ዘመነ ክረምት ክፍል ሁለት

ነሐሴ ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! በክፍል አንድ ዝግጅታችን የመጀመሪያው የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ (ከሰኔ ፳፭ እስከ ሐምሌ ፲፰ ቀን ድረስ ያለው) ዘርዕ፣ ደመና እንደሚባል በማስታዎስ ይህ ወቅት ደመና ሰማዩን የሚሸፍንበት፤ የዝናም መጠን የሚያይልበትና መሬት በዝናም ረክታ ዘር የምታበቅልበት ጊዜ እንደኾነ ጠቅሰን የወቅቱን ኹኔታ ከሕይወታችን ጋር በማዛመድ ለመዳሰስ ሞክረን ነበር፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን ሁለተኛውን የዘመነ ክረምት ክፍለ ጊዜ የሚመለከት ትምህርት ይዘን የቀረብን ሲኾን በወቅቱ ባለማስነበባችን ይቅርታ እየጠየቅን ጽፋችንን እነሆ!

ከሐምሌ ፲፱ እስከ ነሐሴ ፲ ቀን ድረስ ያለው ሁለተኛው ክፍለ ክረምት ‹‹መብረቅ፣ ነጎድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ፣ ጠል›› በመባል የሚታወቅ ሲኾን፣ ይኸውም የመብረቅና የነጎድጓድ ድምፅ በብዛት የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይልበት፤ የምድር ልምላሜ የሚጨምርበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ክፍለ ጊዜ ውስጥ በሚገኙ ዕለታት በቤተ ክርስቲያን በማኅሌቱ፣ በሰዓታቱ፣ በቅዳሴው የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ይህንን ኹሉ ሕገ ተፈጥሮ የሚዳስስና የእግዚአብሔርን አምላካዊ ጥበብ የሚያስረዳ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው፡፡

መብረቅ እና ነጎድጓድ

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ወገብረ መብረቀ ለጊዜ ዝናም፤ መብረቅን ለዝናም ምልክት አደረገ፤›› በማለት እንደ ገለጸው መብረቅ በዝናም ጊዜ የሚገኝ ፍጥረት ሲኾን የሚፈጠረውም ውሃ በደመና ተቋጥሮ ወደ ላይ ከተወሰደ በኋላ በነፋስ ኃይል ወደ ምድር ሲወርድ በደመና እና በደመና መካከል በሚከሠት ግጭት አማካይነት ነው፡፡ ይህንን የመብረቅ አፈጣጠርም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በቅቤና በዐረቄ አወጣጥ ይመስሉታል፡፡

ወተት ሲገፋ ቅቤ እንደሚወጣ፤ ልዩ ልዩ የእህል ዝርያ ከውሃ ጋር ኾኖ በእሳት ሲሞቅ ዐረቄ እንደሚገኝ ኹሉ ደመና እና ደመና ሲጋጩም መብረቅ ይፈጠራልና:: የምድር ጠቢባንም ሞቃት እና ቀዝቃዛ አየር ሲጋጩ መብረቅ እንደሚፈጠር ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ላይ ዘመናዊው ትምህርት ከመምጣቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መብረቅ አፈጣጠር አስቀድሞ ማስተማሩን ልብ ይሏል /መዝሙረ ዳዊት አንድምታ ትርጓሜ፣ መዝ.፻፴፬፥፯/፡፡ ነጎድጓድ ደግሞ መብረቅ በሚፈጠርበት ጊዜ የሚሰማው አስፈሪ ድምፅ ነው /ራእ.፬፥፭/::

መብረቅና ነጎድጓድ በእግዚአብሔር መቅሠፍት እና በቃለ እግዚአብሔር (በቍጣው) ይመሰላሉ፡፡ መብረቅ ብልጭታውና ድምፁ (ነጎድጓዱ) እንደሚያስደነግጥና እንደሚስፈራ ኹሉ እግዚአብሔርም መቅሠፍት ሲልክና ሲቈጣ የሰው ልጅ ይጨነቃል፤ ይረበሻልና፡፡ ‹‹ቃለ ነጎድጓድከ በሠረገላት አስተርአየ መባርቅቲሁ ለዓለም ርዕደት ወአድለቅለቀት ምድር፤ የነጐድጓድህ ድምፅ በዐውሎ ነበረ፡፡ መብረቆች ለዓለም አበሩ፤ ምድር ተናወጠች፤ ተንቀጠቀጠችም፤›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት /መዝ.፸፮፥፲፰/፡፡ ይህም ግብጻውያን እስራኤላውያንን ከባርነት ባለመልቀቃቸው የደረሰባቸውን ልዩ ልዩ መቅሠፍትና መዓት የሚመለክት ምሥጢር ይዟል:፡

እንደዚሁም እስራኤላውያን የኤርትራን ባሕር በተሻገሩ ጊዜ ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ›› እያሉ ለእግዚአብሔር ምስጋና ማቅረባቸውን ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀ ጊዜ እግዚአብሔር አብ ከላይ ከሰማይ ኾኖ ‹‹የምወደውና የማፈቅረው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱንም ስሙት፤›› በማለት መናገሩንና ወንጌለ መንግሥተ ሰማያት (ቃለ እግዚአብሔር) በቅዱሳን ሐዋርያት፣ በሰብዓ አርድእት፣ በአበው ሊቃውንት አማካይነት በመላው ዓለም መሰበኩን ያጠይቃል /ትርጓሜ መዝሙረ ዳዊት/:፡

እንደ ሌሎቹ ፍጥረታት ኹሉ መብረቅና ነጎድጓድም አስገኛቸውን፤ ፈጣያቸውን ልዑል እግዚአብሔርን ያመሰግኑታል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም ይህንን ሥርዓት ‹‹… ዘበጸዐዕ ይትነከር ወእመባርቅት ይትአኰት ወይትናበብ በእሳት ድምፀ ነጎድጓዱ በሠረገላት፤ በብልጭታ የሚደነቅ፤ በመብረቆች የሚመሰገን፤ በእሳት ውስጥ የሚናገር፤ የነጎድጓዱም ድምፅ በሠረገሎች ላይ የኾነ እግዚአብሔር ንጹሕ፣ ልዩ፣ ክቡር፣ ጽኑዕ ነው፤›› ሲል ገልጾታል /መጽሐፈ ሰዓታት/::

ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ ‹‹ይሴብሕዎ ሰማያት ወምድር ባሕርኒ ወኵሉ ዘይትሐወስ ውስቴታ፤ ሰማይና ምድር ባሕርም በእርስዋም የሚንቀሳቀስ ሁሉ ያመሰግኑታል፤›› በማለት ሰማዩም፣ ምድሩም፣ ባሕሩም፣ ወንዙም እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግን ተናግሯል /መዝ.፷፰፥፴፬/፡፡ ይህም እግዚአብሔር በመላእክትም፣ በሰው ልጅም፣ አንድም በትሑታኑም በልዑላኑም፤ በከተማውም በገጠሩም እንደዚሁም በባሕር ውስጥ በሚመላለሱ ፍጥረታት ኹሉ የሚመሰገን አምላክ መኾኑን ያስረዳል፡፡ የማይሰሙ፣ የማይናገሩ፣ የማያዩ ግዑዛን ፍጥረታት እንዲህ እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ከኾነ በእርሱ አርአያና አምሳል የተፈጠረው፤ ሕያዊት፣ ለባዊትና ነባቢት ነፍስ ያለችው የሰው ልጅማ ፈጣሪውን እንዴት አልቆ ማመስገን ይገባው ይኾን?

ከዚሁ ኹሉ ጋርም ደመና እና ደመና ተጋጭተው መብረቅን እንደሚፈጥሩ ኹሉ የሰው ልጅ ባሕርያተ ሥጋም እርስበርስ ሲጋጩና አልስማማ ሲሉ በሰው ልጅ ስሜት ቍጣ፣ ብስጭት፣ ቅንዓት፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የጠባይዕ ለውጦች ይከሠቱና ኀጢአት ለመሥራት ምክንያት ይኾኑበታል፡፡ ‹‹ከልብ ክፉ ዐሳብ፣ መግደል፣ ምንዝርነት፣ ዝሙት፣ መስረቅ፣ በውሸት መመስከር፣ ስድብ ይወጣል፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ማቴ.፲፭፥፲፱/፡፡ የመብረቅና የነጎድጓድ ድምፅ እንደሚያስፈራው ኹሉ እነዚህ በሥጋዊ ባሕርይ አለመስማማት የሚፈጠሩ የኀጢአት ዘሮችም ፍርሃትንና መታወክን በሰው አእምሮ ውስጥ እንዲመላለስ ያደርጋሉ፤ ከኹሉም በላይ በምድርም በሰማይም ቅጣትን ያስከትላሉ:: ለዚህም ነው ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለ ፍርሃት ይኖራል፤›› ሲል የተናገረው /ምሳ.፳፰፥፩/፡፡

እንግዲህ የሰው ልጅ ራሱን ከክፉ ዐሳብና ምኞት በመጠበቅ አእምሮዉን ለመልካም አስተሳሰብና አመለካከት፤ ለክርስቲያናዊ ምግባር ቢያስገዛ በምድር በሰላምና በጸጥታ ለመኖር፤ በሰማይም መንግሥቱን ለመውረስ እንደሚቻለው በመረዳት ባሕርያተ ሥጋችን ተስማምተውልን በጽድቅ ሥራ እንድንኖር እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ ይኖርብናል::

ባሕር እና አፍላግ

ባሕርና አፍላግ በቃልና በመጠን፣ ወይም በአቀማመጥ ይለያዩ እንጂ ሁለቱም የውሃ ክፍሎች ናቸው፡፡ ‹‹ባሕር›› አንድም ብዙም ቍጥርን የሚወክል ግእዝ ቃል ሲኾን ይኸውም በጎድጓዳ መልክዐ ምድር ውስጥ የሚጠራቀም ጥልቅ የኾነ የውሃ ክምችት ማለት ነው /ዘፍ.፩፥፲/፡፡ ‹‹አፍላግ›› የሚለው የግእዝ ቃልም የ‹‹ፈለግ›› ብዙ ቍጥር ኾኖ ትርጉሙም ወንዞች ማለት ነው፡፡ ይህም ከውቅያኖስ፣ ከባሕር ወይም ከከርሠ ምድር መንጭቶ ረጅም ርቀት የሚፈስ የውሃ ጅረትን አመላካች ነው /ዘፍ.፪፥፲፤ መዝ.፵፭፥፬/፡፡ በዚህ ወቅት የባሕርና የወንዞች መጠን ለዋናተኞች፣ ለመርከብና ለጀልባ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እስኪኾን ድረስ ከቀድሞው በበለጠ መልኩ በሙላትና በኃይል ይበረታል፤ ከሙላቱ የተነሣም ሰውን፣ ንብረትን እስከ ማስጠም እና መውሰድ ይደርሳል::

ይህ የባሕርና የወንዞች ሙላትም የምድራዊ ሕይወት መከራና ፈተና፣ ሥቃይና ፈቃደ ሥጋ (ኀጢአት) ማየልን፤ ዳግመኛም በሰው ልጅ ኀጢአት ምክንያት የሚመጣ ሰማያዊም ኾነ ምድራዊ ቅጣትን ያመለክታል፡፡ እንደዚሁም የእግዚአብሔርን የተአምራት ብዛት ይገልጻል፡፡ ‹‹ወዓሠርከኒ ውስተ ማይ ብዙኅ ወኢይትዐወቅ ዓሠርከ፤ መንገድህ በባህር ውስጥ ነው፤ ፍለጋህም በብዙ ውኆች ነው፤›› እንዲል /መዝ.፸፮፥፲፱/፡፡ ይኸውም የእግዚአብሔር መንፈስ በመላው ዓለም ሰፍኖ እንደሚኖርና በሃይማኖት፣ በምግባር ጸንተው፣ ከኀጢአት ተለይተው እርሱን የሚሹ ኹሉ ይቅርታውን እንደ ውኃ በቀላሉ እንደሚያገኙት የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ የኀጢአት ባሕር እንዳያሰጥመን፤ የኀጢአት ወንዝ እንዳይወስደን ኹላችንም ራሳችንን ከፈቃደ ሥጋ (ከስሜታዊነት) ተጠብቀን መንግሥቱን እንወርስ ዘንድ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይርዳን፡

ጠል

‹‹ጠል›› የሚለው ቃል ‹‹ጠለ – ለመለመ›› ከሚል የግእዝ ግስ የወጣ ሲኾን ትርጕሙም ‹‹ልምላሜ›› ማለት ነው፡፡ ዘመነ ክረምት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ልምላሜ ቢኖርም በስፋት የሚነገረው ግን ከሐምሌ ፲፱ ቀን እስከ ነሐሴ ፲ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ይህ ወቅት የሚበሉትም የማይበሉትም አብዛኞቹ ዕፀዋት በቅለው ለምልመው የሚታዩበት ጊዜ ነው፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹በመከር ወራት የውርጭ ጠል ደስ እንደሚያሰኝ እንዲሁ የታመነ መልእክተኛ ለላኩት ነው፤›› በማለት እንደ መሰለው /ምሳ.፳፭፥፲፫/፣ ይኼ የዕፀዋት ልምላሜ በጎ ምግባር ባላቸው ምእመናንና በመልካም አገልጋዮች ይመሰላል፡

በተጨማሪም ዕፀዋት በዝናም አማካይነት በቅለው መለምለማቸው በስብከተ ወንጌል (ቃለ እግዚአብሔር) ተለውጠው፣ በሃይማኖታቸው ጸንተው፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ተግተው፣ በቅዱስ ሥጋው በክቡር ደሙ ተወስነው የሚኖሩ ምእመናንን ሕይወት እና እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሚያድለውን ጸጋና በረከት ያመለክታል፡፡ ‹‹ወይረውዩ እምጠለ ቤትከ፤ ከቤትህ ጠል ይጠጣሉ (ይረካሉ)፤›› እንዲል /መዝ.፴፭፥፰/፡፡ ይኸውም በቤተ መቅደሱ ዘወትር የሚፈተተውን ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን መቀበልና ጠበሉን መጠጣት የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ርካታ ይገልጻል፡፡

በዚህ ክፍለ ክረምት የሚለመልሙ ዕፀዋት የመብዛታቸውን ያህል በለስና ወይንን የመሰሉ ተክሎች ክረምት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ደርቀው ይቆዩና በበጋ ወቅት ይለመልማሉ፡፡ እነዚህም በመልካም ዘመን ራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩና በመከራ ሰዓት ተነሥተው ወንጌልን የሚሰብኩ የሰማዕታት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ በለስና ወይንን የመሰሉ ዕፀዋት በዝናም ጊዜ ደርቀው በፀሐይ ጊዜ እንዲለመልሙ፤ ቅዱሳን ሰማዕታትም በምድራዊ ሹመት፣ በሽልማት ወቅት ተሠውረው፤ ሥቃይና ፈተና በሚበራታበት ጊዜ ምድራዊውን መከራ ተቋቁመው ስለ እውነት (ወንጌል) እየመሰከሩ ራሳቸውን በሰማዕትነት አሳልፈው ይሰጣሉና፡፡ ኹላችንንም እንደ ዕፀዋቱ በወንጌል ዝናም ለምልመን መልካም ፍሬ እንድናፈራ የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይኹንልን፡፡

ይቆየን፡፡