*ከቃል በላይ ትኩረት ለቅዱስ ያሬድ*

ሰኔ ፳፰ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

እሑድ ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ አንድ ልዩ መርሐ ግብር ተካሒዷል፡፡ መርሐ ግብሩን ያዘጋጀው የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ሲኾን፣ ዓላማውም የቤተ ክርስቲያናችን ብርሃን፣ የአገራችን ጌጥ የኾነውን ቅዱስ ያሬድንና ሥራዎቹን መዘከር ነው፡፡

በዕለቱ *ወሰማዕኩ ድምፀ ብዙኃን መላእክት በዐውዱ ለውእቱ መንበር፤ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ* /ራእ.፭፥፲፩/ በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል የሰጡት መጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ *ቅዱስ ያሬድ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእይና በንባብ የነገረንን ሰማያዊ ማኅሌት በዜማ የተረጐመልን፤ ከጠፈር በላይ ያለውን ምሥጢር ለዓለም የገለጠ፤ ቤተ ክርስቲያንን ለምስጋና ያመቻቸ፤ የመላእክትን ዜማ ከሰው ጋር ያስተዋወቀ በአጠቃላይ በተፈጥሮው ሰው፣ በግብሩ መልአክ ነው* ብለው አስተምረዋል፡፡

*እንደ ቅዱስ ያሬድ ያሉ ቅዱሳን የእግዚአብሔር መመስገኛ ዐውዶች ናቸው* ያሉት መጋቤ ሐዲስ ቅዱስ ያሬድ ትምህርቱን፣ ዜማውን ያገኘው ከሰው ሳይኾን ከእግዚአብሔር መኾኑን ገልጸው *የእግዚአብሔር ጸጋ ያላደረበት ሰው ዜማውን መስማትም መሸከምም አይቻለውም* ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ መጋቤ ሐዲስ በመጨረሻም *ከቃል በላይ ትኩረት ለቅዱስ ያሬድ* በማለት የዕለቱን ትምህርት አጠቃለዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ የመጽሐፍ ቅዱስና የቅዱስ ያሬድ ሥራዎችን ዝምድና የሚያስገነዝብ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት መጋቤ ስብሐት ሲሳይ ወጋየሁ በጥናታቸው መጽሐፈ ድጓ ምሥጢሩ ሙሉ በሙሉ የተወሰደው ከመጽሐፍ ቅዱስ መኾኑን ምሳሌዎችን በመጠቀስ አስረድተዋል፡፡

በዕለቱ ቅዱስ ያሬድንና ሥራዎቹን የሚዘክሩ፤ እንደዚሁም ትውልዱ ከውጭው ዓለም ተጽዕኖ ነጻ ወጥቶ እንደ ቅዱስ ያሬድ ያሉ ሊቃውንትን ፈለግ መከተል እንደሚገባው የሚጠቁሙ ቅኔያት በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ደቀ መዝሙር ተበርክተዋል፡፡

በተጨማሪም *ብፅዕት ከርሥ እንተ ጾረተከ ወብፁዓት አጥባዕት እለ ኀፀናከ አልቦ ዘየዐብዮ ወዘይሤንዮ ለላሕይከ ያሬድ ካህን* የሚል ቅዱስ ያሬድን የተሸከመችውን ማኅፀንና የጠባቸውን ጡቶች የሚያደንቅ፤ እንደዚሁም የካህኑ ያሬድን ላሕየ ዜማ (የዜማውን ማማር) የሚያሞግስ ዝማሬ በዋናው ማእከልና የአዲስ አበባ ማእከል ዘማርያን ቀርቧል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የውሉደ ያሬድ ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን *አሠርገዋ ለኢትዮጵያ በስብሐት ወበሃሌ ሉያ ያሬድ ካህን ፀሐያ ለቤተ ክርስቲያን* በማለት ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያን በምስጋና ማስጌጡን የሚያስረዳና የቤተ ክርስቲያን ፀሐይ መኾኑን የሚገልጽ ጣዕመ ዝማሬ አሰምተዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙርና ኪነ ጥበብ አባላትም የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የጠበቀና የቅዱስ ያሬድን ዜማ መሠረት ያደረገ መዝሙር ማጥናትና መዘመር እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ተውኔት አሳይተዋል፡፡

ቅዱስ ያሬድንና ሥራዎቹን ለመዘከር የተዘጋጀው ይህ መርሐ ግብር በጸሎት ተጀምሮ በጸሎት ተጠናቋል፡፡