ነገረ ድኅነት በትንቢተ ነቢያት (ካለፈው የቀጠለ)

ታኅሣሥ ቀን ፳፻፱ .

በመ/ ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

፬. ብርሃን

ነቢያት ዓለምን ለማዳን የመጣውን ሰማያዊ ንጉሥ ‹‹ብርሃን›› በማለት ጠርተውታል፡፡ ጨለማ የተባለ ዲያብሎስን ድል ነሥቶ ከሲኦል ባርነት ነጻ የሚያወጣቸው፤ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ የሚመልሳቸው እርሱ ነውና፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ለይኩን ብርሃኑ ለእግዚአብሔር አምላክነ ላዕሌነ፤ የአምላካችን የእግዚአብሔር ብርሃኑ በእኛ ላይ ይኹን›› (መዝ.፹፱፥፲፯) በማለት መዘመሩም ‹‹እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ሥጋ ተዋሕዶ ያድነን›› ሲል ነው፡፡

አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በፀሐይ ይመሰላሉ፡፡ ፀሐይ ክበብ፣ ብርሃንና ሙቀት አላት፤ ክቡ የአብ፣ ብርሃኑ የወልድ፣ ሙቀቱ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው፡፡ ብርሃን ከፀሐይ ሳይለይ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ጨለማውን አሸንፎ በዚህ ዓለም ላሉት ዅሉ እንዲያበራ፤ በብርሃኑ ታግዘውም ሰዎች ዅሉ እንዲመላለሱበት እግዚአብሔር ወልድም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ሲወለድ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ህልውና አልተለየምና በብርሃን ተመስሏል፡፡

ቅዱስ ዳዊትም የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃንነት በሚመለከት ምሥጢር ‹‹ፈኑ ብርሃነከ ወጽድቀከ እማንቱ ይምርሐኒ ወይሰዳኒ ደብረ መቅደስከ ወውስተ አብያቲከ እግዚኦ፤ ብርሃንህን እና ጽድቅህን ላክ፤ እነርሱ መርተው ወደ ቅድስናህ ተራራና ወደ ማደሪያህ ይውሰዱኝ፤›› (መዝ. ፵፪፥፫) በማለት ዘምሯል፡፡ ነቢያት ‹‹ብርሃን›› በማለት የጠሩት ወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ ከሰማያት ወርዶ ሰው ኾኖ ሲያስተምር ‹‹እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይኾንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም›› (ዮሐ.፰፥፲፪)፤ እንደዚሁም በተመሳሳይ ምሥጢር ‹‹እውነትንም ታውቃላችሁ፤ እውነትም አርነት ያወጣችኋል፤›› (ዮሐ.፰፥፴፪) በማለት የነቢያቱ ትንቢት በእውነተኛው ብርሃን በእርሱ (በክርስቶስ) መፈጸሙን አረጋግጧል፡፡

እንደዚሁ ነቢዩ ኢሳይያስም፡- ‹‹የዛብሎን ምድርና የንፍታሌም ምድር የባሕር መንገድ፣ በዮርዳኖስ ማዶ የአሕዛብ ገሊላ በጨለማ የተቀመጠው ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት አገርና ጥላ ለተቀመጡትም ብርሃን ወጣላቸው፤›› በማለት ተናግሯል (ኢሳ.፱፥፲-፪)፡፡ ይህ ቃለ ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በያገሩ እየተዘዋወረ ድውያነ ሥጋን በተአምራቱ፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርቱ እየፈወሰ በኃጢአትና በደዌ ጨለማ ተውጠው ለነበሩ ዅሉ ብርሃን ኾኗቸዋል (ማቴ.፬፥፲፭-፲፰)፡፡

የአጥቢያ ኮከብ መውጣት የሌሊቱን ማለፍ እንደሚያበሥር ዅሉ የነቢያት ትንቢትም ለሐዋርያት ስብከት መንገድ ጠራጊ ነበር፡፡ ነቢያት ‹‹ይወርዳል፤ ይወለዳል›› ብለው በከፈቱት የትንቢት የሐዲስ ኪዳን በር ሐዋርያት ገብተው ወንጌልን ለዓለም ሰበኩበት፤ የክርስቶስን በሥጋ መገለጥ መሰከሩበት፡፡ የዓለም ብርሃን ክርስቶስ ካደረበት አድረው፣ ከዋለበት ውለው በተማሩት ትምህርት፣ ባገኙት ልጅነት ምክንያት ‹‹የዓለም ብርሃን የብርሃን ልጆች›› ተብለው ለመጠራት በቅተዋል (ማቴ.፭፥፲፪፤ ሉቃ.፲፮፥፰)፡፡

ነቢያት በዐረፍተ ዘመን ስለ ተገቱ ትንቢት የተናገሩለትን፣ ሱባዔ የቈጠሩለትን፣ ብርሃን ብለው የጠሩትን ጌታ በዓይነ ሥጋ አላዩትም፡፡ ሐዋርያት ግን ነቢያት የዘሩትን የትንቢት ፍሬ ሰብስበውታል፡፡ ከጨለማው ዓለም ወጥተው፣ ከሥጋዊ ግብር ተለይተው፣ ከባርነት ወደ ልጅነት፣ ከኃጢአት ወደ ስርየት ተመልሰው ወደ ፍጹም ብርሃን ደርሰው የዓለም ብርሃን ክርስቶስ በደሙ ፈሳሽነት ዓለምን እንዳዳነ፣ ዲያብሎስን ድል አድርጎ የቀደመ ልጅነታችንን እንደ መለሰ እስከ ዓለም ዳርቻ ዞረው መስክረዋል፡፡ ለምዕት ዓመታት በግብጽ ምድር በባርነት ተይዘው የኖሩት እስራኤል ዘሥጋ በዓምደ ብርሃን እየተመሩ ወደ ርስት አገራቸው ከነዓን እንደ ገቡ ዅሉ እስራኤል ዘነፍስም በእውነተኛው ብርሃን በክርስቶስ መሪነት ወደ ገነት (መንግሥተ ሰማያት) ለመግባት ችለዋል፡፡

ቅዱስ ዳዊት ‹‹በውኑ ‹ጨለማ ትሸፍነኛለች› ብል ሌሊት በዙሪያዬ ብርሃን ትኾናለች፤ ጨለማ ባንተ ዘንድ አይጨልምምና፤ ሌሊትም እንደ ቀን ታበራለችና›› በማለት እንደ ተናገረው (መዝ. ፻፴፰፥፲፩-፲፪)፣ በአምላካችን ዘንድም ጨለማ የሚባል ነገር ከቶ የለም፡፡ ‹‹ለሰዉ ዅሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም ይመጣ ነበር፤ በዓለም ነበረ፡፡ ዓለሙም በእርሱ ኾነ፤ ዓለሙም አላወቀውም … ብርሃን በጨለማ ይበራል፤ ጨለማም አላሸነፈውም፤›› (ዮሐ.፩፥፱-፲፭) ተብሎ በቅዱስ ወንጌል የተመሰከረለት፤ ጨለማ የማያሸንፈው፣ ለዘለዓለሙ የማይጠፋው፣ ተራራ የማይጋርደው፣ የቦታ ርቀት የማይከለክለው እውነተኛው ብርሃን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዓለም መጥቶ ሕዝብንና አሕዛብን በአንድነት ወደ ድንቅ ብርሃን (ወደ እርሱ) አቅርቧቸዋል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬምም ይህንን እውነት መሠረት አድርጎ ‹‹ብርሃን ዘበአማን ዘያበርህ ለኵሉ ሰብእ፤ ለሰው ዅሉ የሚያበራ እውነተኛ ብርሃን›› በማለት የክርስቶስን ብርሃንነት (ዓለምን ከጨለማው ዓለም ነጻ ማውጣቱን) መስክሯል /ውዳሴ ማርያም ዘሰኑይ/፡፡

ቅዱሳን ነቢያት በልቡናቸው ትንቢትን እንደ ዝናር ታጥቀው፣ ከሩቅ በሚመለከቱት ተስፋ አሸብርቀው የብርሃኑን መምጣት ሲጠባበቁ ኖረዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም በዚህ ብርሃን ተመርተው ደስ እያላቸው ክርስቶስን በመስበክ በትምህርታቸውና በተአምራታቸው ለጨለማው ዓለምና ለሰው ልጅ ልቡና ወንጌልን አብርተዋል፡፡ ነገር ግን ስለ ብርሃን የተነገረውን የትንቢት ቃል ያልተቀበሉ አይሁድና መሰሎቻቸው በኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ብርሃንነት አላመኑምና በክፋትና በክሕደት ጨለማ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ‹‹ብርሃንም ወደዚህ ዓለም ይመጣ ነበር፤ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ስለ ነበር ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው፡፡ ሥራው ክፉ የኾነ ዅሉ ብርሃንን ይጠላል፡፡ ሥራው እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (ዮሐ. ፫፥፲፱)፡፡

፭. ኖላዊ (ጠባቂ፣ እረኛ)

ኖላዊ ሓላፊነት ለተሰጣቸው ዅሉ ምሳሌ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን መሳፍንት፣ ነገሥታት፣ ነቢያትና ካህናት ኖሎት (እረኞች፣ ጠባቂዎች) ተብለው ተጠርተዋል (ኤር.፳፫፥፩-፬፤ ፳፭፥፴፪-፴፰፤ ሕዝ.፴፬፥፩-፲)፡፡ ነቢያት ዓለሙን ለማዳን ወደዚህ ዓለም የመጣውን መሲሕ ክርስቶስን ከገለጡበት የግብር ስያሜ አንደኛው ‹‹ኖላዊ (ጠባቂ)›› የሚለው ቃል ነው፡፡ መድኀኒታችን ክርስቶስ ጠባቂ እንደሌለው በግ ተቅበዝብዞ የነበረ አዳምን ከነልጆቹ ወደ ቀደመ ክብራቸው መልሷቸዋልና ለግብሩ በሚስማማ ስም ጠርተውታል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፤ የሚያሳጣኝ የለም፡፡ በለመለመ መስክ፣ በዕረፍት ውኃ ያሰማራኛል፤›› እንዲል (መዝ.፳፪፥፩)፡፡

በብሉይ ኪዳን በነቢያቱ ላይ በማደርና በልዩ ልዩ መንገድ እየተገለጠ ሕዝቡን በረድኤት ሲጠብቅ የነበረው እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹ኖላዊሆሙ ለእስራኤል አጽምእ ዘይርዕዮሙ ከመ አባግዐ ዮሴፍ ዘይነብር ላዕለ ኪሩቤል አስተርአየ፤ ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ ተገለጥ፤›› (መዝ.፸፱፥፩) የሚለውን የነቢያቱን ልመና ሰምቶ በሐዲስ ኪዳን ራሱን ለሞት አሳልፎ በመስጠት እኛን በጎቹን ከሞት አድኖ እውነተኛ ቸር ጠባቂአችን መኾኑን አረጋግጦልናል፡፡ እርሱም፡- ‹‹አነ ውእቱ ኖላዊ ኄር ወኖላዊሰ ኄር ይሜጡ ነፍሶ ቤዛ አባግዓሁ፣ ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ ቸር ጠባቂ ስለበጎቹ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል›› በማለት እውነተኛ ቸር ጠባቂአችን መኾኑን ነግሮናል (ዮሐ.፲፥፲፩)፡፡ የነቢያትን ትንቢት፣ የክርስቶስን ትምህርት የተቀበሉት ቅዱሳን ሐዋርያትም ጌታችንን ‹‹ቸር ጠባቂ፣ የእረኞች አለቃ›› ብለውታል፡፡ ‹‹እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፤ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል፤›› እንዲል (ዕብ.፲፫፥፳፤ ጴጥ.፪፥፳፭)፡፡

፮. መድኃኒት

በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹የእስራኤል መድኀኒት›› እየተባለ ይጠራ ነበር (መዝ.፵፫፥፯፤ ኢሳ.፵፫፥፲፩፤ ፵፭፥፳፩)፡፡ በእግዚአብሔር ኀይል እየተመሩ ሕዝበ እስራኤልን ከጠላት ይታደጉ የነበሩ መሳፍንትም ‹‹መድኀኒት›› ተብለው ተጠርተዋል፡፡ በዘመናቸው ሕዝቡን ከጠላት ይታደጉ የነበሩ እነዚያ መሳፍንትና ነገሥታት የአማናዊው መድኀኒት የክርስቶስ ምሳሌዎች ነበሩ፡፡ የብሉይ ኪዳን መሳፍንትና ነገሥታት መድኀኒትነታቸው ለአንድ ወገን ብቻ፣ ይኸውም ከሥጋዊ ጠላት ብቻ ማዳን ነበር፤ በመሳፍንቱና በነገሥታቱ ምሳሌነት፣ በነቢያት ትንቢት የተገለጸው አማናዊው መድኀኒት ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ዓለምን ከዘለዓለም ሞት አድኗል፡፡ ስለዚህም ‹‹መድኀኒታችን›› እንለዋለን (ዮሐ.፬፥፵፪)፡፡

የነቢያት ትንቢት መነሻም መድረሻም መድኀኒት ክርስቶስ እንደሚወለድና ዓለምን እንደሚያድን መናገር ነውና ጌታችን የታመመውን ዓለም በሽታ ለማራቅና ከደዌው ለመፈወስ የመጣ መድኀኒተ ዓለም መኾኑን መስክረዋል፡፡ ‹‹ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ ትንቢት የተናገሩ ነቢያት ስለዚህ መዳን ተግተው እየፈለጉ መረመሩት›› እንዳለ ቅዱስ ጴጥሮስ (፩ኛጴጥ.፩፥፲)፡፡ ጌታችንም ‹‹ሕመምተኞች እንጂ ጤናሞች ባለመድኃኒት አያስፈልጋቸውም፤›› (ማቴ.፱፥፲፪) በማለት መድኀኒቱም ባለመድኃኒቱም እርሱ መኾኑን ተናግሯል፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ደግሞ ‹‹ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኀኒት፣ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የኾነ ተወልዶላችኋል፤›› በማለት ክርስቶስ መድኀኒት መኾኑን ሲመሰክር (ሉቃ. ፪፥፲፩)፣ ሳምራውያን ምእመናንንም ‹‹እርሱ ክርስቶስ የዓለም መድኀኒት እንደ ኾነ እናውቃለን›› ሲሉ በክርስቶስ መድኀኒትነት ማመናቸውን ተናግረዋል (ዮሐ.፬፥፵፪)፡፡

በአጠቃላይ የነገረ ድኅነት መነሻው፣ ለቅዱሳን ሐዋርያት ስብከትም መሠረቱ የነቢያት ትንቢት ነው፡፡ ሐዲስ ኪዳንን የብሉይ ኪዳን ነቢያት በትንቢታቸው አስቀድመው አዘጋጁት፤ ሐዋርያት ደግሞ ለበሱት፤ ተጐናጸፉት፡፡ ነገረ ድኅነትን ባዘለ ምሥጢር ‹‹ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና ባሪያህን አሰናብተኝ›› እያሉ እነስምዖን የመሰከሩለት፤ ሐዋርያት በስሙ ወንጌልን የሰበኩለት መድኀኒታችን ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ ለደዌ ሥጋ ለደዌ ነፍስ ፈውስን በማደሉ፣ እንደዚሁም የዘለዓለም ሕይወትን ለሰው ልጆች በመስጠቱ ነቢያቱ ‹‹መድኃኒት›› ብለውታል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም የወገኖቿን መዳን ለራሷ አድርጋ ‹‹መንፈሴም በአምላኬና በመድኀኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤›› በማለት ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም መድኀኒት መኾኑን መስክራለች (ሉቃ.፩፥፵፯)፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የነቢያትና የሐዋርያት በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡