ከመናፍቃን ስውር ደባ ራሳችንን እንጠብቅ

ጥቅምት ፲፰ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከዲያብሎስ ጋር ተጋድሎዋን የጀመረችው በዓለመ መላእክት ነው፡፡ ቀስቱን ወርውሮ ዝናሩን አራግፎ ቤተ ክርስቲያንን ማሸነፍ ያልቻለው ዲያብሎስ ዛሬም በብዙ መልኩ እየተዋጋት ይገኛል፡፡ በማዕበል መካከል በምትቀዝፍ መርከብ የምትመሰለው ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜም አሸናፊ መሆኗ የታመነ ነው፡፡ ችግሩ መርከቧ ማዕበሉን ብትሻገርም በማዕበሉ የሚናወፁ መኖራቸው ነው፡፡ ከመርከቧ ተሳፋሪዎች ውስጥ ጥቂቶቹ በዓላማ አንዳንዶቹ ደግሞ በየዋህነት በማዕበሉ ተናውጠው ወድቀዋል፡፡ በዓላማ የሚወጡት ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ በመልእክቱ “ከእኛ ዘንድ ወጡ፥ ዳሩ ግን ከእኛ ወገን አልነበሩም፤ ከእኛ ወገንስ ቢሆኑ ከእኛ ጋር ጸንተው በኖሩ ነበር፤ ነገር ግን ሁሉ ከእኛ ወገን እንዳልሆኑ ይገለጡ ዘንድ ወጡ” ብሎ የተናገረላቸው ናቸው (፩ኛ ዮሐ. ፪፥፲፱)፡፡

እነዚህ ለጥፋት የቆሙና ለገንዘብ ወይም ለሌላ ስውር ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን የተዉ ናቸው፡፡ በየዋህነት የሚወጡት ግን በዕውቀት ማነስ፣ በይሉኝታና በመሳሰሉት ተታለው፣ በጠላት ወጥመድ ተጠልፈው የጠፉ ናቸው፡፡ እነዚህ ቀናውን መንገድ (በጎውን) የሚያሳያቸው ቢያገኙ የሚመለሱ ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች እነዚህን የዋሃን የሚያጠምዱባቸው ብዙ ዘዴዎች አሏቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል የኅትመትና የምስል ወድምፅ ውጤቶችን በቅዱሳት ሥዕላት አስውበው በማውጣት የዋሃንን ማደናገርና ከቻሉ በቅዱሳት ሥዕላቱ ሸፍነው የሚፈልጉትን የኑፋቄ ትምህርት የቤተ ክርስቲያን አስመስሎ ማቅረብ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት ሥዕላት ትልቅ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ቅዱሳት ሥዕላትን በሚገባቸው ቦታዎች ላይ ማስቀመጥና የሚገባቸውን ክብር መስጠት ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ነው፡፡ መንፈሳዊ መጻሕፍት ሲጻፉ በመጻሕፍቱ ውስጥ ታሪካቸው የተጠቀሱትን ቅዱሳን ሥዕል በፊት ገጽ ወይም በውስጥ ገጽ ማስቀመጥም የተለመደ ነው፡፡ ምእመናንም በጸሎት ቤታቸው ቅዱሳት ሥዕላትን በማስቀመጥ ለቅዱሳን የሚገባውን ክብር ይፈጽማሉ፡፡ ቅዱሳት ሥዕላትና ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ትልቅ ትስስር ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያት ተሐድሶ መናፍቃን በቅዱሳት ሥዕላት የተሸፈኑ የኑፋቄ መጻሕፍትን ገበያ ላይ እስከሚያወጡ ድረስ የቅዱሳንን ሥዕል የያዘ መጽሐፍ ኦርቶዶክሳዊ መጽሐፍ እንደሆነ “ግምት ይወሰድ” ነበር፡፡ በጎውን ሁሉ የሚጠላና ለማስጠላት የሚሠራ ዲያብሎስ ዛሬ ላይ ቅዱሳንን ለማስጠላት ያነሣሣቸው አንዳንዶች የፊት ገጻቸው የቅዱሳን ሥዕላት ውስጣቸው ደግሞ ቅዱሳንን የሚሳደቡ መጻሕፍትን በማሳተም እያሠራጩ ነው፡፡

ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል በ፳፻፬ ዓ.ም የተወገዘው፣ የከሣቴ ብርሃን ድርጅት አባል የሆነው ጌታቸው ምትኩ የጻፈው “ገድል ወይስ ገደል” የሚለው መጽሐፍ አንዱ ነው፡፡ ይህ መጽሐፍ በፊት ለፊት ገጹ የአቡነ አረጋዊን ሥዕል የያዘ ሲሆን ውስጡ ግን ቅዱሳንን የሚሳደብና የሚነቅፍ ነው፡፡ “አቡነ ተክለ ሃይማኖት እግራቸውን ያጡት በጸሎት ሳይሆን በጦርነት ነው” ከሚለው ውሸት ጀምሮ የቅዱሳንን ተጋድሎ በማናናቅ በጸጋው የሚገኘውን ድኅነት በራሳቸው ጥረት የተኩ አድርጎ የሚያቀርብ የኑፋቄ መጽሐፍ ነው፡፡

“መሪጌታ ሠረቀ ብርሃን ዘወንጌል” በሚል ስም የተጻፈው “የዘመናት እንቆቅልሽ ሲፈታ” የሚለው የኑፋቄ መጽሐፍም ሌላኛው ሁነኛ ማስረጃ ነው፡፡ መጽሐፉ የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ሥዕል የሽፋን ገጹ ላይ በመለጠፍ የዋሃንን የሚያደናግር ነው፡፡ መጽሐፉን ወደ ውስጥ ገጹ ዘልቀን ስናየው ግን ቅዱሳንን አንድ በአንድ እያነሣ የሚሳደብ ነው፡፡ ብዙዎቹ የተሐድሶ መናፍቃን ጽሑፎች ሰይጣን “ጠላቶቼን ስደቡልኝ” ብሎ የቀጠራቸው ጸሓፊዎች የጻፏቸው የሚመስሉና ቅዱሳንን የሚሳደቡ ናቸው፡፡ ይህ መጽሐፍም ከእነዚህ መጻሕፍት አንዱ ነው፡፡

ሌላኛው መጽሐፍ ደግሞ “በውኑ በማርያም ማመን ይገባሃልን?” በሚል ርእስ “መጋቤ ጥበብ ሰሎሞን” በተባለ ሰው የተጻፈው ነው፡፡ ይህ ግለሰብ በ፳፻፬ ዓ.ም ከተወገዙት ፲፮ መናፍቃን መካከል አንዱ ነው፡፡ መጽሐፉ በፊት ገጹ ላይ የእመቤታችንን ምስለ ፍቁር ወልዳ ሥዕል አድርጎ በውስጥ ገጹ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የሚሳደብ መጽሐፍ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያደገ ሰው ይቅርና ጠላት እንኳን በእመቤታችን ላይ ሊናገረው የማይገባውን ብዙ ጸያፍ ነገር አካቷል፡፡ መጽሐፉ፣ ክብር ይግባትና “ማርያም ወላዲተ አምላክ መባል የለባትም”፤ “ከዮሴፍ ጋር በወንድና በሴት ልማድ ኖራለች”፤ “ከጌታችን ውጪ ሌሎች ልጆች አሏት”፤ “ቤተ ክርስቲያን የምታመልከው እግዚአብሔርን ሳይሆን ማርያምን ነው”፤ ወዘተ. የሚሉ የጽርፈት አሳቦችን የያዘ የኑፋቄና የክህደት መጽሐፍ ነው፡፡

ይህ መጽሐፍ ለሁለተኛ ጊዜ ሲታተም አዲስ መጽሐፍ ለማስመሰልና ርእሱም ገበያ ስለከለከለ የተሻለ እንዲሸጥ በሚል እኩይ አሳብ “በእንተ ማርያም” በሚል ርእስ ወጥቷል፡፡ “በእንተ ማርያም” የሚለው ሐረግ የአብነት ተማሪዎች ቁራሽ ለመለመን በየቤቱ ሲዞሩ የሚጠቀሙበት ቋንቋ ነው፡፡ ማንኛውም ኦርቶዶክሳዊ ይህን ቃል ያውቀዋል፡፡ “በእንተ ማርያም” ተብሎ ተለምኖ ሳይሰጥ ዝም ብሎ የሚያልፍ ኢትዮጵያዊ ምእመን የለም፡፡ ይህን በማሰብ ይመስላል ተሐድሶ መናፍቃኑ የመጽሐፉን ርእስ ከ “በውኑ በማርያም ማመን ይገባሃልን?” ወደ “በእንተ ማርያም” በመቀየር እመቤታችንን የሚሳደብ መልእክት ያስተላለፉት፡፡

ጸሓፊዎቹ ሲጽፉ ራሳቸውን “ዲያቆን”፣ “ቄስ”፣ “መምህር”፣ “መጋቤ ጥበብ”፣ “መጋቤ ሐዲስ”፣ ወዘተ. በሚል መዓርግና ስያሜ ነው፡፡ መጻሕፍትን ብቻ ሳይሆን በዚሁ መልክ ባለቤት አልባ በራሪ ወረቀቶችን፣ ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችን፣ የድረ ገጽ ጽሑፎችን፣ ሲዲዎችን፣ ቪሲዲዎችን፣ ወዘተ ያወጣሉ፡፡ ለምሳሌ ይህ በራሪ ወረቀት የእመቤታችንን ሥዕል የያዘ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ (ሎቱ ስብሐት) “አማላጅ እንደሆነ ለማስረዳት” ተብሎ የተሠራጨ የመናፍቃን ትምህርት ነው፡፡

በ፳፻፬ ዓ.ም ከተወገዙት ግለሰቦች መካከል አንዱ የሆነው ጽጌ ስጦታው ከግብረ አበሩ ጋር በመሆን ባወጡት ሲዲም ላይ ግለሰቦቹ በአለባበሳቸው የቤተ ክርስቲያን መምህር መስለው ከመቅረባቸውም በላይ የሲዲው የሽፋን ገጽ የድንግል ማርያምና የአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ሥዕላትን ይዟል፡፡ እነዚህ ሁሉ ወጥመዶች የተዘረጉት ኦርቶዶክሳውያንን ከበረታቸው ለማስኮብለል ነው፡፡ እነዚህ መጻሕፍትና የምስል ወድምፅ ውጤቶች የእኛ መስለውን በስሕተት ገዝተናቸው ይሆናል፡፡ መጻሕፍቱን አንብበን፣ ሲዲዎችን ዐይተን የተደናገርንም እንኖር ይሆናል፡፡

ማንኛውንም ጉዳይ በሩቅ ዐይተን ውሳኔ ላይ ሳንደርስ ቀርበን መመርመር፣ ከእኛ በላይ የሆነውን እውነተኞች አባቶችን በመጠየቅ ራሳችንን ከስሕተት መጠበቅ ይገባናል፡፡ “በሩቅ ያዩት አህያ ፈረስ ይመስላል” እንደሚባለው በሽፋናቸው፣ በውጫዊ ይዘታቸው የሚበሉ መስለው ውስጣቸው የመናፍቃንን የክሕደት መርዝ የያዙ መጻሕፍት ይኖራሉ፡፡ መጻሕፍቱ ወይም የምስል ወድምፅ ውጤቶች ቅዱሳት ሥዕላትን ስለያዙ፣ በግእዝ ቋንቋ ስለተጻፉ ብቻ የእኛ ናቸው ማለት አይደለም፡፡

ከመናፍቃን ስውር ደባ ራሳችንን ለመጠበቅ ምን እናድርግ?

ተሐድሶ መናፍቃን በየጊዜው መልካቸውን እየቀያየሩ ከሚያዘጋጁት የጥፋት ወጥመድ ራሳችንን ከመከላከል እና ሌሎችን ከመጠበቅ አኳያ ማድረግ ያለብንን ጥቂት የጥንቃቄ ነጥቦችን እንመልከት፡-

፩ኛ. ቤተ ክርስቲያንን እና የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ማወቅ

ቤተ ክርስቲያን በሰማይ ያሉ የቅዱሳን፣ በምድር ያሉ የክርስቲያኖች አንድነት ናት፡፡ ይህች አንድነት አሐቲ፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ኵላዊት ናት፡፡ ክርስቶስ በደሙ የመሠረታት ስለሆነች የክርስቶስ አካል ናት፡፡ የክርስቶስ አካሉ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን ለማረም መነሣት “እግዚአብሔርን ለማረም” እንደ መነሣት ነው፡፡ በአስተምህሮዋም ነቅ የሌለባትና ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለችውን ትምህርት ከሐዋርያት ጀምሮ ለዓለም ስትመግብ የኖረችና የምትኖር ናት፡፡ ትምህርቷ እንክርዳድ ያልተቀላቀለበት፣ እንግዳ የሆነ ትምህርት ያልታከለበት ጥንታዊና ቀጥተኛ ነው፡፡ አስተምህሮዋ ከአምላኳ የተቀበለችው ንጹሕ ዘር ነው፡፡ የምታስተምረው እግዚአብሔር ለዓለም የገለጠውን እውነት እንጂ ራሷ የፈጠረችውን ታሪክ አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ከእግዚአብሔር የተቀበለችውን ለዓለም መመስከርና ማስተላለፍ እንጂ የተጣመመ ኖሮ ማቅናት፣ የጎደለ ኖሮ መሙላት፣ ያነሰ ኖሮ መጨመር፣ አላስፈላጊ የሆነ ኖሮ መቀነስ አይደለም፡፡ ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ የተሰጠች መንገድ ናት፡፡ ይህን ለማስተካከል መሞከር ራስን በእግዚአብሔር ቦታ ማስቀመጥ ነው፡፡

ስለዚህ ሁልጊዜም ቤተ ክርስቲያንን እና አስተምህሮዋን ለማወቅ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ብዙ ማወቅ የሚቻለው በመማር ነው፡፡ ስንማር ቤተ ክርስቲያንን እና የቤተ ክርስቲያን የሆነውን ሁሉ ማወቅ እንችላለን፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ሊቃውንትና መጻሕፍት ማወቅ እንግዳ በሆነ አዳዲስ ትምህርት ከመወሰድ ያድናል፡፡ “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል” (ሆሴ. ፬፥፮) እንደተባለ ዕውቀት ማጣት ብዙ ችግሮችን ያመጣል፡፡ በሌሎች ካለመወሰድ አልፎ ሌሎችን ማትረፍ የሚቻለው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ክርስትናን ገንዘብ በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ ሁልጊዜ መማር፣ በመንፈሳዊ ዕውቀትና በመንፈሳዊ ሕይወት ማደግ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ስናደርግ የቤተ ክርስቲያንን ድምፅ ከሌሎቹ ለይተን ማወቅ እንችላለን፡፡ የራሳችንን ካወቅን ደግሞ የሌሎችን የማደናገሪያ ቃል አንሰማም፡፡

፪ኛ. የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ያገባኛል ብሎ መቀበል

ቤተ ክርስቲያን ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ባለው መዋቅሯ  ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን ታስተላልፋለች፡፡ ውሳኔዎች እንዲፈጸሙ መመሪያዎች እንዲተገበሩ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡ ትግበራውን ለማገዝ መጀመሪያ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ጉዳዬ ብሎ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ የኑፋቄ ትምህርት የሚያስተምሩ ሰዎች የሚወገዙት በትምህርት ያልበሰልነውን እንዳያታልሉ ነው፡፡ የኑፋቄ መጻሕፍት መልስ የሚሰጥባቸው እኛን ከኑፋቄ ለመጠበቅና በመንፈሳዊ ዕውቀታችን ለማሳደግ ታስቦ ነው፡፡ ትምህርት የሚሰጠው፣ ጉባኤ የሚዘጋጀው፣ የቤተ ክርስቲያን የውስጥ አገልግሎት የሚፈጸመው እንድናውቅ ብቻ ሳይሆን እንድንጸድቅም ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ልጆቿን በትምህርትና በምሥጢራት እግዚአብሔርን ወደ መምሰል ማሳደግ ነውና፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን መቀበል፣ ማክበርና መፈጸም፤ ጥያቄዎች ሲኖሩንም ኦርቶዶክሳዊ በሆነ መንገድ ማቅረብ፤ ከዚህም ባሻገር ከግለሰቦች ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን መታዘዝ ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች እንዳይፈጸሙ የሚከለክሉ፣ በቤተ ክርስቲያን ስም ግለሰባዊ ፍላጎታቸውን የሚያራምዱ፣ ቅዱስ ሲኖዶስን የማውገዝ ሥልጣን የሌለው አስመስለው የሚያቀርቡ ተሐድሶ መናፍቃንን ሤራ ባለመረዳት የቤተ ክርስቲያንን መልእክት የማያከብሩ የዋሃን አሉ፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ከተወገዙ የተሐድሶ መናፍቃን ድርጅቶችና ግለሰቦች ጉባኤ ላይ የሚገኙ፤ የእነርሱን የኅትመትና የምስል ወድምፅ ውጤቶች የሚያከፋፍሉ፣ የሚሸጡ፣ የሚገዙ፣ የሚያነቡና የሚያዳምጡም አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ክፍተቶች የተፈጠሩት የቤተ ክርስቲያንን መልእክት ጉዳዬ ብሎ ባለመስማትና ባለመቀበል ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያንን መልእክት ሰምቶ በመቀበል እንዲህ ዓይነት የመረጃ ክፍተቶችን መሙላት ከሁላችን ይጠበቃል፡፡

፫ኛ . ስለማናውቀው ነገር መጠየቅ

ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮዋን የምታስፋፋባቸው ብዙ መንገዶች አሏት፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ የጻፏቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ተጠቃሽ የአስተምህሮ ማስፋፊያ መንገዶች ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት የምንላቸው የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የሚያስጠብቁ ናቸው፡፡ እነዚህ መጻሕፍት የቤተ ክርስቲያን መሆናቸውን ማወቅ የምንችለው ያለንን ዕውቀትና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በመጠቀም ነው፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትን ከሌሎች ለመለየት የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ማወቅ ግድ ይሆናል፡፡ ይህም በአንድ ጀንበር የሚሳካ ቀላል ተግባር ባይሆንም መፍትሔው ግን ከባድ አይደለም፡፡ መጻሕፍትን ለመግዛት፣ የምናነባቸውን ለመምረጥ፣ ስናነብ ያልገባንን ለመረዳት፣ ትክክል መስሎ ያልታየን ወይም ያደናገረን ነገር ሲኖር ለማጥራት የቤተ ክርስቲያንን ሊቃውንት እና ከእኛ የተሻለ መንፈሳዊ ብስለት ያላቸውን መምህራን መጠየቅ መልካም ይሆናል፡፡

“ሊሆን ይችላል” ወይም “ለእኔ ተስማምቶኛል” በሚል ሰበብ ሳይገባንና በግል ፍላጎታችን ላይ ተመሥርተን የምንቀበለው “ትምህርት” ሊኖረን አይገባም፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ጠያቂ መሆንና ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ዕድገት ምክር የሚሰጡን መሪዎችን መፈለግና ምክራቸውን መተግበር ተገቢ ነው፡፡ ከዚሁ ሁሉ ጋርም ለትምህርት የምንፈልጋቸውን የኅትመትም ሆነ የምስል ወድምፅ ውጤቶች ስንገዛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን፡፡ በራሳችን ገንዘብ የመናፍቃንን ትምህርት ገዝተን ወደቤታችን ማስገባት የለብንም፡፡ ከመግዛታችን በፊት የጸሓፊውን ማንነት፣ የመጽሐፉን ይዘት ማወቅ፤ ካላወቅነውም መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በስሕተት ገዝተናቸው ያነበብናቸውና ጥያቄ የፈጠሩብንም ካሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን በመጠየቅ መልስ ማግኘት አለብን፡፡

፬ኛ. መጻሕፍቱ መልስ እንዲሰጥባቸው ለሚመለከተው አካል ማቅረብ

ተሐድሶ መናፍቃን ባዘጋጁት ወጥመድ እንዳንሰናከል ለራሳችን ጥንቃቄ ከማድረግ ጎን ለጎን ሌሎችን የማዳን ሥራም ከሁላችን ይጠበቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያን የሆነውን ካልሆነው መለየት የማንኛውም ክርስቲያን ግዴታ ነው፡፡ ባለማወቅ የሚደናገሩትን ከመጠበቅ አንጻር ግን የኅትመትና የምስል ወድምፅ ውጤቶቹ የእኛ አለመሆናቸውን ማወቅ ብቻ በቂ አይሆንም፡፡ ለሚመለከተው አካል ለማቅረብ የኅትመትና የምስል ወድምፅ ውጤቶቹ በማስረጃነት ያስፈልጋሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የሚንዱ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚሳደቡ፣ ቅዱሳንን የሚያቃልሉ የኅትመትና የምስል ወድምፅ ውጤቶች ስናገኝ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ጥቅም ብለን ባንገዛቸውም የዋሃንን እንዳያደናግሩ መልስ እንዲሰጥባቸው አስበን መግዛት ይኖርብን ይሆናል፡፡ በእኛ ዐቅም መልስ ልንሰጥባቸው የማንችል ከሆነም እንኳን በላዔ መጻሕፍት ሊቃውንት ሞልተውናል፡፡ በስሕተት ገዝተን ያስቀመጥናቸው የተሐድሶ መናፍቃን የኅትመትና የምስል ወድምፅ ውጤቶች ለሊቃውንቱ በማቅረብ መልስ እንዲሰጥባቸው ማድረግ ይገባል፡፡ ይህን ስናደርግ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ማትርፍ እንችላለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ማስገንዘቢያ

ይህ ጽሑፍ፣ ከመስከረም ፲፮ – ፴ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በወጣው የስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ዕትም፣ በ “ንቁ” ዓምድ ሥር፣ “የተሐድሶ ስውር ደባ” በሚል ርእስ በገጽ ፮፣ ፯ እና ፲፭ ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡