ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል

መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በሰሙነ ሕማማት ጠቅለል ባለ መልኩ የምናስባቸው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት ‹ዐሥራ ሦስቱ ሕማማተ መስቀል› ይባላሉ፡፡ ለክርስቲያኖች እነዚህን ሕማማተ መስቀል ማወቅና ዘወትር ማሰብ ተገቢ በመኾኑ እንደሚከተለው አቅርበናቸዋል፤

፩. ተኰርዖተ ርእስ (ራስና በዘንግ መመታት)

‹ተኰርዖት› የሚለው ቃል ‹ኰርዐ – መታ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹ርእስ› ደግሞ ራስ ማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን በዘንግ መመታቱንና መቀጥቀጡን የሚገልጥ ነው፡፡ አገረ ገዥው ጲላጦስ ‹‹እኔ ከዚህ ጻድቅ ሰው ደም ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ገርፎ ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች አሳልፎ ሰጥቶት ነበር፡፡ በአይሁድ ሕግ የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም፡፡ እርሱ ጲላጦስ ግን ከገረፈው በኋላ፣ የበደል በደል፣ እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው (ማቴ. ፳፯፥፳፬፤ ማር. ፲፭፥፲፭፤ ሉቃ. ፳፫፥፳፭፤ ዮሐ. ፲፰፥፴፱)፡፡

አይሁድ የእሾኽ አክሊል ጐንጕነው በጌታችን ራስ ላይ ደፍተውበታል፡፡ ራሱንም በዘንግ መትተውታል (ማር. ፲፭፥፲፱)፡፡ የሰው ዘር ከአዳም ጀምሮ በጠላቱ በዲያብሎስ በተጐነጐነ የኃጢአት እሾኽ ራሱ ተይዞ ነበርና ይህንኑ ለማስወገድ ከሰማይ የወረደ ሰማያዊ የኾነ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ አክሊለ ሦክ እንደ ዘውድ ደፋ፡፡ በሲኦል ወድቆ በዲያብሎስ ተረግጦ ራሱ የሚቀጠቀጠውን የሰውን ልጅ ለማዳን መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ራሱን በመቃ ተቀጠቀጠ፡፡ ከራሱ ላይ በሚወርደው ደም ፊቱ ተሸፈነ፡፡

፪. ተፀፍዖ መልታሕት (በጥፊ መመታት)

‹ተፀፍዖ› የሚለው ቃል ‹ፀፍዐ – በጥፊ መታ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲኾን፣ ‹መጥፊ መመታት› ማለት ነው፡፡ ‹መልታሕት› ደግሞ ‹ፊት፣ ጉንጭ› ማለት ነው፡፡ ይኸውም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጃቸው በደም፣ ጣቶቻቸው በበደል በረከሰ በአይሁድ እጅ በጥፊ መመታቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ለሊቀ ካህናት ቀያፋ እውነትን መናገር እንደ ስድብ ተቈጥሮበት አይሁድ ጌታችን መላልሰው ፊቱን በጥፊ መትተውታል፡፡ ፊቱንም በጨርቅ ሸፍነው ‹‹ክርስቶስ ሆይ! በጥፊ የመታህ ማነው? ትንቢት ተናገርልን!›› እያሉ ዘብተውበታል፡፡

በጠላት ዲያብሎስ እጅ ወድቆ በነፍሱ ይቀለድበትና ይንገላታ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ብሎ መድኀኒታችን ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ ወድቆ ተጐሰመ፤ ተንገላታ፤ በጥፊም ተመታ (ማቴ.  ፳፯፥፳፯)፡፡ ጲላጦስ አሳልፎ ከሰጠው በኋላም አክሊለ ሦክ በራሱ ላይ አኑረው ቀይ ልብስ አልብሰው ‹‹የአይሁድ ንጉሥ ሆይ! ሰላም ለአንተ ይኹን!›› እያሉ እየተሳለቁበት በጥፊ መትተውታል (ዮሐ. ፲፱፥፪)፡፡ አላወቁትም እንጂ እርሱ በመንግሥቱ ሽረት፣ በባሕርዩ ሞት የሌለበት የዘለዓለም አምላክ ነው፡፡

፫. ወሪቀ ምራቅ (ምራቅ መተፋት)

‹ወሪቅ› የሚለው ቃል ‹ወረቀ – እንትፍ አለ፤ ተፋ› ካለው ግእዛዊ ግሥ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ‹እንትፍ ማለት፣ መትፋት› ማለት ነው፡፡ ‹ምራቅ› በቁሙ ‹ምራቅ› ማለት ነው፡፡ ወሪቀ ምራቅ፣ አይሁድ በብርሃናዊው በክርስቶስ ፊት ላይ በሚያስጸይፍ ኹኔታ ምራቃቸውን እንደ ተፉበት የሚገልጥ ነው፡፡ በትንቢት ኢሳይያስ ፶፥፮ ላይ ‹‹ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስኩም›› ተብሎ እንደ ተነገረ፣ አይሁድ እየዘበቱ በአምላካችን ላይ ምራቃቸውን ተፍተውበታል (ማቴ. ፳፯፥፳፱-፴፤ ማር. ፲፭፥፲፱)፡፡

በኃጢአት የቆሸሸውን የሰውን ሕይወት ለማጥራት የመጣው ንጹሐ ባሕርይ አምላክ ምራቅ ተተፋበት፡፡ በሥራው ከገነት ተተፍቶ፤ ተንቆ፤ ተዋርዶ የነበረውን የሰውን ልጅ ለማዳን ኃጢአትን ይቅር የሚል እርሱ ጌታችን ያለ ኃጢአቱ ተተፋበት፤ ተናቀ፤ ተዋረደ፡፡ እንኳን በአምላክ ፊት በሰው ፊት እንኳን መትፋት እጅግ ያስነውራል፡፡ እርሱ ግን የኃጢአታችንን ነውር ከእኛ ሊያጠፋ ነውር የኾነውን ምራቅ በትዕግሥት ተቀበለ፡፡

፬. ሰትየ ሐሞት (አሞት መጠጣት)

‹ሰትየ› ማለት በግእስ ቋንቋ ‹ጠጣ› ማለት ሲኾን፣ ‹ሰትይ› ደግሞ ‹መጠጣት› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ‹ሐሞት› የሚለው የግእዝ ቃልም ‹አሞት› ተብሎ በቁሙ ይተረጐማል፡፡ ቃላቱ በአንድ ላይ ‹ሰትየ ሐሞት› ተብለው ሲናበቡ ‹አሞት መጠጣት› የሚል ትርጕም ይሰጣሉ፡፡ ይኸውም ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመልዕልተ መስቀል ሳለ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ መራራ አሞት መጠጣቱን የሚገልጥ ነው፡፡

‹‹ለመብሌ አሞት ሰጡኝ፤ ለጥማቴም ኾምጣጤ አጠጡኝ›› ብሎ ነቢዩ ዳዊትን በመዝሙረ ዳዊት መዝሙር ፷፰፥፳፩ ላይ ትንቢት ያናገረ የነቢያት አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ ‹‹ተጠማሁ›› ባለ ጊዜ ኾምጣጤ በሰፍነግ ሞልተው ወደ አፉ አቀረቡለት፡፡ ውኃ አጠጡኝ ቢላቸው በሐሞት የተደባለቀ የወይን ጠጅ ሊጠጣ አቀረቡለት፡፡ ቀምሶም ሊጠጣው አልወደደም (ማቴ. ፳፯፥፴፬)፡፡ ጌታችንም ኾምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ ‹‹ተፈጸመ›› አለ፡፡ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን በፈቃዱ አሳልፎ ሰጠ (ማቴ.፳፯፥፵፰፤ ማር. ፲፭፥፴፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፴፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፳፱)፡፡

ቢጠጡት ለዘለዓለም የማያስጠማ ውኃ የሚሰጥ አምላክ፤ የተጠማችውን ነፍስ የሚያረካ ጌታ፤ ለዘለዓለም የሚፈልቅ የሕይወት ውኃን የሚያድል ፈጣሪ በተጠማ ጊዜ የፈጠረውን ውኃ እንኳን የሚያጠጣው የሚያቀምሰውም አላገኘም (ኢሳ. ፶፭፥፩)፡፡ ዐርባ ዓመት ሙሉ በቃዴስ በረሃ ሲጓዙ ለነበሩ አባቶቻቸው ከሰማይ መና አውርዶ የመገባቸው፤ ከዐለት ላይ ውኃ አመንጭቶ ያጠጣቸው ክርስቶስ በተጠማ ጊዜ አይሁድ ቀዝቃዛ ውኃ ነፈጉት (ዘዳ. ፲፮፥፩-፳፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፥፫)፡፡ የዝናማት፤ የባሕርና የውቅያኖስ ጌታ በውኃ ጥም ተቃጠለ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሲኦል በረሃ ወድቀው በሕይወት ውሃ ጥም የተቃጠሉትን ነፍሳት ለማርካት ሲል እርሱ ተጠማ፡፡ በኃጢአት ወድቀው፣ በበደል ረክሰው፣ በነፍሳቸው ተጐሳቁለው፣ መራራ መከራን የሚቀበሉትንና ምረረ ገሃነም አፉን ከፍቶ ሆዱን አስፍቶ የሚጠብቃቸውን ዂሉ ለማዳን መራራ ሐሞትን ቀመሰ፤ ኾምጣጣውንም ጠጣ፡፡ የመረረውን የሰው ልጆችን ሕይወት ለማጣፈጥ የመረረውን መጠጥ ተቀበለ፡፡

፭. ተቀሥፎ ዘባን (ጀርባን መገረፍ)

‹ተቀሥፎ› የሚለው ቃል ‹ቀሠፈ – ገረፈ› ካለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን፣ ‹መገረፍ› ማለት ነው፡፡ ‹ዘባን› ደግሞ ‹ጫንቃ፣ ትከሻ፣ ጀርባ› የሚል ትርጕም አለው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጀርባው እስኪላጥ ድረስ ያለ ርኅራኄ የመገረፉን ነገር የሚገልጥ ነው፡፡ ከላይ እንደ ተጠቀሰው በዘመኑ የቅጣት ሕግ መሠረት የተገረፈ አይሰቀልም፤ የሚሰቀል ደግሞ አይገረፍም ነበር፡፡ ቅጣቱን ለማቅለል ዐስቦ ጲላጦስ ኢየሱስ ክርስቶስን ቢያስገርፈውም አይሁድ ግን በግፍ ሰቅለውታል፡፡ ጲላጦስ ‹‹ከደሙ ንጹሕ ነኝ›› ብሎ እጁን ከታጠበ በኋላ ጌታችንን ለአይሁድ አሳልፎ በመስጠት ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› እንዲሉ የታጠበ እጁን መልሶ አቆሸሸው (ማቴ. ፳፯፥፳፰፤ ማር. ፲፭፥፲፭፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጉንጬንም ለጠጉር ነጪዎች ሰጠሁ›› ተብሎ እንደ ተነገረ ጀርባውን ለገራፊዎች አሳልፎ ሰጠ፤ ጽሕሙንም ተነጨ፡፡ በመንፀፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ተጠቅጥቆ በእሳት አለንጋ የሚገረፈውን የሰው ልጅ ለማዳን ሲል ጌታችን ጀርባውን ለግርፋት ሰጠ፡፡ ሥጋው አልቆ አጥንቱ እስኪቈጠር ድረስም ተገረፈ፡፡ አይሁድ አገረ ገዥያቸው ጲላጦስ ላቀረበላቸው ምርጫ ይፈታላቸው ዘንድ ነፍሳትን ከሲኦል የሚያወጣውን ክርስቶስን ሳይኾን ራሱን እንኳን ከምድራዊ ወኅኒ ማውጣት ያልቻለውን ወንበዴውን በርባንን መረጡ፡፡ መገረፍ ይገባው የነበረ በርባን ተለቀቀ፡፡ ይህ ዂሉ የኾነውም የሰው ልጅ ከሚያድነው አምላክ ይልቅ የሚገርፈውንና የሚዘርፈውን ወንበዴ መርጦ ስለተገኘ ነው፡፡ በእርግጥ ክርስቶስ ካልሞተ ዓለም አይድንምና ሳያውቁም ቢኾን መድኃኒታቸውን መርጠዋል፡፡

፮. ተዐርቆተ ልብስ (ከልብስ መራቆት)

‹ተዐርቆተ› ማለት በግእዝ ቋንቋ ‹መታረዝ፣ መራቆት› ማለት ነው፡፡ ይኸውም አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልብሱን መራቆቱን የሚገልጥ ነው፡፡ ፀሐይና ከዋክብትን ብርሃን አልብሶ የፈጠረ አምላክ ለእኛ ሲል ተራቆተ፡፡ ጸጋውን ለዕሩቃን የሚያለብስ አምላክ ለዓለም ድኅነት ሲል ራቁቱን ለፍርድ ቆመ፡፡ ጨለማን ለብሶ ጨለማን ተንተርሶ ይኖር የነበረውን ሰው መልሶ ብርሃን ያለብሰው ዘንድ የብርሃናት ጌታ፣ የዓለሙ ዂሉ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ ተገፈፈ፤ ተራቆተ፡፡ የሲኦል ወታደሮች አጋንንት የሰውን ልጅ ጸጋ ገፍፈውት ነበርና ይህን ጸጋ ለማስመለስ ሲል ጌታችን በአይሁድ ወታደሮች ልብሱን ተገፈፈ፡፡

፯. ርግዘተ ገቦ (ጎንን በጦር መወጋት)

‹ርግዘት› የሚለው ቃል ‹ረገዘ – ወጋ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የወጣ ሲኾን ‹በጦር መወጋት› የሚል ትርጕም አለው፡፡ ‹ገቦ› ማለት ‹ጎን›፤ ‹ርግዘተ ገቦ› ደግሞ ‹ጎንን በጦር መወጋት› ማለት ነው፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን ለሞት አሳልፎ ከሰጠ በኋላ ጎኑን በስለታም ጦር ተወግቷል፡፡ ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፡፡ በዚህ ጊዜ ድኅተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ የሚሰጥ ደምና ውኃ ከጎኑ ፈሰሰ (ዮሐ. ፲፱፥፴፫)፡፡ መላእክትም ደሙን ተቀብለው በዓለም ረጭተውታል፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል ያደርገው ዘንድ ሞተ፤ የሰው ልጅ በዘለዓለማዊ ሞት ተይዞ ነበርና፡፡ ትልቁ ሞት በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየት ነው፡፡ በጌታችን ሞት ግን ሞት ራሱ ድል ተነሣ፡፡ የሞት መውጊያ በኾነ ኃጢአት የሞተውን ሰው ለማዳን ሲል አምላካችን ጎኑን በጦር ተወጋ፡፡ በሰው ልቡና ተተክሎ የነበረውን ኃጢአት ከነሥሩ ነቅሎ ስለ ጣለው ‹‹ሞት ሆይ፥ መውጊያህ የት አለ?›› ተብሎ ተዘመረ፡፡ የሞት መውጊያው ኃጢአት በክርስቶስ ሞት ድል ተደርጓልና (ኢሳ. ፳፭፥፰፤ ሆሴ. ፲፫፥፲፬፤ ፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፶፬-፶፭)፡፡

ከተወጋው ከጌታችን ጎን የፈሰሰው ደምና ውኃም የእግዚአብሔርን ልጅነትና የዘለዓለምን ሕይወት አጥቶ የነበረው ሰው ልጅነቱና ሕይወቱ እንደ ተመለሰለት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጎኑ በፈሰሰው ውኃ ተጠምቆ ልጅነትን፣ ደሙንም ጠጥቶ የዘለዓለም ሕይወትን ማግኘት ይቻላልና (ዮሐ. ፫፥፭፤ ፮፥፶፬)፡፡

፰. ተአሥሮተ ድኅሪት (ወደ ኋላ መታሠር)

‹ተአሥሮት› የሚለው ቃል ‹አሠረ (ሲነበብ ይላላል) – አሠረ› ወይም ‹ተአሥረ – ታሠረ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲኾን ትርጕሙም ‹መታሠር› ማለት ነው፡፡ ‹ድኅሪት› የሚለው ቃል ደግሞ ‹ተድኅረ – ወደ ኋላ አለ› ከሚለው ግሥ የወጣ ነው፡፡ ሁለቱ ቃላት በአንድ ላይ (ተአሥሮተ ድኅሪት) ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት እጆቹን ወደ ኋላ የፊጥኝ መታሠሩን የሚገልጥ ትርጕም ይሰጣሉ፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ለአይሁድ አሳልፎ በሰጠባት በዚያች ዕለት ሻለቃውና ጭፍሮቹ የአይሁድም ሎሌዎች እጁን የኋሊት አሥረው መሬት ለመሬት ጎትተውታል (ዮሐ. ፲፰፥፲፪)፡፡ በኃጢአት ሰንሰለት የኋሊት ታሥሮ ጠላት ዲያብሎስ የሚያፍገመግመውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ ሰውንም ከኃጢአት እሥራት ለመፍታት ሲል መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በጠላቶቹ በአይሁድ እጅ የኋሊት ታሠረ፡፡

ከ ፱ – ፲፫ ያሉት የሕማማተ መስቀል ክፍሎች ደግሞ አምስቱ ቅንዋተ መስቀል ናቸው፡፡

በስምንቱ ሕማማት ላይ ሲደመሩ ዐሥራ ሦስት ይኾናል፡፡ ‹ቅንዋት› የሚለው ቃል ‹ቀነወ – ቸነከረ› ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹መስቀል› ማለት ደግሞ የተመሳቀለ ዕንጨት ማለት ነው፡፡ ‹ቅንዋተ መስቀል› – መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተቸነከረባቸውን አምስቱን ጠንካራ የብረት ችንካሮች (ምስማሮች) የሚገልጥ ነው፡፡ አምስቱ ቅንዋተ መስቀል፡- ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ፤ ሮዳስ በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህም የአምስቱ አዕማደ ምሥጢራት ምሳሌዎች መኾናቸውን አበው ያስተምራሉ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡