አንቀጸ መድኃኒት ቤተ ክርስቲያን  – የመጀመሪያ ክፍል

የካቲት ፳፪ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ነገረ ቤተ ክርስቲያን ስለ ቤተ ክርስቲያን ያለው ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ምን እንደ ሆነ የምንማርበት የትምህርት ዘርፍ ነው፡፡ ምንም እንኳን ትምህርቱ እጅግ ጥልቅና ራሱን የቻለ መጽሐፍ የሚወጣውና ሰፊ አሳቦችን የያዘ ቢሆንም በዚህ ጽሑፍ ግን በተለያዩ አካላት ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚነሡ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያህል ብቻ በጥቂቱ ለማንሣት እንሞክራለን፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማም ቤተ ክርስቲያን ድርጅት (ተቋም) ዲኖሚኔሽን ናት፤ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ድኅነት ይገኛል፤ ለቤተ ክርስቲያን ስግደት አይገባም፤ ቤተ ክርስቲያን መሔድ አያስፈልግም፤ ቤተ ክርስቲያን ትሳሳታለች፣ ስለዚህ ትታደሳለች፤ ወዘተ” የሚሉ የተሳሳቱ አሳቦችን ለሚያነሡ አካላት መልስ መስጠት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል ሦስት ዓይነት ሰዋስዋዊና ዘይቤአዊ ትርጕም አለው (አባ ጎርጎርዮስ ፲፱፻፸፰፣ ገጽ ፲፪-፲፯)፡፡

  • የመጀመሪያው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ያመለክታል፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ወደ ማኅበር ስትሰበሰቡ በመካከላችሁ መለያየት እንዳለ እሰማለሁ (፩ኛ ቆሮ. ፲፩፡፲፰) እንዳለው የክርስቲያኖች ቤት፣ የክርስቲያኖች መኖሪያ ማለት ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ባወቀ የክርስቶስ ደም በነጠበበት የምትተከል፣ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በቅዱስ ሜሮን የከበረች፣ ሥላሴ በአንድነት በሦስትነት የሚመሰገኑባት፣ የክርስቶስ ሥጋዌ የሚነገርባት፣ ሥጋውና ደሙ የሚፈተትባት ቅድስት መካን ቤተ ክርስቲያን ተብላ እንደተጠራች ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ይገልጻሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያን እንሒድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ (መዝ. ፻፳፩፡፩)፤ በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ” (ሐዋ. ፲፩፡፳፮) የሚሉት ንባቦች የቤተ ክርስቲያን አንደኛው ዘይቤአዊ ትርጕም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ዳግመኛም የእግዚአብሔር ቤት (ዘፍ. ፳፰፡፲፯)፣ በምሕረትህ ብዛት ወደ ቤትህ እገባለሁ (መዝ. ፭፡፯)፣ የአባቴ ቤት (ሉቃ. ፪፡፵፱)፣ የእግዚአብሔር ቤት (ዕብ. ፲፡፳፩) የሚሉት ይህን የሚያስረዱ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለይም ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ለወለደው ልጁ ለጢሞቴዎስ፡- ብዘገይ ግን፣ በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፣ የሕያው እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ነው (፩ኛ ጢሞ. ፫፡፲፭) በማለት የገለጠው የእግዚአብሔር ቤት (ሕንፃ) ቤተ ክርስቲያን እንደሚባል ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

  • ሁለተኛው ደግሞ እያንዳንዱ ምእመን (ክርስቲያን) ቤተ ክርስቲያን የሚባል መሆኑን የሚያስገነዝብ ትርጕም አለው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ (፩ኛ ቆሮ. ፫፡፲፮)፣ “… ወይስ ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደ ሆነ አታውቁምን? በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም፤ ስለዚህ በሥጋችሁ እግዚአብሔርን አክብሩ (፩ኛ ቆሮ. ፮፡፲፱) በማለት የገለጸው ይህን ነው፡፡ ይኸውም በመንፈሳዊና በምሥጢራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ፥ እርሱ አድሮባቸው የሚኖሩ፥ በቅዱስ ሜሮን የታተሙ (፩ኛ ዮሐ. ፪፡፳) እና ሥጋውንና ደሙን የተቀበሉ ምእመናንን ለማመልከት ነው፡፡
  • ሦስተኛው ትርጕም ደግሞ በባቢሎን ያለች ቤተ ክርስቲያን ልጄም ማርቆስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል (፩ኛ ጴጥ. ፭፡፲፫) እንዲል የክርስቲያኖችን ኅብረት ወይም አንድነት (ማኅበረ ምእመናንን) የሚያመለክት ነው፡፡ በሰማይ ያሉ የድል ነሺዎች፣ በምድር ያሉ ከፍትወታት፣ ከኃጣውእና ከርኵሳን መናፍስት ጋር የሚጋደሉ የክርስቲያኖች አንድነትና ኅብረት ማለት ነው፡፡ ይህች ኅብረትና አንድነት ራሷ ክርስቶስ የሆነላት፣ የክርስቶስ አካል ናት፡፡ ኅብረታችንም በደስታ ከተሰበሰቡት አእላፋት መላእክት፣ በሰማያትም ከተጻፉ ከበኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ከሚሆን ከእግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ከሆኑት ከጻድቃን መንፈሶች (ዕብ. ፲፪፡፳፪-፳፬) ጋር እንደሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ነግሮናል፡፡ እኛም በዚህ ክፍል ትኵረት የምናደርገው በዚሁ በሦስተኛው ትርጓሜ ላይ ነው፡፡

እኛ ኦርቶዶክሳውያን በግእዝ ቋንቋ ቤተ ክርስቲያን” የምንለውን ጽርዓውያን (ግሪካውያን) ኤክሌሲያ ይሉታል፡፡ ትርጓሜውም ለአንድነትና ለአንድ ልዩ ዓላማ የተጠሩ ማለት ነው፡፡ ይኸውም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- ወደ ጌታችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ኅብረት የጠራችሁ እግዚአብሔር የታመነ ነው (፩ኛ ቆሮ. ፩፡፱) ብሎ ከገለጸው ጋር የተስማማ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን ዓላማ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር አንድነትና ሰማያዊ ዓላማ በሃይማኖት መጥራት ነውና፡፡ ግሪኮች ኤክሌሲያ” የሚለውን ቃል መጀመሪያ አንድን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ወይም አስተዳደራዊ ችግር ለመፍታት ለተሰበሰቡ ሽማግሌዎች መጠሪያ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በ፪፻፹፬ ከክርስቶስ ልደት በፊት ብሉይ ኪዳንን ከዕብራይስጥ ወደ ጽርዕ የተረጐሙት ሰብዓ ሊቃናት ግን ቀሃል የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል ኤክሌሲያ” ብለው ተርጕመውታል፡፡ ትርጕሙም የእስራኤልን ጉባኤ የሚገልጽ ነው፡፡ እንደ ምሳሌም የሚከተሉትን ኃይለ ቃላት እንመልከት፤

ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው (ዘሌ. ፰፡፫)፡፡ እዚህ ላይ ማኅበሩ ተብሎ የተገለጠው በምሥጢር ስለዚህች ጉባኤ ነው፡፡ በዚህች ጉባኤም አሮን ሊቀ ካህን ሆኖ ተሾሟል (ዕብ. ፭፡፬)፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም እንዳስተማረው፥ ይህ የአይሁድ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን አምሳል፣ መርገፍ ወይም ጥላ ነበር (The Catechetical Lectures of St. Cyril, Archbishop of Jerusalem, P. 335)፡፡ እንደ ሊቁ አስተምህሮ አብዛኞቹ አይሁዳውያን በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ባለማመናቸው ምክንያት ከዚሁ ጉባኤ ቢወጡም ጉባኤው ግን አልተበታተነም፤ ሊበታተንም አይችልም፡፡ ይልቁንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፡- በዚህም ዓለት ላይ ቤተ ክርስቲያኔን (ጉባኤዬን) እሠራለሁ፤ የገሃነም ደጆችም አይችሏትም (ማቴ. ፲፮፡፲፰) በማለት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ጉባኤ አጸናት እንጂ፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም በሰዎች አመለካከት የተለያየ ዓይነት ስያሜ (እንደ አይሁዳውያኑና አሁን እንደምንሰማው ብዙ ስም) ቢሰጠውም ይህ የሰዎች የተሳሳተ ግንዛቤ የባሕርይ አምላክነቱን ሊለውጠው አይችልም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የገሃነም ደጆች አይችሏትም የሚለው ኃይለ ቃልም ይህን ጥልቅ ነገረ ሃይማኖታዊ ጽንሰ ሐሳብ በውስጡ የያዘ ነው፡፡ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ይህቺ ጉባኤ (ቤተ ክርስቲያን) በቅድስት ሥላሴ ባለው እምነቷ ህልውናዋን የጀመረችው በዓለመ መላእክት ማለትም ሰው ከመፈጠሩ በፊት ነው፡፡ ከዚያም ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ በነበረው የደጋግ ሰዎች አንድነት ቀጠለች፡፡

በቅዳሴያችን እግዚአብሔር ይስማዕከ ኵሎ ዘሰአልከ ወይትወከፍ መሥዋዕተከ ወቊርባነከ ከመ መሥዋዕተ መልከ ጼዴቅ ወአሮን ወዘካርያስ ካህናተ ቤተ ክርስቲያኑ ለበኵር፤ እግዚአብሔር የለመንኸውን ሁሉ ይስማህ፤ የቀደመችዋ ቤተ ክርስቲያን ካህናት የሚሆኑ የመልከ ጼዴቅንና የአሮንን የዘካርያስንም መሥዋዕት እንደተቀበለ መሥዋዕትህን ቊርባንህንም ይቀበልልህ የሚለው ንባብ የቤተ ክርስቲያን ህልውና ግእዛን ያላቸው ፍጥረታት ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በመጨረሻ ከላይ እንደገለጥነው በክርስቶስ ደም ጸናች፡፡ አሁንም ይህ ጉባኤ ከሥላሴ ጋር ያለው ግንኙነት ዘወትር አይቋረጥም፡፡

ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ናት ሲባል ግን አንዳንዶች እንደሚሉት እንዲሁ የሰዎች ስብስብ ሳትሆን የምርጦች ስብስብ ናት፤ የተጠሩ ብዙ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና (ማቴ. ፳፡፲፮)፡፡ እነዚህ ጥቂትና የተመረጡትም የልጅነት ሥልጣን የተሰጣቸው (ዮሐ. ፩፡፲፫)፣ እግዚአብሔርን በአንድነቱና በሦስትነቱ የሚያመልኩ፣ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ (ማቴ.፲፮፡፲፮) በሚል ጽኑዕ መሠረት የታነፁ ናቸው እንጂ እንዲሁ በአንድ ቤት ውስጥ የተሰበሰቡ ሰዎች አይደሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያን አካለ ክርስቶስና ሕያዊት ናት (ኤፌ. ፩፡፳፪-፳፫)፡፡ የክርስቶስ ሙሽራ (መኃ. ፭፡፩፣ ዮሐ. ፫፡፳፱፣ ራእ. ፳፩፡፱)፣  የእግዚአብሔር ሕያው ቤተ መቅደስ (ኤፌ. ፪፡፳፩)፣ የእውነት ዓምድና መሠረት (፩ኛ ጢሞ. ፫፡፲፭) ትባላለች፡፡

እነዚህ ስያሜዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መለወጥ የማይስማማው የአምላካችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካል መሆኗን በግልጽ ያስረዳሉ፡፡ የክርስቶስ አካል ስለሆነች አትሳሳትም፣ አትለወጥም፡፡ ትምህርቷም ከአምላኳ ከእግዚአብሔር የተቀበለችውና በመንፈስ ቅዱስ የሚጠበቅ ስለሆነ ስሕተትና ነቅ አይገኝበትም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ትክክል ለመሆኗ ማስረጃችን መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ለመሆኑ ደግሞ ምስክሯ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ (ኤፌ. ፫፡፲) የሚለው የቅዱስ ጳውሎስ ቃል ለዚህ ሁነኛ ማስረጃ ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ ራሷ የሆነላት ቤተ ክርስቲያን አርጅታለች ትታደስ፣ ተሳስታለች ትመለስ አትባልም፡፡ እንዲህ ማለት ክርስቶስን ማረም፣ ክርስቶስን ማስተካከል ይሆናልና፡፡ አምላካችን ደግሞ መለወጥ የማይስማማው ፍጹም አምላክ መሆኑን በነቢዩ በሚልክያስ አድሮ እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም (ሚል. ፫፡፮) በማለት የነገረን ሲሆን፤ ቅዱስ ጳውሎስም ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘለዓለምም ያው ነው። ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ(ዕብ. ፲፫፡፰-፱) ብሎ በየጊዜው የሚሻሻል አዲስ ትምህርት እንደሌላት አስረግጦ ነግሮናል፡፡

ቅዱስ ያሬድ በድጓው አንቀጸ መድኃኒት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እምነ ይእቲ ንበላ በሐ ወይእቲ ትኩነነ መርሐቅድስት ቤተ ክርስቲያን የድኅነት በር ናት፤ እናታችን ናት፤ ለድኅነታችን መንገድ መሪ እንድትሆነን ሰላም እንበላት በማለት የድኅነት በር እንደሆነችና ለእርሷ ሰላምታ ማቅረብ እንደሚገባን ይነግረናል (ጾመ ድጓ ዘቅድስት)፡፡ በጾመ ድጓ ዘዘወረደም ላይ እንዲሁ አመ ኖኅ ይእቲ መድኃኒት እንተ ኮነት አንቀጸ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ቅድስትክብርት የምትሆን ቤተ ክርስቲያን ከኖኅ ዘመን ጀምሮ የሕይወት መንገድ (በር) ናት በማለት ብቸኛዋ የድኅነት በር እንደሆነች ያስረዳናል፡፡

በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፲ ላይ የተጠቀሰው በወንበዴዎች የተደበደበው ሰው የተወሰደባት የእንግዶች ማረፊያ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በደጉ ሳምራዊ የተመሰለው ክርስቶስ አዳምን ለማዳን የፈጸመውን ማዳን በምሥጢራት በማደል ሰዎችን ከቁስለ ኃጢአት እንድትፈውስ ሥልጣን የተሰጣት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ መድኃኒትነቷም የክርስቶስን ሥጋና ደም በመፈተትና በማቀበል ነው፡፡ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከቤተ ክርስቲያን ውጪ አይፈጸሙም፡፡ ሰው ደግሞ ሳይጠመቅና ሥጋ ወደሙን ሳይቀበል የክርስቶስ አካል፣ የመንግሥተ ሰማያት አባል መሆን አይችልምና ቤተ ክርስቲያን መሔድ የግድ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡

ወደ ቤተ ክርስቲያን የምንሔደው እግዚአብሔር ሌላ ቦታ ሆነን ብንጸልይ ስለማይሰማን ሳይሆን ያለ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ድኅነት ተሳታፊ ስለማንሆንና እነዚህን ምሥጢራት ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ማግኘት ስለማንችል ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውን ሳያምኑ፣ በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ሳይሆኑ ድኅነት የለም፡፡ በአጠቃላይ ከክርስቶስ ውጪ የሆነች ቤተ ክርስቲያንን፣ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ የሚገኝ ድኅነት የለም፡፡

የቤተ ክርስቲያን ባሕርያት

ቤተ ክርስቲያን አራት ባሕርያት አሏት፡፡ እነዚህ ባሕርያቷ እንዲሁ የተጠራችባቸው ሳይሆኑ እጅግ ጥልቅ የሆነ የነገረ ሃይማኖትን ትምህርት የሚያስረዱ ናቸው፡፡ እነዚህም በጸሎተ ሃይማኖታችን ሁልጊዜ የምንመሰክራቸው ናቸው “… ከሁሉ በላይ (ኵላዊት) በምትሆን (፩) ሐዋርያት በሰበሰቧት (፪) በአንዲት (፫) ቅድስት (፬) ቤተ ክርስቲያን እናምናለን፡፡”

. ኵላዊት

ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት ሲባል በብዙዎቻችን ልቡና የሚመጣው በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ስፍራ፣ ለሁሉም ሰው ያለች የሚል ትርጓሜው ነው፡፡ ርግጥ ነው ቤተ ክርስቲያን በሁሉም ቦታ፣ በሁሉም ስፍራ፣ ለሁሉም ሰው አለች፡፡ ነገር ግን በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት ሲባል ከዚህ ያለፈ (የላቀ) ትርጓሜ አለው፡፡ ኵላዊት የሚለው ቃል ከብዛት ይልቅ ርቀትንና ምልዐትን፣ ርቱዕነትን፣ እውነተኛነትን፥ ፍጹምነትን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት ናት ስንል ፍጽምት ናት፤ ሁሉንም የምትይዝ ናት፤ ምንም የሚጐድላት ነገር የለም ማለታችን ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን እንደ አሁኑ በዓለም ሁሉ ከመስፋፋቷ በፊት እንኳን ኵላዊት ትባል ነበር፡፡ የኢየሩሳሌም የአንጾኪያ፣ የኤፌሶን፣ የቆሮንቶስ፣ የሮም አብያተ ክርስቲያናት ኵላዊት ይባሉ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት መባሏ ከቦታ ወይም ከቊጥር አንጻር ሳይሆን የክርስቶስ አካል በመሆኗ ያገኘችው ነው፡፡ ዳግመኛም ቤተ ክርስቲያን ኵላዊት የምትባለው ከእግዚአብሔር የተገኘች የሐዋርያት ትምህርታቸው፣ የክህነት ውርሳቸው (ቅብብሎሽ) ስላላት ነው፡፡ ኵላዊት ናት ስንል ምልዕትና ፍጽምት ናት ማለት ነው፡፡ የማትታደሰውም፣ የማትለወጠውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ክርስቶስ ራስ የሆነላት ሕያዊትና ፍጽምት አካሉ ናትና፤ እግዚአብሔር እንደማያረጅ እርስዋም አታረጅምና የሚገቡባትን ታድሳለች እንጂ አትታደስም፡፡

ይቆየን

ይህ ጽሑፍ፣ ከታኅሣሥ ፩ – ፲፭ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም በታተመው ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በንቁ ዓምድ ሥር ለንባብ መብቃቱን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡