ኒቆዲሞስ

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹ጾምን ቀድሱ፤ ጉባኤውንም ዐውጁ፡፡ ሽማግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ዅሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ሰብስቡ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ፡፡ በጽዮን መለከት ንፉጾምንም ቀድሱ፤›› በማለት የዐዋጅ አጽዋማትን እንድንጾም እግዚአብሔር አምላካችን በነቢዩ ኢዩኤል ላይ አድሮ ነግሮናል (ኢዩ. ፩፥፲፬፤ ፪፥፲፭)፡፡ ከእነዚህ አጽዋማት መካከልም ዐቢይ ጾም አንዱ ነው፡፡

ይህ ጾም የጠፋውን የሰውን ልጅ ለመፈለግ፣ የሞተውን አዳምን ለማስነሣት ሰው ኾኖ ወደዚህ ዓለም የመጣው፣ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመብል የተጀመረውን የሞት መንገድ ለማጥፋት ሲል የጾመው ጾም ነው፡፡ እኛም አባቶቻችን በሠሩልን ሥርዓት መሠረት በዐቢይ ጾም ወራት ‹ዘወረደ› ብለን ጀምረን በዓለ ትንሣኤን እስከምናከብርበት ዕለት ድረስ ያሉትን ሰንበታት በልዩ ልዩ ስያሜ በመጥራት የተከፈለልንን ዋጋ እያሰብን ቃለ እግዚአብሔር እንማራለን፤ እንዘምራለን፤ እንጸልያለን፡፡ ከእነዚህ ሰንበታት መካከል በሰባተኛው ሳምንት የሚገኘው ወቅት ‹ኒቆዲሞስ› ይባላል፡፡

ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን የአይሁድ አለቃ የነበረው ሰው ነው፡፡ የአይሁድ አለቆች አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ‹‹ምልክት አሳየን›› እያሉ ይፈታተኑት ነበር፡፡ ጌታችን ስለ ሞቱና ትንሣኤው በምሳሌ እያስረዳ ቢያስተምራቸውም እነርሱ ግን አልገባቸውም ነበር፡፡ ከዚህም አልፎ ጌታችን በተአምራቱ የታመሙትን ሲፈውስ ‹‹ሕጋችን ተሻረ›› ይሉ ነበር፡፡ በዚህ ዅሉ ተአምራትና ትምህርት የአይሁድ አለቆች ክርስቶስን ለመክሰስ በሚፈልጉበት ወቅት ከአይሁድ አለቆች አንዱ ኒቆዲሞስ በቀን እንዳያደርገው አይሁድን ቢፈራ፣ አንድም ጊዜ ባያደርሰው እንደ ባልንጀሮቹ ክርስቶስን ሳይቃወም በሌሊት ወደ ጌታችን ዘንድ እየሔደ ወንጌልን ይማር ነበር፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በነፍስ የታመሙትን በቃሉ፣ በሥጋ የታመሙትን በተአምራቱ ሲፈውስ ኒቆዲሞስ ሰምቶ፣ ተመልክቶ በመምህርነቱ ሳይኮራ አለቅነቱን መመኪያ ሳያደርግ በልቦናው የተሳለውን እውነትን የመፈለግ ስሜት አንግቦ ከጌታው፣ ከመምህሩ ከክርስቶስ ዘንድ በሌሊት ይገሰግስ ነበር (ዮሐ. ፫፥፩)፡፡ ምስክርነቱንም እንዲህ ሲል መስጠት ጀመረ፤ ‹‹መምህር ልታስተምር ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከኾነ በቀር አንተ የምታደርገውን ተአምራት ሊያደርግ የሚችል የለምና፤›› (ዮሐ. ፱፥፳፬፤ ሐዋ. ፲፥፴፰)፡፡

ይህን ምስክርነቱን በሚሰጥበት ጊዜም ጎዶሎን የሚሞላ፤ አላዋቂነት በአዋቂነት የሚለውጥ፤ ከምድራዊ ዕውቀት ወደ ሰማያዊው ምሥጢር የሚያሸጋግር አምላክ ‹‹ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም፤›› በማለት የአይሁድ መምህር ለኾነው ኒቆዲሞስ ቢያስተምረው ምሥጢሩ አልተገለጠለትም ነበርና ‹‹ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይቻላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?›› በማለት ጥያቄ አቅርቧል (ዮሐ. ፫፥፮፤ ፩ኛጴጥ. ፩፥፳፫)፡፡ ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፡፡ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፤›› (ኤፌ. ፭፥፳፮) በማለት አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ቢያስረዳውም ምሥጢሩ ከአቅሙ በላይ ስለ ኾነበት እንደምን ይቻላል? በማለት ጠይቋል፡፡

አበ ብዙኃን አብርሃም ከአምላኩ ሞገስን አግኝቶ የሰዶምና ገሞራ ጥፋት እንዳይደርስ ለመማለድ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር እንደ ነበረ፤ ኒቆዲሞስም አላዋቂነቱን አምኖ ያልገባውን ምሥጢር ከአምላኩ በጠየቀ ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስም፡- ‹‹አንተ የእስራኤል መምህራቸው ኾነህ ሳለ ይህን ነገር አታውቅምን? በምድር ያለውን ስንነግራችሁ ካላመናችሁ በሰማይ ያለውን ብንነግራችሁ እንደምን ታምናላችሁ? ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለምሙሴምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለ የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀላል፡፡ ያመነበት ዅሉ ለዘለዓለም ሕያው እንዲኖር እንጂ እንዲጠፋ አይደለም ...፤›› እያለ ሰው በመብል ምክንያት የአምላኩን ትእዛዝ አፍርሶ ከእግዚአብሔር ቢለይም የሰው ልጅ ያጣውን ልጅነት ለመመለስ፣ ስመ ክርስትናን፣ ሀብተ ወልድን ለመስጠት ጌታችን መምጣቱን አስረዳው (ዮሐ. ፫፥፲፬)፡፡ ይህን የክርስቶስን የማዳን ሥራና በሥጋ መገለጥም ‹‹ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ አመከርከኒ ወኢተረከ ዐመፃ በላዕሌየ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ እጓለ እመሕያው፤ ልቤን ፈተንኸው፡፡ በሌሊትም ጐበኘኸኝ፤ ፈተንከኝም፡፡ ምንም አላገኘህብኝም፡፡ የሰውን ሥራ አፌ እንዳይናገር ፈቃዴ ነው፤›› (መዝ. ፲፮፥፫) በማለት ቅዱስ ዳዊት ከኒቆዲሞስ ሕይወት ጋር በማዛመድ አመሥጥሮታል፡፡

በሌሊት ከአምላኩ ተምሮ ምሥጢሩ የተገለጸለት ኒቆዲሞስ ቀድሞ በአደባባይ ሔዶ መማርን ይፈራ እንዳልነበረ ምሥጢሩ ሲገለጽለት ግን አይሁድ ጌታችንን በሰቀሉት ዕለት ፍርኃት ርቆለት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ቅዱስ ሥጋውን ገንዞ ለመቅበር በቃ፡፡ ‹‹ወአልቦ ፍርኃት ውስተ ተፋቅሮትነ፤ ፍጹም ፍቅር ፍርኃትን አውጥቶ ይጥላል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ማቴ. ፳፯፥፶፰፤ ፩ኛዮሐ. ፬፥፲፰)፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ያመነየተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ፣ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል›› (ማር. ፲፮፥፮) በማለት በሰጠን ቃል ኪዳን መሠረት በአምላክነቱ አምነን የመንግሥቱ ወራሾች እንኾን ዘንድ ለኒቆዲሞስ ምሥጢሩን እንደ ገለጸ ለእኛም ይግለጽልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡