ነገረ ድኅነት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

በማኅበረ ቅዱሳን ትምህርተ ወንጌልና ሐዋርያዊ አገልግሎት ማስተባበሪያ 

በስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ዋና ክፍል የተዘጋጀ

የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

የዚህ ጽሑፍ መዘጋጀት መሠረታዊ ዓላማ፡-

  • ስለ ሰው መዳን ግልጽ ያልኾነላቸው አካላት ስለ ድኅነት የሚናገሩት ከቅዱሳት መጻሕፍት ውጪ መኾኑን ማሳየት፤
  • በእምነት (በማመን) ብቻ እንድናለን የሚሉ አካላት አስተምህሮ ስሕተት እንዳለበት መግለጽ፤
  • በመስቀል ላይ በተደረገው ድኅነት አዳምና ልጆቹ የዳኑት ከምን እንደ ኾነ ማብራራት፤
  • እንዴትና ከምን እንደ ዳንን ለመግለጽ፤
  • ድኅነታችን እንዴት እንደምንፈጽም በማስረዳት ስለ ሰው መዳን ግልጽ ላልኾነላቸው (የተሳሳተ ትምህርት ለሚሰጡ) አካላት ምላሽ ለመስጠት ነው፡፡

መግቢያ

የሰው ልጅ ትእዛዘ እግዚአብሔርን በማፍረሱ ከእግዚአብሔር ተለየ፤ በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዞ በዲያብሎስ ክፋት ተመርዞ አምስት ሺ ከአምስት መቶ ዘመናትን ኖረ፡፡ ከሰው ልጅ ውድቀት ጀምሮ የሰው ልጅ ፍላጎት ድኅነትን ማግኘት ነበር፡፡ የሰው ልጅ የመዳን ተስፋውን ከፈጣሪው ተቀብሎ በተስፋ ኖረ፡፡ የሰው መዳን የእግዚአብሔር ማዳን በሰጠው ተስፋ መሠረት በነቢያት ትንቢት ተነገረ፤ ሱባዔ ተቈጠረ፡፡ ከዚህ ከደረሰበት መከራ ፍጡር ሊያድነው አይችልምና በእሩቅ ብእሲ (በሰው) ደም ነጻ ሊወጣ አልተቻለውም፡፡ የሰው ልጅ ባቀረበው መሥዋዕት፣ ባደረሰው ጸሎት የነበረበትን ዕዳ መሠረዝ ተሳነው፡፡ ነቢያት፣ ካህናት ለዘመናት የበሬ፣ የላም፣ የበግ መሥዋዕት የፍየል፤ የእኽል፤ የዋኖስ እና የርግብ መሥዋዕት አቀረቡ፤ ስብ አጤሱ፤ የእንስሳትን ደም አፈሰሱ፤ ሰውን ግን ማዳን አልተቻላቸውም፡፡ ‹‹ጽድቃችን እንደ መርገም ጨርቅ ኾነ›› እንዳለ ነቢዩ ኢሳይያስ (ኢሳ. ፷፬፥፮)፡፡

ለአዳም በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ድኅነት የናፈቀውን፤ መከራ ያስጨነቀውን የሰውን ልጅ ያድነው ዘንድ ነቢያት በተናገሩት ትንቢት፣ በቈጠሩት ሱባዔ፣ እግዚአብሔር አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ድኅነት ርቆት፣ መከራ በዝቶበት መዳን ሲፈልግ ከነበረው ሥጋ ጋር ወሀቤ ሕይወት (ሕይወት ሰጭ) አዳኝ ይኾነው ዘንድ መለኮት ተዋሐደ፡፡ ድኅነትን አጥቶ ሲሰቃይ ለነበረው የሰው ልጅ ፈጣሪ የተዘጋ ርስቱን (ገነትን)፣ የተቀማ ልጅነቱን፣ ያጣውን አንድነቱን መለሰለት፡፡ ስለዚህም የምሥራች ተነገረ፤ ድኅነት ተበሠረ፡፡ በዚህም የሰው ልጅ ተጠቀመ፤ የነቢያት ትንቢትም ተፈጸመ፡፡

ሰው የዳነው ከምንድን ነው?

፩. ከበደለው በደል (ጥንተ አብሶ)

የሰው ልጅ በአምላክ ሰው መኾን የበደሉትንም ያልበደሉትንም ያስቀጣ ከነበረው በደል ነጻ ኾኗል፡፡ አሁን ማንም ሰው በአዳም በደል አይጠየቅም፡፡ በራሱ ፈቃድ ሕግ ጥሶ፣ ትእዛዝ አፍርሶ የተከፈለለትን ዋጋ መጠቀም ባለ መቻሉ ይቀጣል እንጂ፡፡ “ከባላጋራችን የተነሣ በትእዛዝ የተጻፈዉን የዕዳችንን ደብዳቤ ደመሰሰልን፤ ከመካከላችንም አራቀው፤ በመስቀሉም ቸነከረው፤” (ቈላ. ፪፥፲፬፤ ራእ. ፩፥፭)፡፡ ለነበረብን በደል ይቅርታ አድርጎ ደሙን አፍስሶ ሥጋውን ቈርሶ ይቅርታ ሰጠን፡፡ ባሮች ነበርን፤ ልጆቹ አደረገን፡፡ የነቢያት ጩኸት ይህን የተመለከተ ነበር፤ “… የቀደመ በደላችንን አታስብብን፤ አቤቱ፥ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፤ እጅግ ተቸግረናልና፤” የሚል (መዝ. ፸፰፥፰)፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ጩኸቱን አይቶ ልመናውን ሰምቶ በደሉን አስወግዶለታል፡፡

፪. ከዘለዓለም ሞት (ፈርሶ በስብሶ ከመቅረት፣ ከሞተ ነፍስ)

ሞት ማለት አንደኛ የነፍስና የሥጋ መለያየት ነው፤ የነፍስና የሥጋ መለያየት በትንሣኤ አንድ ኾነው እንደሚነሡ ክርስቶስ በሥጋ ወደ መቃብር፣ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ በሲኦል የነበሩትን ከሞተ ነፍስ ከመከራ ነጻ አወጣ፤ ሙስና መቃብርን አጠፋ፡፡ ለሰው ልጅ፣ ከሞት በኋላ ሕይወት፣ ከመቃብር ባሻገር ትንሣኤ መኖሩን አሳየ፡፡ “ሞት ሆይ፥ እንግዲህ መውጊያህ ወዴት አለ? መቃብር ሆይ፥ አሸናፊነትህ ወዴት አለ?” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (፩ኛ ቆሮ. ፲፭፥፶፭)፡፡ “ከሲኦል እጅ እታደጋቸዋለሁ፤ ከሞትም እቤዣቸዋለሁ፤” (ሆሴ. ፲፫፥፲፬) ተብሎ የተነገረው የነቢዩ ቃል ይፈጽም ዘንድ የሰው ልጅ ከሞት (ከዲያብሎስ) ባርነት ከሲኦል ግዛት ድኗል፡፡ “ከጨለማ አገዛዝ አዳነን፤ ወደ ተወደደው ልጁ መንግሥትም መለሰን፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ቈላ. ፩፥፲፫)፡፡

የሰው ልጅ በተከፈለለት ዋጋ ከሞተ ነፍስ የሚድንበትን መንገድ አገኘ፤ ፈጣሪው ሰው ኾኖ ከሞት የሚያመልጥበትን መንገድ አስተማረው፡፡ ሞተ ሥጋን በትንሣኤው ድል ነሣለት፤ የተዘጋውን ገነት ከፍቶ ለዘለዓለም በሕይወት መንገድ መራው፡፡ ስለዚህም ነው ጌታችን “እውነት እውነት እላችኋለሁ፤ ቃሌን የሚሰማ በላከኝም የሚያምን የዘለዓለም ሕይወትን ያገኛል፡፡ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይሔድም፤” በማለት ያስተማረን (ዮሐ. ፭፥፳፬)፡፡ ይህም በእኛ ሥራ ሳይኾን በእግዚአብሔር ቸርነት የተደረገልን የማዳን ሥራ ነው፡፡ ራሱ ባለቤቱ በይቅርታው ብዛት ያደረገልን ነው፡፡ አምላካችን ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አስወገደልን፤ ከሞተ ነፍስም አዳነን፡፡ ሞተ ነፍስ ከእግዚአብሔር መለየት ነበር፤ እግዚአብሔር ሰው ሲኾን ይህ ሞት ተወገደ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ኾኗልና (ሮሜ. ፰፥፴፩)፡፡

በዚህ መንገድ ከእግዚአብሔር መለየት ቀረልን፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆኗልና፤ ማለት ከሥጋችን ሥጋ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ በተዋሕዶ ከእኛ ጋር ተዛምዷል፤ ስለዚህ የእኛን ሞት እርሱ ሞተልን መከራችንንም ተቀበለልን፡፡ “በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ፤ ሕመማችንንም ተሸከመ፤ ስለ እኛም ታመመ፤” እንዳለ ኢሳይያስ (ኢሳ. ፶፫፥፬)፡፡ ደዌያችንን ተቀብሎ ሕመማችንን ተሸክሞ ሞታችንን ሞቶ ሕይወትን ሰጠን፤ ከሞት አዳነን “ዘዚአነ ሞተ ነሥአ ወእንቲአሁ ሕይወተ ወሀበነ፤ የእኛን ሞት ሞቶ የእርሱን ሕይወት ሰጠን፤” እንዳለ ቅዱስ ኤፍሬም፡፡

ክርስቶስ ሞቶ ከተነሣ በኋላ ሞት ኃይሉን አጥቷል፤ ከዚያ በፊት ሞት ሰውን ዂሉ ወደ ሲኦል ወደ ሁለተኛ ሞት የሚያጓጉዝ ነበር፤ አሁን ግን ሰውን ወደ  ሕይወት የሚያደርስ ነው፡፡ ሞት ወደ ገነት ወደ መንግሥተ ሰማያት የምንጓዝበት መንገድ ኾኗል፡፡ ሰዎች የሚፈሩት ሳይኾን የሚፈልጉት ኾኗል፤ ወደ እግዚአብሔር የምንሔድበት ስለ ኾነ፡፡ ከአዳም ጀምሮ እስከ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ድረስ የበደሉትም ያልበደሉትም በመስቀል ላይ በተከፈለው ዋጋ ድነዋል፡፡ ጌታችን ይህን ድኅነት የሚናገሩ፣ የምሥራቹን የሚያወሩ፣ ላለፈው ይቅርታ መደረጉን፣ ለሚመጣው ሕግ መሠራቱን የሚመሰክሩ ሐዋርያትን መርጦ ሾመ፡፡ ለወደፊቱ ለሚመጣው ትውልድ ድኅነት እንደሚገኝ ለማስተማር በዓለም ዂሉ ላካቸው፤ በቃላቸውም የሚድኑትን ዕለት ዕለት በእነርሱ ላይ ይጨምር ነበር (ሐዋ. ፪፥፵፯)፡፡

አሁን እንዴት እንድናለን?

የታመሙት ድነዋል፤ ሲኦል የነበሩት ወጥተዋል፡፡ እኛስ ድነናል ወይስ እንድናለን? እኛማ እንድናለን፡፡ ካሣው ለዂሉም ተከፍሏል፤ አምላካችን የሞቱትን አድኗልና፡፡ በሕይወተ ሥጋ ያለን እኛ ግን ድኅነቱን ተቀብለን በሃይማኖት (በእምነት)፣ በጥምቀት፣ ቅዱስ ሥጋውን በመብላት፣ ክቡር ደሙን በመጠጣት የተሠራውን ሕግ በመጠበቅ ድኅነትን እናገኛለን፡፡ ድነናል ብለን የምናወራ ከኾነ ሕግ ለምን አስፈለገን? በገነት ለሚኖሩት ከሲኦል ለወጡት ሕግ አያስፈልጋቸውም፡፡ በተጻፈ ሕግ አይመሩም፤ እኛ ግን በተጻፈ ሕግ ከኦሪት ወደ ወንጌል የተሸጋገርነው የምንጠብቀው እና የሚጠብቀን የሚያድነን ሕግ ተሠርቶልናል፡፡

በዚህ እንድናለን፤  በሕጉ ካልኖርን ደግሞ እንቀጣለን፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹የሚድኑትን›› የሚለውን ቃል ልብ ማለት ያሻል፡፡ ‹‹የዳኑትን›› አይደለም ያለው፤ ‹‹የሚድኑትን›› አለ እንጂ፡፡ ስለዚህ ክርስትና ወይም ሕገ ወንጌል የዳኑትን ለማዳን የተሰጠ ሕግ ሳይኾን ያልዳኑት እንዲድኑ የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ የኦሪት ሕግ (የኦሪት መሥዋዕት) ማዳን የሚችል አልነበረም፤ ወንጌል ግን ለዓለም ድኅነት የተሰጠ ሕግ ነው፡፡ ሐዋርያት ዓለም እንዲድን የሕይወትን ወንጌል ይዘው ዞሩ፤ አስተማሩ፡፡ ወንጌል የተሰበከው ለዳኑት ሳይኾን ለሚድኑት ነው፡፡ ስለዚህ ለመዳን ምን ያስፈልጋል? የሰው ልጅ ለመዳን የሚስፈልጉት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፤

፩ኛ ማመን

የሰው ልጅ፣ ከዂሉ አስቀድሞ የዓለም መደኀኒት ክርስቶስ ሕግን እንደ ሠራለት አምኖ መመለስ ያስፈልገዋል፡፡ “ለሰው ዂሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም (ወደ ሰው) የመጣው ነው፡፡ በዓለም ነበረ፤ ዓለሙም በእርሱ ኾነ፤ ዓለሙ ግን አላወቀውም፡፡ ወደ ወገኖቹ መጣ፤ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም፡፡ ለተቀበሉት ዂሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲኾኑ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡ እነርሱም ከእግዚእሔር ተወለዱ …፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዮሐ. ፩፥፱)፡፡ ቀደም ሲል የነበረው ድኅነት ለተቀበሉትም ላልተቀበሉትም የተደረገ፤ ላመኑትም ላላመኑት የተፈጸመ ድኅነት ነው፡፡ አሁን ግን ላመኑ እንጂ ላላመኑ የሚሰጥ ድኅነት የለም፡፡

፪. መጠመቅ

“ያመነ የተጠመቀ ይድናል” (ማር. ፲፮፥፲፮) ተብሎ በቅዱስ ወንጌል እንደ ተነገረው ለመዳን እምነት ያስፈልጋል፤ ከእምነት ቀጥሎ መጠመቅ ያሻል፤ ይህን ካሣ ተፈጽሞ የተሠራውን ሕግ መፈጸም ግዴታ ነው፡፡ ለመዳን ማመን ብቻ አይበቃም፡፡ እምነትማ አጋንንትም አላቸው፡፡ ዕለት ዕለት የሚድኑበት፣ የሚጨመሩበት መንገዱ እምነትና ጥምቀት ነው፡፡ የቅዱሳን ሐዋርያት ተግባርም ይህ ነበር፡፡ ሕይወትን ድኅነትን መስበክ፤ ያመነውን ማጥመቅ፤ የድኅነቱ ተሳታፊ ማድረግ ወደ ድኅነቱ ማስገባት፤ የሕይወትን ቃል ለዂሉ መመስከር ነው፡፡ ዓላማው ለማሳመን፣ ለማጥመቅ፣ ለማዳን ነው፡፡ ለመዳን አምኖ መጠመቅ የግድ አስፈላጊ መኾኑን በሐዋርያት ሥራ የተመዘገበው የጃንደረባው ታሪክ ያስረዳናል (ሐዋ. ፰፥፴፭-፴፯)፡፡

ማመን ብቻውን ስለማያድን ጃንደረባው ‹‹አምናለሁ›› ብሎ ከማመን አልፎ ሃይማኖቱን መስክሯል፤ ፊልጶስም ‹‹ድነሃል፤ ሒድ›› አላለውም፤ አጠመቀው እንጂ፡፡ ስለዚህ ከእምነት ቀጥሎ መጠመቅ ለድኅነት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ነው ዓለምን ለማዳን የመጣው አምላካችን ሐዋርያትን ወደ ዓለም ዂሉ የላከው (ማቴ. ፳፰፥፲፱)፡፡ ተልዕኮውም በቃ ‹‹አድኛቸዋለሁ›› አይደለም፤ እንዲያምኑ፣ እንዲጠመቁ፣ ትእዛዙን እንዲጠብቁ፣ ደቀ መዛሙርት እንዲኾኑ ነው፡፡ ድኅነት የሚገኘው በዚህ መንገድ ነው፡፡ በማውራት ብቻ ‹‹ድኛለሁ›› ብሎ ተዘልሎ በመቀመጥ አይደለም፡፡ “… እነዚህ ሰዎች የልዑል እግዚአብሔር አገልጋዮች ናቸው፤ የሕይወትንም መንገድ ያስተምሯችኋል …” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ሐዋ. ፮፥፲፯)፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት የመዳንን መንገድ የሚነግሩን እንድናየው አይደለም፤ እንድንጓዝበት ነው እንጂ፡፡ “… ‹ጌቶቼ፥ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተ እና ቤተሰቦችህ ትድናላችሁ› አሉት፡፡ የእግዚአብሔርንም ቃል ለእርሱና በቤቱ ላሉት ዂሉ ነገሩአቸው … በዚያው ጊዜ ከቤተ ሰቡ ዂሉ ጋር ተጠመቀ፤” (ሐዋ. ፲፮፥፴-፴፬)፡፡ ከዚህ ላይ ‹‹ድናችኋል›› ሳይኾን ‹‹ትድናላችሁ›› የሚለውን ቃል ልብ ይሏል፡፡ “ዳግመኛ ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” እንዳለ (ዮሐ. ፫፥፭)፡፡ ስለዚህ ሰው አምኖ ይጠመቃል፤ ከእግዚአብሔርም ይወለዳል፤ በዚህ ድኅነትን ገንዘብ ያደርጋል፡፡ ከእግዚአብሔር ካልተወለደ በፍጹም ሊድን አይችልም፡፡ መዳን ማለት የእግዚአብሔርን መንግሥት ወርሶ ስሙን ቀድሶ መኖር ነው፡፡ ስለዚህ የሕይወት እና የድኅነት ወንጌል ለዓለሙ ዂሉ ይሰበካል፤ ዂሉም ይድን ዘንድ (ማር. ፲፮፥፰)፡፡

፫. ሥጋውን መብላት ደሙን መጠጣት

ሰው ካመነ ከተጠመቀ በኋላ ማድረግ ያለበት ቅዱስ ሥጋውን መብላት፣ ክቡር ደሙን መጠጣት ነው፡፡ ሥጋ ወደሙ ሕይወት የሚገኝበት የእምነት እና የጥምቀት ማተሚያ መደምደሚያ ነው፡፡ እምነት መሠረት፤ ጥምቀት መሰረት የሚጸናበት ከእግዚአብሔር የምንወለድበት፤ ሥጋው እና ደሙ ማረጋገጫ ነው፡፡ ያመነ በጥምቀት ይወለዳል፤ የተወለደ ደግሞ የሚያድግበት ምግብ ያስፈልገዋል፡፡ ምግቡም ሥጋውና ደሙ ነው፡፡ ይህን በልቶ ጠጥቶ የሚኖር የእግዚአብሔር ልጅ፣ የእግዚአብሔር የመንግሥቱ ወራሽ፣ የስሙ ቀዳሽ ይኾናል፡፡

“የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ለዘለዓለም ሕይወት ለሚኖር መብል ሥሩ እንጂ ለሚጠፋው መብል አይደለም፤ ይህን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና … የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ፤ ለዓለም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና …” ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዮሐ. ፮፥፳፯-፶፬፤ ሮሜ. ፭፥፱፤ ኤፌ. ፩፥፯፤ ፩ኛ ዮሐ. ፩፥፯)፡፡ ስለዚህ አምነን ተጠምቀን ሥርየት የተገኘበትን እና የሚገኝበትን ሥጋውን መብላት ያፈልጋል፡፡ በሃይማኖት ከብረን፣ በጥምቀት ተወልደን፣ በሥጋው በደሙ ታትመን ድኅነትን ገንዘብ እናደርጋለን፡፡

፬. መልካም መሥራት (ዐቂበ ሕግ)

ያመነ፣ የተጠመቀ፣ ሥጋውን የበላ፣ ደሙን የጠጣ ዂሉ በመልካም ሥራ መኖር አለበት፡፡ መልካም ሥራ የሌለው እምነት፣ ጥምቀት፣ ቊርባን ብቻውን አያድንም፤ ያመነ የተጠመቀ ሰው ፈጣሪውን በሃይማኖት መከተል በግብር መምሰል አለበት፡፡ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ፤” (ማቴ. ፭፥፲፮)፡፡ የሰው ልጅ ከላይ የተዘረዘሩ ተግባራትን ከፈጸመ እንንደየሥራው መጠን ዋጋውን እንደሚቀበል ቅዱሳት መጽሐፍት ምስክሮች ናቸው፡፡ “እነሆ በቶሎ እመጣለሁ፤ ለእያንዳንዱ እንደየሥራው መጠን እከፍለው ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር ነው፤” (ራእ. ፳፪፥፲፪፤ ያዕ. ፪፥፳፮)፡፡

አምላካችን ለፍርድ ሲመጣ የሚጠይቀው ሃይማኖት ብቻ ሳይኾን ሥራ መኾኑን መዘንጋት ሞኝነት ነው፡፡ “… ብራብ አላበላችሁኝም፤ ብጠማ አላጠጣችሁኝም፤ ብታረዝ አላለበሳችሁኝም …” እንዳለ ጌታችን (ማቴ. ፳፭፥፴፭-፵፭)፡፡ ስለዚህ ለድኅነቱ ተግባር አስፈላጊ ነው፡፡ ከተግባር ጋር ዐቂበ ሕግ (ሕግ መጠበቅ) ተገቢ ነው፡፡ “የዘለዓለም ሕይወትን አገኝ ዘንድ ምን ላድርግ?” ብሎ ለጠየቀው ጐልማሳ ጌታችን የሰጠው ምላሽም “… ትእዛዛትን ጠብቅ” የሚል ነው (ማቴ. ፲፱፥፲፮-፲፯)፡፡ የዘለዓለም ሕይወትን ለመውረስ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሚቀበለው መልካም ሥራ ወሳኝ ጉዳይ ነውና፡፡

፭. መጽናት

ለመዳን ከማመን፣ ከመጠመቅ፣ ሥጋውን ከመብላት፣ ደሙን ከመጠጣት በተጨማሪ በዚሁ ጸንቶ መኖር ያስፈልጋል፡፡ ገብተው የወጡ፤ አምነው የካዱ ዂሉ ድኅነት የላቸውም፡፡ “በዂሉም ዘንድ ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትኾናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል፤” (ማቴ. ፲፥፳፪፤ ፳፬፥፲፫፤ ማር. ፲፫፥፲፫)፡፡ “እኛም የምንደፍርበትን የምንመካበትን ተስፋ እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ ቤቱ ነን … የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ኾነናል …” (ዕብ. ፫፥፮-፲፬)፡፡ “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ኹን፤ የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ፤” (ራእ. ፪፥፲)፡፡

“ድል ለነሣውና እስከ መጨረሻ ሥራዬን ለጠበቀው እኔ ደግሞ ከአባቴ እንደ ተቀበልኩ በአሕዛብ ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፡፡ በብረት በትር ይገዛቸዋል፤ እንደ ሸክላ ይቀጠቅጣቸዋል፤” (ራእ. ፪፥፳፮)፡፡ የሰው ልጅ የሚድነው በእምነት፣ በጥምቀት፣ በሥጋው በደሙ፣ በመልካም ሥራ ጸንቶ ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ጸንተን እንድኖር እና መንግሥቱን እድንወርስ፤ ስሙን እንድንቀድስ አምላካችን በቸርነቱ ይርዳን፡፡ እንግዲህ ዂላችሁም ወደ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በመመለስ (በመምጣት) ድኅነታችሁን በመፈጸም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የተዘጋጃችሁ ኹኑ መልእክታችን ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡