ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር

ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

ሊቀ ልሣናት ቀሲስ ከፍያለው ጥላሁን

ሥነ ምግባር፡- ማለት ደግነት፣ በጎነት፣ መልካም ጠባይ ማለት ሲሆን ክርስቲያን የሚለው ቃል ሲጨመርበት ደግሞ የተሟላና የተለየ ያደርገዋል፡፡ መልካም ጠባይ ማንም ሰው ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የተሟላ ዘላቂና የሁል ጊዜ ሆኖም ለሰማያዊ መንግሥት የሚያበቃው በክርስትና እምነት ሲኖሩ ነው፡፡

ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፡- በምድር እያለን ሰማያዊ ኑሮ ኖረን ለሰማያዊ መንግሥት የምንበቃበት ሕይወት ነው፡፡ ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስደሰት ነውና፡፡ በመሆኑም ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሚከተሉት ሕግጋት ሊለካ ይችላል፡፡

 

1.    ሕገ እግዚአብሔር

መጀመሪያውና ዋነኛው የክርስቲያን ሥነ ምግባር መለኪያው ቃለ እግዚአብሔር ነው፡፡ አንድ ሰው ምናልባትም ሕይወቱ በሰው ፊት ሲታይ የማያስደስት በአፍአ ያለው ጠባዩ እንከን የማይወጣለት ሊሆን ይችላል፡፡ በሕገ እግዚአብሔር ተመዝኖ ካላለፈ ዋጋ የለውም በሰው ፊት መልካም ሆኖ የሚታይ ምግባር እግዚአብሔርን ሊያስደስት ያስፈልጋል፡፡ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች እንጂ ለሰው ደስ እንደምታሰኙ ለታይታ የምትገዙ አትሁኑ፡፡” ፌፌ.6፥6

 

ፈሪሳውያን ከእነርሱ ውጪ የሆነውን ሁሉ የናቁ ያለእኛ ሕገ እግዚአብሔርን አክባሪ ከእኛም በላይ ጻድቅ የለም ባዮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዞችና ሥራቸው ሁሉ ከንቱ እንደሆነ ነገራቸው፡፡ እንዲያውም “ጽድቃችሁ ከጻፎችና ከፈሪሳውያን ጽድቅ ካልበለጠ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም” ማቴ.5፥20 በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስጠነቀቀ፡፡ እንዲያውም ከእነርሱ እርሾ /ትምህርት/ እንዲጠበቁ አስጠነቀቃቸው፡፡ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ ተጠንቀቁና ተጠበቁ” ማቴ.16፥6 አለ፡፡ ከዚህም ሌላ ብዙ ሠርተናል ሥነ ምግባራችን አስደሳች ነው እያሉ ለመወደስ በኩራት ይቀርቡ የነበሩትን ሁሉ አፍረው እንዲመለሱ አድርጓል፡፡ ማቴ.19፣16-22

 

የንጉሥ ሳዖል ሥራ በራሱ በንጉሡ አሳብ ሲመዘን ምክንያታዊና ትክክልም ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔርን ሊያስደስት አልቻለም፡፡ ቃሉን ስላላከበረ ለእርሱም ስላልታዘዘ ንቀኸኛልና ንቄሃለሁ ተባለ፡፡ ከንግሥናውም ወረደ፡፡ 1ሳሙ.15፥10-22 “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይቻልም፡፡” ዕብ.11፥6

 

ክርስቲያን በጉዞው ሁሉ በጭፍን በራሱ እውቀት ብቻ አይመራም፡፡ በቃለ እግዚአብሔር ሕይወቱን እየመዘነ ሊራመድ ያስፈልጋል፡፡ “በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ ራሳችሁን ፈትኑ፡፡” 2ቆሮ.13፥5 የክርስትና እምነት እያጸኑና እየጠነከሩ እየበሰሉ የሚጓዙበት ሕይወት ነው፡፡ በመሆኑም አንድ ክርስቲያን ከትላንት ዛሬ ከአምና ዘንድሮ አድጐ ጠንክሮ መገኘት አለበት፡፡ “ንቁ በሃይማኖት ቁሙ ጐልምሱ ጠንክሩ” 1ቆሮ.16 በሃይማኖት መጠንከር ሲባል በጊዜውም /በተመቸ ጊዜ/ አለ ጊዜውም /ባልተመቸ ጊዜ/ መጠንከር ይገባል፡፡ “በጊዜውም አለ ጊዜውም ጽና፡፡” 2ጢሞ.4፥2 እንዲል፡፡

 

ከሰው ሕግ ይልቅ የእግዚአብሔር ሕግ ቅርብ ነው፡፡ ከሰው ሕግ መደበቅ መሸሽ ይቻላል፡፡ ከእግዚአብሔር ግን ማምለጥ አይችልም፡፡ የእያንዳንዱ ሰው ሥራ በእርሱ ዘንድ የተገለጠች ናት፡፡ የጲጥፋራ ሚስት ዮሴፍን ማንም አያየኝም ኀጢአት እንሥራ ብላ ለሁለት ዓመታት ባባበለችው ጊዜ ኩፋ.27፥25 እግዚአብሔር ከእርሱ እንደማይለይ እያንዳንዱም ሥራው በፊቱ የተገለጠ እንደሆነ ያመነው ኀጢአትን እንዴት እሠራለሁ በማለት መለሰለት፡፡ ዘፍ.39፥9፣ መዝ.138፥2-12

 

ስለዚህ ክርስቲያናዊ አኗኗራችን መልካም ምግባራችን ትክክለኛ የሚሆነው በእግዚአብሔር ሲመዘን ብቻ ነው፡፡ ብልጣሶርን “በሚዛን ተመዝነህ ቀለህ ተገኘህ” ዳን.5፥27 የተባለው ለዚህ ነው፡፡ የሰው ልጁ ሕግ ተለዋዋጭና ጊዜያዊ ነው፡፡ ሕገ እግዚአብሔር ግን በዘመናት ብዛት የማይሻርና ቋሚ በመሆኑ ምግባራችን ከዚህ አንጻር ሊለካ ያስፈልጋል፡፡ “እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ፡፡ ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሠላም ነው፡፡” ሮሜ.8፥5‐6

 

2.    ሕገ ልቡና

እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥረው ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ ሁኔታ የሚመራመር ክፉና በጎውን ለይቶ የሚያውቅ አእምሮ ሰጥቶታል፡፡ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፡፡” መዝ.139፥10 እንዲል፡፡ በተጨማሪም “ሕግህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴ ብርሃን ነው፡፡”መዝ.118፥105 ብሏል፡፡ ሕግ ለሙሴ ከመስጠቱ በፊት ደጋግ አባቶች በዚህ ሕግ እየተመሩ እንደሚገባ ኖረዋል፡፡

 

የሰው ልጅ ማንም ባያስተምረውና ባይነግረው የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ያውቃል፡፡ “እያንዳንዱ ሰው ባልንጀራውን እያንዳንዱም ወንድሙን እግዚአብሔርን እወቅ ብሎ አያስተምርም ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ያውቁኛልና ይላል እግዚአብሔር፡፡” ኤር.31፥34 ምሳሌ አቤል “ከበጎቹ በኩራትና ከላቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ ወደ ቃየል እና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፡፡” ዘፍ.4፥4-5 ሄኖክ “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ስላደረገ አልተገኘም እግዚአብሔር ወስዶታልና፡፡” ዘፍ.5፥24 ኖኅ “ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ አገኘ በትውልዱ ጻድቅ ፍጹምም ሰው ነበረ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ፡፡” ዘፍ.6፥9 እነዚህና ሌሎችም በሕገ ልቡና ተመርተው መልካም ተግባር የፈጸሙና እግዚአብሔርም ሥራቸውን የወደደላቸው ናቸው፡፡ ዕብ.11፥4-7

 

የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር በራቀ ቁጥር ግብሩ ወደ እንስሳነት ይለወጥና የሚወቅሰው ኅሊና እንኳን ያጣል፡፡ “የሰው ልጅ ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ፡፡” መዝ.48፥12 ናቡከደነፆር በበደል ላይ በደል በመጨመሩ ለእግዚአብሔር ሕግ አልገዛም በማለቱ ግብሩ ሁሉ የእንስሳ ሆነ፡፡ ዳን.4፥32 ስለዚህ ክርስቲያን በመጽሐፍ ከተዳፈነው የእግዚአብሔር ሕግ በተጨማሪ በልቡናው ለተቀረጸው ሕግ ይገዛል፡፡ ራሲንም እየመረመረ ይጓዛል አጥፍቶም እንደሆነ ማንም ሳይፈርድበት በራሱ ላይ ይፈርዳል፤ ንስሐ ይገባል የጠፋው ልጅና በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ለዚህ ምስክር ይሆኑናል፡፡ ሉቃ.15፥11-19፣ ሉቃ.23፥41

 

3.    የሰው ሕግ

ይህን በሁለት ከፍሎ መመልከት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የአንድ ሀገር መንግሥት ወይም የሚያስተዳድር አካል ሕዝቡን ለማስተዳደር የሚያወጣው ሕግ ከሆነ ሁለተኛው ደግሞ ኅብረተሰቡ በባሕሉ ትክክል ነው ብሎ የተቀበለውና በወረቀት ያልተጻፈው ሕግ ነው፡፡ “በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን የተማራችሁትን ወግ ያዙ” 2ተሰ.2፥15 እንዲል፡፡

 

ክርስቲያን ለእግዚአብሔር ሕግ እንደሚገዛ ሁሉ የሰውንም ሕግ ከእግዚአብሔር ጋር እስከ አላጣላው ድረስ ሊያከብር ይገባል፡፡ አንድ ሰው ምንም ብጾም ብጸልይ፣ ለእግዚአብሔር እገዛለሁ ቢል የሚያስተዳድረውን አካልና የኅብረተሰቡን መልካም ባሕል ካፈረሰ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባሩን ጎደሎ ያደርገዋል፡፡ በሥራ ቦታ የታዘዘውን ካልፈጸመ፣ የሥራ ሰዓት ካላከበረ፣ በቤተ ክርስቲያን ያለውን ምግባሩን በሌላ ሥፍራ ካልገለጸው ዋጋ አይኖረውም፡፡ ለእግዚአብሔር እንደሚገዛ ሁሉ በሰውም ፊት ያለነቀፋ ሊኖር  ያስፈልጋል፡፡ “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ በእነርሱም መካከል የሕይወት ቃል እያቀረባችሁ በዓለም እንደ ብርሃን ትታያላችሁ” ፊል.2፥15

 

ሐዋርያው ከዚህም በተጨማሪ “ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን በእግዚአብሔር ፊት ብቻ ያይደለ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን እናስባለን” ብሏል፡፡ 2ቆሮ.8፥20 ይህ ሲባል ኀጢአትም ሲሆን የሰው ሕግ ወይም ባሕል ነውና ሁሉን መፈጸም አለበት ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ያስፈልጋል፡፡

 

ለምሳሌ ከአንድ በላይ ማግባት፣ ጫት መቃም፣ ዋርሳ መያዝ፣ ባሕል በሆነበት አካባቢ የሚኖር ክርስቲያን ከሰው ጋር ለመኖር በሚል ሰበብ ይህንና ይህን የመሰለ የአረማውያኑን ኑሮ ይኑር ማለት አይደለም፡፡ እንዲያውም ክርስቲያን በእንዲህ ዓይነት ሰዎች መካከል ሲኖር የቅድስናን ሕይወት በተግባር በመኖር ማንነቱን ሊገልጥ ያስፈልጋል፡፡ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፡፡” ማቴ.5፥16

 

ከዚህ አንጻር ብዙ ወጣቶች ሕገ እግዚአብሔርን ከኑሮአቸው ጋር አጣጥመው መጓዝ ሲከብዳቸው ይታያሉ፡፡ በእምነት የጸኑትን ሠለስቱ ደቂቅን፣ ዮሴፍን ሶስናን አይመለከቱም፡፡ እንኳን ክርስቲያን የሚለውን ስም የተሸከሙ ሲጠራም የሰሙት የማይመስሉ አሉ፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሰውና በእግዚአብሔር ፊት የምንኖረው ኑሮ እንደመሆኑ መጠን የግል መንፈሳዊ ሕይወትና ማኅበራዊ ኑሮ በማለት በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን፡፡

 

ሀ. የግል መንፈሳዊ ሕይወት፡-

የግል መንፈሳዊ ሕይወት ማለት እኛ ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት የሚኖረን ሕይወት ነው፡፡ ይህም ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን ግንኙነት ይመሠረታል፡፡ አንድ ሰው ፍቅሩ እግዚአብሔር ከሆነ ምግባሩ መንፈሳዊ ሕይወቱ ይህንኑ የሚገልጥ ይሆናል፡፡ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረው ሕይወት የጠበቀ ለማድረግ ከሚያስፈልጉት ነገሮች ውስጥ ቃለ እግዚአብሔር፣ ንስሓ፣ ቅዱስ ቁርባን፣ ጸሎት ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡

 

ቃለ እግዚአብሔር ለአንድ ክርስቲያን የሕይወት መስመሩን የሚያቃናለት ነው፡፡ “ቃልህ ተገኝቷል እኔም በልቸዋለሁ አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ በስምህ ተጠርቼአለሁና ቃልህ ሐሴትና የልብ ደስታ ሆነኝ፡፡” ኤር.15፥16

 

ንስሓ ማለት መጸጸት ማለት ነው፡፡ የክርስትና ሕይወት የንስሓ ሕይወት ነው፡፡ በንስሓ የበደለ ከበደሉ ይነዳል፡፡ ኀጢአተኛውም ጻድቅ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ለግል መንፈሳዊ ሕይወት ሥራችሁን አቅኑ፡፡” ኤር.18፥11 ከንስሐ በኋላ ቅዱስ ቊርባን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ “የሰውን ልጅ ሥጋ ካልበላችሁ ደሙንም ካልጠጣችሁ ሕይወት የላችሁም፡፡” ዮሐ.6፥53

 

እንግዲህ ቃሉን ሰምተን ንስሓ ገብተን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ስንቀበል የግል መንፈሳዊ ሕይወታችን የተስተካከለ ይሆናል፡፡ የግል መንፈሳዊ ሕይወት ጽናት ደግሞ ለማኅበራዊ ኑሮአችን ወሳኝ ነውና፡፡ “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አሳብ ይህንም አዘውትር፡፡ ለራስህና ለትምህርትህ ተጠንቀቅ፡፡ በእነዚህ ጽና ይህን ብታደርግ ራስህንም የሚሰሙህንም ታድናለህ፡፡” 1ጢሞ.4፥15

 

ለ. ማኅበራዊ ኑሮአችን

ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮው ከሌሎች ጋር በሠላምና በፍቅር ሊኖር እንዲሁም አልጫውን ዓለም በምግባሩ ሊያጣፍጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያን በማኅበራዊ ኑሮ ተሳትፎ ውስጥ ሊይዝ  የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ እነዚህም፡-

 

ዓላማ፡- ክርስቲያን እንደ ውኃ ላይ ኩበት እየተንሳፈፈ ወንዙ ወደ ሚወርድበት አቅጣጫ አይጓዝም፡፡ እንደሚወዛወዝ ዛፍም ወደ ነፈሰበት አያጋድልም፡፡ የራሱ የሆነ ውሳጣዊ ዓላማና አቋም አለው፡፡ “በምትሄድበት ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፡፡” ኢያሱ.1፥7 ከዚህ የተነሣ የሚሠራውን በጽናትና በትጋት ይሠራል፡፡ የጀመረውን ከፍጻሜ ያደርሳል፡፡ በመከራ አይናወጥም፡፡ መስሎ ለማደር እንደ ጊዜው አይለወጥም፡፡ በዓላማ ስለሚጓዝ ዓላማውን ያሳካል፡፡

 

ክርስቲያን ምን ዓይነት ዓላማ ሊኖሩት ያስፈልጋል?

መንግሥተ ሰማያትን መውረስ፡- አንድ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጣው ለጊዜያዊ ችግሩ ብቻ መፍትሔ ለማግኘት አስቦ ሳይሆን ሰማያዊ ክብርና ዋጋ ለማግኘት ነው፡፡ “ድንኳን የሆነው ምድራዊ መኖሪያችን ቢፈርስ በሰማይ ያለ በእጅ ያልተሠራ የዘለዓለም ቤት የሚሆን ከእግዚአብሔር የተሠራ ሕንፃ እንዳለን እናውቃለን፡፡ 2ቆሮ.5፥1

 

የሚታወቅና ግልጽ ዓላማ፡- ክርስቲያን ያለ ዓላማ በጭፍን አይጓዝም፡፡ ሳይታሰብ በድንገት በአጋጣሚ የሚል ነገር በርሱ ዘንድ እምብዛም ቦታ አይኖረውም፡፡ የሚታወቅ ግልጽ ዓላማ ኖሮት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሳካለት ይጸልያል፡፡ “ሳታቋርጡ ጸልዩ፡፡” 1ተሰ.5፥18 ከዚህ አንጻር አንዱን ዓላማው አድርጎ ይጓዛል ጋብቻ ወይም ምንኩስና መካከል ሆኖ አያወላውልም፡፡

 

ራስን መግለጽ፡- ክርስቲያን በሄደበት ሁሉ ማንነቱን መግለጥ አለበት፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ መሰወር አትችልም፡፡ ይህም ሲባል እኔ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን ነኝ እያለ በማወጅ ወይም በማስታወቂያ ሳይሆን አኗኗሩ ማንነቱን ይገልጠዋል፡፡ ይህም ኑሮው በቤተሰብ፣ በት/ቤት፣ በሥራ ቦታ፣ በአካባቢው ኅብረተሰብ ዘንድ ወዘተ…… መገለጥ አለበት፡፡

 

ታማኝነት፡- እውነተኛ ክርስቲያን ምሎ የማይከዳ፣ አደራ የማያጠፋ፣ የማያወላውል ለምስክርነት የሚበቃ ነው፡፡ ታማኝ ሰው መልካም የሚለውን ይናገራል፡፡ የሚናገረውን ይሠራል በሓላፊነት ቢቀመጥ ያለ አድልዎ ወገናዊነት ያስተዳድራል፡፡ “በጥቂቱ ታምነሃል በብዙ እሾምሀለሁ፡፡” ማቴ.25፥21 ይባልለታል፡፡ ታማኝነት ለራስ ታማኝ መሆን ለእግዚአብሔር ሰዎች በመታመን ይገለጣል፡፡ ይህም በትዳር፣ በሥራ፣ በተሰጠው ሓላፊነት መታመን አለበት፡፡ ምሳሌ ዮሴፍ ዘፍ.39፥9

 

ፍቅር፡- ክርስቲያናዊ ፍቅር የያዘ ሰው በሰውና በእግዚአብሔር ፍቅር ያለነቀፋ ይኖራል፡፡ ፍቅር የክርስቲያንነታችን መገለጫ ነው፡፡ አምላክን ከዙፋኑ ያወረደው ራሱንም እስከ ሞት አሳልፎ ለሰው ልጅ እንዲሰጥ ያደረገው ፍቅር ነው፡፡ ስለዚህ አንደ ሰው ፍቅር ከሌለው ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር የለውም ማለት ይቻላል፡፡ የምናፈቅረው ማንን ነው?

 

እግዚአብሔርን፡- እግዚአብሔርን ማፍቀር ሲባል እግዚአብሔርንና የእርሱ የሆነውን ሁሉ ማፍቀር ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ፍቅረ እግዚአብሔርን በሁለት ከፍለን ማየት እንችላለን፡፡

 

  1. ትእዛዙን ማክበር፡- እግዚአብሔርን መውደድ ትእዛዛቱን በመፈጸም ይገለጣል፡፡ “ትእዛዙ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፡፡” ዮሐ.14፥21

  2. የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ መውደድ ይህን በሦስት ከፍለን መመልከት እንችላለን

2.1.    ቅዱሳንን መውደድና ማክበር፡- ቅዱሳን እግዚአብሔር የመረጣቸው ያከበራቸውና የወደዳቸው ናቸው፡፡ “የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኗልና አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው የጠራቸው እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው ያጸደቃቸው እነዚህን ደግሞ አከበራቸው፡፡” ሮሜ.8፥29 ፍቅረ እግዚአብሔር የእርሱ የሆኑ ቅዱሳንን በማክበር እንገልጻለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር የትሕትናና የኦርቶዶክሳዊነት ውጤት ነው፡፡

2.2.   ሀገርን መውደድ፡- ሀገር የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሰጠው ሀገር ሆኖ እርሱን ሊያመሰግን ሀገሩን ሊወድ ግዴታ አለበት፡፡ ሀገር ከሌለ ሠላም ካልሆነ እግዚአብሔርን በደስታ ማመስገን አይቻልምና፡፡ “ኢየሩሳሌም ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ ባላስብሽ ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድ፡፡” መዝ.136፥5

2.3.   ቤተሰብን መውደድ፡- ክርስቲያን እምነትን፣ ምግባርን፣ ሥርዓትን በመጀመሪያ የሚማረው ከቤተሰቡ ነው፡፡ ቤተሰብ የመጀመሪያዎቹ ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡ ነቢዩ ሙሴ የእግዚአብሔርን፣ የወገንን፣ የሀገርን ፍቅር የተማረው ከእናቱ ነውና፡፡ ወልደው፣ አሳድገው፣ አስተምረው ለትልቅ ደረጃ ያበቁትን ቤተሰቡን ክርስቲያን ሊወድ ይገባዋል፡፡ “ስለ ቤተሰቦቹ የማያስብ ማንም ቢኖር ሃይማኖትን የካደ ከማያምን ሰው ይልቅ የከፋ ነው፡፡” 1ጢሞ.5፥8

3.   የሰው ልጆችን ሁሉ ማፍቀር፡- /ፍቅረ ቢጽ/ የሰውን ልጅ ሁሉ ማፍቀሩ ፍቅረ ቢጽ ይባላል፡፡ ይህም በሥላሴ አርአያ የተፈጠረውን ሰው ሁሉ መውደድና ማፍቀር ነው፡፡ ይህም ኀጥእ ጻድቅ፣ አማኒ መናፍቅ፣ ዘመድ ባዕድ ሳይሉና ሳይለዩ ሁሉን አስተካክሎ መውደድ ነው፡፡ ይህም ትእዛዝ ጠላትን እስከመውደድ በመድረስ ነው፡፡ “በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ የሚረግሟችሁን መርቁ፣ ለሚጠሏችሁ መልካም አድርጉ ስለሚያሳድዷችሁ ጸልዩ፡፡” ማቴ.5፥44

 

በአጠቃላይ ክርስቲያን ከአለባበሱ ጀምሮ ውጫዊ አቋሙም ሆነ አጠቃላይ ሕይወቱ በማናቸውም ጊዜና ቦታ ሁሉ ክርስቲያንነቱን ሊገልጡ ይገባቸዋል፡፡ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ኖረው ለሰውም ብርሃን ሆኖ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር የሆኑትን አስደሰተ የሚባለው ያን ጊዜ ነው፡፡ እንግዲህ ክርስቲያን በምድር ሲኖር በግል ሕይወቱም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮው ምን መምሰል እንዳለበት ራሱን ከላይ በተገለጸው በሦስቱ ሕግጋት አንጻር እየመረመረ መጓዝ አለበት፡፡ በግል ሕይወቱ ዘወትር ንስሓ እየገባ ቅዱስ ቁርባን በመቀበል እየጾመ፣ እየጸለየ፣ እየመጸወተ ሰማያዊ መንግሥትን ተስፋ በማድረግ ይጓዛል፡፡ በማኅበራዊ ኑሮውም ደግሞ ሰዎችን በሐዘናቸው ጊዜ ማጽናናት፣ በደስታቸው ተካፋይ መሆን፣ ከቸገራቸው ለችግራቸው ደራሽ በመሆን እውነተኛ ፍቅሩን ሊገልጽ ያስፈልጋል፡፡ “የኢየሱስ ሕይወት ደግሞ በሥጋችን ይገለጥ ዘንድ ሁል ጊዜ የኢየሱስን መሞት በሥጋችን ተሸክመን እንዞራለን፡፡” 2ቆሮ.4፥10