የ፳፻፱ ዓ.ም ርክበ ካህናትን አስመልክቶ ከቅዱስ ፓትርያርኩ የተበረከተ ቃለ ምዕዳን  

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

‹‹ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ ወኵሎ መራዕየ ዘሀሎ ኀቤክሙ፤ አሁንም ራሳችሁንና በእናንተ ሥር ያለውን መንጋ ዅሉ ጠብቁ፤›› (ሐዋ. ፳፥፳፰)፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

መዋዕለ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞና ከበዓለ ትንሣኤው አድርሶ፣ እንደዚሁም ዅላችንን ከየሀገረ ስብከታችን አሰባስቦ በዚህ ዓመታዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በአንድነት ስለሰበሰበን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይኹን፤ እናንተም እንኳን በደኅና መጣችሁ!

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ከላይ የተጠቀሰው ኃይለ ቃል የመንጋው እረኞች የኾን ዅሉ በቃለ እግዚአብሔር ጐልብተን፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተቃኝተን ራሳችንንና ምእመናንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን የሚያመለክት የእግዚአብሔር ታላቅ የጥሪ ቃል ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትና ቀደምት ቅዱሳን አበው የሥልጣነ ክህነትና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የኾነው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ በቋሚነትና በመደበኛነት እንደዚሁም ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አስፈላጊ ኾኖ በተገኘ ጊዜ ዅሉ እየተሰበሰበ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ እንዲገመግም፣ እንዲያጠና እና መፍትሔ እንዲሰጥ መደንጋጋቸው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡

የጉባኤው መሠረታዊ ዓላማ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስቀድሞ እንደ ተናገረው ከመጀመርያ አንሥቶ ልዩ ልዩ ፈተና ተለይቶአት የማያውቅ ቤተ ክርስቲያን በመከራው ጽናት ተሰቃ ወይም ተስፋ ቈርጣ ዓላማዋን እንዳትስት እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ሊዘልቅ የሚችል ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ ለማድረግ እንዲቻል ነው፡፡

ይህም በመኾኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማካይነት ነገራተ ቤተ ክርስቲያንን በጥልቀትና በአስተዋይነት እየተረጐመች፣ እንደዚሁም መንፈስ ቅዱስን መሪ በማድረግና አስፈላጊው መሥዋዕትነትን በመክፈል ከውጭና ከውስጥ የሚሰነዘሩባትን ጥቃቶችን እየተቋቋመች እነሆ በአሸናፊነት ከዘመናችን ደርሳለች፡፡ ይህም ሊኾን የቻለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተቃኙ ቅዱሳን አበው በፈጸሙት ተጋደሎና ወደር የለሽ መሥዋዕትነት እንደ ኾነ አይዘነጋም፡፡

የመንፈሳዊ ጥበቃና ክትትል ተግባር በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ ቀኖና መሠረት በቤተሰብ ደረጃ በነፍስ ወከፍ ጠባቂ ካህን ወይም የነፍስ አባት እንዲኖር የተደረገበት ዐቢይ ምክንያትም የጥበቃውንና የክትትሉን ተግባር አስተማማኝና ዘላቂ ለማድረግ ነው፡፡ የተግባሩ መነሻም የጌታችን ትምህርትና ትእዛዝ ነው፡፡

እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ሕፃኑንም ወጣቱንም፣ ጐልማሳውንና ሽማግሌውንም አንድ አድርገን እንድንጠብቅና እንድናሰማራ ጌታችን በባሕረ ጥብርያዶስ ‹‹ግልገሎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን ጠብቅ፤ በጎቼን ጠብቅ፤›› በማለት ለቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት አዞናል (ዮሐ. ፳፩፥፲፭-፲፯)፡፡ እኛም ትእዛዙንና ሓላፊነቱንም ወደንና ፈቅደን ተቀብለናል፡፡

ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን የሚካሔደውና ረክበ ካህናት ተብሎ የሚታወቀው፣ በዛሬው ዕለት የምንጀምረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም መሠረቱ ይህ የባሕረ ጥብርያዶስ የጥበቃ ትእዛዝና ትምህርት እንደ ኾነ ይታወቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያን ዐቢይ እና ዋና ተልእኮም ዐቂበ ምእመናን እንደ ኾነ በቅዱስ ወንጌል በተደጋጋሚ ተጽፏል፡፡ በመኾኑም ቅዱሳን ሐዋርያትም ኾኑ ቅዱሳን አበው ዋነኛ ተግባራቸው ምእመናንን ማስተማር፣ ማሳመን፣ ማጥመቅ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ማደል፣ ከዚያም ምእመናንን በዕለተ ተዕለት ኑሮአቸው መጠበቅና ክትትል ማድረግ ነበር፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ሐዋርያዊት፣ ህልወተ ኵሉ ወይም በዅሉም ያለች፣ አንዲትና ቅድስት የኾነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የሁለት ሺሕ ዘመናት ጉዞዋ አንድነቷ ሳይናጋ፣ ሐዋርያዊ ተልእኮዋ ሳይቋረጥ ለዘመናት የዘለቀችው ካህናት በነፍስ አባትነት እያንዳንዱን ቤተሰብ በመጠበቃቸው፣ በማስተማራቸውና በመከታተላቸው ነው፡፡ ዛሬም ቢኾን እየተስፋፋ ለመጣው የምእመናን ቅሰጣ ዋና መከላከያው የነፍስ አባትን ተልእኮ ማእከል ያደረገ በቤተሰብ ውስጥ የነፍስ ወከፍ ጠበቃ ሲጠናከር ብቻ እንደ ኾነ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

ይህንን የግብረ ኖሎት ሥራ በተፈለገው መጠን ግቡን እንዲመታ በየሀገረ ስብከቱ የካህናት ማሠልጠኛ በማቋቋም፣ ዘመኑን ያገናዘበና በቀላሉ ወደ ተግባር የሚያሸጋግር የሥልጠና መርሐ ግብር በመንደፍ ካህናቱን ከዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ፣ አስተማማኝ ጥበቃ ማረጋገጥ ይኖርብናል፤ ይህንን ተግባር ለማፋጠን የሊቃነ ጳጳሳት ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በከፊል

እንደ እውነቱ ከኾነ ዛሬም ለሃይማኖቱ ተቆርቋሪ የኾነ፣ ለእምነቱ አድርግ የተባለውን የሚያደርግ ሕዝብ እግዚአብሔር አልነሣንም፤ በእኛ በኩል ግን የሚቀር ብዙ ሥራ እንዳለ አይካድም፡፡ ከዚህ አንጻር እተየፈታተነን ያለውን የቅን አገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ክፍተት በፍጥነት አስተካክለን ወደ ሕዝቡ የጥበቃ ተግባር መሠማራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መኾኑን ማስተዋል አለብን፡፡

አሁን ባለው የጥበቃና የክትትል ክፍተት ቍጥር በርከት ያለ ወጣት እየኮበለለ እንደ ኾነ ማወቅ አለብን፤ አለሁ የሚለው ወጣትም ቢኾን ኦርቶዶክሳዊ መርሕና ቀኖናን በቅጡ ባለማወቁ ሲደናገርና የተቃራኒ አካላት ባህልና ሥርዓትን ሲደበላልቅ ይታያል፡፡ ይህ ዅሉ ሊኾን የቻለው ጌታችን እንዳስተማረንና እንዳዘዘን ከግልገልነት ዕድሜ ጀምረን ወጣቱን ባለመጠበቃችንና ባለመከታተላችን እንደ ኾነ ሊሠመርበት ይገባል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ስኖዶስ አባላት

በቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሰጪነትና የበላይ ተቆጣጣሪነት የሚመራው የግብረ ኖሎት ጥበቃ የምእመናንን ዅለንተናዊ ሕይወት የሚያካልል ሊኾን ይገባል፡፡ ምእመናን ለሃይማኖታቸው የሚታመኑ፤ ለአገራቸው ዕድገትና ልማት የሚቆረቆሩ፤ በአንድነት፣ በስምምነትና በፍቅር የመኖር ጥቅምን የሚገነዘቡ፤ በማንነታቸውና በባህላቸው፣ በታሪካቸውና በእምነታቸው የሚኮሩ በአጠቃላይ የተስተካከለ መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ሰብእናን የተላበሱ እንዲኾኑ በርትተን የማስተማር፣ የመጠበቅና የመከታተል ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ሓላፊነት አለብን፤ ይህም በታቀደ፣ በተደራጀ፣ በተጠናከረና ተከታታይነት ባለው የአፈጻጸም ሥልት ሊከናወን ይገባል፡፡

በመጨረሻም

በዚህ ዓመታዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የቀረቡትን አጀንዳዎች ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት በማስተዋልና ለቤተ ክርስቲያናችን በሚበጅ መልኩ በማጤን፣ እንደዚሁም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና መጠበቅ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሐዋርያዊ ግዳጁን እንዲወጣ እያሳሰብን የሁለት ሺህ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መጀመሩን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን!

 ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤

ግንቦት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም፤

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡፡