ከመገልገያው አገልጋዩ መቅደም እንዳለበት ተነገረ

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስና ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ

                                                                                                                                                                 በካሳሁን ለምለሙ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መቄት ወረዳ አሰፋ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተገነባው የአብነት ትምህርት ቤት ሕንፃ ሚያዝያ ፳፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በተመረቀበት ወቅት ከመገልገያው አገልጋዩ መቅደም እንዳለበት የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ተናገሩ፡፡
እንደ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ገለፃ አብነት ትምህርት ቤቶች የቤተ ክርስቲያን የዕውቀት ማእከል በመሆናቸው ከተዳከሙ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሊኖር የማይችል መሆኑን ገልጠዋል፡፡ አብነት ትምህርት ቤቶች ትኩረት ከተሰጣቸውና ዘመኑን የዋጁ ካህናት ማውጣት ከተቻለ የቤተ ክርስቲያን ህልውናን ማስቀጠል እንደሚቻል ብፁዕነታቸው አስገንዝበዋል፡፡
“በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ አስተምር በነበረበት ወቅት የንስሓ አባት ሆኜ አገለግላቸው የነበሩ ገንዘብ አሰባስበው በዛሬው ዕለት ለምርቃት የበቃውን የአብነት ትምህርት ቤት ሕንፃ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብተው አስረክበዋል” ብለዋል፡፡
የተገነባው ሕንፃ ሙሉ በሙሉ የአብነት ትምህርት ቤቶችን ችግር ባይፈታም እንደ ጅምር መልካም መሆኑን የገለጡት ብፁዕነታቸው ትልልቅ ካቴድራሎችን ከመሥራት አስቀድመን                በካቴድራሎች ሊያገለግሉ የሚችሉ ዘመኑን የዋጁ አገልጋዮችን አስተምረን ማውጣት የምንችልባቸውን የትምህርት ተቋማት ማጠናከር ይኖርብናል “ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የአብነት ተማሪዎች ቁራሽ ለምነው ይማሩ እንደነበር ብፁዕነታቸው አስታውሰው ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን ብቻ እያሳቡ እንዲማሩ ለማድረግ በገቢ የሚደጉሙ ተዛማጅ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአብነት ትምህርት ቤቱን በዘላቂነት ለመደገፍ አራት የእህል ወፍጮ እና የወተት ሀብት ልማት ፕሮጅክት በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ ከፕሮጅክቶች ከሚገኘው ገቢ 40 በመቶው ለአብነት ትምህርት ቤቱ አገልግሎት የሚውል ይሆናል፡፡ በተለይ መንግሥት በሰጠው 6.6 ሄክታር መሬት በተቋቋመው የወተት ሀብት ልማት ፕሮጀክት የሚገኘው ገቢ ለተማሪዎቹ ልብስ ቀለብና የንጽሕና መጠበቂያ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለሟሟላት እንደሚውል ብፁዕነታቸው ገልጸዋል፡፡
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ተገኝተው ቡራኬ የሰጡት የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የደብረ ሮሐ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የበላይ ጠባቂ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ “መኖር ለመሥራት፣ መሥራት፣ ደግሞ ለመኖር ሊሆን ይገባል፡፡ ለመኖር መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ የአብነት ትምህርት ቤት ሕንፃ ግንባታ ላይ የተሳተፋችሁ በመሉ ለመኖር የሚያበቃችሁን ሥራ ሠርታችኋልና ደስ ይበላችሁ” ብለዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊ ዶክተር ኂሩት ካሳው በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን የገነባችና እየገነባች ያለች መሆኗን ገልጠው ቀለም በጥብጣ፣ ብራና ዳምጣ፣ ብዕር ቀርጻ ትውልድ ስታስተምር መኖሯን አስረድተዋል፡፡
“ቤተ ክርስቲያን የራሷ ፊደል ባይኖራት ኖሮ ኢትዮጵያውያን ተለይተን የምንታወቅበት ማንነት ባልኖረን ነበር፡፡ ሀገር ሊገነባ የሚችለውም በዕውቀት፣ በጥበብና በትምህርት ብቻ ነው” ብሏል፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን ስትመራባቸው የኖሩ ሕግጋት የተወሰዱት ከቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሀገርን እንደ ሀገር ለመምራት እንዲሁም ሕግ ለማውጣት መነሻ፣ የዕውቀትና የጥበብ መፍለቂያ መሆኗን ሓላፊዋ ገልጠዋል፡፡
“ለሀገራችን የዕውቀትና የጥበብ መነሻና የልህቀት ማእከል የሆኑት የአብነት ትምህርት ቤቶች በአደገኛ ሁኔታ ላይ እንዲገኙ ቸል ብለናቸዋል ያሉት ዶክተር ኂሩት የሀገራችንን ህልውናና ጥበብ የምናስቀጥልባቸውን የአብነት ትምህርት ቤቶች ልንደርስላቸው ይገባል በማለት አሳሳበዋል፡፡
የመቄት ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሃይማኖት ጋሹ “መቄት ወረዳ የታላላቅ ገዳማትና የበርካታ ጥንታዊ ቅርሶች መገኛ ናት፡፡ በአባታችን ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ያስተማሯቸው ምእመናን ዘመናዊና ሁሉን አቀፍ የአብነት ትምህርት ቤት ሕንፃ ገንብተው ለመቄት ወረዳ ሕዝበ ክርስቲያን ማበርከት በመቻላቸው የተሰማኝ ደስታ የላቀ ነው፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቱ፣ የወተት ሀብት ልማት ፕሮጀክቱና የእህል ወፍጮ ልማቱ ዘላቂና አስተማማኝ እንዲሆን ወረዳው ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል፡፡
የአብነት ትምህርት ቤቱ ወደሚቀጥለው ትውልድ እንዲተላለፍ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ የአካባቢውም ሆነ የአብነት ትምህርት ቤቱ ተቀብሎት ለሚያስተምራቸው 70 ተማሪዎች መቀመጫ ወንበሮች እንዲሁም መብራትና ውሃ ለማስገባት በቅርቡ በወረዳ አስተዳዳሩ ስም ቃል እገባለሁ ብለዋል፡፡
የልማት ማኅበሩ ጸሐፊ አቶ ቻለው እንደሻው “የልማት ማኅበሩ በአባታችን በብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የተመሠረተ ሲሆን በመንፈሳዊ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ላይ እንድንሳትፍ አባታችን ባቀረቡልን ጥያቄ መሠረት በየወሩ ገንዘባችን በማውጣትና፣ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር፣ ለቤተ ክርስቲያን አሳቢ አባቶችን በማነጋገርና ገቢ በማሰባሰብ ይህንን የመሰለ የአብነት ትምህርት ቤት ሕንፃ ለመገንባት ችለናል ብለዋል፡፡
ጥር ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ በእግዚአብሔር ፈቃድ ግንባታው ተፈጽሞ በዛሬው ዕለት ለምርቃት በቅቷል፡፡ ማኅበሩ በቀጣይ የአብነት ትምህርት ቤት የሚያስፈልጋቸውን አካባቢዎች በመለየት ትምህርት ቤት ይሠራል፡፡ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን አጥቢያዎችና ገዳማት ይደግፋል ያሉት ጸሐፊው አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ከ6.7 ሚሊዮን ብር በላይ መፍጀቱን ተናግረዋል፡፡
                              ምንጭ ፤ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ቁጥር 14/ቅጽ25 ቁጥር 388 ከሰኔ16-30/ቀን2010ዓ.ም