ኤጲስ ቆጶሳቱ ሳይለግሙ ምእመናንን እንዲያገለግሉ ፓትርያርኩ አሳሰቡ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የኤጲስ ቆጶሳት ሥርዓተ ሲመት በተፈጸመበት ዕለት በሰጡት ቃለ ምዕዳን ለዚህ በዓለ ሢመት ያደረሳቸውን ልዑል እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ ለኤጲስ ቆጶሳቱም የሚከተለውን አባታዊ ምክር ለግሰዋል፤

‹‹እግዚአብሔር የሰጣችሁን ሕዝብ በቀንም በሌሊትም ከእርሱ ሳትለዩ፣ በዅለንተናዊ ሕይወታችሁ ባለ አቅማችሁ ዅሉ ሳትለግሙ አገልግሉት፡፡ ከስደት፣ ከእንግልት ተገላግሎ የልማት ኃይል በመኾን አገሩን እንዲገነባ፤ ሃይማኖቱንና ባህሉን እንዲጠብቅ ያለመታከት አስተምሩት፡፡ ከመንፈሳዊ መሠረተ ትምህርት ጀምሮ እስከ ኤጲስቆጶስነት ድረስ እየመገበና እየተንከባከበ ለታላቅ ክብር ያበቃችሁን ሕዝብ የልቡን ሃይማኖታዊ ትርታ እያዳመጣችሁ በወቅቱ እየደረሳችሁ አስተምሩት፤ አጽናኑት፡፡ ልጆቹን በተኩላዎች ከመነጠቅ አድኑለት፡፡ ወጣቱ ትውልድ ከሐሺሽ፣ ከአደንዛዥ ዕፅ፣ ከሱሰኝነት፣ ከሥራ ፈትነትና ከመጤ ጎጂ ባህል እንዲላቀቅ አድርጉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ከሃይማኖት አባቶች የሚፈልገው ይህንኑ ነው፡፡››

የጸሎተ አስኬማ ሥርዓቱ በከፊል

ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በየሀገረ ስብከቱ በየመንበራቸው ተገኝተው ከሕዝቡ ጎን ሳይለዩ ተግተው የሚሠሩ፤ ዅሉንም ወገን በእኩል ዓይን የሚያዩና የሚያስተናግዱ፤ በሕዝቡ መካከል ሰላምን የሚሰብኩ፤ ከማናቸውም ርዕዮተ ዓለም ደጋፊነት የተለዩና ከጣልቃ ገብነት የጸዱ፤ ከዅሉም በላይ ለአንዲት ሉዓላዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት መከበር በጽናት የቆሙ አባቶችን አገራችን ኢትዮጵያ እንደምትሻ ገልጸው፣ ‹‹ዓለሙ በውስጡ ያለና የሌለ ኃይሉን አግበስብሶ እንደሚታገላችሁ አትርሱ፤ ነገር ግን የድል አድራጊው ጌታ ሠራዊት ናችሁና የመጨሻው ድል የእናንተ መኾኑን አትጠራጠሩ›› በማለት ኤጲስ ቆጶሳቱ በምንም ዓይነት ፈተና ሳይበገሩ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተሰጣቸውን ሓላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ መክረዋል፡፡

የጸሎተ አስኬማ ሥርዓቱ በከፊል

ሹመት ማለት የሥራ መገልገያ መሣርያ እንጂ የግል መገልገያ እንዳልኾነ፤ አገልግሎቱም መውጣት መውረድን፣ መንገላታትን፣ ድካምን ከዚያም አልፎ መሥዋዕትነትን እንደሚጠይቅ ያስታወሱት ፓትርያርኩ፣ ‹‹በዚህ ሐዋርያዊ ጉዞ ብዙ መሰናክሎች ሊገጥሟችሁ ቢችሉም ዅሉም ችግሮች ከሞት በታች እንጂ ከሞት በላይ አይደሉምና ከሐዋርያዊ ተልእኳችሁ የሚገታችሁ ምንም ነገር አይኖርም፡፡ ምክንያቱም የገባችሁት ቃል ኪዳን እስከ ሞት ድረስ ለመዳፈር ነውና›› ሲሉ እስከ ሞት ድረስ በመታመን የቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ እንዲያስፋፉ ለኤጲስ ቆጶሳቱ መልእክታቸውን አስተላለፈዋል፡፡

የኤጲስ ቆጶሳቱ ሥርዓተ ሲመት አፈጻጸም በከፊል

ቅዱስነታቸው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስትነጻጸር በምእመናን ብዛት፣ በሃይማኖት ጽናት፣ በሐዋርያዊ ትውፊት፣ በአበው ቀኖና፣ በሃይማኖታዊ ባህልና በሥርዓተ አምልኮ አፈጻጸም ቀዳሚውን ሥፍራ እንደምትይዝ አውስተው፣ ቤተ ክርስቲያን በአበው ሐዋርያዊ ተጋድሎ ጠብቃ ያቆየችውን ይህን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ ለመጭው ትውልድ ለማስተላለፍ ብቃትና ተነሣሽነት ያላቸውን ኤጲስ ቆጶሳት መሾም ተቀዳሚ ተግባሯ እንደ ኾነ፤ የኤጲስ ቆጶሳት ሹመትም ሐዋርያዊ ተልእኮውን ለማስፋፋት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል፡፡

ሥርዓተ ሲመት የተፈጸመላቸው ኤጲስ ቆጶሳት በከፊል

አገራችን ኢትዮጵያ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅኝት የተቀረፀ፤ ለሃይማኖት፣ ለሥነ ምግባር፣ ለፍትሕ፣ ለልማትና ለአንድነት የተመቸ ሕዝብ እንዳላት፤ ይህን የተቀደሰ ባህልና ሥነ ምግባር ለማስቀጠልም ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ብዙ እንደሚጠበቅ የገለጹት ቅዱስ ፓትርያርኩ ‹‹በተለይም ብፁዓን አበው ሊነ ጳጳሳት እና ኤጲስ ቆጶሳት ኢትዮጵያውያንን በአባትነት መንፈስ በማቅረብ ዅሉም በሰላም፣ በወንድማማችነት፣ በመከባበር፣ በመተማመንና በመቻቻል አብረው እንዲኖ፤ እንደዚሁም ትውልዱ እንደ አባቶቹ ደማቅ ታሪክ ሠርቶ እንዲያልፍ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይኖርባችኋል›› ብለዋል፡፡

ሥርዓተ ሲመት የተፈጸመላቸው ኤጲስ ቆጶሳት በከፊል

በመቀጠልም ቤተ ክርስቲያናችን በሃይማኖት አስተምህሮ እና ይዘት፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን፣ በሐዋርያዊ ትውፊት፣ በሥርዓተ አምልኮ አፈጻጸም እና በቅዱስ ባህል ምሥረታ እንከን የለሽ ብትኾንም በአስተዳደር፣ በፋይናንስና ንብረት አያያዝ፣ በምእመናን ክብካቤና በሐዋርያዊ ተልእኮ ክንውን፣ በእናቶችና በወጣቶች አያያዝ ከዘመኑ ጋር መራመድ አለማቻሏ የወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን ተግዳሮት መኾኑን ቅዱስነታቸው ጠቅሰው፣ ይህን ተግዳሮት ከሥር መሠረቱ ነቅሎ በመጣል ወደሚፈለገው መልካም አስተዳደር ለመሸጋገር የአሁኖቹ ሥዩማን ኤጲስ ቆጶሳት ከቀደሙት ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመቀናጀት ጉልህ ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

እንደ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ማብራርያ በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖት እና ሥነ ምግባር እጅግ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ከመኾናቸው አኳያ፣ የዘመኑ ትውልድ በሃይማኖት የጸና፤ በሥነ ምግባር የቀና፤ ለአገር እና ለወገን ክብር የቆመ እንዲኾን የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን ማስፋፋት እና የአባቶች አርአያነት ያለው ሕይወት መኖር ቍልፍ መሣርያ ነው፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ እንደዚሁም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና በክልል ትግራይ ደቡባዊ ማይጨው ዞን፣ ደቡብ ምሥራቅና ምሥራቃዊ አዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዕለቱ ባስተላለፉት መልእክት ለኤጲስ ቆጶስነት መመረጥ የእግዚአብሔር ጥሪ መኾኑን በማስረዳት ኤጲስ ቆጶሳቱ አባታዊ ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲፈጽሙ፤ ሕዝበ ክርስቲያኑም ለአባቶች በመታዘዝ ኦርቶዶክሳዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አስተምረዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተመረጡት ዐሥራ አምስቱ ኤጲስ ቆጶሳት ቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ሐምሌ ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ገዳም ጸሎተ አስኬማ ከተደረሰላቸው በኋላ በነጋታው ሐምሌ ፱ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ ሥርዓተ ሢመት ተፈጽሞላቸዋል፡፡

ኤጲስ ቆጶሳቱ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በመጠበቅና በማስጠበቅ የተሰጣቸውን አባታዊ አደራ በሓላፊነት እንደሚወጡ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና በሕዝበ ክርስቲያኑ ፊት ሃይማኖታዊ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡

በአቋማቸውም በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ አምላክነት እንደሚያምኑ፤ በኒቅያ፣ ቍስጥንጥንያ እና ኤፌሶን በተወሰነው ውሳኔ መሠረት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ጠብቀው እንደሚያስጠብቁና እንደሚያስምሩ፤ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በእግዚአብሔር ወልድ የባሕርይ አምላክነት፣ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክነት፣ ዘለዓለማዊ ድንግልናዋ እና አማላጅነቷ፤ እንደዚሁም በቅዱሳን መላእክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ሰማዕታት እና ጻድቃን አማላጅነት አምነው እንደሚያስተምሩ፤ ይህን ትምህርት የሚቃወሙትንና ተሐድሶ ነን የሚሉ መናፍቃንን እንደሚያወግዙም ቃል ገብተዋል፡፡

ኤጲስ ቆጶሳቱ ቃለ መሐላ ሲፈጽሙ

ምሥጢረ ቍርባንን በተመለከተም “ካህኑ ሲባርከው ኅብስቱ ተለውጦ አማናዊ ሥጋ ወልደ እግዚአብሔር፣ ወይኑም ተለውጦ አማናዊ ደመ ወልደ እግዚአብሔር መኾኑን፤ ጥምቀት አንዲት መኾኗን እናምናለን፤ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ያሉ ምእመናን በተዋሕዶ ሃይማኖት ጸንተው፣ ቀኖናዊ ሥርዓቷን አክብረውና ጠብቀው እንዲኖሩ ተግተን እናስተምራለን፡፡ ይህን ዅሉ ለማድረግ እግዚአብሔር ይረዳን ዘንድ እንማጸናለን፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ፊት ቃል ኪዳን እንገባለን” የሚል ቃለ መሐላ ፈጽመዋል፡፡