ዘመነ አስተምሕሮ (አስተምህሮ) የመጀመሪያ ክፍል

ኅዳር ፳፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ባቀረብነው ዝግጅት እንዳስታወስነው በቤተ ክርስቲያናችን የዘመን አከፋፈል መሠረት ከኅዳር ፮ ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ፯ ወይም ፲፫ ቀን ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምሕሮ ይባላል፡፡ ትርጕሙም በሃሌታው ‹ሀ› (‹‹አስተምህሮ›› ተብሎ) ሲጻፍ የቃለ እግዚአብሔር ማስተማሪያ (የትምህርተ ወንጌል) ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም ‹‹መሀረ – አስተማረ›› የሚለው የግእዝ ግስ ሲኾን፣ ይኸውም የእግዚአብሔር ቸርነቱ፣ ርኅራኄው፣ ትዕግሥቱና የማዳን ሥራው በቤተ ክርስቲያን በስፋት የሚሰበክበት ጊዜ ነው፡፡ በሐመሩ ‹‹ሐ›› (‹‹አስተምሕሮ›› ተብሎ) ሲጻፍ ደግሞ የምሕረት፣ የይቅርታ ዘመን ማለት ነው፡፡ ሥርወ ቃሉም ‹‹መሐረ – ይቅር አለ›› የሚለው የግእዝ ግስ ነው፡፡ ዘመነ አስተምሕሮ ስለ እግዚአብሔር ቸርነትና ርኅራኄ፤ እርሱ በደላችንን ዅሉ ይቅር እንደሚለን እኛ ምእመናንም እርስበርስ ይቅር መባባል እንደሚገባን ትምህርት የሚሰጥበት ወቅት ነው፡፡

ባለፈው ዝግታችን በዘመነ አስተምሕሮ ውስጥ የሚገኙ ሰንበታት (እሑዶች) አስተምሕሮ፣ ቅድስት፣ ምኵራብ፣ መጻጉዕ እና ደብረ ዘይት በመባል እንደሚጠሩ ጠቅሰን ነበር፡፡ ነገር ግን ከመጀመሪያው ሳምንት ከአስተምሕሮ በስተቀር የአራቱ እሑዶቹ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ጋር ተመሳሳይ በመኾኑ መደናገራቸውን አንዳንድ ምእመናን ገልጸውልናል፡፡ እውነት ነው፤ የሰንበታቱ ስያሜ ከዐቢይ ጾም ሰንበታት ጋር ተመሳሳይ ይኹን እንጂ የሚዘመሩ መዝሙራት፣ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ ምንባባትና የሚቀርቡ ትምህርቶች ግን ይለያያሉ፡፡ ልዩነታቸውን ለማነጻጸርና ለመረዳት እንዲያመቸንም በእነዚህ ሰንበታት የሚነገረውን ቃለ እግዚአብሔር ይዘት እንደሚከተለው በአጭሩ እንመለከታለን፤

፩. አስተምሕሮ

የመጀመሪያው የዘመነ አስተምሕሮ ሳምንት ‹‹አስተምሕሮ›› ይባላል፤ ይህም ከኅዳር ፮ – ፲፪ ያሉትን ሰባት ቀናት ያካትታል፡፡ በዕለቱ (እሑድ) የሚቀርበው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ‹‹ኢተዘኪሮ አበሳ ዚአነ ኢኀደገነ ፍጹመ ንማስን ….፤ ኀጢአታችንን አላሰበብንም፤ እንጠፋ ዘንድም ፈጽሞ አልተወንም ….›› የሚለው ሲኾን፣ በተጨማሪም ‹‹ፈጽም ለነ ሠናይተከ እንተ እምኀቤነ ….፤ በአንተ ዘንድ ያለችውን በጎነት ፈጽምልን ….›› የሚለውም እንደ አማራጭ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ምስባኩ ‹‹ኢትዝክር ለነ አበሳነ ዘትካት ፍጡነ ይርከበነ ሣህልከ እግዚኦ እስመ ተመንደብነ ፈድፋደ፤ የቀደመውን በደላችንን አታስብብን፡፡ አቤቱ ምሕረትህ በቶሎ ያግኘን፡፡ እጅግ ተቸግረናልና፤›› የሚለው የዳዊት መዝሙር ነው /መዝ.፸፰፥፰/፡፡ ወንጌሉ ማቴዎስ ፮፥፭-፲፮ ሲኾን፣ ቅዳሴውም ቅዳሴ እግዚእ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት እግዚአብሔር አምላካችን ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመት የመርገምና የጨለማ ዘመን ዓለምን ማውጣቱ፣ ቸርነቱ፣ ርኅራኄውና ትዕግሥቱ፤ እንደዚሁም ምእመናንን ከሞተ ሥጋ ከሞተ ነፍስ ማውጣቱ ይነገርበታል፡፡

፪. ቅድስት

ከኅዳር ፲፫ – ፲፱ ያሉትን ሰባት ቀናት የሚያካትተው የዘመነ አስተምሕሮ ሁለተኛው ሳምንት ‹‹ቅድስት›› ይባላል፤ ቅድስት የተባለበት ምክንያትም ሰንበትን ለቀደሰ ለልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ማቅረብ እንደሚገባ የሚነግርበት ሳምንት መኾኑ ነው፡፡ በዚህ ዕለት (እሑድ) ‹‹ሎቱ ስብሐት ወሎቱ አኰቴት ለዘቀደሳ ለሰንበት ….፤ ሰንበትን ላከበራት ለእርሱ ክብር ምስጋና ይኹን (ይድረሰው፤ ይገባዋል) ….›› የሚለው የቅዱስ ያሬድ መዝሙር ይቀርባል፤ በቅዳሴ ጊዜም ‹‹ኵሎ ዘፈቀደ ገብረ እግዚአብሔር በሰማይኒ ወበምድርኒ በባሕርኒ ወበኵሉ ቀላያት፤ በሰማይና በምድር፣ በባሕርና በጥልቆችም ዅሉ እግዚአብሔር የወደደውን ዅሉ አደረገ፤›› የሚለው ምስባክ ይሰበካል /መዝ.፻፴፬፥፮/፡፡ ወንጌሉ ዮሐንስ ፭፥፲፮-፳፰ ሲኾን ቅዳሴው ደግሞ አትናቴዎስ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ስለ ዕለተ ሰንበት ቅድስትነት እና ሰንበትን ስለቀደሰ ስለ እግዚአብሔር ቅድስና ሰፊ ትምህርት ይቀርባል፡፡

በአንጻሩ በዓቢይ ጾሙ ቅድስት መዝሙሩ፡- ‹‹ግነዩ ለእግዚአብሔር››፤ ምስባኩ፡- ‹‹እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ አሚን ወሠናይት ቅድሜሁ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ፈጠረ፡፡ እምነትና በጎነት በፊቱ፣ ቅድስናና የክብር ጋናናነት በመቅደሱ ውስጥ ናቸው፡፡›› /መዝ.፺፭፥፭-፮/፤ ወንጌሉ፡- ማቴዎስ ፮፥፲፮-፳፭፤ ቅዳሴው ደግሞ ኤጲፋንዮስ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ስለ እግዚአብሔር ይቅር ባይነትና ለእርሱ ስለ መገዛት፣ ስለ ቅድስና እና ስለ ክብረ ሰንበት የሚያስረዳ ነው፡፡

 ፫. ምኵራብ

ሦስተኛው የዘመነ አስተምሕሮ ሳምንት ‹‹ምኵራብ›› የሚባል ሲኾን ይህም ከኅዳር ፳ – ፳፮ ያሉትን ሰባት ቀናት የሚያካትት ሳምንት ነው፡፡ በዕለቱ (እሑድ) የሚቀርበው መዝሙር፡- ‹‹አምላክ ፍጹም በህላዌሁ ዘሀሎ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም ….፤ ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ የነበረው አምላክ (እግዚአብሔር) በህልውናው (አነዋወሩ) ፍጹም ነው ….››  የሚለው ሲኾን፣ ምስባኩም፡- ‹‹ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ ወኢይትኀፈር ገጽክሙ ዝንቱ ነዳይ ጸርሐ ወእግዚአብሔር ሰምዖ፤ ወደ እርሱ ቅረቡ፤ ያበራላችሁማል፡፡ ፊታችሁም አያፍርም፡፡ ይህ ችግረኛ ጮኸ፤ እግዚአብሔርም ሰማው፤›› የሚል ነው /መዝ.፴፫፥፭-፮/፡፡ ወንጌሉም ከማቴዎስ ፰፥፳፫ እስከ መጨረሻው ድረስ ነው፡፡ ቅዳሴው ደግሞ እግዚእ፡፡ በዚህ ሳምንት ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራበ አይሁድ ሕዝቡን እየሰበሰበ ማስተማሩ፤ ባሕርና ነፋሳትን መገሠፁ፤ አጋንንትን ከሰዎች ማውጣቱ ይነገራል፡፡

በዓቢይ ጾሙ ምኵራብ መዝሙሩ፡- ‹‹ቦአ ኢየሱስ ምኵራቦሙ ለአይሁድ››፤ ምስባኩ፡- ‹‹እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዕሌየ ወቀፃዕክዋ በጾም ለነፍስየ፤ የቤትህ ቅናት በልቶኛልና፣ የሚሰድቡህ ስድብም በላዬ ወድቋልና፡፡ ሰውነቴን በጾም አደከምኋት፡፡›› /መዝ.፷፰፥፱-፲/፤ ወንጌሉ፡- ዮሐንስ ፪፥፲፪ እስከ ፍጻሜው ሲኾን ቅዳሴው ግን ተመሳሳይ (ቅዳሴ እግዚእ) ነው፡፡ በሳምንቱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኵራበ አይሁድ ማስተማሩንና በቤተ መቅደሱ ዓለማዊ ሸቀጥ ይለውጡ የነበሩ ገበያተኞችን ማስወጣቱን የሚመለከት ትምህርት ይቀርባል፡፡

ይቆየን