አባ ሙሴ ጸሊም

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብዙ ቅዱሳንን ከተለያየ ዓለማዊ ሥራ ጠርቶ ቃሉን ለመስበክ፣ ስሙን ለመቀደስና ክብሩን ለመውረስ ያበቃቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡

በዛሬው ዝግጅታችን በኃጢአት ሕይወት ከኖሩ በኋላ በንስሓ ከተመለሱ ቅዱሳን መካከል አንዱ የኾኑትን በዓለ ዕረፍታቸው ሰኔ ፳፬ ቀን የሚዘከረዉን የአባ ሙሴ ጸሊምን ታሪክ በአጭሩ እናቀርብላችኋለን፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን በሊቀ ነቢያት ሙሴ ስም የሚጠሩ ብዙ ቅዱሳን ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም አንዱ አባ ሙሴ ጸሊም /ጥቁሩ ሙሴ/ ሲኾኑ በቆዳቸው ቀለም ምክንያት ጸሊም /ጥቁር/ በሚል ቅጽል ስም ይጠራሉ፡፡ እኒህ ቅዱስ ለሰማዕትነት ክብር ከመብቃታቸው በፊት በቆዳቸው ብቻ ሳይኾን በግብራቸውም ጥቁር ማለትም ኀጢአትን የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ያለመጠን ይበሉና ይጠጡ፣ ይቀሙና ያመነዝሩ እንዲሁም ሰው ይገድሉ ነበር፡፡

በሥጋቸው ጠንካራ፣ በጉልበታቸውም ኃይለኛ በመኾናቸውም ሊቋቋማቸው የሚችል ማንም አልነበረም፡፡ *እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል* ተብሎ እንደ ተጻፈ /ማቴ.፲፩፥፲፪/ አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍተዋታል፤ ማለትም የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያወርሰውን የጽድቅ ሥራ ትተው ወደ ገሃነም በሚያስጥል ኃጢአት ኖረዋል፡፡

እግዚአብሔርን ካለማወቃቸው የተነሣ በባዕድ አምልኮ ተይዘው የኖሩት አባ ሙሴ ጸሊም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይም ነበሩ፡፡ በዚህ ዓይነት ልማድ እየኖሩ ሳሉ የሰውን ጠፍቶ መቅረት የማይወደው አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ወደ ቤቱ ሊመልሳቸው በወደደ ጊዜ የፀሐይን ፍጡርነትና ግዑዝነት ስለገለጸላቸው ብዙ ጊዜ ወደ ፀሐይ በማንጋጠጥ *ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንክ አነጋግረኝ፤* ደግሞም *የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ* ይሉ ነበር፡፡

አባ ሙሴ ጸሊም በዚህ ዓይነት ልማድ ሲኖሩ የገዳመ አስቄጥስ መነኰሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ ያዩታል፤ እንዲሁም ያነጋግሩታል እየተባለ ሲነገር ይሰሙ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ስሙን እንዲቀድሱ፣ መንግሥቱንም እንዲወርሱና ሊያደርጋቸው ወድዷልና ወደ ገዳሙ ይሔዱ ዘንድ አነሣሣቸው፡፡ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደዉም ከካህናቱ አንዱ የኾኑትን አባ ኤስድሮስን *እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጥቻለሁ* አሏቸው፡፡

እርሳቸውም እግዚአብሔርን ፍለጋ ወደ ገዳሙ መምጣታቸዉን አድንቀው ከአባ መቃርስ ጋር አገናኟቸው፡፡ አባ መቃርስም የክርስትና ሃይማኖትን አስተምረው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጠመቋቸው፡፡ ከዚያ በኋላ *ታግሠህ የማስተምርህን ትምህርተ ወንጌል ከጠበክ እግዚአብሔርን ታየዋለህ* እያሉ በተስፋ ቃል ያጽናኗቸው ነበር፡፡

ከዓመታት በኋላም በልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና ፈትነው አመነኰሷቸው፡፡ አባ ሙሴ ጸሊምም ብዙ ገድልን ከሚጋደሉ ቅዱሳን አብልጠው መጋደል በጀመሩ ጊዜ ሰይጣን ለማሰናከልና ከገዳሙ ለማስወጣት በማሰብ ቀድሞ ያሠራቸው በነበረው ግብረ ኃጢአት ሊዋጋቸው ጀመረ፡፡ አባ ኤስድሮስም እያጽናኑና እየመከሩ በተጋድሏቸው ይበልጥ እንዲጸኑ ያተጓቸው ነበር፡፡

አባ ሙሴ የውኃ መቅጃ ሥፍራው ሩቅ ነበርና አረጋውያን መነኮሳት በመንገድ እንዳይደክሙ ዘወትር ውኃ እየቀዱ በሚተኙበት ጊዜ በየበዓታቸው ደጃፍ በማስቀመጥ ያገለግሏቸውና ድካማቸውን ይቀንሱላቸው ነበር፡፡ እንዲህ እያደረጉ በመጋደልና በማገልገል ለብዙ ዓመታት ሲኖሩ ጸላዔ ሠናያት ሰይጣን እግራቸውን በከባድ ደዌ መታቸውና ለብዙ ቀናት የአልጋ ቁራኛ ኾነው ኖሩ፡፡ እርሳቸውም በደዌ የሚፈታተናቸው ጥንተ ጠላት ሰይጣን መኾኑን ተረድተው ሰውነታቸው ደርቆ በእሳት የተቃጠለ እንጨት እስኪመስል ድረስ ተጋድሏቸውን እጅግ አበዙ፡፡ እግዚአብሔርም ትዕግሥታቸውን ዓይቶ ከደዌያቸው ፈወሳቸው፤ የሰይጣንንም ውጊያ አርቆ ጸጋውን አሳደረባቸው፡፡

ከዚህ በኋላ እርሳቸው ወደሚኖሩበት ገዳም የተሰበሰቡ ፭፻ የሚኾኑ ወንድሞች መነኮሳትን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ እያሉ ቅዱስ ጳውሎስ *በመልካም ለሚያገለግሉት ከፍተኛውን ሹመት ይስጧቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ብዙ ባለሟልነት አለና* /፩ኛጢሞ.፫፥፲፫/ በማለት እንዳስተማረው በማኅበረ መነኮሳቱ ለቅስና መዓርግ ተመረጡ፡፡ ሊሾሟቸው ወደ ቤተ መቅደስ በአቀረቧቸው ጊዜ ግን ሊቀ ጳጳሳቱ የቅስናን መዓርግ ሊሰጧቸው አልፈቀዱም ነበርና አረጋውያኑን *ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት? ከዚህ አውጡት* አሏቸው፡፡

አባ ሙሴም ይህን ቃል ከሊቀ ጳጳሳቱ ሲሰሙ *መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ መልካም አደረጉብህ* እያሉ ራሳቸውን እየገሠፁ ከቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ በሌላው ቀን ጽናታቸውንና ትዕግሥታቸውን የተመለከቱት ሊቀ ጳጳሳቱ አስጠርተው በአንብሮተ እድ በቅስና መዓርግ ሾሟቸውና *ሙሴ ሆይ እነሆ በውስጥም በውጭም ኹለመናህ ነጭ ኾነ* በሚል የደስታ ቃል ተናገሯቸው፡፡ ከዚህ በኋላ በተቀበሉት መዓርግ እግዚአብሔርን፣ መነኮሳቱንና ገዳሙን ሲያገለግሉ ኖረዋል፡፡

እግዚአብሔር በአባ ሙሴ ላይ አድሮ ከአደረጋቸው ተአምራት መካከል ያለ ወቅቱ ዝናብ እንዲዘንብ ማድረጋቸው አንደኛው ነው፤ ከዕለታት አንድ ቀን በበዓታቸው ምንም ውኃ በሌለበት ቀን አረጋውያን በእንግድነት መጡባቸው፡፡ ውኃ የሚቀዳበት ቦታ በጣም ሩቅ ነበርና የሚያደርጉትን አጡ፡፡ እንግዶቹን ወደ በዓታቸው ካስገቡ በኋላም እግዚአብሔርን *ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ?* እያሉ በጸሎት ይጠይቁት ጀመሩ፡፡ በስሙ ለሚታመኑ ድንቅ ሥራውን መግለጥ ልማዱ የኾነው እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ ዝናብ አዘነበላቸውና የውኃ ጉድጓዶችን ሞላላቸው፡፡

እንግዶቹንም እንደ ሥርዓቱ እግራቸውን አጥበው፣ ምግብና ውኃ ሰጥተው አስተናገዷቸው፡፡ አረጋውያኑም በዝናቡ መጣል እየተገረሙ አባ ሙሴን *ብዙ ጊዜ ትወጣ፣ ትገባ የነበረው ለምንድን ነው?* ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም *እግዚአብሔርን ውኃ እንዲሰጠኝ እየተማጸንኩት ነበር፡፡ በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን* አሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በቅዱሳኑ አድሮ ድንቅ ድንቅ ተአምራቱን የሚገልጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ በአባ ሙሴ ቅድስናም ተደነቁ፡፡

በአንዲት ዕለትም አባ ሙሴ ከአረጋውያን ጋር ወደ አባ መቃርስ በሔዱ ጊዜ አባ መቃርስ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው *ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ* በማለት ለአባ ሙሴ ጸሊም ስለተዘገጀው የሰማዕትነት ክብር አስቀድመው ትንቢት ተናገሩ፡፡ አባ ሙሴም ይህን ቃል ሲሰሙ *አባቴ ሆይ እኔ እሆናለሁ፡፡ /በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው/ የሚል ጽሑፍ አለና* ብለው መለሱ፡፡

በብሉይ ኪዳን በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይሙት፤ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ፤ ወዘተ የሚል ሕግ ነበር /ዘፀ.፳፩፥፳፬-፳፭፤ ማቴ.፭፥፴፰/፤ አባ ሙሴ ጸሊምም ለገዳማዊ ሕይወት ከመብቃታቸው በፊት ሰዎችን በሰይፍ ሲያጠፉ እንደነበሩት ኹሉ እርሳቸውም በሰይፍ መሞት እንደሚገባቸው በማመን ራሳቸውን ለሞት አዘጋጁ፡፡ ይህም በንጹሕ ልቡናቸው ወደ እግዚአብሔር መመለሳቸውን የሚያመለክት ነው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ያገኙትን ኹሉ በሰይፍ የሚገድሉ የበርበር ሰዎች ወደ በዓታቸው መጡ፡፡ አባ ሙሴም አብረዋቸው የነበሩትን መነኮሳት *መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ* አሏቸው፡፡ እነርሱም *አባታችን አንተስ አትሸሽምን?* አሏቸው፡፡ እርሳቸውም እኔ */በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላል/ ስለሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ይቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠባበቃት ኖሬአለሁ* በማለት ለሰማዕትነት መዘጋጀታቸውን ነገሯቸው፡፡

ይህን እየተነጋገሩ ሳሉም የበርበር ሰዎች ከበዓታቸው ገብተው በሰይፍ ቈርጠው ገደሏቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋርም ሰባት መነኮሳት ተገደሉ፡፡ አንደኛውም ከምንጣፍ ውስጥ ተሠውረው ከቆዩ በኋላ በእጁ አክሊል የያዘ የእግዚአብሔር መልአክ ቆሞ ሲጠባበቅ በተመለከቱ ጊዜ ከተሠወሩበት በመውጣት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አባ መቃርስ *ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ* በማለት የተናገሩት ትንቢት ተፈጸመ፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም *አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው* ሲል የተናገረው ቃል ደረሰ /ሮሜ.፰፥፴/፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም በሰማዕትነት ያረፉት ሰኔ ፳፬ ቀን ሲኾን፣ ሥጋቸውም በአስቄጥስ ገዳም ደርምስ በተባለ ቦታ እንደሚገኝና ከእርሱም ብዙ ድንቃ ድንቅና ተአምራት እንደሚታዩ በመጽሐፈ ስንክሳር ተጽፏል፡፡

በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር እቅፍ ርቀን የምንኖር ኹሉ፤ ከሃዲና ነፍሰ ገዳይ፣ ቀማኛና ዘማዊ የነበረውን ሰው ወደ አሚነ እግዚአብሔርና ወደ ገቢረ ጽድቅ በመለወጥ ደግ አባት፣ መምህር፣ የሚያጽናና ሥርዓትን የሚሠራ ካህን፣ እንዲሁም ሰማዕት፤ በተጨማሪም በኹሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ስሙ ለዘለዓለሙ እንዲጠራ ያደረገችውን የንስሓን ኃይል በማስተዋል ዛሬዉኑ በንስሓ ልንመለስ ይገባል፡፡ አምላካችን እግዚአብሔር እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን፣ ኃጢአትንም ይቅር የሚል አምላክ ነውና ኀጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድ ዘወትር እንማጸነው /ዘፀ.፴፬፥፯፤ ማቴ.፮፥፲፪/፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፡፡ እኛንም በአባ ሙሴ ጸሊምና በሰማዕታት ሁሉ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከታቸውም ከእኛ ጋራ ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፬ ቀን፡፡