ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ፡፡

በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን፡፡

ጥር  17 ቀን  2011 ዓ.ም

እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፡፡ / 1ኛ ጴጥ 4፤7/

በማንኛውም የሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችንና ግድያዎችን ሁሉ እናወግዛለን፡፡  በየቦታው የተከሰቱ ችግሮች እንዲቆሙም በድርጊቱ የሚሳተፉ አካላትን ሁሉ እንማጸናለን፤  እናሳስባለንም፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን

የክርስትና ሃይማኖት ማእከላዊ ጉዳዩ ሰው ነው፡፡ አምላክ ሰው ሆነ፣፤ ሰውም አምላክ ሆነ፣ የሚለው የትምህርቱ አስኳል ዋና ነጥብም የሚያመለክተው የነገራችን ሁሉ ማእከል ሰው መሆኑን ነው፡፡ ይህም ለሰው ሲባል አምላክ እንኳ ራሱን ዝቅ አድርጎ በተዋሕዶ ሰው ሆኖ መገለጡንና በዚሀም ሰውን ከወደቀበት ማንሣቱን፤  ከዚያም በላይ ሰውን በተዋሕዶ ለአምላክነት ክብር ማብቃቱን የሚገልጽ ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ  ሀገራዊ ብቻ ሳይሆን ዐለምአቀፋዊ ሆነው በትልቁ የሚከበሩት የአምላካችን ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤና ዕርገት ሁሉ ማእከላዊ ነጥባቸው ሰው ነው፡፡ ሁሉም ነገሮች አምላክ ለሰው ሲባል ያደረጋቸው ናቸውና፡፡

ሌሎች አስተምህሮዎች ሁሉ አሁንም ሰውን ለማስረዳት ሲባል የተለያዩ አርእስት ይሰጣቸው እንጂ ማእከላዊ ነጥባቸው አንድ ነው፤ የሰው ድኅነትና ደኅንነት፡፡ የአንድ ሰው ጽድቁም ኃጢአቱም የሚለካው ለሰው በሚያደርገው ወይም በሰው ላይ በሚያደርገው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህም በምድር ላይ ከሰው በላይ የከበረና ጥንቃቄ ሊደረግለት የሚገባው ምንም ፍጥረት የለም፡፡ በምድር ላይ ጥንቃቄና ዕርምት የሚወሰድበት ነገር ሁሉ የመጨረሻ ዓላማው ሰውን ለመጥቀም ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ ከሰው የሚጣላ ከአምላኩም ከአጠቃላይ ከፍጡራንም ሁሉ ጋር የሚጣላ ይሆናል፡፡ በሰው ላይ ያልተገባውን ድርጊት የሚፈጽም ሁሉ በፈጣሪው ላይ የሚያደርግ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፤ ፈጣሪ ሰው መሆንን በተዋሕዶ ገንዘብ አድርጎ ሰው ሆኖ ተገልጧልና በሰው የሚደረግ ሁሉ በእርሱ ላይ የሚደረግ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

የክርስትና ሃይማኖት መምህራንና ተቋማት ዋና ዐላማና ተልእኮም ሊመነጭ የሚችለው ከዚህ መሠረታዊ የሰው ክብርና ዋጋ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም የዓለም ክፍል በማንኛውም ሰው ላይ የሚፈጸሙ መጥፎ ተግባራት ይልቁንም ከሕግ ማሕቀፍ የወጡትንና በሴራና በተንኮል የሚፈጸሙትን እንደ ማኅበር አብዝተን እናወግዛቸዋለን፤ እንጸየፋቸዋለንም፡፡ ይልቁንም በሀገራችን በኢትዮጵያ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣው ንጹሐንን ሰለባ እያደረገ ያለው የተቀነባበረና የተነጣጠረ የሚመስለው ጥቃት በእጅጉ የሚያሳስብ መሆኑ ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡

በሀገራችን በኢትዮጵያ ከተከሰተው የለውጥ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ብዙ ማኅበራዊ ችግሮች መከሰታቸው የሚታወቅ ነው፡፡ በለዉጥ ወቅት እንዲህ አይነት ተግባራት መከሠታቸው የሚጠበቅ ቢሆንም እንኳ ለብዙዎች የጥቃቱ ሰለባዎች ዱብ እዳ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ እነዚህ በወገኖቻችን ላይ የደረሱ ውጣ ውረዶች፣ ልዩነቶች፣ ግጭቶች፣ መፈናቀሎች፣ ድብደባዎች፣ ግድያዎች እጅግ ብዙ ሰዎችን ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውም የሚታወቅ ነው፡፡ ሆኖም ችግሩ አሁንም በመቀጠል ላይ ከመሆኑም በላይ እየሔደበት ያለው መንገድ ደግሞ የበለጠ አሳሳቢና አስፈሪ እያደረገው ይገኛል፤ ጥቃቶቹ ሃይማኖታዊና ጎሳዊ ግጭቶችን  ለማቀጣጠል በሚመስል መልኩ በተደጋጋሚ እየተከሠቱ ነውና፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በሃይማኖት ተቋማት ጥቃት ማድረስ፣ ለጸሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን የሄዱትን ማጥቃት፤ ወጣት ዜጎች በብዙ ስብጥር በአንድነትና በኅበረት ትምህርትን ዐላማ አድርገው በሚኖሩባቸው ዩኒቨርስቲዎች የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ ድብደባዎችና የተለያዩ ትንኮሳዎች የነገሩን ከፍተኛ አሳሳቢነት እንድንመርመርና ለመፍትሔውም እንድንነሣ የሚጋብዙ ናቸው፡፡

እጅግ በቅርብ ጊዜ ከተፈጸሙት መካከል ለአብነት ያህል እንኳን ብናነሳ፡-

  • በዐለም አቀፍ ደረጃ በሚከበረዉ የጌታችንና መድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዐለ ጥምቀት ወቅት በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖች በዐሉን እንዳያከብሩ መከልከል ወይም የጥምቀተ ባሕር ቦታዎችን መቀማት በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ በዐሉን በማክበር ላይ በነበሩ ምእመናን ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ ማድረግ
  • አብያተ ክርስቲያናትን ማቃጠል (ለምሳሌ በሶማሌ፣ በባሌ በተደጋጋሚ፣ በአርሲና በሌሎች አካባቢዎችም በየወቅቱ የሚደረጉ ጥቃቶች የሚጠቀሱ ናቸው )
  • በዚህ ሳምንት ውስጥ ደግሞ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ኦርቶዶክሳዊያን ተማሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ሔደው ጸሎት አድርሰው በመመለስ ላይ ሳሉ የተፈጸመው ጥቃት እጅግ አሰቃቂና አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ ከዚህም በፊት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የታዩት ችግሮችም በርካታና ሊዘነጉ የማይችሉ ክስተቶች ናቸው፡፡

በመሆኑም

1ኛ) በየትኛውም የሀገራችን አካባቢ በማንኛውም ሰው ላይ ይልቁንም ደግሞ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን፣ ግድያዎችንና ለማኅበረሰብ ቁርሾና ጠብ የሚጋብዙ ትንኮሳዎችን ሁሉ እናወግዛለን፡፡

2ኛ) በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይልቁንም በቅርቡ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ከቤተ ክርስቲያን ሲመለሱ የተፈጸመውን ዘግናኝና አሳዛኝ ጥቃት በእጅጉ እናወግዛለን፡፡

3ኛ) በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች መንግሥታዊ ወይም ሀገራዊ ኃፊነታቸውንና ሥልጣናቸውን አላግባብ ተጠቅመው በየትኛውም የሃይማኖት ተቋም ላይ ይልቁንም ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን እና በምእመናን ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን፣ ቃጠሎዎችን፣ የመብት ክልከላዎችንና ትንኮሳዎችን ሁሉ እናወግዛለን፡፡

 የፖለቲካ ትግል ለምታካሄዱ ወገኖቻቸን  ደግሞ የሚከተሉትን መልዕክቶች ልናስተላልፍ እንወዳለን፡፡

 በየትኛውም ሀገርና ሕዝብ እንደሚደረገው በእኛ ሀገርም በየዘመኑ የፖለቲካ ትግል ነበረ፣ አሁንም አለ፤ ወደፊትም እንደሚቀጥል የሚጠበቅም የሚታወቅም ነው፡፡ በመሆኑም የትኛውም ዜጋ ያልተሰማማበትን ይልቁንም አድሏዊና አግላይ የመሰለውን ሁሉ መታገልና ለሀገር ይበጃል ያለውን ሐሳብ መግለጽ ይችላል፡፡ ይህን በመፈጸሙም ማንም ውግዘትና ጥላቻ እንደማይገባው እናምናለን፡፡ ሆኖም በትግል ምክንያትም ሆነ ሰበብ ያለአግባብና በስሕተት ወይም በጊዜያዊ ጥቅም፣ እልህና በመሳሰሉት ምክንያቶች ከራሱ እታገላለሁ ከሚለው ሰው ጀምሮ የማንም ሰው ክቡር ሕይወት ያለ አግባብ መጎዳት የለባትም፡፡ ስለዚህም  ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን የሚከተሉትን ጉዳዮች በጥሞና አጢናችሁ ተግባራዊ ምላሽ እንድትሰጡ ይማጸናችኋል፣ ያሳስባችኋልም፡፡

1ኛ) ፖለቲከኞች ሁላችሁም የትግል ቦታችሁን ከተማሪዎችና ከትምህርት ተቋማት በሙሉ የራቀ እንድታደርጉ በታላቅ አክብሮትና ስሜት እንማጸናችኋለን፤ እናሳስባችኋለንም፡፡ በሀገራችን የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንደ ተማሪና ትምህርት ቤቶች የፖለቲካ ተጠቂ የሆነ ያለ አይመስልም፡፡ ከንጉሡ ዘመን ጀመሮ ያለው የፖለቲካ ትግል ተማሪዎችን ማእከል አድርጎ መቆየቱ ታሪክ ሳይሆን የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ሌላውንና ጥልቅ ጥናቱን ለፖለቲከኞችና ለታሪክ ወይም ለመሰል ጠበብት የምንተወው ቢሆንም በእኛ አስተሳሰብ ሀገራችን ከጉዳት አዙሪት እንዳትወጣ ካደረጉ እና እያደረጉ ካሉት ጉዳዮች አንዱና ዋናው ተማሪዎችን የፖለቲካ ሰለባ፤ የትምህርት ተቋማትንም የወጣት ዜጎች የአስተሳሰብ ጠለፋ ማካሔጃ ቦታ ማድረጉ ነው፡፡  ምንአልባትም የሀገራችን የፖለቲካ ሂደት የልጅነት ጨዋታ ከሚመስል የብሽሽቅ& የእልህ& የስም ማጥፋትና የበቀል ስሜት መውጣት ያቃተው በዚሁ ልጆችን አእምሮ አስቀድሞ በመበከል የሚጠነሰስ በመሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ ተማሪዎች በአዳጊ አእምሮአቸው በእውቀት ታንጸው በአእምሮ በስለው፤ ዝመት፣ ጥላቻና ቅራኔ ሳይቀስሙ ቢወጡ በኋላ በሳል ፖለቲከኞችና የሀገር መሪዎች የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ሆኖ ሳለ በትምህርት ገና ባግባቡ ሳይታነጹ በፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ ስሌት ጠልፎ በመጣል በእነርሱ ላይ የደረሰው ጉዳት በተማሪነት እድሜ ላይ ሳሉ ከደረሰባቸው አካላዊ፣ ሥነ ልቡናዊና መንፈሳዊ ጉዳት ይልቅ በዘለቄታው ሀገራችንን የጥላቻና የፍረጃ ፖለቲካ ማዕከል በማድረጉ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ይሰማናል፡፡ ስለዚህም ፖለቲከኞቻችን ሁሉ ሰለነገዋ ሀገራችንና ዜጎቿ ስትሉ ተማሪዎችንና የትምህርት ተቋማትን የፖለቲካ ትግል የፍልሚያ ቦታ ከማድረግና የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑትን  የአሁኖቹን ተማሪዎች ከማኮላሸት ትቆጠቡ ዘንድ ከልብ እንማጸናችኋለን፣ እናሳስባችኋለንም፡፡

2ኛ) ምንም እንኳ የትግል ስልታችሁን የመምረጥ መብቱ የእናንተ ቢሆንም ልክ እንደ ትምህርት ቤቶቹ የሃይማኖት ተቋማትን፣ ቦታዎቻቸውን፣ አማኞቻቸውንና በዐላቶቻቸውን ሁሉ ለዚህ ዐላማ ከማዋል እንድትቆጠቡ በጥብቅ እንለምናችኋለን፣ እናሳስባችኋለንም፡፡ እንዲህ ዐይነት ድርጊቶች በፖለቲከኞች ዘንድ እንዴት እንደሚወሰዱ ባናውቅም በእኛ እምነት ሃይማኖታዊ ተቋማትን፣ አካላትን፣ በዓላትንና ሥርዓተ አምልኮዎችን ከራሱ ከእምነቱ አስተምህሮና ሥርዓት ውጭ ጠልፎ ለራስ የፖለቲካ ዐላማ የመጠቀም ፍላጎት ሲጀመር የደካማነት መገለጫ ነው፡፡ በራሱ ቆሞና ታግሎ መለወጥ ያቃተውን በሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት በማድረስና በዚያ ተቃውሞ በማነሣሣት ወይም ደግሞ በተቋማቱና በመሪዎቹ ቀሚስና ሰናፊል በመጠለልና ሌላ ሰብእናን ሸፍኖ ከእምነት ተቋሙ ውጭ ለሌላ ዐላማ ለመጠቀም መንቀሳቀስ ጊዜያዊ ትርፍ ቢያሰገኝ እንኳ በዘለቄታው ውስብስብ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ምንም እንኳ የራሳቸውን የእምነት ተቋማት ከእነዚህ ሁሉ የመጠበቅ  ሓላፊነት የየእምነት ተቋማቱ መሪዎችና የአማኞቻቸው ቢሆንም እናንተ ፖለቲከኞችም ግን እነርሱን ከመጠቀም እንድትታቀቡ እንማጸናችኋለን፣ እናሳስባችኋለንም፡፡

3ኛ) መንግሥት ዜጎቹን በሕግና በሕግ አግባብ ብቻ የመጠበቁን ተግባር ከመቼውም ጊዜ በላይ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ብዙዎቹ ጉዳቶች ወደ ተግባር የሚቀየሩት መንግሥታዊ መዋቅሩንም ለራስ የፖለቲካ ጥቅም ሊያግዝ እንዲችል አድርገው ሊጠቀሙ በሚያስቡ ደካማ ሰዎች ድርጊትም ጭምር ይመስላል፡፡ ስለዚህ መንግሥት በሌሎች አካላት ላይ ብቻ ሳይሆን ሹመት ወይም ኃላፊነት የሚሰጣቸው ሰዎች በፖለቲካም ሆነ በሃይማኖታዊ አድሎ ጊዜያዊ ጥቅም በማስላት በሚወስኗቸው ውሳኔዎች ሀገር እንዳይፈርስ፤ ዜጎችን እንዳይፈናቀሉና ክቡር የሰው ሕይወት እንዳይቀጠፍ ማሳሰብና ማስጠንቀቅ ምልክቱንም ሲያይ ሳይውል ሳያድር እርምት መውሰድ ይኖርበታል፡፡ ዜጎች ሁሉ ይልቁንም ከቤተሰብ ርቀው ለሚሄዱ ተማሪዎች ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች ባሉበት ያሉ አካባቢ የሚገኙ መስተዳድሮችና የጸጥታ ሓላፊዎች ለየትኛውም ጥቃት ሓላፊነቱን ከተጠያቂነቱ ጋር ሊወስዱ ይገባቸዋል ብለን እናምናለን፡፡

በመጨረሻም ሓላፊነት ያለብን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ወጥተን በዘላቂ የሀገርና የሰው ጥቅም ላይ ተመሥርተን ካለፈው ይልቅ በሚመጣው ላይ አተኩረን ተገቢ  ሰብአዊ ሓላፊነታችንን እንድንወጣ በታላቅ አክብሮት እናሳስባለን፡፡ እንደሚታወቀው ሰው ከሌሎች  ምድራዊ ፍጥረታት ሁሉ የሚለየው ባለ አእምሮ የመሆኑ ጉዳይ በመሆኑ ሐዋርያው እንዳለው ሁሉንም አካላት በአምላከችን ቃል እንደ ባለ አእምሮ እንድናስብና እንደ ባለአእምሮም እንድንሠራ በአምላካችን በልዑል እግዚአብሔር ስም እንማጸናችኋለን፣ እናሳስባለንም፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያ ሀገራችንን መላውንም ዐለም ይባርከ፤ ለሰው ዘር ሁሉ ሰላም ይሁን፤ አሜን፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን

ጥር  17 ቀን  2011 ዓ.ም