ከታሪክ አንድ ገጽ

እንደዚህ ሆነ፡፡
በአንዲት መንደር ውስጥ አንድ ሰው ነበረ፡፡ አንደበቱ ከጸሎት እጁ ከምጽዋት ልቡ ከጠዋሐት ተለይቶ የማያውቅ፤ ሰው ተጣላ ማን ያስታርቅ፣ ልጅ አገባ ማን ይመርቅ ቢባል በመጀመሪያ የሚጠራው እርሱ ነው፡፡

ለሽማግሌዎች መኩሪያ ለታዳጊዎች አርአያ መሆንን የሚያነሣ የለም፡፡ ኃጢአትን ሊሠራት ቀርቶ ስሟን ያውቃታል ብሎ የሚገምት የመንደሩ ነዋሪ ከማግኘት አንድ ቀን ሰይጣን ሊመለስ ይችላል ብሎ ተስፋ የሚያደርግ ማግኘት ይቀላል፡፡
ለብዙዎች መለወጥ፣ ለብዙዎች ለጽድቅ መመረጥ፣ ለብዙዎች ከዓለም መመለስ፣ ለብዙዎች ዓለምን ጥሎ መመንኮስ አንድም መሪ ያለያም አበረታች መካሪ እርሱ ነው፡፡
የተናገረው ከልቡና ያስተማረው ከኅሊና ጠብ ሲል ልብ ያደርሳል ኩላሊት ያድሳል፡፡
ያለ ሠርክ ሰዓት እህል የማይቀምስ ያለ ተርታ ነገር ነጠቅ መንጠቅ ያለ የማይለብስ መሆኑን በአካባቢው ሐይቅ ስለሌለ የባሕር ዓሦች ካልሆኑ በቀር የማይመሰክር ፍጥረት አለ ማለቱ ይቸግራል፡፡

ትዳሩን አክባሪ ባለቤቱን አፍቃሪ በመሆኑ ከአብርሃምና ከሣራ ቀጥሎ ለሰርግ ምርቃት እርሱና ባለቤቱ ሳይጠሩ አይውሉም፡፡ አንድ ቀን ከቤተክርስቲያን መልስ ወደ ቤቱ በማምራት ላይ እያለ ዓይኑን ዓይኑ አንድ የማይወራውን ነገር ተመለከተ፡፡ አንድ አገር ያስቸገር መናፍቅ ከርሱ ቤት ግቢ ወጣ፡፡ ለምን?

 
ባለቤቱን አግኝቶ እስኪጠይቃት ነፍሱ የቸኮለችውን ያህል የመኪና እሽቅድድም ተወዳዳሪዎች ቸኩለው አያውቅም፡፡ ገባ፤
‹‹ ይኸ ሰውየ እንዴት መጣ?››
‹‹ ረጋ በልና አስረዳሃለሁ፡፡››
‹‹ ለመናፍቅ ምን እርጋታ ያስፈልገዋል››
‹‹ እኮ ረጋ በል››
‹‹ ለምን ታረሳሽኛለሽ?››
‹‹ ምኑን?›› የሆነ ነገር ብልጭ አለበት፡፡ ሰይጣን እሳት ጫረና ቤንዚን ለቀቀበት፡፡
‹‹ምን ሊሰራ መጣ?››
‹‹ለምን ትቆጣለህ?›› ሰይጣን እሳቱን እፍ በማለት ላይ ነው፡፡
እርስዋ ራስዋ ሰይጣን መስላ ታየችው፡፡ ደክሞታል፡፡ ተናዷል፡፡ ዝሏል፡፡ አእምሮው ዕረፍትን ብቻ ነበር የሚሻው፡፡ ውሳኔ ለመስጠት፤ ነገር ለማመዛዘን ዐቅሙም አልነበረውም፤ ብቻ ሳይሆን ዐቅሙ እንደሌለውም አላወቀም፡፡ አደርጎት የማያውቀውን ዓይኑን አጉረጠረጠና ገፈተራት፡፡ ወደ ኋላ ተንደረደረችና አንገትዋ ኮመዲኖው ጠርዝ ላይ አረፈ፡፡ በስተመጨረሻም መሬት ላይ ተኛች፡፡ ላንዴም ለመጨረሻም፡፡
ነቃ፣ ነቃና አያት፤ ያደረገውን ለማስታወስ ሞከረ፡፡ እርሱ ወይስ ሌላ ሰው? ምንድን ነው የፈጸመው? ሚስቱን ገደላት ማለት ነው? ገዳይ-ወንጀለኛ-ጨዋ-ሰላማዊ-አርአያ-ምሁር- መምህር-ገዳይ-ወንጀለኛ፡፡
ጮኸ – ከማለት ይልቅ የጩኸቱ ደምጽ ፈነዳ ማለቱ ይቀላል፡፡ አካባቢው በሰው ተጥለቀለቀ፡፡
 
እርሱ ያለቅሳል፡፡ ሰውም ያለቅሳል፡፡ አለቃቀሳቸው ግን ለየቅል ነበር፡፡ አንዱ ‹‹ክፉ ተናግራው መልአክ ቀስፏት ነው፡፡ ይላል፡፡ አንዱ ደግሞ ‹‹ የጻድቅ ሰው ዕንባ፡፡ ድሮም የማይናገር ሰው ዕንባው ሰይፉ ነው፡፡›› ሌላው ‹‹ አሁንኮ ወይ እማታለሁ ወይም እገላለሁ ብላ ይሆናል፡፡ ይቺ ሰው መሳይ በሸንጎ የርሱ ደግነት ክፋቷን ሸፍኖላት ዛሬ እግዜር አጋለጣት፡፡›› እርሱ ይገላል ቀርቶ ዝንብ ያባርራል ብሎ የጠረጠረ የለም፡፡ ወንጀሉ ሁሉ የርስዋ ሆነ፡፡
እርሱ ግን የደም ዕንባ አለቀሰ፡፡ የሰዎችን ንግግር በሰማ ቁጥር ዕንባው ይጨምር ነበር፡፡ ‹‹እኔ ነኝ እኔ ነኝ እኔ ነኝ›› አለ ድምፁን ከፍ አድርጎ፡፡
‹‹አይ የዋህ ሰው፡፡ ከባቴ አበሳ አይደል፡፡ ስሟ በክፉ እንዳይነሳ ብሎእኮ ነው›› ይላል አንዱ፡፡
‹‹ስላዘንኩባት ነው ማለቱኮነው›› ቀጠለ ሌላው፡፡ ሊያምነው ቀርቶ ሊሰማው የወደደ የለም፡፡ ሰው የሚናገርለት እና እርሱ የሆነው እየተጋጨበት ኅሊናው ዞረ፡፡ ማን ይመነው፡፡
ለያዥ ለገራዥ ቢያስቸግርም በሽማግሌ ጥረት ሊቀመጥ ቻለ፡፡ ‹‹አይዞህ አንተ አልገደልካት እግዜር መታት እንጂ›› ይሉታል ሽማሎች ሰብሰብ ብሎው፡፡ ያ ለርሱ መርፌ ነው ልብ የሚወጋ፡፡
‹‹እንዲያው እግዚአብሔርን ማመስገን አለብህ፡፡ ፊትህ ላይ ተአምሩን ሲያሳህ›› ሲሉት ደግሞ የተወጋው ልቡ መድማት ጀመረ፡፡
‹‹እኔ አይደለሁም እንዴ አለና መጠራጠር ያዘ፡፡›› አሰበው /ድርጊቱን ሁሉ አሰበው/ ነው እርሱ ነው እኔ ነኝ፡፡ እኔ ነኝ ገዳይዋ- ተንሰቀሰቀ፡፡
‹‹ወይ ግሩም ጻድቃን የወንድማቸው ኃጢአት ከሚገለጥ የራሳቸው ኃጢአት ቢገለጥ የተባለው ደረሰ።›› አሉ አንዲት ወይዘሮ፡፡
‹‹የነ አባ እንጦንስ ታሪክ ሲደገም በዓይናችን አየንኮ›› ሌላዋ ተቀበሉ፡፡
ማን ይመነው፡፡ የልቡን ማን ይወቅ፡፡ እሳት እየከመሩበት መሆኑን ማን ይረዳ፡፡
ጊዜያት ነጎዱ፡፡ ሰው ሁሉ ሊረሳው ጀመረ ጉዳዩን፡፡ እርሱ ግን የሚንተገተግ እሳት ሆኖበታል፡፡
በመጨረሻ እንዲህ ወሰነ፡፡ ለአንድ ለሚወደው ጓደኛው ሊነግረው፡፡ ሐሳብ ቢከፍልልኝ ምክር ቢለግሰኝ ብሎ፡፡
ያደረገውን፡፡ የሆነውን ሁሉ ነገረው፡፡ እየማለ እየተገዘተ የጓደኛው ፊት ሲለዋወጥ ታየው ነጣ- ከዚያ ቀላ መጨረሻ ላይ ጠቆረ፡፡ ‹‹ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ….ለካ አንድ ሰው የለም ባገሩ፡፡ አንተ ስናምንህ ስናከብርህ- ለካ አውሬ ኑረሃል…›› ሰቀጠጠው፡፡ እናም ሸሸው ‹‹ ለኔም ፈራሁህ ››
‹‹እኔኮ የነገርኩህ… ›› አላስጨረሰውም ‹‹ዝም በል!››
ልቡ  ሌላ ነገር ፀነሰ፡፡ የነገርኩት እንዲቀልድብኝ አይደለምኮ አለና ‹‹ባይሆን ነገሩን በልብህ ያዘው›› ሲል ለመነው፡፡
‹‹ገና በአደባባይ ትሰቀላለህ›› ሲል መለሰለት፡፡
ብልጭ አለበት- ሰይጣን እሳት ጫረ፡፡ ዓይኑ ዘወር ዘወር አለ ክትክታ አነሣና ሠነዘረ፡፡ ተጥመልምሎ ወደቀ፡፡ ትኩር  ብሎ ሲያየው ነፍሱ ሸሽታዋለች፡፡ እያለቀሰ፡ ደረቱን እየደቃ ወጣ፡፡ ከቤቱ ብቻ ሳይሆን ከመንደሩ ወጣ፡፡ ወደ በረሃው ሰው ወደ ሌለበት ዘለቀ፡፡ ልክ መንገዱን ሲጨርስ አንድ ሽማግሌ አገኘ፡፡
‹‹ እንደምን ዋሉ አባቴ ››
‹‹እግዚአብሔር ይመስገን ይኼ ደም ምንድነው ልጄ››ልብሱን አሳዩት ደነገጠ፡፡
‹‹እይውልዎት›› አለና ታሪኩን መናገር ሲጀምር ደነገጡና አፈገፈጉ፡፡
‹‹ ዘወር በል አንተ ሰይጣን፡፡!››
‹‹ ይምከሩኝ አባቴ ምን ላድርግ እባክዎ አያውግዙኝ››
‹‹ ዘወር በል ዲያብሎስ እኔንም እንዳትጨምረኝ››
‹‹እኔ እኮ ከቁስሌ ትፈውሰኝ ብዬ እንጂ በቁስሌ ላይ እንጨት የሚሰሰድማ መች አጣሁ፡፡›› አለና ክትክታውን አነሣ እኒያ ሽማግሌ ወደቁ፡፡
ሰው ሁሉ አውሬ መሰለው፡፡ ልቡ እየደነደነ መጣ፡፡ ‹‹ታዲያ ምን ይሁን›› አለው ሰይጤ ‹‹አንተ የመጀመሪያው አይደለህ ››
‹‹ ካሁን በኋላ ማንም ቁስሌን ሊነካ አይችልም ›› አለና በፍጥነት በረሃውን ማቋረጥ ጀመረ፡፡ ማዶ ማዶ ነው አንድ አረጋዊ ካህን ደበሏቸውን ለብሰው ዛፍ ሥር ተቀምጠው ጸሎት ያደርሳሉ፡፡
‹‹ለመጨረሻ ጊዜ›› አለ ‹‹ለርሳቸው ነግሬ መፍትሔ ካልሰጡኝ፤ በቁስሌ ላይ ዘይት መጨመር ትተው ኮምጣጤ ከደፉብኝ የሰው ልጅ ሁሉ ጠላቴ ነው ማለት ነው።›› ወሰነ፡፡
ቀና ብለው አዩት፡፡ ያስፈራል ፡፡ ልብሱ ደም ነክቶታል፡፡
‹‹ ምን ሆንክ ልጄ?›› አሉና ከመቀመጫቸው ተነሡ፡፡ ሠይጣን አንድ ርምጃ አፈገፈገ፡፡
‹‹ ተቀመጥ ደክሞሃል›› ድንጋዩን ለቀቁለት፡፡ ሰይጣን ተናደደ፡፡
‹‹ ምን ሆነሃል?››
በዕንባ ጀምሮ በዕንባ ጨረሰው፡፡
‹‹በተሰቀለው ክርስቶስ ዛሬ ጓደኛ አገኘሁ፡፡›› ዕልል አሉ፡፡
ሰይጣን ፈረጠጠና ዛፍ ሥር ተሸጉጦ ማየት ቀጠለ።
በመገረም ተመለከታቸው፡፡ ‹‹ይገርምሀል፡፡ ሚስቴን ገድዬ፤ ልጆቼን አርጄ፣ የሰው ሀብት ዘርፌ፣ ስንት ልጃገረዶች አባልጌ፣ ሰው መቀመጫ ሲነሳኝ ጻድቅ መስዬ እዚህ ተቀምጫለሁ፡፡ ያንተማ ምን አላት፡፡ በኔ አይነትኮ ያንተ በጥቂት ቀኖና ትሻራለች፡፡››
የፊቱ ጥቁረት ቀነሰ
ክትክታው ከእጁ ወደቀ፡፡
‹‹ በል አሁን ካንድ ሁለት ይሻላል፡፡ ሰው እንደሆነ ቂመኛ ነው ይቅር አይለንም፡፡ እግዚአብሔር ግን መሐሪ ነው፡፡ በዚህ ከቀጠልን እኛ ራሳችን ከሰይጣን መብለጣችን ነው፡፡ ስለዚህ ገደል እንቆፍርና እዚያ ውስጥ ገብተን ንስሐ እንግባ፡፡›› አሉት፡፡ ፈነደቀ፡፡ ዘሎ ተነሣና ዐቀፋቸው፡፡ እናም በዚያው ክትክታ መቆፈር ጀመረ፡፡ እጅግ አድካሚ ሥራ ነው፡፡ አባ ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም ይደግማሉ፡፡ ቀና ብሎ አየና እርሱም ጸሎቱን ቀጠለ፡፡
ቀን-ሳምንት-ወር-ሁለት- ሦስት- ወር ፈጀ ቁፋሮው፡፡
ቅጠል ይበላሉ፡፡ አብረው ስለጥንቱ እያወሩ፡፡ ከዚያ ደግሞ ስለ እግዚአብሔር መሐሪነት ያስተምሩታል ዐረፍ ሲሉ፡፡ ይቆዩና ደግሞ ይቆፍራሉ፡፡
በሰው ቁመት ልክ ገደሉ ተቆፈረ፡፡
እንዴት እንግባ፡፡
‹‹አንተ እዚያው ቆየኝ ዕቃውን ሰብስቤ ምግባችንን ይዤ እኔ መጣሁ፡፡›› ተስማማ፡፡
በገመዱ ተንጠልጥለው አባ ወጡ፡፡እላይ ከደረሱ በኋላ ገመዱን ሳቡት፡፡ ደነገጠና ቀና ብሎ አያቸው፡፡
‹‹ ልጄ አሉት አባ›› የነገርኩህ ታሪክ ውሸት ነው፡፡ ‹‹ አንተ እንዳይሰማህ ብዬ ነው ከአሁን በኋላ ምግብህን አመጣልሃለሁ እየሰገድህ፣ እየጾምክ ጸልይ፡፡ እግዚአብሔር ይምራል››  አሉት፡፡ ተናደደ ክትክታው አጠገቡ የለም፡፡ ከግራ ገደል ከቀኝ ገደል አለቀሰ፡፡ አነባ፡፡
‹‹ዕንባ የኃጢአት ክምር ትንዳለች ›› አሉ አባ፡፡
ምንም አማራጭ የለም፡፡ ጸሎቱን ጀመረ፡፡
አባም በዘጠኝ ሰዓት ምግቡን አስበው ያመጡ ነበር፡፡
ከሰባት ዓመት በኋላ አባ ምግቡን ሊያደርሱለት ሲሄዱ ክንፍ አውጥቶ ሲበር አዩት፡፡
 
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ምንጭ፦  ሐመር 7ኛ ዓመት ቁጥር 3 ሰኔ/ሐምሌ 1991 ዓ.ም.