ዕቅበተ እምነት በመጽሐፈ ምሥጢር – የመጀመሪያ ክፍል

የካቲት ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ዕቅበተ እምነት የቤተ ክርስቲያን የዕለት ከዕለት አገልግሎት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ በጎላና በተረዳ ለመናገር የዐቃብያነ እምነት ዘመን የሚባል ወቅት ቢኖርም ቤተ ክርስቲያን የዕቅበተ እምነት ተግባር ያልፈጸመችበት ጊዜ የለም፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ በቃልም በመጽሐፍም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ያስጠበቁ ብዙ ሊቃውንትን እናገኛለን፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ከእነዚህ ስመ ጥር ዐቃብያነ እምነት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በድርሰቱ ዳግማዊ ያሬድ”፣ በመንፈሳዊ ዕውቀቱ ዐምደ ሃይማኖት”፣ መናፍቃንን ተከራክሮ በመርታቱ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ” ተብሎ ይጠራል፡፡

ዜና ገድሉን የጻፈው ሊቁ ወልደ አብ እንደ ሙሴ የኦሪት መምህር፣ እንደ ሄኖክ የተሰወረውን የሚያይ፣ እንደ ኤልያስ ለአምላኩ ሕግ የሚቀና፣ እንደ ኢሳይያስ ልዑለ ቃል (ቃሉ ከፍ ያለ)፣ ጎልያድን የገደለው ዐዲሱ ዳዊት፣ የመንግሥተ ሰማያት መክፈቻዎችን የተቀበለ ጴጥሮስ፣ ከኢየሩሳሌም እስከ እልዋሪቆን ያስተማረ ልሳነ ዕፍረት ጳውሎስ፣ …” (ገድለ አባ ጊዮርስ ምዕራፍ ፩፡፲፮-፲፰) በማለት ክብሩን ልዕልናውን ይገልጸዋል፡፡ የሊቁን ዜና ዕረፍት በሰሙ ጊዜ ንጉሡና ሕዝበ ክርስቲያኑ ያለቀሱት ለቅሶ የአባ ጊዮርጊስን ጸጋና ተወዳጅነት የሚያስረዳ ነበር፡፡ አባ ቸር ጠባቂ፣ አባ የምስጋና ክቡር ዕቃ፣ አባ ዐዲሱ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ አባ ቀዩና አረንጓዴው ወርቅ፣ አባ ሰማያዊ ሰውና ምድራዊ መልአክ፣ አባ የማይዛባ የሃይማኖት ምሰሶ፣ አባ የኢትዮጵያ ብሩህ ፀሐይና በምልዐቱ የሚታይ ጨረቃ፣ አባ ሰማያዊ ኮከብ፣ በእውነት መለኮታዊ እሳት የተዋሐደውን ቅዱስ ቍርባን የዳሰሱ እጆችህ ደረቁን? እግሮችህስ በሞት መግነዝ ተገነዙን? አባ በእውነት ዐይኖችህ ተከደኑን? አፍንጮችህስ ተዘጉን? አፍና ከንፈሮችህስ ተከደኑን? …” በማለት ነበር ኀዘናቸውን የገለጹት፡፡

አባ ጊዮርጊስ በመጻሕፍት አዋቂነቱ እና በቅድስናው የተመሰከረለት አባት ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተነሡ የመናፍቃንን ጥያቄዎች በቃልም በመጽሐፍም በመመለስ ይታወቃል፡፡ በገድሉ ላይ ተጠቅሰው ከምናገኛቸው የቃል ክርክሮች አንዱ የአይሁዳዊው ታሪክ ነው፡፡ በአንድ ወቅት አንድ አይሁዳዊ ጌታችሁ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነአልዓዛርን የት ቀብራችሁት?› ብሎ ለምን ጠየቀ?” ብሎ በጠየቀ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እግዚአብሔር አብ በኦሪት ለምንአዳም ሆይ ወዴት ነህ?› ብሎ ጠየቀው? አብርሃምንስሚስትህ ሣራ ወዴት ናት?› ብሎ ለምን ጠየቀው?” በማለት እንዳሳፈረው በገድሉ ተጽፏል፡፡

አባ ጊዮርጊስ ብዙ ድርሳናትን ደርሷል፤ የሚበዙት የምስጋና ድርሰቶች ናቸው፡፡ ከጻፋቸው ብዙ መጻሕፍት መካከል አንዱ መጽሐፈ ምሥጢር ነው፡፡ መጽሐፈ ምሥጢር በቤተ ክርስቲያናችን ከሚጠቀሱ የዕቅበተ እምነት መጻሕፍት ውስጥ አንዱ ሲሆን የአባ ጊዮርጊስ የነገረ ሃይማኖት ሊቅነቱ የተመሰከረበት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ አባ ጊዮርጊስ በነገረ እግዚአብሔር ላይ ጽርፈት የተናገሩ መናፍቃንን ለመገሠጽና ለእነርሱ መልስ ለመስጠት የጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ በምን ዓይነት ቅንዐተ መንፈስ ቅዱስ ተነሣሥቶ መልስ እንደሰጠ ሲነግረን “… የቅዱሳንን ዜናቸውን ለመናገር ፍቅር ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ከሐዲዎችን እነቅፋቸው ዘንድ ያስገድደኛል፤ ፍቅር ክርስቶስን እንዳመሰግነው ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ሰይጣንን አወግዘው ዘንድ ያስገድደኛል፤ ፍቅር የክርስቶስን ሐዋርያት እንድከተላቸው ያስገድደኛል፤ ቅንዐትም ዝንጉዎችን እንድዘልፋቸው ግድ ይለያኛል፤ ፍቅር ሰማዕታትን አወድሳቸው ዘንድ ግድ ይለኛል፤ ቅንዐትም ጠንቋዮችን እንድዘልፋቸው ያስገድደኛልበማለት ይገልጽልናል፡፡

አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በዚህ መንፈሳዊ ቅናቱ ምክንያት እግዚአብሔር የገለጠለትን ምሥጢር አምስት ጸሐፊዎችን ሰብስቦ እርሱ በቃል እየነገራቸው በሁለት ዕለታት ጽፈውታል፡፡ መጽሐፉ ሲያልቅ ጸሓፊዎቹ እጅግ አደነቁ፡፡ ምሥጢረ እግዚአብሔርን እየሰማ ያጻፈው አባ ጊዮርጊስም ጽሑፉን ተመልክቶ አደነቀ፤ እኔ የዚህን መጽሐፍ ቃል አልተናገርኩም፤ መንፈስ ቅዱስ በእኔ አንደበት ተናገረ እንጂ በማለት ተናግሯል፡፡ ይህንም መጽሐፍ የመለኮትን ነገር ይናገራልና መጽሐፈ ምሥጢር”  ሲል ሰየመው፡፡ መጽሐፉ በመጀመሪያ የተጻፈው በግእዝ ቋንቋ ሲሆን አሁን ግን ወደ አማርኛ ተተርጕሞ በብዙዎች እጅ ደርሷል፡፡

የመጽሐፈ ምሥጢር አጻጻፍ ወይም መልስ አሰጣጥ ስልትን ስንመለከት አባ ጊዮርጊስ በየምዕራፉ በምስጋና ይጀምራል፡፡ ከምስጋና ቀጥሎ መልስ የሚሰጣቸውን መናፍቃን ኑፋቄና ጥንተ ታሪክ ይገልጻል፡፡ ደርሰውበት የነበረውን የክህነት መዐርግ ጠቅሶ ከተናገሩት የክሕደት አዘቅት ጋር በማወዳደር ይወቅሳቸዋል፡፡ ከዚያም ለኑፋቄያቸው የተራቀቀ የነገረ ሃይማኖት ዕውቀቱን ተጠቅሞ ከብሉይና ከሐዲስ እየጠቀሰ መልስ ይሰጣል፡፡ በመልሱ ውስጥ በብሉይም ሆነ በሐዲስ የተነገሩ ትንቢትና ምሳሌዎችንም መንፈስ ቅዱስ በገለጠለት መሠረት ትርጉም ለአንባብያን ግልጥ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ አባ ጊዮርጊስ ለመናፍቃኑ መልስ በአብዛኛው የጠቀሰው ከብሉይና ከሐዲስ ነው፡፡ ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ለመናፍቃኑ መልስ የሰጠበትን ክፍል ዘለፋ፣ ወቀሳ” ይለዋል፡፡

ሊቁ በእግዚአብሔር ላይ የነቀፋ ቃል የተናገሩትን ይዘልፋቸዋል፣ ይገዝታቸዋል፣ ይረግማቸዋል፡፡ በሥላሴ ላይ የነቀፋ ቃል ባይናገሩም እንኳን የተሳሳተ ትምህርት ያስተማሩትን ደግሞ በጽድቅ ጎዳና ስላልቆሙ እንዘልፋቸዋለን፤ ርግማን ግን በሥላሴ ላይ ሐሰት ስላልተናገሩ አንረግማቸውም በማለት በተግሣጽ ያልፋቸዋል፡፡ በየአርእስቱ መጨረሻም በሃይማኖት አባቶቹን እንደሚመስል በምግባር ግን ደካማ እደሆነ በመጥቀስ አንባብያን በጸሎት እንዲያግዙት በመማጸን ያጠቃልላል፡፡ ይህም ቅዱስ ጴጥሮስ በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በየዋሕነትና በፍርሃት ይሁን (፩ኛ ጴጥ. ፫፡፲፭) ያለውን ፍርሃትና የዋህነት የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤ ዳግም የወንጌልን ምሥጢር በግልጥ እንዳስታውቅ አፌን በመክፈት ቃል ይሰጠኝ ዘንድ፣ ስለ እኔ ለምኑ፤ ስለ ወንጌልም በሰንሰለት መልእክተኛ የሆነው መናገር እንደሚገባኝ ስለ እርሱ በግልጥ እናገር ዘንድ ለምኑ በማለት እንዳስተማረው፡፡

አባ ጊዮርጊስ በመጽሐፉ ለአሕዛብ፣ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለሚታወቁ መናፍቃንና በዘመኑ ለተነሡ እንደ ቢቱ ላሉ መናፍቃን መልስ ሰጥቷል፡፡ አጠቃላይ መልስ የሰጠባቸውን ርእሰ ጉዳዮች ስናይ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፣ ነገረ ክስቶስ፣ ነገረ መንፈስ ቅዱስ፣ ነገረ ማርያም ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ በአንድ ማሕቀፍ ሥር የማይጠቃለሉ ለሌሎች ልዩ ልዩ ጉዳዮችም መልስ ሰጥቷል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ መናፍቃንና ከሐዲያን  ላነሧቸው የኑፋቄ ትምህርቶች የሰጠዉን መልስ በማሳየት ምእመናን ከመሰል ክሕደቶች እንዲጠበቁ ማድረግ ነው፡፡ የእኛ ታሪክ አለማወቅ እንጂ አዲስ ኑፋቄም፤ አዲስ ትምህርትም አለመኖሩን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ለሚያጠና በሦስቱ ዓለም አቀፍ ጉባኤያት መልስ የተሰጠባቸውን ኑፋቄዎች አባ ጊዮርጊስ የጻፈውን መጽሐፈ ምሥጢር በቅርቡም መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ እና አለቃ አያሌው ተአምሩ የሰጧቸውን መልሶች ማየት ተገቢ ነው፡፡

ከሐዋርያት ጀምሮ እስከ ዘመነ ሊቃውንት ለተነሡት መናፍቃን የቤተ ክርስቲያን አባቶች መልስ ሰጥተዋል፡፡ ጉባኤ ዘርግተው፣ ተከራክረው መንፍቃንን አሳፍረው መልሰዋል፡፡ ሊቁ አባ ጊዮርጊስ የቀደሙ አባቶችን አክሎና መስሎ ቅዱሳት መጻሕፍትን በመተርጎምና የሊቃውቱን ቃል በማራቀቅ መልስ በመስጠቱ የአባቶቹ የግብር ልጅ መሆኑን አስመሰከረ፤ የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሯችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፣ የኑሯቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው የሚለውንም አሳየን፡፡ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ ከሰጠው ትምህርት መካከልም የሚከተለው ኃይለ ቃል ተጠቃሽ ነው፤ አብ ብርሃን አንደሆነ ወልድም ለሰው ሁሉ የሚያበራ ብርሃን ነው፡፡ ወልድ ብርሃን እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም ፍጹም በሆነ አንድ ጸዳል ያለ ብርሃን ነው፡፡ አብ የማይዳሰስ እሳት እንደሆነ ወልድም የማይያዝ እሳት ነው፡፡ ወልድ የማይያዝ  እሳት እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም በሃይማኖት ሙቀት ቤተ ክርስቲያንን የሚያሞቃት እሳት ነው፡፡ አብ የማይታይ ኃይል እንደሆነ ወልድም ሰው በመሆኑ ካልሆነ በቀር የማይገለጥ ኃይል እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም ከጥፋት ሰዎች መነሣሣት የተነሣ እንዳትናወጽ ቤተ ክርስቲያንን የሚጠብቃት ኃይል ነው፡፡ አብ ፍጹም አምላክ እንደሆነ ወልድም ፍጹም አምላክ ነው፡፡ ወልድ ፍጹም አምላክ እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም በአንድ ኅብር መልክእ ያለ ፍጹም አምላክ ነው፡፡

ከዚህ በመቀጠል መናፍቃን አንሥተዋቸው ሊቁ በመጽሐፈ ምሥጢር ኦርቶዶክሳዊ መልስ የሰጠባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች እናቀርባለን፡፡

፩. ምሥጢረ ሥላሴ

፩.፩ ሰባልዮስ

ሰባልዮስ በአባ ጊዮርጊስ አጠራር ሰብልያኖስ” ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ መናፍቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር አንድ ገጽ ነው፤ አንዱ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን አብ፣ በሐዲስ ኪዳን ወልድ፣ በበዓለ ኀምሳ ደግሞ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ ተገለጠይላል፡፡ በአጭሩአብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ገጽ ነው የሚል የኑፋቄ ትምህርት ያስተማረ መናፍቅ ነው፡፡ በሊቃውንቱ ቋንቋ የሰባልዮስ ኑፋቄ አንድ ገጽ (ሞናርኪያኒዝም) ሲባል ተከታዮች ደግሞ ሰባልዮሳውያን” ይባላሉ፡፡ የሥላሴን አካላት አንድ አድርገው በመናገራቸውም ሰቃልያነ አብ ይባላሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ለሰባልዮስ ከብሉይ ከሐዲስ እየጠቀሰ መልስ ሰጥቷል፡፡ ሊቁ እኛ ግን ሦስት ገጽ አንድ ባሕርይ፣ ሦስት አካል አንድ አምላክ፣ ሦስት ስሞች አንድ እግዚአብሔር እንላለን በማለት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ይመሰክራል፡፡ ሰባልዮስንም ተጠራጣሪ ሆይ እንግዲህ ባንተ ያለውን ክሕደት ትተህ በሥላሴ እመን፤ ለሥላሴ ገጻትም ምስጋናን አቅርብ በማለት ይመክረዋል፡፡

ይቆየን