ከሰላም የምታደርሰንን መንገድ እንያዝ

 

ብዙዎቻችን ስለ ሰላም እንናገራለን እንጂ ሰላም በውስጣችን አለመኖሩን የሚያሳዩ ተግባራትን ስንፈጽም እንታያለን፡፡ ሰላም የምንሻ ከሆነ ሰላማውያን ከመሆን በተጨማሪ ሌሎችም ሰላማውያን እንዲሆኑ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ከጥፋት ልንድን ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ከጥፋት ልንታደግ እንደሚገባ “ወንድሞቻችን ሆይ ከእናንተ ከጽድቅ የሳተ ቢኖር ከኃጢአቱ የመለሰውም ቢኖር ኃጢአተኛውን ከተሳሳተበት መንገድ የሚመልሰው ራሱን ከሞት እንዳዳነ ብዙ ኃጢአቱንም እንደአስተሰረየ ይወቅ” (ያዕ. ፭፥፲-፱፳) በማለት ቅዱስ ያዕቆብ አስተምሮናል፡፡

ሰላም በስምምነት፣ በአንድነት፣ በፍቅር የምንኖርበት የዕረፍት እና የተስፋ ስሜት የተሞላበት ሕይወት ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት ሰላምን እንከተላት ዘንድ የሚያሳስበንም ሰላም ጥቅም እንጂ ጉዳት የሌለባት በመሆኑ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰው ማንም ያሳድደኛል ብሎ ሳይሰጋ ተረጋግቶ ይኖራልና፡፡ በእጁ ጥፋት በሕሊናው በደል ስለሌለበትም ደስተኛ ሆኖ ይኖራል፡፡ ክርስቲያኖች ሰላማዊ የሚሆኑትም የሰላምን ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን ስለሚከተሉ ነው፡፡ ክርስቲያኖች ብርሃናቸው በሰው ፊት የሚገለጠውና ምግባራቸው አርአያ የሚሆነውም ለሰላም ሲሉ ለራሳቸው የሚገባውንም ቢሆን አሳልፈው ስለሚሰጡ ነው፡፡ የሌላውን የሚቀሙ ቢሆኑ ኖሮ ሰላማቸው ይወሰድባቸው ነበር፡፡ የብጥብጥና የረብሻ ምክንያትም ይሆኑ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች ሲገደሉ የኖሩትም ለምን ሰላማዊ ሆናችሁ? ለምን ዓለምን በፍቅር ለማሻነፍ ተነሣችሁ ተብለው መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

ሰላም የሚያስፈልገው ለክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ተስማምቶ ለመኖር ጭምር ነው፡፡ በቀላል ነገር ሁሉ የሚከፋን፣ በጥቂት ሆድ የሚብሰን ከሆነ ሰላማችን ይደፈርሳል፡፡ ወጥተን መግባት፣ ተኝተን መነሣት አንችልም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ስለ ሰላም ከመናገር ባለፈ ሰላም እንዲመጣ ቁርጥ ውሳኔ መወሰን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ የሚሰማው ጦርነት፣ ግጭት፣ መለያየት ነው፡፡ እነዚህ ሰላም ካላመጡ ብዙ ወጭ የማይጠይቀውን ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ይቅርታን መያዝ ይኖርብናል፡፡

ስጋት፣ ፍራቻ፣ መጠራጠር የሌለበት ይልቁንም ተስፋ፣ ፍቅር፣ እምነት፣ የሚገኝበት ሕይወት የሀገርን ሰላም ጠብቆ ለዜጎች ወጥቶ መግባት ዋስትና ይሰጣል፡፡ ሰላማውያን የሆኑ ክርስቲያኖች እንኳን ከሰው ከአራዊት ጋርም ለመኖር ችለዋል፡፡ ክርስቲያኖች በዚህ ምድር ሲኖሩ ሰላማውያን ናቸው፡፡ ለክርስቶስ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጥ ለእነሱ የሚገባውን ሳይቀር አሳልፈው የሚሰጡ፣ ለእኔ ይቅርብኝ ለአንተ ይሁን የሚሉ ናቸው፡፡ ነቢዩ የሚመክረንም ከስግብግብነት ርቀን ያለንን እየሰጠን ሃይማኖታችንን በምግባር እንድንገልጥ ነው፡፡ ከምግባር ዕሴቶች አንዱ ደግሞ ሰላም ነው፡፡ ሰላም የሚመሠረተውም በሆደ ሰፊነት፣ በአርቆ አሳቢነት፣ ስምን ተክሎ ለማለፍና ለትውልድ የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ከመፈለግ ነው፡፡ ዓለምን የለወጡ፣ ለጨለማው ዓለም ብርሃን የሆኑ ሰላማውያን ሰዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች ተከብረው የሚኖሩ፣ ታሪክ በመልካም ሲያነሣቸው የሚኖሩ መሆናቸውን መረዳት ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሰላም የምትሰብከው ከሰላም ትርፍ እንጂ ኪሳራ፣ ጥቅም እንጂ ጉዳት ስለሌለው ነው፡፡

ሰላም የሚጠፋው እንዴት ነው?

ሰላም በአርቆ አሳቢነትና በይቅርባይነት፥ እንደሚገኝ ሁሉ በተለያዩ ሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ሊጠፋ ይችላል፡፡ መላእክት በተፈጠሩ ጊዜ ያልሆነውን ሆኛለሁ፣ ያልፈጠረውን ፈጥሬአለሁ ብሎ በሐሰት በተነሣው በሳጥናኤል ምክንያት በዓለመ መላእክት መካከል ጦርነት እንደተፈጠረ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ ሰላምን የሚያደፍርሱ ወገኖች ለጊዜው ኃይል ያላቸውና የተሳካላቸው ቢመስሉም መጨረሻቸው እንደማያምር ከሳጥናኤል ተምሮ እውነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ዕርቅን ገንዘብ ማድረግ ይገባል፡፡ ዓለመ መላእክትን የበጠበጠው ሳጥናኤል እንዳይነሣ ሆኖ የወደቀው መውደቁ አልበቃው ብሎ ሌሎችንም ለመጣል በመፈለጉ ነው፡፡ ሰላምን የሚያጠፉ ወገኖች መጨረሻም እንዲሁ ነው፡፡ አወዳደቃቸው አያምርም እንደ ዲያብሎስ ወደ ታች እየወረዱ ወደ ላይ የሚወጡ ስለሚመስላቸው ከወደቁበት አረንቋ ሳይነሡ ይቀራሉ፡፡

መላእክት ሳጥናኤል በተናገረው ነገር ሳይረበሹ ምንት ንህነ መኑ ፈጠርነ እምኀበ አይቴ መፃዕነ፤ ምንድን ነን? ከየት መጣን? ማን ፈጠረን? ማለት ጀመሩ፡፡ የመላእክትን ጥያቄ ተከትሎ ሳጥናኤል በሐሰት እኔ ፈጠርኳችሁ አለ፡፡ የሳጥናኤን ንግግር ተከትለው ፈጠርከን ያሉም፣ ፈጥረህ አሳየን ያሉም፣ ከሁለቱም ያልሆኑ ወገኖች ነበሩ፡፡ በያለንበት እንጽና የሚለው የቅዱስ ገብርኤል ንግግር ደፍርሶ የነበረውን ሰላም አረጋጋው፡፡ ወዲያውም እምኀበ አልቦ ኀበቦ የፈጠራቸው አምላካቸው ልዑል እግዚአብሔር ተገልጦ ዲያብሎስ ያጠፋውን ሰላማቸውን መለሰላቸው፡፡ የመላእክትን ሰላም ለማደፍረስ የሞከረውን ዲያብሎስም በጨለማ ጠቅልሎ እንጦሮጦስ አውርዶታል፡፡ እኛም በዚህ ዓለም ስንኖር ሰላማችን እንዳይጠፋ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ሰላም ከሚደፈርስባቸው ምክንያቶች ጥቂቶችን ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡

  • ለእኔ ብቻ ባይ መሆን፡- የክርስቲያኖች ምግባር የሚገለጠው ከራሳቸው ይልቅ ሌሎችን ማስቀደም በመቻላቸው ነው፡፡ ሀገራችን ተከብራ የምትኖረው በመቻቻል፣ በይቅርባይነትና ሰላማውያን ለመሆን ራሳችንን ስናዘጋጅ ነው፡፡ ለእኔ ብቻ የምንል ከሆነ እንኳን ከሌሎች ጋር ከራሳችንም ጋር ተስማምተን መኖር አንችልም፡፡ ሁልጊዜ ለእኔ ስለምንል ለፍላጎታችን ወሰን ስለማይኖረው ሰላማችን ይታወካል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን ሆደ ሰፊ ነገር አላፊ መሆን ይገባል፡፡ ሀገራችን እንደ ሀገር እንድትከብርና እንድትሻሻል ሰላማዊ ዜጎች መሆን፣ ሰላም ሲደፈርስ ለማስተካከል መሞከር ይኖርብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በሃይማኖት የጸና በምግባር የተገራ ትውልድ ያስፈልጋል፡፡ ማኅበረሰብ ሰላሙ ተከብሮ የሚኖረው አርቀው በሚያስቡ፣ ሰላማዊ በሆኑ፣ ለእኛ የሚያስፈልገን ለሌሎችም ያስፈልጋቸዋል በሚሉ ወገኖች ነው፡፡

ሰላም ሲታወክ የሚኖረው ውስጣዊ ሰላማቸውን ባጡ፣ አካላት ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ለራስ ከመጠን ያለፈ ቦታ መስጠትንና ከእኛ በላይ ለሆኑት ቦታ እንዳንሰጥ ለሁሉ ነገር እኔ ብቁ ነኝ ማለትን ያስከትላል፡፡ ይህም ለሰላም መደፍረስ ምክንያት ይሆናል እንጂ ሰላምን ማምጣት አይችልም፡፡ ሰላም የሌላቸው ወገኖች ደጋፊ ሲያገኙ ሰላም እየጠፋ፣ ጉልበት ያላቸው ብቻ የሚፈልጉትን እየፈጸሙ ይኖራሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንኳን በእግዚአብሔር በሰውም የተጠላ ነው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉትም ዘራቸው በአንድ ትውልድ ተደምስሶ መቀጣጫ ሆነዋል፡፡

ሰላም የሚገኘው ግን ለእኔ ብቻ በማለት ሳይሆን በትሕትናና በይቅርባይነት ነው፡፡ ለእኔ ብቻ ማለትም ልዩነትን እንጂ ሰላም አያመጣም፡፡ ለዘመናችን የሚያስፈልገው መደማመጥ፣ መከባበር፣ ለእኔ የሚያስፈልገኝ ለሌላውም ያስፈልገዋል ብሎ ማሰብና ያሰቡትን በተግባር መግለጥ ነው፡፡

ያልፈጠረውን ፈጥሬያለሁ ያለው ዲያብሎስ የመላእክትን ሰላም በማደፍረስ እንዳልቆመ ለእኔ ብቻ ባዮችም የብዙዎችን ሰላም ያደፈርሳሉ፡፡ ዲያብሎስ የወደቀው ለእግዚአብሔር የሚገባውን ለእኔ ይገባል በማለቱ ነው፡፡ በጎደለው ነገር በእሱ ምትክ የተፈጠረውን የሰውን ልጅ ማወኩን ቀጠለ፡፡ የሰው ልጅ ይኖርባት ዘንድ በተሰጠችው በገነት እያመሰገነ እንዳይኖር የፈጠረውን እግዚአብሔርን እንዳይከተል ዲያብሎስ ለእርሱ የማይገባውን መልካም አስመስሎ በማሳየት አታለለው፡፡ የማይገባንን መሻትና ለእኔ ማለት በዓለም ላይ ጦርነት እንዲነግሥና ሰላም እንዲታጣ ሲያደርግ ኖሯል፡፡ ይህ የማያዋጣ በመሆኑና ከእግዚአብሔርም ስለሚለየን ሰላማዊ ለመሆን መዘጋጀት ይኖርብናል፡፡

  • ለክፉዎች ደጋፊ መሆን፡- ሰዎች ባለማወቅ ወይም በየዋህነት ለክፉዎች ደጋፊ ይሆናሉ፡፡ በዚህም ሌሎችንም ራሳቸውንም ይጎዳሉ፡፡ የሰው ልጅ በዲያብሎስ ምክር ተታልሎ የነበረውን ክብር አጥቶ አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ያለ ሰላም፣ ያለ ዕረፍት ኖሯል፡፡ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ ገነትን ያህል ቦታ አጥቷል፡፡ በርደተ መቃብር ላይ ርዕደተ ገሃነም ተፈርዶበታል፡፡ ለክፉዎች ሰዎች ደጋፊ ስንሆንም ሰላማችንን ከማጣት በተጨማሪ ሕይወታችንንም እናጣለን፡፡ በምድር ላይ ዕድሜያችን እንዲረዝምና ከስጋት ለመዳን ሰላማችንን ከሚያደፈርሱብን፣ ከእግዚአብሔር ከሚለዩን መራቅ ይኖርብናል፡፡ የተቀደሰውን ቃል ለግል ዓላማ ማስፈጸሚያ ከሚያደርጉ ወገኖች መራቅ ይገባል፡፡ ኃጢአት ከሚያሳስቡን መሸሽ ሰላማችን ተጠብቆ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ የራሳቸውን ድብቅ ዓላማ ለማሳካት የሚፈልጉ ወገኖች አርቀው የማያስቡ አካላትን ጥግ አድርገው ፍላጎታቸውን ያሳካሉ፡፡ መረዳት የሚገባው ግን በእንዲህ ዓይነት መንገድ ሰላም የማይገኝ መሆኑን ነው፡፡
  • ትዕግሥት በማጣት፡- ትዕግሥት የሁሉ ነገር መሠረት ነው፡፡ ትዕግሥት ተደማምጦ ሥራ ለመሥራት አሳብ ለመለዋወጥ፣ የሚገጥምን ፈተናን ድል ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ ቅዱሳን የእግዚአብሔርን መንግሥት የወረሱት በትዕግሥት ነው፡፡ የሚገጥማቸውን ፈተና ይዋል፣ ይደር በማለት ያሸንፉታል፡፡ ቀስ በቀስም እግዚአብሔር ፈተናውን የሚታገሡበትን፣ ለድል አክሊል የሚበቁበትን ጥበብ ይገልጥላቸዋል፡፡ ፈተናን ድል ማድረግ የሚያስገኘውን በቊዔት ስለሚረዱም እግዚአብሔርን እየጠየቁ፣ ታላላቆቻቸውን እያማከሩ በሚገጥማቸው ፈተና ላይ ይሠለጥኑበታል፡፡ በትዕግሥታችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ትወርሳላችሁ ተባልን እንጂ በችኮላና በስሜታዊነት ትወርሳላችሁ አልተባልንም፡፡ የታዘዝነው መከራ ሲገጥመን መታገሥና ሰው በሌለበት ጊዜ ሰው ሆኖ መገኘት መሆኑን “ወንድሞች ሆይ ልዩ ልዩ መከራ በሚመጣባችሁ ጊዜ በሁሉ ደስ ይበላችሁ፡፡ በሃይማኖታችሁ የሚመጣባችሁ ፈተና ትዕግሥትን እንደሚያደርግላችሁ ዐውቃችሁ ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ጤነኞች ትሆኑ ዘንድ ትዕግሥት ፍጹም ግብር አላት” (ያዕ. ፩፥፪፬) የሚለውን የሐዋርያውን ትምህርት መረዳት ይገባል፡፡

ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ይልቅ ሥርዓተ ሰብእን፣ ከትዕግሥት ይልቅ ስሜታዊ መሆንን ስንመርጥ በእግዚአብሔር ሕግ ከመመራት ይልቅ ስሜታዊነት ይቆጣጠረናል፡፡ ፍትሕንም በራሳችን ለማግኘት፣ የፈለግነውን ለመወሰንና ለመፈጸም እንነሣሣለን፡፡ ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር ያርቀናል፡፡ በስሜታዊነትና ትዕግሥት በማጣት የፈጸምነው ጥፋት ለጸጸትና ለሕሊና ወቀሳ ይዳርገናል፡፡ ሰው ስናይ የምንበረግግ፣ ኮሽ የሚል ነገር ሁሉ የሚያስደነግጠን እንሆናለን፡፡ እንዲህ ላለመሆን ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ ለራሳችንም፣ ለቤተሰቦቻችንም፣ ለሀገራችንም ይጠቅማል፡፡ ሐዋርያው የሚመክረንም “በትሕትና ሁሉና በየዋህነት፣ በትዕግሥትም እርስ በራሳችሁ በፍቅር ታገሡ፣ በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ (ኤፌ. ፬፥፪-፫) በማለት በመሆኑ ምክሩን በተግባር ለመፈጸም መትጋት ይኖርብናል፡፡ ሐዋርያው ከእግዚአብሔር ከሚያርቁንና ሰላማችንን ከሚነጥቁን እንድንርቅ ከመከረን በኋላ መከተል የሚገባንን ደግሞ “አንተ ግን የእግዚአብሔር ሰው ሆይ ከዚህ ሽሽ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል፣ እምነትንም፣ ፍቅርንም፣ መጽናትንም፣ የዋህነትንም ተከተል፡፡ መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፤ የተጠራህበትንም በብዙ ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን፣ የዘለዓለምን ሕይወት ያዝ (፩ኛ ጢሞ. ፮፥፲፩-፲፫) በማለት ይመክረናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም “መከራን የሚታገሥ ሰው ብፁዕ ነው፤ ተፈትኖ እግዚአብሔር ለሚወዱት ተስፋ ያደረገላቸውን የሕይወት አክሊል ይቀበላልና” (ያዕ. ፩፥፲፪) በማለት እንድንጸና ያሳስበናል፡፡ሰላም የሚደፈርሰው ከላይ በዘረዘርናቸውና በሌሎችም መሰል ምክንያቶች ነው፡፡ እነዚህ መጥፎ ተግባራት ለራስም፣ ለቤተሰብም አይጠቅሙም፡፡ ቤተሰብን ይበትናሉ፤ ሀገርንም ያፈርሳሉ፡፡ ለዚህ ነው ነቢዩ ሰላምን ገንዘብ በማድረግ ሰላማዊ ሆነን እንድንኖር የሚመክረን፡፡

  • ሰላም እንዴት ይገኛል?
  • ለሌሎች ቅድስሚያ በመስጠት፡- ሰላም ከሚገኝባቸው መንገዶች አንዱ ራስን ከስግብግብነት በመጠበቅ ለሌሎች ቅድሚያ በመስጠት ነው፡፡ ለሌሎች ቅድሚያ ስንሰጥ ለመጣላት ተዘጋጅተው የነበሩት ስሜታቸው ይቀዘቅዝና በድርጊታቸው ያፍራሉ፡፡ ቆይተውም ራሳቸውን ይወቅሳሉ፡፡ በሌላ በኩል የራሳቸውን ታናሽነት ቅድሚያ የሰጣቸውን አካል ታላቅነት ይቀበላሉ፡፡ ቀስ በቀስም እነሱም መልካም ወደማድረግና ተቀብለው ከመደሰት ሰጥተው ወደ መደሰት ይሸጋገራሉ፡፡ ቅድሚያ ለእኔ የሚሉ ወገኖች ልዩነትን እንደሚፈጥሩና ሰላምን እንደሚያደፈርሱ ሁሉ እኔ ይቅርብኝ ቅድሚያ ለእናንተ የሚሉ ደግሞ ሰላምን ያመጣሉ፡፡ የክርስቲያኖች መርሕም ይህ ነው፡፡ ለእነሱ የሚያስፈልገውን ለሌላው ይሰጣሉ፡፡

ለእስራኤል ርስትን ያወረሰው ኢያሱ የወሰደው የማይረባውን ሲሆን ለሌሎች ያከፋፈለው ግን ምርታማውንና ለም የሆነውን መሬት ነው፡፡ ኢያሱ ይህን ቢያደርግም እግዚአብሔር ደግሞ በበረከት ጎብኝቶት ከማይረባው ቦታ ለራሱና ለወገኖቹ የሚበቃ ምርት ሲሰበስብ ኖሯል፡፡ ከዚህም በመንገብገብ የምናተርፈው፣ ለሌሎች በመስጠትም የሚጎድልብን አለመኖሩን እንረዳለን፡፡ ከእግዚአብሔር ይሰጣችኋል የተባሉት ሁሉን ለእኔ የሚሉት ሳይሆኑ ይህስ ለወገኔ ይገባል የሚሉት እንደሆኑ መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ ቅድሚያ ለእኔ በማለታችን በሰው ፊት ከመናቃችንም በተጨማሪ ሕሊናችንም ሰላም አይሰጠንም፡፡ ሕሊናችንን ሰላም የማይሰጠውን ተግባር ከመፈጸም ይልቅ ሌሎችን በማስቀደም ሕሊናችንን የሚያስደስት ተግባር መፈጸም ይገባል፡፡ በየሔድንበት የሰው መጠቋቆሚያ የሕሊና ወቀሳ ከምናተርፍ የሰላም እንቅልፍ ተኝተን የምናድርበትን ሥራ መሥራት ለራሳችንም ለሀገራችንም ይጠቅማል፡፡ ይህም ማለት የምንሠራውን እንወቅ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ስለዚህ እንደ ቸርነቱ የሰጠን ይህ መልእክት አለንና አንሰላችም፡፡ ነገር ግን በስውር የሚሠራውን አሳፋሪ ሥራ እንተወው፤ በተንኰልም አንመላለስ፤ የእግዚአብሔርንም ቃል በውሸት አንቀላቅል፤ ለሰውም ሁሉ አርአያ ስለመሆን እውነትን ገልጠን በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን እናጽና” (፪ኛ ቆሮ. ፬፥፩-፪) በማለት እንደመከረን ልብ እንበል፡፡

  • ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ፡- የእግዚአብሔር ሰዎች ተብለው የተመሰገኑት ስሜታቸውን ተቈጣጥረው፣ ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳቸው ያስገዙት ናቸው፡፡ እንዲህ የሚያደርጉ ወገኖች እንኳን ከሰው ከአራዊት ጋር ተስማምተው ይኖራሉ፡፡ ስሜታቸው የጠየቃቸውን ሁሉ ለማግኘት የፈለጉ፣ ለፈቃደ ሥጋቸው አርነት የሰጡ ወገኖች መጨረሻቸው አላማረም፡፡ በአንጻሩ ትዕግሥትን ገንዘብ ያደረጉት ግን በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ተመስግነዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በፈቃደ ሥጋቸው ላይ የሠለጠኑ በመሆናቸው በቀላሉ ከሰዎች ጋር ግጭት ውስጥ አይገቡም፡፡ እንዲህ ተደረጋችሁ ቢባሉም በስሜት ተገፋፍተው ወደ መጣላት አይሔዱም፡፡

በጾም ወቅት ብሉ፣ ብሉ የሚል ስሜት ሲመጣባቸው ትንሽ ልቆይ እያሉ ረሃብን ድል ይነሡታል፡፡ ፈቃደ ሥጋቸው ተነሣሥቶ ወደ ዝሙት የሚገፋ ፈተና ሲገጥማቸውም እግዚአብሔርን በጸሎት በመማጸን ከመምህራን ምክርን በመጠየቅ ፈተናውን ያልፉታል፡፡ ከዚያ በኋላ ፈቃደ ዝሙት ይጠፋላቸዋል፡፡ ያየውን ሁሉ ለእኔ የሚል ስሜት ሲመጣም በትዕግሥት ድል ነሥተው ራሳቸው ከጸጸት ተጠብቀው እግዚአብሔርንም ያስደስታሉ፡፡ ለተከታዮቻቸውም አርአያ ይሆናሉ፡፡ በአጠቃላይ ከክርስቲያኖች የሚጠበቀው የመንፈስ ፍሬዎችን በመፈጸም ጽድቅን ገንዘብ ማድረግ ነው፡፡ ሐዋርያው “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ምጽዋት፣ ቸርነት፣ እምነት፣ ገርነት፣ ንጽሕና ናቸው፡፡ ከዚህ ሕግ የሚበልጥ የለም፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኃጢአት ለዩ፡፡ አሁንም በመንፈስ እንኑር በመንፈስም እንመላለስ፡፡ ኩሩዎች አሁንም እርስ በርሳችንም አንተማማ፤ እርስ በርሳችንም አንቀናና” (ገላ. ፭፥፳፪-፳፮) በማለት እንዳስተማረን፡፡

ትዕግሥት በሃይማኖት ሰዎች፣ በመሪዎች፣ ለሀገር በሚያስቡ ሰዎች ውስጥ ካልተገኘች ተቻችሎ መኖር አይቻልም፡፡ ትዕግሥት የፈለጉትን የምታሰጠው በእርጋታ ለማሰብ መሠረት በመሆኗ ነው፡፡ ክርስቲያኖች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉ የተባሉት በትዕግሥት ነው፡፡ ከትዕግሥት ትርፍ እንጂ ኪሳራ ስለሌለው በሰላም ለመኖር ትዕግሥትን ገንዘብ ማድረግ ይገባል፡፡

  • ዕርቅ፡- ሰላም ለማምጣት መሠረት የሆነው ዕርቅ ነው፡፡ “የሚያስታርቁ ብፁዓን ናቸው የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (ማቴ. ፭፥፱) የተባለው ዕርቅ በዚህ ዓለም በሰላም ለመኖር በወዲያኛው ዓለም መንግሥተ ሰማያትን ለማውረስ ወሳኝ በመሆኑ ነው፡፡ ዕርቅ ማድረግ የሚጀምረው ከራስ ነው፡፡ ከራስ ጋር ዕርቅ የፈጸመ ሰው ከሌላው ጋር ታርቆ በሰላም ለመኖር ይችላልና፡፡ ዕርቅን የፈጸመ ሰው ክፋትን ይጸየፋል፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ “እንግዲህ ክፋትንም ሁሉ፣ ሐሰት መናገርንም ሁሉ፣ ጥርጥርንም መተማማትን፣ መቃናትንም ከእናንተ አርቁ፡፡ ዛሬ እንደተወለዱ ሕፃናትም ሁኑ፤ ለመዳን በእሱ ታድጉ ዘንድ ቅልቅል የሌለባትን የቃልን ወተት ተመኙ” (፩ኛ ጴጥ. ፪፥፩-፫) በማለት ያስተማረውን መረዳት ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አርቆ ማሰብ፣ የምንፈጽመው ነገር የሚያስከትለውን በጎም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ መመዘን ዕርቅ ለማድረግ ይጠቅማል፡፡ ከራሱም ከእግዚአብሔርም ጋር ተጣልቶ ሲቅበዘበዝ ከኖረው ከቃየን ሕይወት መለየት በሰላም ለመኖር ያስችላልና ሰላምን የሚያሰፍን ሥራ ለመሥራት እንዘጋጅ፡፡

ምንጭሰምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 26ኛ ዓመት ቁጥር 1 ቅጽ 26ቁጥር 394 ከመስከረም 16-30ቀን 2011ዓ.ም