹ይባርክዎ ኵሉ ግብረ እግዚእ ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ ኵሉ ማያት ዘመልዕልተ ሰማያት ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ ጠል ወዝናም ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ ቍር ወአስሐትያ ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ በረድ ወጊሜ ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ በረድ ወጊሜ ለእግዚአብሔር … ይባርክዎ መብረቅ ወደመና ለእግዚአብሔር ስቡሕኒ ውእቱ ወልዑልኒ ውእቱ ለዓለም፤ የጌታ ፍጥረቶች ዅሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … ከሰማዮች በላይ ያሉ ውኃዎች ዅሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … ጠል እና ጤዛ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … ብርድ እና ውርጭ እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … በረድ እና ጕም እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል … መብረቅ እና ደመና እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፤ እርሱ ለዘለዓለም የተመሰገነ ነው፤ ከፍ ከፍ ያለም ነው፤›› (ዳን. ፫፥፴፭-፶፩)፡፡

ይህም እግዚአብሔር በመላእክትም፣ በሰው ልጅም፣ አንድም በትሑታኑም በልዑላኑም፤ በከተማውም በገጠሩም እንደዚሁም በባሕር ውስጥ በሚመላለሱ ፍጥረታት ዅሉ የሚመሰገን አምላክ መኾኑን ያስረዳል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በሰዓታት ድርሰቱ ‹‹… ዘበጸዐዕ ይትነከር ወእመባርቅት ይትአኰት ወይትናበብ በእሳት ድምፀ ነጐድጓዱ በሠረገላት፤ በብልጭታ የሚደነቅ፤ በመብረቆች የሚመሰገን፤ በእሳት ውስጥ የሚናገር፤ የነጐድጓዱም ድምፅ በሠረገሎች ላይ የኾነ እግዚአብሔር ንጹሕ፣ ልዩ፣ ክቡር፣ ጽኑዕ ነው፤›› ሲል ከፍጥረታቱ ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የአምልኮ ሥርዓት ገልጾታል፡፡ የማይሰሙ፣ የማይናገሩ፣ የማያዩ ግዑዛን ፍጥረታት እንዲህ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ከኾነ፣ በእርሱ አርአያና አምሳል የተፈጠረው፤ ሕያዊት፣ ለባዊትና ነባቢት ነፍስ ያለችው የሰው ልጅማ ፈጣሪውን እንዴት አልቆ ማመስገን ይጠበቅበት ይኾን?

ባሕር እና አፍላግ

ባሕርና አፍላግ በቃልና በመጠን፣ ወይም በአቀማመጥ ይለያዩ እንጂ ሁለቱም የውኃ ክፍሎች ናቸው፡፡ ‹ባሕር› የግእዝ ቃል ሲኾን ይኸውም በጎድጓዳ መልክዐ ምድር ውስጥ የሚጠራቀም ጥልቅ የውኃ ክምችት ማለት ነው (ዘፍ. ፩፥፲)፡፡ ‹አፍላግ› የሚለው የግእዝ ቃልም የ‹ፈለግ› ብዙ ቍጥር ኾኖ ትርጕሙ ወንዞች ማለት ነው፡፡ ይህም ከውቅያኖስ፣ ከባሕር ወይም ከከርሠ ምድር መንጭቶ ረጅም ርቀት የሚፈስ የውኃ ጅረትን አመላካች ነው (ዘፍ. ፪፥፲፤ መዝ. ፵፭፥፬)፡፡ በዚህ ወቅት የባሕርና የወንዞች መጠን ለዋናተኞች፣ ለመርከብና ለጀልባ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እስኪኾን ድረስ ከቀድሞው በበለጠ መልኩ በሙላትና በኃይል ይበረታል፤ ከሙላቱ የተነሣም ሰውን፣ ንብረትን እስከ ማስጠም እና እስከ መውሰድ ይደርሳል፡፡

ይህ የባሕር እና የወንዞች ሙላትም የምድራዊ ሕይወት መከራን፣ ሥቃይን፣ ፈቃደ ሥጋን (ኀጢአትን) እና ፈተናን፤ ዳግመኛም በሰው ልጅ ኀጢአት ምክንያት የሚመጣ ሰማያዊም ኾነ ምድራዊ ቅጣትን ያመለክታል፡፡ እንደዚሁም የእግዚአብሔርን የተአምራቱን ብዛት ይገልጻል፡፡ ‹‹ወዓሠርከኒ ውስተ ማይ ብዙኅ ወኢይትዐወቅ ዓሠርከ፤ መንገድህ በባሕር ውስጥ፤ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፤›› እንዳለ መዝሙረኛው (መዝ. ፸፮፥፲፱)፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር መንፈስ በመላው ዓለም ሰፍኖ እንደሚኖርና በሃይማኖት በምግባር ጸንተው፣ ከኀጢአት ተለይተው እርሱን የሚሹ ዅሉ ይቅርታውን እንደ ውኃ በቀላሉ እንደሚያገኙት የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ ‹‹እስመ ማይ ለኵሉ ርኩብ›› እንዲሉ ሊቃውንት፡፡ እኛም የኀጢአት ባሕር እንዳያሰጥመን፤ የኀጢአት ወንዝም እንዳይወስደን ተግተን ነቅን ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ እንደ ውኃ ለዅሉም የሚፈሰው የእግዚአብሔር ይቅርታው ደርሶን የመንግሥቱ ወራሾች እንኾን ዘንድም ፈቃደ ሥጋችንን ለፈቃደ ነፍሳችን እናስገዛ፡፡

ጠል

‹ጠል›፣ ‹ጠለ – ለመለመ› ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲኾን ትርጕሙም ‹ልምላሜ› ማለት ነው፡፡ ይህ ወቅት ለምግብነት የሚዉሉም ኾኑ የማይዉሉ አብዛኞቹ ዕፀዋት በቅለው፣ ለምልመው የሚታዩበት ጊዜ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹በመከር ወራት የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ነው፤›› በማለት እንደ መሰለው (ምሳ. ፳፭፥፲፫)፣ ይኼ የዕፀዋት ልምላሜ በጎ ምግባር ባላቸው ምእመናንና በመልካም አገልጋዮች ይመሰላል፡፡ በተጨማሪም ዕፀዋት በዝናም አማካይነት በቅለው መለምለማቸው በስብከተ ወንጌል (ቃለ እግዚአብሔር) ተለውጠው፣ በሃይማኖታቸው ጸንተው፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ተግተው፣ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ተወስነው የሚኖሩ ምእመናንን ሕይወት፤ እግዚአብሔር አምላክ ለሰው ልጆች የሚያድለውን ጸጋ እና በረከት ያመለክታል፡፡ ‹‹ወይረውዩ እምጠለ ቤትከ፤ ከቤትህ ጠል ይጠጣሉ (ይረካሉ)፤›› እንዳለ ነቢዩ በመዝሙሩ (መዝ. ፴፭፥፰)፡፡ ይኸውም በቤተ መቅደሱ ዘወትር የሚፈተተውን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን መቀበል፣ እንደዚሁም የቅዳሴ ጠበሉን መጠጣት የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ርካታ ይገልጻል፡፡

በዘመነ ክረምት የሚለመልሙ ዕፀዋት የመብዛታቸውን ያህል በለስና ወይንን የመሰሉ ተክሎች ክረምት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ደርቀው ይቆዩና በበጋ ወቅት ይለመልማሉ፡፡ እነዚህም በመልካም ዘመን ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩና በመከራ ሰዓት ተነሥተው ወንጌልን የሚሰብኩ የሰማዕታት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በለስና ወይንን የመሰሉ ዕፀዋት በዝናም ጊዜ ደርቀው በፀሐይ ጊዜ እንዲለመልሙ፤ ቅዱሳን ሰማዕታትም በምድራዊ ሹመት፣ በሽልማት ወቅት ተሠውረው፤ ሥቃይና ፈተና በሚበረታበት ጊዜ ምድራዊውን መከራ ተቋቁመው ስለ እውነት (ወንጌል) እየመሰከሩ ራሳቸውን በሰማዕትነት አሳልፈው ይሰጣሉና፡፡ ዅላችንንም እንደ ዕፀዋቱ በወንጌል ዝናም ለምልመን መልካም ፍሬ እንድናፈራ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ይቆየን