በጸሎተ ሐሙስ የሚፈጸም ሥርዓት

መጋቢት ፳፯ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በዚህ ዕለት ስግደቱ፣ ጸሎቱ፣ ምንባቡ እንደ ተለመደው ይከናወናል፡፡ መንበሩ (ታቦቱ) ጥቁር ልብስ ይለብሳል፡፡ ጸሎተ ዕጣን ይጸለያል፤ ቤተ ክርስቲያኑም በማዕጠንት ይታጠናል፡፡ ኅፅበተ እግር ይደረጋል፡፡ ቅዳሴ ይቀደሳል፡፡ በየቤቱ ደግሞ ጉልባን ይዘጋጃል፡፡

ኅፅበተ እግር

ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ዲያቆኑ ሁለት ኵስኵስቶችን ውኃ ሞልቶ ያቀርባል፤ አንዱ ለእግር፣ አንዱ ለእጅ መታጠቢያ፡፡ ‹ጸሎተ አኰቴት› በመባል የሚታወቀው የጸሎት ዓይነት ይጸለያል፡፡ ወንጌል ተነቦ ውኃው በካህኑ (በሊቀ ጳጳሱ) ይባረክና የኅፅበተ እግር ሥርዓት ይከናወናል፡፡ ይኸውም ጌታችን የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠብ ያሳየውን የተግባር ትምህርት ለማሳየት ነው (ዮሐ. ፲፫፥፲፬)፡፡ ከውኃው በተጨማሪ የወይራና የወይን ቅጠልንም ለሥርዓተ ኅፅበቱ ማስፈጸሚያነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ ምሥጢሩም የሚከተለው ነው፤

ወይራ ጸኑዕ ነው፡፡ ይህም ክርስቶስም ጽኑዕ መከራ መቀበሉን ከማስረዳቱ ባሻገር እኛም (እግራችንን የሚያጥቡን አባቶች እና የምንታጠበው ምእመናን) መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ሥርዓተ ኅፅበቱን በወይራ እንፈጽማለን፡፡ የወይኑ ቅጠልም መድኃኒታችን ክርስቶስ በወይን የተመሰለ ደሙን አፍስሶ ለምእመናን የሕይወት መጠጥ አድርጎ መስጠቱን ለማዘከር በወይን ሥርዓተ ኅፅበትን እናከናውናለን (ማቴ. ፳፮፥፳፮)፡፡ በቀኝና በግራ የቆሙ ሊቃውንትም ‹‹ሐዋርያቲሁ ከበበ እግረ አርዳኢሁ ኀፀበ›› እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ይህ ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኋላ ምእመናን ሥርዓተ ቅዳሴው ተከናውኖ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡

 ቅዳሴ

የጸሎተ ሐሙስ ቅዳሴ የሚከናወነው በተመጠነ ድምፅ ሲኾን፣ እንደ ደወል (ቃጭል) የምንጠቀመውም ጸናጽልን ነው፡፡ ልዑካኑ የድምፅ ማጉያ ሳይጠቀሙ በለኆሣሥ (በቀስታ) ይቀድሳሉ፡፡ ምክንያቱም ይሁዳ በምሥጢር ጌታችንን ማስያዙን ለማመልከት ሲኾን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የዘመነ ብሉይ ጸሎት ዋጋው ምድራዊ እንደ ነበር ለማስታወስ ነው፡፡ በመቀጠል ክብር ይእቲ፣ ዕጣነ ሞገር፣ ዝማሬ የተባሉ የድጓ ክፍሎች ተዘምረው አገልግሎቱ ይጠናቀቃል፡፡ ሕዝቡም ያለ ኑዛዜና ቡራኬ ይሰናበታሉ፡፡

ጉልባን

ጉልባን ከባቄላ ክክ፣ ከስንዴ ወይንም ከተፈተገ ገብስ ጋር አንድ ላይ ተቀቅሎ የሚዘጋጅና የጸሎተ ሐሙስ ዕለት የሚበላ ንፍሮ ነው፡፡ በጸሎተ ሐሙስ በቤት ውስጥ ከሚፈጸሙ ተግባራት አንዱ ጉልባን ማዘጋጀት ነው፡፡ ጉልባን እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ሲወጡ በችኮላ መጓዛቸውን የምናስታውስበት ከእስራኤላውያን የመጣ ትውፊታዊ ሥርዓት ነው፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ አብዛኞቹ የትውፊት ክንዋኔዎች የብሉይ ኪዳን መነሻ ስላላቸው ይህ ሥርዓት ዛሬም በኢትዮጵያውያን ምእመናን ዘንድ ይከበራል፡፡

ጉልባን እስራኤላውያን ከባርነት በወጡ ጊዜ አቡክተው፣ ጋግረው መብላት አለመቻላቸውን ያስታውሰናል፡፡ በወቅቱ ያልቦካውን ሊጥ እየጋገሩ ቂጣ መመገብ፤ ንፍሮ ቀቅለው ስንቅ መያዝ የመንገድ ተግባራቸው ነበርና፡፡ ይህን ታሪክ ለማሰብም በሰሙነ ሕማማት በተለይም በጸሎተ ሐሙስ ቂጣና ጉልባን ይዘጋጃል፡፡ በጸሎተ ሐሙስ የሚዘጋጀው ጉልባንና ቂጣ ጨው በዛ ተደርጎ ይጨመርበታል፡፡ ይኸውም ጨው ውኃ እንደሚያስጠማ ዅሉ፣ ጌታችንም በመከራው ወቅት ውኃ መጠማቱን ለማስታወስ ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡