ብዙ ከተሰጠው ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል

ሐምሌ 4 ቀን 2005 ዓ.ም.

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት አህጉረ ስብከት ሁሉ ለየት የሚልበት ባሕርያት አሉት፡፡ ሀገረ ስብከቱ የሀገሪቱ ዋና ከተማ እንደመሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ከሁሉም አህጉረ ስብከት የሚመጡ ክርስቲያኖች አገልግሎት የሚያገኙባቸው ገዳማትና አድባራት ያሉበት ሀገረ ስብከት ነው፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ የተለያዩ ባህሎች ያሏቸው የቤተ ክርስቲያን ቤተሰቦች ተገናኝተው በአንድነት መንፈስ አገልግሎት የሚያገኙበትና የሚቀበሉበት ሀገረ ስብከትም ነው፡፡

ሀገረ ስብከቱ በርካታ የቤተ ክርስቲያናችን መምህራን ሊቃውንት የሚገኙበትም ሀገረ ስብከት ነው፡፡ በመንፈሳዊው ትምህርት ብቻ ሳይሆን በዓለሙ የሚሰጠውን ማኅበራዊና የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የሙያና የቀለም ትምህርቶች የተማሩ አንቱ የተባሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችም የሚገኙበት ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን በታላቅ ፍቅር የሚጠብቃት፣ አገልግሎቷን ዕለት ዕለት የሚሻ ቸርና የዋህ ሕዝበ ክርስቲያን ያለበት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያን የምትተዳደርበትን ብዙ የገንዘብ የቁሳቁስና የሰው ኃይል ሀብት ይዞ የሚገኝ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አርአያነት ያለው አግልግሎትን ሊሰጥም እንደሚችል የሚታሰብ ነው፡፡

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሀገረ ስብከቱን ልዩ የሚያደርጉ ባሕርያቱ፤ ሀገረ ስብከቱ ያሉትን ብዙ ሀብቶች የሚያሳይ ነው፡፡ ብዙ ካለው ደግሞ ብዙ ይፈለግበታል የሚለው መጽሐፋዊ ቃል ከሀገረ ስብከቱ የምንሻውን ነገር በተሰጠው ልክ እንድንጠብቅ ያስገድዳል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በነገር ሁሉ ለሌሎች አህጉረ ስብከት የሚኖረውን አርአያነት፡፡

ሀገረ ስብከቱ ብዙ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ እንደመሆኑ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሌሎች አህጉረ ስብከት ምሳሌ የሚሆን የገንዘብ አስተዳደርና አጠቃቀም ሥርዓት ሊኖረው ይገባል፡፡ ብዙ የገንዘብ አስተዳደር ሊቃውንት የሆኑ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ባለሙያዎች ያሉበት ሀገረ ስብከት በመሆኑ ቀጥሮ በማሠራትም ይሁን የነጻ አገልግሎት ሥርዓት በመዘርጋት አሠራሩን ዘመናዊ፣ ግልጽነት ያለው፣ ተጠያቂነት ያለበት፣ ለሙስና በር የማይከፍት ማድረግ ይቻለዋል፡፡ በአጠቃቀም ረገድም በግልጽነት በተሠራ ዕቅድና የዕቅድ አፈጻጸም ሥርዓት፣ አጠቃላይ አገልግሎቱን ባገናዘበ ሁኔታ፣ አሳማኝ በሆነ መንገድ ሊተገበር ይገባዋል፡፡ የንብረት አስተዳደሩም በተመሳሳይ መቃኘት ይገባዋል፡፡

ሀገረ ስብከቱ ያሉት ቅርሶች አያያዝና ጥበቃ ጉዳይም እንዲሁ መሻሻል ያለበትና በተሻለ አያያዙም ለሌሎች በቅርስ ሀብታቸው ለበለጸጉ አህጉረ ስብከት ምሳሌ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ ያለውን ለአገልግሎት የሚያስፈልግ የሰው ኃይልም ወጥ በሆነ ሥርዓት መምራት አለበት፡፡ አድባራትና ገዳማት ከልክ በታች ወይም ከልክ በላይ መያዝ አለመያዛቸውን፣ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን ሙያ ይዘው መገኘት አለመገኘታቸውን፣ ተገቢ እና ወጥነት ባለው የቅጥርና የዝውውር ሥርዓት እየተመራ መሆኑን፣ ከዚያ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሙስናና የአድልዎ አሠራሮች መኖር አለመኖራቸውን መመርመርና ማረጋገጥ ሀገረስብከቱ ወደፊት በአሠራር የለውጥ ሂደቱ ውስጥ ሊመረምራቸው የሚገቡ ነጥቦች ናቸው፡፡ በሀሜት ደረጃ የሚነሡትን የጎጠኝነት፣ የጎሰኝነት እና የቤተሰባዊ አሠራሮች መኖር አለመኖራቸውን መመርመር እንዳይከሠቱም የሚያደርግ ግልጽነት ያለው አሠራር ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡

ሀገረ ስብከቱ አርአያ ሊሆን የሚገባው በውስጥ አስተዳደራዊ ሥርዓቱ ብቻ አይደለም በስብከተ ወንጌልና በሌሎችም መንፈሳዊ አገልግሎቶችም ጭምር መሆን አለበት፡፡ በርካታ ሰባክያነ ወንጌልን ማሠልጠን፣ ማፍራት ጊዜው የሚጠይቀውን የትምህርትና ሥልጠና ዘዴዎች ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ በቂና ብቁ አገልጋይ ካህናትን ማፍራት አለበት፤ ወይም ያሉትን በዚያ ደረጃ ማድረስ ይገባዋል፡፡ በዚህም ላይ ተመሥርቶ ለሃይማኖት ቤተሰቦች ለእንግዶችና መጻተኞች ተፈላጊውን የምስጢራት አገልግሎት ሊሰጥ፣ አርኪ የስብከተ ወንጌል ዐውድማ ሊሆን ይገባል፡፡ ሌሎች አህጉረ ስብከቶችንም ተንቀሳቅሰው የሚያስተምሩ የሚመክሩ ሊቃውንትን ማፍራት አለበት፡፡ ዘመናዊ የሆኑ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ይጠበቅበታል፡፡ በቂ የሚዲያ አውታሮች ያስፈልጉታል፡፡ በርካታ የብቃት ማእከሎችን ሊገነባ ይፈለግበታል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱ መንፈሳዊ አገልግሎቶች በተጓዳኝ የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ለሕዝበ ክርስቲያኑም ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ ሲያደርግ መታየት አለበት፡፡ ቢያንስ ትምህርት ቤቶችንና የሕክምና ማእከላትን ከዚህ በፊት የነበሩ መልካም ጅምሮችን መነሻ አድርጎ በዓይነት፣ በቁጥርና በጥራት ማሳደግና ማስፋፋት ከዚህ ሀገረ ስብከት በእጅጉ ይጠበቃል፡፡  

ይህ ሁሉ እንዲሆን ግን ሀገረ ስብከቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶችና የአሠራር ሥርዓቱን በመላና ግምት ሳይሆን በጥናት አስደግፎ በምክክርና አሳማኝ በሆኑ አካሔዶች እንዲመራ ይጠበቅበታል፡፡ ማኅበረ ካህናቱ እርስ በእርስ የሚኖራቸው ግንኙነት ከምእመናን ጋር የሚኖራቸው ትስስር በየጊዜው ሊያድግ ሊሻሻል ይገባል፡፡ ምእመናን በሰበካ ጉባኤያት ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግና ቤተክርስቲያናቸውን በቅርበት የሚያገለግሉበት በቤተክርስቲያናቸው አሠራር ውስጥ አስተያየት እንዲሰጡ እንዲወስኑም ሆነው ሊታቀፉ ይገባል፡፡ በሀገረ ስብከቱ የሚገኙ ገዳማትና አድባራት ከሚታሙበት የሙስናና አድሏዊ አሠራር መጽዳት አለባቸው፡፡ አገልጋይ ካህናቱ በትምህርተ ወንጌልና በተለያዩ ዘርፈ ብዙ ሙያዎች ሊታነጹ ይገባል፡፡ ሕግ የጸናበት ሥርዓት የሚከበርበት ሀገረስብከት መሆን አለበት፡፡

ሀገረ ስብከቱ የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድ አሁን የጀመራቸው ጥረቶች የሚበረታቱ ናቸው፡፡ ከላይ እንደጠቀስነው በጥናትና በጥንቃቄ ለመፈጸም ጥረት የሚደረግ ከሆነ ውጤት እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው ሁሉ ማለትም የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ ማኅበረ ካህናቱ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ምእመናን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቤተሰብ የሆኑ ሁሉ አገልግሎት ማግኛ የሆነው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በሚፈለገው አርኪ የአገልግሎት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የየድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትም ሀገረስብከቱ የሚሻውን አስፈላጊ ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት ለመግለጽ ይወዳሉ፡፡

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር 

 

  • ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት 21ኛ ዓመት ቁጥር 2 ሰኔ 2005 ዓ.ም.