mariam[1].gif

አስደናቂው ሞት

ዲ/ን ታደለ ፋንታው
ነሐሴ 1/ 2003 ዓ.ም.

ክብረ ድንግል ማርያም

እግዚአብሔር ዘላለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን ለዓለም ከገለጸበት ታላቅ ሥራ መካከል በእመቤታችን በቅድስት ድንግል mariam[1].gifማርያም የገለጸው ድንቅ ሥራው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ይህንን ሁኔታ ድንግል ማርያም “ብርቱ የሆነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል ስለዚህም ምክንያት ፍጥረት ሁሉ ያመሰግኑኛል” ሉቃ.፩፥፵፱/1፥9/ በማለት ገለጸችው፡፡ ቅድሰት ኤልሳቤጥም የጌታዬ እናት” አለቻት /ሉቃ.፩፥፵፫/1፥43/ “መልአኩ ቅዲስ ገብርኤል ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ” /ሉቃ.፩፥፳፰/1፥28/ አላት፡፡ ቅዱስ ዳዊት ልጄ ይላታል መዝ.፵፬፥፱/44፥9/ ሰሎሞን እኅቴ ይላታል /መኃ.፭፥፩/5፥1/ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም እናት ሆና ተሰጠችው /ዮሐ.፲፱፥፳፮/19፥26/ ይህንን ድንቅ ሥራ ውስንና ደካማ የሆነ አእምሮ ሊገነዘበው ከሚችለው በላይ ነው፡፡

ቅዱስ አግናጢዎስ ዘአንጾኪያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደገለጸው” የቅድስት ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ አማኑኤልን መውለዷ፤ የማይሞተው ጌታ ሞት” እነዚህ ሦስቱ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና ገዢዎች የተሰወሩ ምሥጢራት ነበሩ፤ እነዚህ ድንቅ ምሥጢሮች በራሳቸው ከንግግርና ከቋንቋዎች ሁሉ በላይ ሁነው የሚነገሩ በእግዚአብሔር የዝምታ መጎናጸፊያ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢሮች ናቸው ይላል፡፡

ምስጋናዋ የበዛለት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ “አቤቱ መሰንቆ ልቡናዬን አነቃቃ የልቤንም እንዚራ፤ ድምፁን ከፍ አድርጎ የዳዊት ልጅ የሆነችውን የጌታውን እናት ድንግል ማርያምን ያመሰግናት ዘንድ፥ ለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን የወለደች እናቱ የሆነች እርሷን ከፍ ከፍ ያደርጋት ዘንድ” ብሏል፡፡ በሌላም አንቀጽ “ከሕሊናት ሁሉ በላይ ለሆነ ለዚህ ነገር አንክሮ ይገባል፤ ምድራዊት ሴት ፈጣሪዋን ወለደችው እርሱም እናቱን ፈጠረ” አለ፡፡ ስለ እነዚህ ነገሮች ሁሉ ምን ማለትን እንችላለን? እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለ ድንግል ማርያም ያልተናገረበት ጊዜ ያላናገረው ቅዱስ እንደሌለ እንመለከታለን፡፡

በእግዚአብሔር በሰውና በመላእክቱ ፊት የከበረ ሰው መታሰቢያው ለዘለዓለም ነው፡፡ በቤቱ በቅጥሩ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምን ይቀበላልና፡፡ /ኢሳ.፶፭፥፫/55፥3/ ይህንን ታላቅ በረከት እንደሚሰጣቸው የተናገረ የማይዋሸው ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ወልድ እናት ከድንግል ማርያም የበለጠ በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ማንን ልንጠራ እንችላለን? ከእርሷስ ሲታሰብ ሊከበርም የሚችል በቅድስና ሕይወት ያለፈ ማን ይኖራል?

አስቀድሞ ሁሉን ያዘጋጀ እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ እግዚአብሔር ፍጥረቱንና ዓለሙን ለማዳን የመረጠው ጊዜ በደረሰ ጊዜ ከድንግል ማርያም በድንግልና ተወለደ፡፡ አስቀድሞ በመልአኩ አፍ እንዳናገረ ክብሩ በእርሷ ላይ ታየ /ኢሳ.፷፥፪/60፥2/ ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በእርስዋ አደረ፡፡ በእመቤታችን ያደረ መንፈስ ቅዱስ “ያነጻቸው ዘንድ ይቀድሳቸውም ዘንድ በሥጋም በነፍስም መርቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያገባቸው ዘንድ በነቢያት በሐዋርያት ላይ እንዳደረው አይደለም፤ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየስስ ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ ሆነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህን ዘለዓለማዊ እውነት “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” /ሉቃ.፩፥፵፭/1፥45/ በማለት ገልጾታል፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ደራሲና ገጣሚ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ “የእስራኤል ንጉሥ በእስራኤል ልጅ አደረ፤ የዳዊት አምላክ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ለበሰ፤ የዕብራውያን ጌታ በዕብራውያን ልጅ ማኅፀን ተወሰነ፡፡ ለአብርሃም የዕብራይስጥ ልሳን ያስተማረው ከቀድሞም ያልሰማውን ልሳን እንዲናገር አፉን ጆሮውን የከፈተለት ከዕብራዊት ድንግል ተወለደ፤ በድንግልና ወተት አደገ፤ ጥቂት ጥቂት እያለ አደገ፥ የሕፃናትን ሥርዓት እንዳያጎድል አፉን የሚፈታባት ዘመን እስኪፈጸም ጥቂት ጥቂት እያለ በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፡፡ ለሙሴ በዕብራይስጥ ልሳን በጣቶቹ የተጻፉትን ዐሠርቱ ቃላት በድንጋይ ሰሌዳ የተጻፈውን የሰጠው የዕብራይስጥ ፊደል ለመማር ከመምህር እግር በታች ተቀመጠ፡፡ የባቢሎን አውራጃ በምትሆን ሰናዖርም የፍጥረትን ሁሉ ቋንቋ የበተነ እርሱ የአሕዛብን ቋንቋ እንደማያውቅ ሁሉ እናቱ አፍ በፈታችበት ልሳን በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፤ ጆሮ ይህንን ነገር ከመስማት የተነሣ የሚለመልምበት ይህ ነገር ዕጹብ ድንቅ ነው፡፡ ለዚህ አንክሮ ይገባል አለ፡፡ ይህ በሰው ጥበብ በብራናና በቀለም የተጻፈ እውነት ሳይሆን ለድኅነት በተጠሩ ሰዎች ሁሉ ልቡና በአምላክ ጥበብ የተጻፈ እውነት ነው፡፡

አስደናቂው የድንግል ማርያም ሞት

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ አርጋኖን ድርሰቱ ከሚያሰጥመው ባሕር ሞገድ የተነሣ የማትነቀነቅ፥ መልኅቆቿም በሦስቱ ሥላሴ ገመድ የተሸረቡ ናቸው ይህቺ ደግሞ ከነፋሳት ኃይል የተነሣ የማትናወጥ በጭንጫ ላይ ያለች የዕንቈ ባሕርይ ምሰሶ ናት፤ እርሷን የተጠጋ መውደቅ መሰናከል የለበትም” የሚላት እመቤታችን ሞት አይቀርምና እርሷም እንደሰው የምትሞትበት ጊዜ ደረሰ፡፡ እግዚአብሔር አያዳላምና፡፡ /ሮሜ.፪፥፲፩/2፥11/ ቅድስት ድንግል ማርያም የኃያሉ እግዚአብሔር እናቱ፥ መቅደሱ፥ ታቦቱ፥ መንበሩ ሆና እያለ ሞትን መቅመሷ በራሱ የሚያስገርም ምሥጢር ነው፡፡ ከቤተ ክርስትያን ወገን ሞትን እንዳያዩ የተወሰዱ ቅዱሳን ሄኖክ፥ ኤልያስ፥ ሌሎችም እንዳሉ የቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት አለ፡፡ ይህ ከኅሊናት ሁሉ በላይ የሆነው ምሥጢር ርቀቱ በመጽሐፈ ዚቅ እንዲህ ተብሏል፡፡ “ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ ኢያድለወ  ሞት ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአጽብ ለኩሉ፡፡ ኃይለኛ በኃይሉ ለምን ይታጀራል? ባለ ጸጋም በሀብቱ ብዛት፡፡ ክርስቶስ ለአካሉ አላዳላም፤ ሞትስ ለሟች ይገባዋል የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው”

እመቤታችን ያረፈችው በጥር ሃያ አንድ ቀን ነው፤ በአባት በእናቷ ቤት ሦስት ዓመት ኖረች፤ ዐሠራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ ኖረች፤ ከልጇ ጋር ሠላሣ ሦስት ዓመት ከሦስት ወራት፤ ከጌታ ስቅለት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመታት ኖረች፤ ጌታን የጸነሰችበትን ወራት ስንጨምር በዚህ ዓለም በሥጋ የቆየችበት ጊዜ ስድሳ አራት ዓመት ይሆናል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት የድንግል ማርያም ሞት በሚከተሉት ምክንያቶች እንደሆነ ያስረዳል፤ የመጀመሪያው “ለመለኮት ማደርያ ለመሆን የበቃችው ኃይል አርያማዊት ብትሆን ነው እንዷ ምድራዊት ሴትማ እንደምን ሰማይና ምድር የማይችለውን ልትሸከመው ይቻላታል?” የሚሉ ወገኖች ነበሩና በርግጥም እግዚአብሔር ወልድ የተዋሐደው የሰው ልጆችን ሥጋ እንጂ የመላእክትን አለመሆኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ይህንን ሁኔታ ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ “እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፥ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፥ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፥በሕይወታቸው ሁሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ እንዲያወጣ፥ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም” አለ፡፡ /ዕብ.፪፥፲፬-፲፭/2፥14-15/ በዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር መሆኗ ታወቀ፡፡ ሁለተኛው ቅዱስ ያሬድ እንዳለው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት መሆኑ ይታወቅ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በለበሰው ሥጋ ሞትን ይቀምስ ዘንድ የግድ ነውና፡፡

ትንሣኤ

በቃል መነገሩ በአንደበት መዘከሩ ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና “ከሞት ወጥመድ በላይ እንኳን የሆነ ሌላ ኃይል አለ፤ ይሄውም ሞት ፈጽሞ ሊያሸንፈውና ሊገዳደረው የማይችል የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል ነው፡፡ በሰይጣን ዘንድ ያለው የሞት ኃይል ነው ሕያው እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነውና ሞት ሊያሸንፈው ሊደርስበትም የማይችለውን ሕይወት ይሰጣል፡፡ ይህንን እግዚአብሔር የሚሰጠውን ሕይወት ሰይጣን በእጁ ሊነካው ከቶውንም አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ለሙታን ሕይወትን ይሰጣል የሞትና የሕይወት ባለቤት ነው፡፡” የእመቤታችን ድንግል ማርያም ዕርገት

ከሞት ሥልጣንና ኃይል በላይ የሆነው ይኸው የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣን የድንግል ማርያምን ሥጋ መልካምም ሆነ ክፉ ለሠሩ ሰዎች ዋጋ ይከፍል ዘንድ ለፍርድ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ በመቃብር ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ፤ ፈርሶና በስብሶ በምድር ላይ እንዲቀር አላደረገም፡፡ ከሙታን መካከል ተለይታ ተነሥታለች፡፡ እንድትነሣም ያደረገ የጌታ ኃይል ነው፤ በራሷ የተነሣች አይደለችም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በድንግልና ጸንሳ በድንግልና መውለዷን በትንቢት እንዳናገረ ትንሣኤዋንም በትንቢት ሲያናግር ኑሯል፡፡ ይህ ታላቅ ምሥጢር በቅዱስ ዳዊት አንደበት “ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦትም” /መዝ.፻፴፩፥፰/131፥8/ ብሎ ገልጾታል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በዚህ የትንቢት ክፍል ትንሣኤዋን አስረድቷል፡፡ ታቦት የጽላቱ ማደሪያ ነው፡፡ በታቦቱ ውስጥ የሚያድረው በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፈው ሕጉ ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ያከበረው ነገር ሆኖ ሊመጣ ላለው ነገር ማሳያ ነው፡፡ እውነተኛዋ ታቦት ማርያም ናት፡፡ ሙሴ በተቀበለው ታቦት ውስጥ ያለው ጽላት በውስጡ የያዘው ሕጉን ነው፤ በድንግል ማርያም ላይ ያደረው ግን የሕጉ ባለቤት ነውና፡፡ ከፍጡራን ከፍ ከፍ የማለቷ ድንቅ ምሥጢርም ይህ ነውና፡፡ ትምክህቷም፣ ትውክልቷም ጌታ እግዚአብሔር እንደሆነ በወንጌላውያኑ ተነግሮላታል፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያላናገራቸውን ከልባቸው አንቅተው አይጽፉምና፡፡ እርሷም” ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴትን ታደርጋለች” አለችን /ሉቃ.፩፥፵፯/1፥47/፡፡ ይህ ቃል ንጽህናዋ ቅድስናዋ በተረዳ ነገር ታውቆ ፍጥረት ሁሉ ከልቡ ከሚያከብራት እመቤት የተነገረ ቃል እንጂ ራሳቸውን ያለአጥርና ያለከልካይ አድርገው ቃሉን ከሚሸቃቅጡ ሰዎች ወገን የተሰጠ ምስክርነት አይደለም፡፡

እርስዋ ከኪሩቤል ትበልጣለች፤ ከሱራፌልም ትከብራለች ጌታችን የሱራፌልን፥ ኪሩቤልን ባሕርይ ባሕርዩ አላደረገም፡፡ የመላእክትንም ባሕርይ እንደዚሁ፥ የእርሷን አካል ባሕርዩ አደረገ እንጂ፡፡

የክርስቲያኖችን ትንሣኤ ሙታን የሚመሰክር ልዕልና

ከምድር ሰዎች ሁሉ ጥበበኛ የሆነው ሰሎሞን እንዲህ አለ፡- “ወዳጄ ሆይ ተነሽ፤ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፥ ዝናሙም አልፎ ሄደ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፥ የዜማም ጊዜ ደረሰ፥ የቁርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ”፡፡ /መኃ.፪፥፲-፲፬/2፥10-14/ ይህ ትንቢት የዚህ ዓለም ድካሟ ሁሉ መፈጸሙን ያስረዳል፡፡ ልጇን ይዛ ከሀገር ሀገር በረሀብና ጥም የተንከራተተችበት ጊዜ አሁን አለፈ፡፡ ታናሽ ብላቴና ሳለች ልጇን አዝላ በግብጽ በረሃ የተቀበለችው መከራ ሁሉ ፍጻሜ አገኘ፡፡ ከእግረ መስቀል ሥር ወድቃ የልጇን የቆሰለ ገላ እየተመለከተች የደረሰባት ልብ የሚሰነጥቅ ኀዘን ወደ ደስታ ተለወጠ፡፡ በነፍሷ ሰይፍ ያልፋል ተብሎ የተነገረው ልብ የሚሰነጥቅ መከራ እንደ ነቢዩ ቃል ትንቢት የሚቀጥልበት ጊዜ ተፈጸመ፡፡ እርሷ ባለችበት ሥፍራ የሕይወት ትንሣኤ ያላቸው ሰዎች ይሆኑ ዘንድ አስቀድማ ከሙታን ተለይታ በመነሣት የተጠበቀልን ተስፋ ማሳያ ሆነችን፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ስደት መከራ ኃዘን ሰቆቃ የለም፤ መገፋት መግፋትም የለም፡፡

እመቤታችን ትንቢቱ የተፈጸመባት ሁና እያለ ከማንኛውም ሐዋርያ በላይ ለእግዚአብሔር ቃል መስፋፋት የወንጌል ዘር በተዘራበት ቦታ ሁሉ ነበረች፡፡ ለመንግሥቱም እንደሚገባ ሁና ኑራለች፡፡ በማኅፀን የተጀመረው የማዳን ሥራ፤ ፍጻሜውን ያገኘው በቀራንዮ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የጌታ ልደቱና ጥምቀቱ፣ ሞቱ ትንሣኤው ዕርገቱና ዳግመኛ መምጣቱ በነገረ ድኅነት ትምህርታችን እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ቤተልሔም የሥጋዌውን ምሥጢር ሲያሳይ ዮርዳኖስ ቀዳማዊ ልደቱን ያሳያል፡፡ የመጀመርያው የእኛ ባሕርይ ሲሆን ሁለተኛ የጌታ የራሱ የባሕርይ ገንዘቡ የሆነ ነው፡፡ እርሱ የሰው ልጅ ሆነ፤ እኛ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ሆንን ይህ ሁሉ የተደረገው ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ነው፡፡ እርሱ የእኛን ተፈጠሮ ገንዘቡ ስላደረገ፤ እኛ ደግሞ የእርሱን ቅድስና ገንዘብ በማድረግ የመንግሥቱ ተካፋዮች ሆንን፡፡ የእኛ የሆነው ሁሉ የእርሱ የእርሱ የሆነው የእኛ በመሆኑ ከፍ ከፍ እናደርገዋለን፡፡ ለዚህ ክብር በቀታ ያከበረችንን ከእግዚአብሔር ጋር ያዛመደችንን እመቤት እንደምን አናከብራትም?

የእኛ መንፈሳዊ ልደት የተገኘው ጌታ በሥጋ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው ልደት ነው፡፡ “የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅጸን አምላክና የሰው ልጆች የተገናኙበት፤ አምላክና ሰው የተዋሐዱበት መካነ ምሕረት ነው፡፡ እግዚአብሔር ዙፋኑን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት የዘረጋበት መካነ ሰላም ነው፤ የእግዚአብሔር ዙፋን ፍጹም በማይናወጥና ጸጥታ በነገሠበት ስፍራ የሚዘረጋ የክብር ዙፋን ነው፡፡ ይህም ዙፋን የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅጸን ነው፡፡”

በቀራንዮ አደባባይም በኀዘን ነበረች፡፡ ሐዋርያት ጉባኤያትን ሲያበዙ አብራቸው ነበረች፤ ይህ ሁሉ ታላቅ ሥራ ከተፈጸመ በኋላ ዓረፍተ ዘመን ገታት፡፡ በሥጋ ዓረፈች፡፡ ያረፈችው በጥር ሃያ አንድ ቀን ነው፤ ሐዋርያትም ሊቀብሯት ሲሹም ከአይሁድ ክፋት የተነሣ ልጇ ሌላ ክብርን ደረበላት ከጌቴሴማኒ ሥጋዋ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር እስከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች፡፡ ልጇ ወዳጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሥልጣኑ እንዳሸነፈ የልጇ መለኮታዊ ኃይል ሞትን አሸንፋ እንድትነሣ አደረጋት፤ ጠቢቡ ሰሎሞን ስለ ትንሣኤዋ የተናገረው ቃል ተፈጸመ፡፡ ሊቁ “ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሰናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ ከሞት ወደ ሕይወት ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና፤ ያለው ይኸንን ነው”፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ልጇ ሲንገላታ፣ ሲሰደድ ሲገረፍ፣ ሲሰቀል፣ ሲቸነከር ያየችበት ዓለም አለፈ፡፡ አሁን የልጇን ልዕልና ከሚያደንቁ ጋር ታደንቃለች፤ ከፍ ከፍ ከሚያደርጉት ጋር ታከብረዋለች፡፡ ይኸም ከገቡ የማይወጡበት ኀዘን መከራ ችግር በሌለበት ሰማያዊት ሃገር ነው፡፡ ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው የድል አክሊልን የሚቀዳጁበት ሥፍራ ነው፡፡ በዚህም ከፍጡራን ሁሉ ከፍ ባለ በታላቅ ክብርና ጸጋ ለዘላለም እንደምትኖር እናምናለን፡፡

ልመናዋ ክብሯ ፍቅሯ አማላጅነቷ የልጇም ቸርነት በሁላችንም ላይ አድሮ ይኑር፡፡

ምንጭ ፡ ሐመር 18ኛ ዓመት ቁጥር 5