ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከትናንት እስከ ዛሬ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥቅምት ፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ግብረ ኖሎት

በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደተጻፈው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ምሳ ተመግቧል፡፡ የተዘጋጀው የምግብ ማዕድ ካበቃ በኋላም ቅዱስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጠርቶ ‹‹ትወደኛለህን?›› እያለ ጠይቆታል፡፡ እንደሚወደው ምላሽ መስጠቱን ተከትሎም ‹‹በጎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ፤ ግልገሎቼን ጠብቅ፤›› በማለት አዝዞታል (ዮሐ. ፳፩፥፩-፲፯)፡፡

ይህ ምሥጢር ለጊዜው ጌታችን ሐዋርያትን፣ ሰብዐ አርድእትንና ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስትን በአጠቃላይ መቶ ሃያውን ቤተሰብእ እንዲጠብቅና እንዲከባከብ ለቅዱስ ጴጥሮስ ሓላፊነት መስጠቱን ያመላክታል፡፡ ለፍጻሜው የቤተ ክርስቲያን አባቶች (ጳጳሳት) መምህራንን፣ ካህናትን እና ሕዝበ ክርስቲያንን እንዲጠብቁ፣ እንዲያስተዳድሩ በእግዚአብሔር መሾማቸውን የሚያስረዳ ምሥጢር አለው፡፡ መምህራንና ካህናትም በየመዓርጋቸው ወጣንያን፣ ማእከላውያን እና ፍጹማን ምእመናንን የመጠበቅ፣ የማስተማር፣ የመከታተል ሓላፊነት እንዳለባቸው ከዚህ ትምህርት እንገነዘባለን፡፡ ይኸውም ሐዋርያዊ ግብረ ኖሎት (ሐዋርያዊ የእረኝነት አገልግሎት) ነው፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ

ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጣቸውን አምላካዊ ትእዛዝ እና የኖላዊነት ሥልጣን (ሥልጣነ ክህነት) መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የኖላዊነት ተልእኮውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሐዋርያዊ ተልእኮዉን ለማከናወን የሚያስችሉ ሕግጋትን ለማውጣት፣ መመሪያዎችንም ለማጽደቅ በዓመት ሁለት ጊዜ መንፈሳዊ ጉባኤ ያደርጋል፡፡ የመጀመሪያው ጉባኤ ጥቅምት ፲፪ ቀን (በቅዱስ ማቴዎስ ክብረ በዓል)፤ ሁለተኛው ደግሞ በዓለ ትንሣኤ በዋለ በሃያ አምስተኛው ቀን (በርክበ ካህናት) ይካሔዳል፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ብቻ በሚሳተፉበት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አባቶቻችን በጋራ በመሰባሰብ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቀላጠፈ አገልግሎት፣ ለምእመናን በሃይማኖት መጽናትና መንፈሳዊ ዕድገት የሚበጁ መመሪያዎችንና ውሳኔዎችን ያሳልፋሉ፡፡

አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ

ከቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በተጨማሪ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ድረስ ያሉ መንፈሳውያን ሰበካ ጉባኤያትም ቃለ ዓዋዲውንና የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን መነሻ በማድረግ በየጊዜው ጉባኤ በማድረግ ለሐዋርያዊ ተልእኮው መዳረስ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት የሚበጁ የጋራ አቋም መግለጫዎችንና ደንቦችን ያወጣሉ፡፡ ከእነዚህ ጉባኤያት መካከልም የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

በየዓመቱ በጥቅምት ወር በሚካሔደው በዚህ ጉባኤ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚጠቅሙ፣ ለመንፈሳዊ አስተዳደሯም የሚበጁ መሠረታዊ ጉዳዮች ይነሣሉ፤ መመሪያዎችና ውሳኔዎች ይወጡና በአባቶች ተመዝነው አስፈላጊነታቸው ከታመነበት ይጸድቃሉ፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት፣ በመላው ዓለም የሚገኙ አህጉረ ስብከት፣ የድርጅቶችና የመንፈሳዊ ኮሌጆች እንደዚሁም የማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎት ሪፖርቶች በዚህ ጉባኤ ይቀርባሉ፡፡ በሪፖርቶቹ ላይም ውይይትና የልምድ ልውውጥ ይደረግና የላቀ ውጤት ያስመዘገቡት ይሸለማሉ፤ ይበረታታሉ፡፡ ዝቅተኛ የአገልግሎት ፍሬ ይዘው የመጡ ደግሞ ከጉባኤው ልምድ ቀስመው አገልግሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ይመከራሉ፡፡

የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አመሠራረት ታሪክ በአጭሩ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በእጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ሰብሳቢነት፣ በፀባቴ ጥዑመ ልሳን ጸሐፊነት፣ በሰባ ሁለት የአድባራት አስተዳዳሪዎችና አገልጋይ ካህናት አባልነት የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ የሚወስን መንፈሳዊ ጉባኤ መስከረም ፰ ቀን ፲፱፻፲፰ ዓ.ም ተቋቁሞ እንደነበር፤ ከዚያም በ፲፱፻፶፱ ዓ.ም መንግሥት ያወጣው የመሬት ግብር ዓዋጅ በቤተ ክርስቲያን ላይ ችግር በማምጣቱ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ተቋማት ለማዋቀር በዓዋጅ ቍጥር ፵፰/፶፱ እና ፹፫/፷፭ ሕጋዊ ፈቃድ እንደተሰጣት፤ በዚህ ሥልጣን መሠረትም ቤተ ክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ቃል ተመርታ፣ በሀብቶቿ በምእመናን ተጠቅማ፣ ከመንግሥት ጥገኝነት ነጻ ኾና፣ ራሷን ችላ መተዳደር እንደጀመረች የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

ሰማዕቱ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ፓትርያርክ ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ምእመናንን የሚያሳትፍ የቤተ ክርስቲያን መተዳደሪያ ደንብ (ቃለ ዓዋዲ) አዘጋጅተው በ፲፱፻፷፭ ዓ.ም የሰበካ ጉባኤ አስተዳደርን አቋቁመዋል፡፡ ወጣቶችን ጭምር የሚያሳትፈው ይህ ቃለ ዓዋዲም አገልጋይ ካህናት የወር ደመወዝ እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባሻገር በካህናትና በምእመናን መካከል ያለው ኅብረት እንዲጠናከርም አድርጓል፡፡ ስለዚህም ስለሰበካ ጉባኤ መቋቋም ሲነገር ወጥነት ያለው መንፈሳዊ የአስተዳደር መዋቅር እንዲዘረጋ ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት ሰማዕቱ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ አብረው ይዘከራሉ፡፡

ቅዱስነታቸው የጀመሩት ይኼው መዋቅራዊ አሠራር እና ያፋጠኑት ሐዋርያዊ አገልግሎትም በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመን ይበልጥ ተስፋፍቷል፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ኾነው ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉት ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ የሰበካ ጉባኤን በማጠናከር ረገድ ያደረጉት ብርቱ ጥረትም የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በዚህ መልኩ እየተጠናከረ የመጣው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ፣ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት በማሳደግ፣ አስተዳደሯንም በማቀላጠፍ ዓመታትን አልፎ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ቅዱስ ሲኖዶስ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት የወቅቱንና የዘመኑን አካሔድ በሚዋጅ መልኩ ቃለ ዓዋዲው ተሻሽሎ ሊታተም ዝግጅት ላይ ነው፡፡

የታሪኩ ምንጮች፡-

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ፤ አክሱም ማተሚያ ቤት፣ አዲስ አበባ፤ ፳፻፯ ዓ.ም፣ ገጽ 168 – 169፡፡
  • ዝክረ ነገር ዘመልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪኹን፣ ማኅበረ ቅዱሳን፤ አዲስ አበባ፣ ፳፻፱ ዓ.ም፤ ገጽ 140 – 141፡፡
  • ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት፣ የመጀመሪያው ልዩ ዕትም፤ አዲስ አበባ፣ የካቲት ወር 2001 ዓ.ም፤ ገጽ 14 – 15፡፡

የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ እና ተግባር

በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው ቃለ ዓዋዲ አንቀጽ ፭ ላይ እንደተገለጸው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ዓላማ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲኾን ማድረግ፤ የቤተ ክርስቲያንን አገልጋዮች በሐዋርያዊ ተግባር ማደራጀትና ችሎታቸውንና ኑሯቸውን ማሻሻል፤ ምእመናንን ማብዛትና በመንፈሳዊ ዕውቀት ጐልምሰው፣ በምግባር በሃይማኖት ጸንተው በክርስቲያናዊ ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ፤ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር ማሻሻልና በማናቸውም ጉዳይ ራሳቸውን ማስቻል ነው፡፡

ይህን መንፈሳዊ ዓላማ ለማስፈጸም የተዋቀረው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤም የእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፤ ከየመንበረ ጵጵስናው የተወከሉ ካህናት፣ ምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ከብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እና ከጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ሓላፊዎች ጋር በአንድነት ተሰባስበው የሚመሠርቱት ጉባኤ ሲኾን፣ በዓመት አንድ ጊዜ የሚሰበሰብ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ እንዳለውና ይህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ስብሰባ እንደኾነ በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ ፵፮ ላይ ተደንግጓል፡፡

በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ ፵፯ ላይ በተቀመጠው ድንጋጌ መሠረት በአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ዓመታዊ ጉባኤው ላይ ፓትርያርኩ ርእሰ መንበር፤ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ምክትል ሊቀ መንበር፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት አባላት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አባልና ጸሐፊ፤ የአጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው አስተዳደር ጉባኤ (ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) አባል፤ የአህጉረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች አባላት፤ ከየአህጉረ ስብከት መንፈሳውያን አስተዳደር ጉባኤያት የተወከሉ ካህናት፣ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አባላት፤ በውጭ አገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች አባላት ኾነው የሚሳተፉበት ታላቅ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ነው፡፡

የአህጉረ ስብከትን ሪፖርቶችና ዕቅዶች ከሰማ በኋላ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ እና ተመካክሮ ውሳኔ ማሳለፍ፤ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ለማጠናከር ከፍተኛ መንፈሳዊ ት/ቤቶች፣ የካህናት፣ የሰባክያንና የሰንበት ት/ቤት መምህራን ማሠልጠኛዎች እንደዚሁም የልማትና በጎ አድራጎት ተቋማት በሀገረ ስብከት እና በማእከል ደረጃ እንዲቋቋሙና እንዲደራጁ ማድረግ፤ የአጠቃላዩን አስተዳደር ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ (ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ) መምረጥ በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ ፵፰ የተዘረዘሩ የጉባኤው ሥልጣንና ተግባራት ናቸው፡፡ በዚሁ አንቀጽ እንደተጠቀሰው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ተሳትፎ በጉባኤው

ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተመሠረተ ሕጋዊ ማኅበር እንደመኾኑ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት አመራርና አስፈጻሚ አባላቱን እየወከለ በአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ ማኅበሩ ስብከተ ወንልን በማስፋፋት፣ አዳዲስ ምእመናንን በማስጠመቅ፤ ለገዳማትና አብነት ትቤቶች ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ፤ ለአባቶች የስብከተ ወንጌልና ከአስተዳደር ጋር የተያያዙ ሥልጠናዎችን በመስጠት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መስፋፋት ያከናወናቸው ዐበይት ተግባራቱ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ከአህጉረ ስብከት ሪፖርቶች ጋር ተካተው ሲቀርቡ መቆየታቸውም የሚዘነጋ አይደለም፡፡

ለአብነትም በጠረፋማ አካባቢዎች ስብከተ ወንጌልን በማዳረስ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከስድሳ ዘጠኝ ሺሕ ለሚበልጡ አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን ማሰጠቱ፤ ለአብነት መምህራን እና ደቀ መዛሙርት ወርኃዊ የገንዘብ እና አስቸኳይ የቀለብ ድጋፍ ማድረጉ፤ የአብነትና ዘመናዊ ት/ቤቶችን፣ የመጠጥ ውኃና ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በልዩ ልዩ አህጉረ ስብከት ማስገንባቱ፤ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለሚገኙ ከሁለት መቶ ሺሕ በላይ የሚኾኑ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ትምህርተ ወንጌል ማስተማሩና ዐርባ አምስት ሺሕ ያኽሉን ማስመረቁ፤ ከዚሁ ዅሉ ጋርም ከሰባት መቶ ዐሥር ሺሕ በላይ ልዩ ልዩ የመዝሙር ቅጂዎችንና የኅትመት ውጤቶችን እንደዚሁም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሐመር መጽሔቶችንና ስምዐ ጽድቅ ጋዜጦችን ማሠራጨቱ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ሪፖርት ተካቶ በ፴፭ኛው አጠቃላይ መንፈሳዊ የሰበካ ጉባኤ ላይ መቅረቡ የሚታወስ ነው (ዐዋጅ ነጋሪ መጽሔት፣ ጥቅምት ወር ፳፻፱ ዓ.ም፤ ገጽ 75)፡፡

በመንፈሳዊ አገልግሎት ዋጋ የሚከፍል እግዚአብሔር ነውና ‹‹ይኽን ሠርተናል፤ ይኽን ፈጽመናል›› ብሎ ስለሠሩት ተግባር መናገርም ሌላ አካል እንዲናገር መሻትም ተገቢ አይደለም፡፡ ኾኖም ግን ለቍጥጥር፣ ለዕቅድና ለክንውን ያመች ዘንድ የአገልግሎት ሪፖርት ማቅረብ አንዱ የሥራ አፈጻጸም አካል ነው፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ልዩ ልዩ መምሪያዎች፣ ድርጅቶችና መንፈሳዊ ኮሌጆች እንደዚሁም የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት በአጠቃላይ ጉባኤው በሪፖርት መልክ የሚቀርበውም ከዚህ አኳያ ነው፡፡ የማኅበሩ አገልግሎት የየአህጉረ ስብከት ሪፖርት አካል ኾኖ መቅረቡ ማኅበረ ቅዱሳን አባላቱንና በጎ አድራጊ ምእመናንን በማስተባበር በሚቻለው አቅም ዅሉ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሐዋርያዊ ተልእኮ የመደገፍ ዓላማ እንዳለው ያመላክታል፡፡ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች ጋር በመመካከር የልጅነት ተግባሩን በመወጣት ላይ እንደሚገኝም ያስረዳል፡፡ ማኅበሩ፣ በ፳፻፱ ዓ.ም የአገልግሎት ዘመንም በተመሳሳይ መልኩ በርካታ መንፈሳውያን ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ለወደፊትም እግዚአብሔር እስከፈቀደለት ጊዜ ድረስ አገልግሎቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

፴፮ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ

ለቤተ ክርስቲያን ዅለንተናዊ አገልግሎት አስፈላጊ የኾነው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ካሁን ቀደም ይደረግ እንደነበረው ዂሉ፣ በዘንድሮው ዓመትም ከጥቅምት ፮ – ፲፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ለሠላሳ ስድስተኛ ጊዜ ይካሔዳል፡፡ በዚህ ጉባኤ ሪፖርት ከማቅረብና መግለጫዎችን ከማውጣት ባለፈ ለቤተ ከርስቲያን አገልግሎት መፋጠን የሚተጉ አባቶች፣ እናቶችና ወንድሞች ይበረታታሉ፡፡ የመንፈሳዊ አገልግሎት ማኅበራትና የበጎ አድራጎት ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ ድጋፍ ያገኛሉ የሚል እምነት አለን፡፡

በአንጻሩ ደግሞ በኑፋቄ፣ ገንዘብ በመመዝበር፣ ሕገ ወጥ አሠራርን በማስፈንና በሌላም ልዩ ልዩ በደል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የሚፈታተኑና መንፈሳውያን አባቶችን የሚያስነቅፉ አንዳንድ ግለሰቦች ተመክረውና ተገሥፀው ከስሕተታቸው እንዲመለሱ ይደረጋሉ፤ እንቢ ካሉ ደግሞ አስፈላጊውን ቅጣት ይቀበላሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በአንዳንድ አገልጋዮች ዘንድ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ አሠራር እና በፍቅረ ንዋይ መታለልን ተከትሎ የሚመጣውን፣ ለብዙዎች መሰናክል የሚኾነውን አእምሯዊ ጥፋት፣ መንፈሳዊ ዝለትና አስተዳደራዊ ግድፈት ለመግታትም የዘንድሮው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የማያዳግም ውሳኔ እንደሚያሳልፍ፤ ውሳኔውንም በቅዱስ ሲኖዶስ አጸድቆ ተግባራዊ እንደሚያደርግ እንጠብቃለን፡፡

ማጠቃለያ

‹‹ለመንጋው ምሳሌ ኹኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፡፡ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ፤›› (፩ኛ ጴጥ. ፭፥፫-፬) ተብሎ እንደተጻፈው ግብረ ኖሎት (የመንፈሳውያን እረኞች ተግባር) ለምድራዊ ጥቅም እና ዝና በመጨነቅ ሳይኾን ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን ዋጋ በማሰብ በበግ የሚመሰሉ ምእመናን በአጋንንት ተኩላዎች እንዳይነጠቁ፣ በለምለሟ መስክ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየተሰባሰቡ ምግበ ሥጋ ምግበ ነፍስ የኾነውን ቃለ እግዚአብሔር እንዲመገቡ፣ ሰማያዊ ሕይወት የሚያስገኘውን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንዲቀበሉ በማድረግ በዐቢይነት ወደ ዘለዓለማዊ ማረፊያቸው ገነት (መንግሥተ ሰማያት) እንዲገቡ የድኅነት መንገዱን ማመቻቸት ነው፡፡

ስለኾነም ቅዱስ ሉቃስ ‹‹በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ዅሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤›› (ሐዋ. ፳፥፳፰) በማለት እንዳስተማረው እረኞቻችን የቤተ ክርስቲያን አባቶች ሳያስጨንቁ በሥርዓትና በጥንቃቄ በጎች ምእመናንን መምራት፤ እኛ ምእመናኑም ከአባቶች ጋር የምንወርሰውን የእግዚአብሔር መንግሥት ተስፋ በማድረግ እረኞቻችንን ማክበር፣ ትእዛዛቸውንም መፈጸም ይጠበቅብናል፡፡ ከዚሁ ዂሉ ጋርም እያንዳንዳችን፣ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የመጨረሻው ወሳኝ አካል በኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡ ውሳኔዎችን እና በአጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤው የሚዘጋጁ ድንጋጌዎችን ተቀብለን የመፈጸምና የማስፈጸም ክርስቲያናዊ ግዴታ እንዳለብን አንርሳ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡