ከሃያ አምስት በላይ የግብጽ ምእመናን በቦምብ ፍንዳታ ሕይወታቸው ዐለፈ

news

ታኅሣሥ ፫ ቀን ፳፻፱ .

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በግብጽ ካይሮ ከተማ እሑድ ታኅሣሥ ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ረፋድ ላይ ከቅዱስ ማርቆስ ካቴድራል አጠገብ በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በደረሰ የቦምብ ፍንዳታ ከሃያ አምስት በላይ የግብጽ ምእመናን ሕይወታቸው ዐለፈ፡፡

ፍንዳታው የደረሰው በሴቶች መቆሚያ በኩል መኾኑን ከግብጽ አካባቢያዊ የመረጃ አውታሮች ለመረዳት ተችሏል፡፡

በጥቃቱ ዐርባ ዘጠኝ ሰዎች መቍሰላቸውንና ከእነዚህ መካከልም አብዛኞቹ ሴቶች መኾናቸውን የግብጽ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር አሕመድ ኢማድ ተናግረዋል፡፡ እንደ ጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ መግለጫ ከቍስለኞቹ መካከል ሦስቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡

egypt-7

ጕዳቱ ለደረሰባቸውና ሕክምና ላይ ለሚገኙት ቍስለኞች የደም ልገሳ እንዲደርግላቸው በማኅበራዊ ሚድያዎች አማካይነት የግብጽ ሆስፒታሎች ጥሪ ማቅረባቸውም ታውቋል፡፡

በፍንዳታው ምክንያት በግብጻውያን ምእመናን ላይ ለደረሰው ሞትና ጉዳት አገሪቱ የሦስት ቀን ኀዘን እንደምታውጅ የግብጽ ፕሬዚዳንት አብደል ፈታሕ አል ሲሲ አስታውቀዋል፡፡

ለድርጊቱ ሓላፊነቱን የወሰደ አካል ግን እስካሁን ድረስ አልተገኘም፡፡

fun-5

በፍንዳታው ሕይወታቸው ያለፈ ምእመናን ሥርዓተ ቀብርም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ታዎድሮስ ካልዕ መሪነት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ብዙ ሺሕ የግብጽ ምእመናን በተገኙበት ታኅሣሥ ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በግብጽ ቅድስት ማርያም እና ቅዱስ አትናቴዎስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

ምንጭ፡

Orthodoxy Cognate PAGE – Media Network

http://www.dailynewsegypt.com

http://english.ahram.org.eg