ኖላዊ ኄር

በመሪጌታ ባሕረ ጥበባት ሙጬ

ታኅሣሥ ፳፮ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

‹‹ኖላዊ ኄር›› የሚለው ሐረግ ‹ኖላዊ› እና ‹ኄር› ከሚሉ ሁለት ቃላተ ግእዝ የተዋቀረ ነው፡፡‹ኖላዊ› ማለት ‹እረኛ፣ ጠባቂ› ማለት ሲኾን፣ ‹ኄር› ደግሞ ‹መልካም፣ ቸር ርኅሩኅ፣ አዛኝ› የሚል የአማርኛ ትርጕም አለው፡፡ ስለዚህ ‹ኖላዊ ኄር› ማለት ‹መልካም እረኛ› ማለት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ቅዱስ ያሬድ ባዘጋጀው ስያሜ መሠረት ከታኅሣሥ ፳፩-፳፯ ያለው ሳምንት ‹ኖላዊ› ተብሎ ይጠራል፡፡ ሳምንቱ ካልጠፉት ዘጠና ዘጠኝ መንጋዎች ይልቅ የጠፋውን አንዱን በግ ፍለጋ የመጣው የእረኞች አለቃ፣ መልካሙ እረኛ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚታሰብበት ሳምንት ነው፡፡ ቸር ጠባቂያችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኝነት የባሕርዩ ነው፡፡ ‹‹አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር ዘበአማን፤ እውነተኛ ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤›› በማለት እንደ ተናገረው (ዮሐ. ፲፥፲፩)፡፡ ጌታችን ይህን መለኮታዊ ሥልጣኑን ለቅዱሳን በጸጋ አድሏቸዋል፡፡ ‹‹… ግልገሎቼን አሰማራ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን አሰማራ›› በማለት ለቅዱስ ጴጥሮስ የሰጠው ሥልጣን ለዚህ ማሳያ ነው (ዮሐ. ፳፩፥፲፭-፲፯)፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ስለ መንጋቸው ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡትን ታላላቅ መልካም እረኞችን የመረጣቸው ከበግ እረኝነት ነው፡፡ አምላካችን ለሕዝቡ የሚራራ ቸር ጠባቂ ነውና የጦር ስልት ከሚያውቁ ኃያላን የጦር ዐርበኞች በግ ጥባቂዎችን ለእረኝነት ይመርጣል፡፡ ቀድሞም ለበግ ጥበቃ በትረ ሙሴ እንጂ የጦር መሣሪያ መቼ ያስፈልግና? መልካም እረኞች የበጎችን ጠባይዕ ያውቃሉ፡፡ ለበጎች ምን እንደሚያስፈልጋቸውም ይረዳሉ፡፡ መልካም እረኞች ለበጎች ይራራሉ፤ ስለዚህም ወደ ለመለመ መስክ፣ ወደ ንጹሕ ምንጭ ይመሯቸዋል። የተሰበሩትን ይጥግኗቸዋል፤ የደከሙትንም ያበረቷቸዋል፡፡ ከዚሁ ዅሉ ጋርም በጎችን ከአንበሳ መንጋጋ፣ ከተኩላ ንጥቂያ ይከላከላሉ፡፡

ከበግ እረኝነት ወደ ታላቅ የሕዝብ መሪነት ከተመረጡት አንዱ ሊቀ ነቢያት ሙሴ ነው። ለሙሴ በእግዚአብሔር ዓይን ሞገስ ያስገኘለት የቤተ መንግሥት ኃያልነት፤ ዐርበኝነት እና የልዑልነት ማዕረግ ሳይኾን ለእግዚአብሔር መታመኑና ለ፵ ዓመታት በምድያም ተራራዎች፣ በሲና በረሃዎች በሎሌነት ያሳለፈው የበግ እረኝነት ተግባሩ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክም ሙሴ ከግብፅ ያመጣውን ትጥቅ አልፈለገውምና ‹‹ኢትቅረብ ዝየ ፍታሕ አሣዕኒከ እምእገሪከ እስመ መካን እንተ አንተ ትቀውም ባቲ ምድር ቅድስት ይእቲ፤ የቆምኽባት ምድር የተቀደሰች ናትና ጫማኽን ከእግርኽ አውጣ፤›› በማለት አዝዞታል (ዘፀ. ፫፥፭)፡፡ የቃል ኪዳኗ ምድር የምትወረሰው በእረኛ በትር እንጅ በልዑላን ሰልፍ አይደለምና፡፡ ሙሴ ከሕፃንነት እስከ ጕልምስና የሚያውቀው የፈርኦንን ሕግ እንጅ ስለ እረኞች አልነበረም፡፡ ለመቶ ዓመታት በባርነት ስቃይና ከሞት ጋር ሲተናነቅ ለኖረ ሕዝብ የፈርኦናውያን ሕግ ምን ለውጥ ያመጣለታል?

ክንደ ብርቱው ሙሴ ከቤተ መንግሥት ልዑልነት ይልቅ ወደ ሎሌነት ወርዶ፣ ሥጋዊ ሓላፊነትን ንቆ፣ የቤተ መንግሥት ዝናሩን አውልቆ፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ በተሰጠው የእረኝነት ሥልጣን የኃያልነት ዝናርን ታጥቋል፡፡ ለበጎቹ ሲልም በሲና በረሃ እሳት ነዶበታል። በእረኝነቱም ሕዝቡን ከጥፋት ለመታደግ ከበረሃ አውሬዎች ጋር ታግሏል፡፡ በእረኝነት ተግባር ብቻ ሳይኾን በየዋህቱም አርአያ ኾኗል፡፡ በመከራ እና በስቃይ የኖረ ሕዝብ የቃል ኪዳኗን ምድር ለመውረስ የሚጓዘው ሙሴ በረኝነት በነበረበት የበረሃ ምድረ አቋርጦ ነው፡፡ ጉዞው የሚወስደው ጊዜ ደግሞ ዐርባ ዓመታትን ነው፡፡ መንጋውን ለመምራት ለ፵ ዓመት የበረሃውን ሕይወት ከሚያውቀው ከሙሴ በቀር ማን ይችላል? ለዚህም ነው ቀን በደመና ሌሊት በብርሃን ዓምድ ውኃ እያፈለቀ፣ መና እያወረደ የቃዴስን ሐሩር ያሳለፋቸው፡፡ የእግዚአብሔር ቁጣ  በእስራኤል ልጆች ላይ በነደደች ጊዜ እንኳን ራሱን ስለ እነርሱ አሳልፎ የሚሰጥ መልካም እረኛ ኾኖ ተገኝቷል – ነቢዩ ሙሴ፡፡ ‹‹ወይእዜኒ እመ ተኀድግ ሎሙ ዘንተ ኃጢአተ ኅድግ ወእመ አኮሰ ደምስስ ኪያየኒ እመጽሐፍከ ዘጸሐፍከኒ፤ ሕዝብኽን ይቅር የማትላቸው ከኾነ እኔን ከጻፍኸው መጽሐፍኽ ደምስሰኝ›› በማለት መማጸኑም ስለዚህ ነው፡፡ የዚህ መልካም እረኛ ጸሎትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አግኝቷል (ዘፀ. ፴፪፥፴፪)፡፡

‹‹ረከብክዎ ለዳዊት ወልደ ዕሴይ ብእሴ ምእመነ ዘከመ ልብየ፤ ዘይገብር ኵሎ ፈቃድየ፤ ፈቃዴን ዅሉ የሚያደርግ የዕሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ›› (ሐዋ. ፲፫፥፳፪) ብሎ እግዚአብሔር የመሰከረለት ቅዱስ ዳዊት የተጠራውም ከበግ ጠባቂነት ነው፡፡ ለንጉሥ ሳኦል በወታደርነት የሚያገለግሉት የጦርነት ልምድ ያላቸው፣ በሰውኛ ዓይን ለቅብዐ መንግሥት ይበቃሉ ተብለው የሚታሰቡት ታላላቆቹ የዕሴይ ልጆች የነቢዩ ሳሙኤልን ቀርነ ቅብዕ ሲጠባበቁ ታናሹ ብላቴና ዳዊት ግን ያባቱን በጎች በዱር ይጠብቅ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ስለ ብጎቹ ሲል ከአንበሳ ጋር የሚተናነቀውን ታናሹን ብላቴና ዳዊትን መረጠ፡፡ እግዚአብሔር ዳዊትን ለንግሥና እንደ መረጠው የተረዳው ነቢዩ ሳሙኤልም መልእክተኛ ልኮ ዳዊትን አስጠርቶ ቅብዐ መንግሥትን ቀብቶ አነገሠው፡፡ የእግዚአብሔርም መንፈስ ከዚያን ቀን ጀምሮ በዳዊት ላይ አደረ (፩ኛ ሳሙ. ፲፮፥፲፪-፲፫)፡፡

ስለ መልካም እረኛ ሲነሣ በአብነት ከሚጠቀሱ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል በረከታቸው ይደርብንና ኢትዮጵያዊው ሰማዕት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አንደኛው ናቸው፡፡ ጠላት አገራችንን በወረረበት፣ በመንጋው ላይ መከራ እና ችግር በጸናበት፣ እንደዚሁም የንጹሐን ደም በግፍ በፈሰሰበት በዚያ በፈተና ወቅት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለቤተ ክርስቲያንም ለአገርም የሚያስቡ መልካም እረኛ እንደ ነበሩ የታሪክ መዛግብት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ከዐርበኞች ጋር ኾነው ሕዝቡ ለጠላት እጁን እንዳይሰጥና ሃይማኖቱን እንዳይለውጥ ከማስተማራቸው፣ ከማጽናናታቸው ባሻገር በጠላት ፊት ለፍርድ በቀረቡበት ጊዜም መልካም እረኝታቸውን በዐደባባይ መስክረው፣ ለሕዝብ፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር በመቆርቆራቸው በጥይት ተደብድበው በሰማዕትነት አልፈዋል፡፡

ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ፥ ወንበዴም ነው፡፡ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው፡፡ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል፡፡ ምንደኛ (ቅጥረኛ) እረኛ ግን ለበጎቹ አይጨነቅም፤ በጎቹም አያውቁትም (ዘካ. ፲፩፥፬-፭፤ ዮሐ. ፲፥፩-፲፪)፡፡ ዛሬም በእናት ቤተ ክርስቲያናችን የተሾሙ አባቶች እንደነሙሴ፣ እንደነዳዊት፣ እንደነብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለቤተ ክርስቲያንም ለአገርም የሚጨነቁ ሊኾኑ ይገባል፡፡ እኛ ምእመናንም እግዚአብሔር አምላካችን መልካም እረኞችን እንዳያሳጣን መለመን ይኖርብናል፡፡ እንደዚሁም ራሳችንን ለሃይማኖታችን ማስገዛት፣ መልካም እረኞችንም አብነት ማድረግና መከተል ይጠበቅብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡