ዕለታተ ሰሙነ ሕማማት

በመምህር ቸሬ አበበ

ሚያዝያ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

የእግዚአብሔር ቸርነት 

ከአባታችን አዳም በደል ወይም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሠፍታት፣ ወዘተ. በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የኾነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ ጥሮ ግሮ ወጥቶ ወርዶ ለፍቶ ማስኖ የዕለት ጉርስ፣ የቀን ልብስ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ ዅልጊዜ የሰው ልጅ ቢያጠፋ ቢበድል ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳ የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የኾነ አምላክ የጠፋውን ሊፈለግ፣ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ያጣውን ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላምን ሊሰጥ፣ ተስፋ ለሌለው ተስፋን ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኃጢአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም፤ ዲያብሎስን ድል አድርጐ እኛም ዲያሎስን ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ኾነን፡፡

ሰሙነ ሕማማት 

ሰሙን ‹ሰመነ – ስምንት አደረገ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲኾን ትርጕሙም ሳምንት፣ ስምንት ማለት ነው፡፡ ‹ሕማማት› ቃሉ ‹ሐመ – ታመመ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ብዙ ሕማምን ያመላክታል፡፡ ‹ሰሙነ ሕማማት› ስንልም ‹የሕማም ሳምንት› ማለታችን ነው፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ዅሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ለማውጣት ሲል የተቀበለውን መከራ የምናስብበት ወቅት ነው፡፡ ሰሙነ ሕማማት ከዕለተ ሆሣዕና ሠርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኵነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፤ የሚያለቅሱበት፤ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው እግዚአብሔርን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን ለካህን የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ልዩ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልዕት (የምግብ ዓይነቶች) አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ፣ በመጠማት፣ በመውጣት፣ በመውረድ፣ በመስገድ፣ በመጸለይ፣ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ በማሰብ ወቅቱን እናሳልፋለን፡፡ በዚህ ሳምንት አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ቅዱሳት መጻሕፍት በየሰዓቱ ይነበባሉ፡፡ በዚህ ሳምንት መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታህ›› አይሉም፡፡ ሥርዓተ ፍትሐት አይደረግም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት፤ ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመኾኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የሚያሰሙትን የመለከት ድምፅ፤ በዚያች ሰዓት ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ከሞት እንደሚነሡ ለማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜአቸው

ዕለተ ሰኑይ (ሰኞ)

ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ (የቤተ መቅደስ መንጻት) እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው (ማቴ.፳፩፥፲፰-፳፪፤ ማር. ፲፩፥፲፩፤ ሉቃ. ፲፫፥፲፮)፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ፡- ‹‹… ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፡፡ ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም፤›› በማለት በበለስ ስለ ተመሰለው የሰው ልጅ እና በንስሐ ተመልሶ በሕይወት መኖር እንደሚገባው እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያስረዳል፡፡ በለሷ እንደ ጠወለገችና እንደ ተቈረጠች ዅሉ፣ ንስሐ አልገባም አልመለስም የሚሉም የምግባር ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቈረጡ፤ እንደዚሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል፤ ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባር ነው፡፡ ዅላችንም ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት እና ምግባርን አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንኾን፣ ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል መፈጸም ይጠበቅብናል፡፡

ዕለተ ሠሉስ (ማክሰኞ)

ይህ ቀን ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የጥያቄ እና የትምህርት ቀን በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን ‹‹በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ የሚል ነበር (ማቴ. ፳፩፥፳፫-፳፯)፡፡ ጌታችንም «… እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል፤›› ሲል አስተምሯል (ማቴ. ፳፩፥፳፰)፡፡

ዕለተ ረቡዕ

ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ ‹የምክር ቀን› በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ መኾኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ዕለቱ ‹ጸሎተ ሐሙስ› በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትናንና ፍቅርን እንደዚሁም የአገልግሎትን ትርጕም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ዕለቱ ‹ሕጽበተ ሐሙስ› በመባልም ይጠራል፡፡ ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር ባጠበ ጊዜም፡- «… ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን?… እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስኾን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል፤››  በማለት የእርሱን አርአያነት መከተል እንደሚገባ አስተምሯል (ዮሐ. ፲፫፥፲፪-፳)፡፡

ዕለተ ሐሙስ ጌታችን ‹‹… ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው፤ እንካችሁ ብሉ፡፡ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው፤ ከእርሱ ጠጡ፤›› በማለት ምሥጢረ ቍርባንን የመሠረተበት የጀመረበት ቀን በመኾኑ ‹የምሥጢር ቀን› ተብሎም ይጠራል (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱)፡፡ ይኸውም ምእመናን ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን፤ ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው፡፡ አይሁድ ጌታችንን የያዙበት ቀን ስለ ኾነ በዚህ ዕለት በለኆሣሥ (ብዙ የድምፅ ጩኸት ሳይሰማ) የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ መላው ሕዝበ ክርስቲያን የሕጽበት፣ የምሥጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሐ ታጥበው፣ ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዐርብ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «አውቀውስ ቢኾን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት» በማለት እንደ ተናገረው (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፰) ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ንጹሕና ጻድቅ የኾነውን ጌታ ያለበደሉና ያለጥፋቱ በሐሰት ወንጅለው የሰቀሉበት፤ ጌታችንም በፈቃዱ በመስቀል የተሰቀለበት ዕለት ነው፡፡ ይህ ዕለት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ዅሉ መድኃኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልዕልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው (ማቴ. ፳፯፥፴፭-፸፭)፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደ ተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ፤ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ‹‹ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ›› አለ፡፡ እነርሱ ግን ‹‹እኛስ ምን አግዶን?  አንተው ተጠንቀቅ፤›› አሉ፡፡ ይሁዳም ብሩን በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡ የካህናት አለቆችም ብሩን አንሥተው ‹‹የደም ዋጋ ነውና ወደ መባዕ ልንጨምረው አልተፈቀደም፤›› አሉ፡፡ ተማክረውም ለእንግዶች መቃብር የሚኾን የሸክላ ሠሪ መሬት ገዙበት፡፡ ስለዚህ ያ መሬት እስከ ዛሬ ድረስ ‹የደም መሬት› ተባለ (ማቴ. ፳፯፥፫-፱)፡፡

ዕለተ ዓርብ እኛ የሰው ልጆች በዘር ኃጢአት (ቁራኝነት) እንኖርበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመባትና ፍጹም ድኅነት ያገኘንባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ዅልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ የክርስቶስን ሕማሙን፣ ስቅለቱንና ሞቱን የምናስብበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት፤ የሕይወት መቅጫ አርማ ኾኖ ሳለ ለእኛ ግን የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው፤ በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን ስለአገኘን በዚህም ምክንያት ዕለቱ ‹መልካሙ ዓርብ› በመባል ይታወቃል፡፡

ቀዳሚት ሥዑር

ዕለተ ቅዳሜ እግዚአብሔር አምላካችን የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሔዱትን፣ በክንፍ የሚበሩትን እና በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን፣ በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈባት ዕለት ነች፡፡ የመጀመሪያዋ ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፡፡ እግዚአብሔርን ፍጥረታትን ፈጥሮ ከፈጸመ በኋላ ስላረፈባት ‹ሰንበት ዐባይ› (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች፡፡ ይህቺን ዕለት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል፡፡ ዕለተ ቀዳሚት (ሰንበት ዐባይ) በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ እግዚአብሔር ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንዳደረገባት ዅሉ፣ የፍጥረት ርእስ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው አምላካችን ክርስቶስ በመቃብር አርፎባታል (ማቴ. ፳፯፥፷፩)፡፡

ቀዳሚት ሰንበት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር አርፎ የዋለባት ዕለት በመኾኗ ‹ቀዳሚት ሥዑር› ትሰኛለች፡፡ ‹ሥዑር› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለምትጾም (የጾም ቀን በመኾኗ) ነው፡፡ የጌታችን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት ጀምሮ ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እኽል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብና ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

እመቤታችንና ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾምና በመጸለይ ዕለቷን እንዳከበሯት ዅሉ የተዋሕዶ ልጆችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው በማክፈል (በመጾም) እኽል ውኃ ሳይቀምሱ ለሁለት ቀናት ያድራሉ፡፡ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡ በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸምም ካህናቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡ ምእመናን የምሥራች ቄጠማ ያድላሉ፡፡

ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማቆራኘት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ኾነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል (ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)፡፡

ቄጠማ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደ ኾነ ዅሉ፣ አሁንም ‹‹በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ፤›› ስትል ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የኾነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ዅሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከዋዕየ ሲኦል (የሲኦል ቃጠሎ) ወደ ጥንተ ማኅደራቸው ገነት መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡