ትንሣኤ /ለሕፃናት/

ሚያዝያ 6/2004 ዓ.ም.

በልያ አበበ

ልጆች መግደላዊት ማርያምን ታውቋታላችሁ? መግደላዊት ማርያም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፈወሳቸው ሕመምተኛ የነበሩ ሰዎች አንዷ ናት፡፡ ከነበረባት በሽታ ከዳነች ጊዜ ጀምሮ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያስተምረውን ትምህርት በሙሉ የምትከታተል እና እርሱንም የምታገለግል ነበረች፡፡
መግደላዊት ማርያም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁድ እጅ ተገርፎ ሲሰቀል ከሌሎች ከገሊላ ከመጡ ብዙ ሴቶች ጋር ሆና በጣም አዝና በሩቅ ስትመለከት ነበር፡፡
ዮሴፍና ኒቆዲሞስ የተባሉት እግዚአብሔር የባረካቸው ደጋግ ሰዎች የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ ከጲላጦስ ተቀብለው እያመሰገኑ በንጹሕ በፍታ ወይም የመግነዝ ጨርቅ ሲከፍኑት፤ በአዲስ መቃብርም አኑረው የመቃብሩን ደጃፍ ሲዘጉ መግደላዊት ማርያም በመቃብሩ አንጻር ተቀምጣ ትመለከት ነበር፡፡
አይሁድ የጌታችን መቃብርን እንዲጠብቁ ጠባቂ ወታደሮችን አዝዘው ነበር፡፡ መግደላዊት ማርያም እሑድ ዕለት በጠዋት የጌታችንን ቅዱስ ሥጋ ለመቀባት ያዘጋጀችውን ሽቱ ይዛ ሌሎቹንም ሴቶች አስከትላ ወደ መቃብሩ ወጣች፡፡ ወደመቃብሩ ስትደርስ የመቃብሩ ድንጋይ ተንከባሎ ነበር፡፡ በድንጋጤ ወደ ውስጥ ስትገባም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ አላገኘችውም፡፡ የጌታችንን ሥጋ ማን እንደወሰደው ልታውቅ አልቻለችም፡፡
እየሮጠችም ወደ ሐዋርያት መጥታ “ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም” አለቻቸው፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስ ይህን በሰሙ ጊዜ ወጥተው ወደ መቃብሩ ሮጡ፡፡ ወደ መቃብሩ ውስጥ ሲመለከቱም የተከፈነበትን ጨርቅ ብቻ ተመለከቱ፡፡ ስለዚህም ወደ ቤታቸው ተመለሱ፡፡ መግደላዊት ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ ውጭ ቆማ ቆየች፡፡ ድንገት ወደ መቃብሩ ዝቅ ብላ ብትመለከት ሁለት መላእክት የጌታችን ሥጋ በነበረበት ቦታ ላይ ተቀምጠው አየች፡፡
እነርሱም ለምን እንደምታለቅስ ጠየቋት፡፡ እርስዋም “ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም” አለቻቸው፡፡ ይህንንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል አንድ ሰው ቆሞ አየች፡፡ የአትክልት ቦታው ጠባቂ መስሏት፡፡ ሰውየው “ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ?” አላት እርሷም የጌታዬን ሥጋ አንተ ወስደኸው ከሆነ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ” አለችው፡፡
ልጆች ያነጋግራት የነበረው ሰው ግን የአትክልት ቦታ ጠባቂው አልነበረም፡፡ ማን እንደሆነ አወቃችሁ? አዎ፡፡ የሚወደን ስለ እኛ የሞተልን ከሙታንም መካከል ተለይቶ በሦስተኛው ቀን የተነሣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ በመጨረሻም በስሟ ማርያም ብሎ ሲጠራት አወቀችው፡፡ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ ለሐዋርያት በሙሉ እንድትነግር ላካት፡፡ እርሷም በደስታ ወደ ሐዋርያት ተመልሳ ነገረቻቸው፡፡ ልጆች ጌታችን ከሙታን ከተነሣ በኋላ በመጀመሪያ ያየችው መግደላዊት ማርያም ነበረች፡፡
ልጆች በጌታችን ትንሣኤ ደስ አልተሰኛችሁም? ክርስቲያኖች በሙሉ በትንሣኤ በዓል በደስታ እንዘምራለን አምላካችንን እናመሰግናለን፡፡ መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንላችሁ፡፡
ልጆች ይህን ታሪክ የምታገኙት ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20 ቁጥር 1 ላይ ነው፡፡