በጎቹና ፍየሎቹ

የ”እናስተውል” 1ኛና መለሰተኛ 2ኛ ደረጃ የሕዝብ ትምህርት ቤት ለስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የተዘጋጀ የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት የአማርኛ ትምህርት ፈተና
በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
 

ለፈተናው የተሰጠ ሰዓት ፡- 0፡05    
የተማሪው ሙሉ ስም:_________________ ቁጥር:______                            

   

የሚከተለውን ምንባብ በጥንቃቄ አንብቡ
በጎቹና ፍየሎቹ
 
ከዕለታት በአንዱ ቀን በአንድ ሀገር ትልቅ የበጎች በረት ነበረ፡፡ በዚህ የበጎች በረት ውስጥ ብዙ በጎች ይኖሩ ነበር፡፡ ይህ የበጎች በረት ለረዥም ዓመት የቆየ እና ብዙ ታሪክ ያለው በረት ሲሆን በጎቹ ሁሉ ግን የሚኖሩበትን በረት ጥንታዊነት እና ታሪክ በሚገባ የሚያውቁ አይደሉም፡፡ በቅርብ ጊዜ ከሚወለዱት በጎች መካከል ለመስማት ፈቃደኞች ያልሆኑ አሉ እንጂ በረቱን እስከ ዛሬ ድረስ ጠብቆ ለማቆየት ብዙ በጎች ከሚያገሳ አንበሳ ጋር ጭምር ተታግለው ብዙ ድል አድርገዋል፡፡ ብዙ በጎችም ለዚሁ በረት መቆየት ሲሉ አንገታቸውን እስከመስጠት ድረስ ደርሰው ነበር፡፡ ከአሁኑ በጎች ውስጥ ግን አንዳንዶቹ እንኳን ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገው ሊሰጡ የቀድሞዎቹ በጎች የፈጸሙትን ገድል እንኳን ለማመን ይከብዳቸዋል ፤ ለመስማትም ይሰለቻሉ፡፡
   
በዚህ በረት ውስጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አንድ ችግር ተፈጥሯል፡፡ የችግሩ መነሻ አንዳንድ ፍየሎች በጎች መስለው ከመንጋው መቀላቀላቸው ነው፡፡ እነዚህ ፍየሎች ምንም እንኳን ሥራቸው ፣ ድምፃቸው ፣ አኗኗራቸው ሁሉ ፍየል መሆናቸውን የሚመሰክር ቢሆንም ከበጎቹ በረት ረዥም ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው ብዙ በጎችን ግራ ያጋባ ነው፡፡ አንዳንዶቹ አስተዋይና የበግን ጠባይ ከፍየል ለይተው የሚያውቁ በጎች ‹‹ኸረ እነዚህ ፍየሎች ናቸው ፣ ድምፃቸው ፣ አነጋገራቸውና አኗኗራቸው ያስታውቃል!›› እያሉ ሲሟገቱ ከጥቂቶች በቀር የሚሰማቸው አላገኙም፡፡
 
አንዳንዶቹ በጎች ‹‹ምን ችግር አለው ፤ አነጋገራቸው እንደ በግ ባይሆንስ? እስከ መቼ እንደ በግ ብቻ እንናገራለን!›› እያሉ ከመቃወማቸውም በላይ በግ የመሰሉትን ፍየሎች ለመምሰል እነርሱም የፍየሎችን አኗኗር ለመኮረጅ ሞከሩ፡፡ የሚያሳዝነው ግን እውነተኛዎቹ በጎች በግ በመሆናቸው ፍየሎቹን ለመምሰል ያደረጉት ጥረት አልተሳካላቸውም፡፡ ሌሎቹ የዋሃን በጎች ደግሞ ምን ችግር አለው? ‹‹የምንመገበው አንድ ዓይነት ምግብ እስከሆነ ድረስ አንድ እኮ ነን!›› ብለው መከራከር ጀመሩ፡፡ ‹‹ኸረ ከመቼ ወዲህ ነው ፍየሎች አንድ የሆንነው?›› ብለው የተቃወሙ በጎች ደግሞ በእነዚህ በፍየሎች በተታለሉ በጎች ጥርስ ውስጥ ገቡ ‹‹አክራሪ ፣ ጽንፈኛና ወግ አጥባቂ በጎች››  የሚል ስያሜም ወጣላቸው፡፡
 
ይህንን ትርምስ አስቀድሞም ይፈልጉት የነበሩት በግ መሳይ ፍየሎችም ጉዳዩን ማራገብ ጀመሩ፡፡ ‹‹እኛ ለበረታችን ያልሆነው ነገር የለም ፤ እኛ ታማኝ በጎች ነን ፤ ይህቺ በረት ድሮ እንዲህ እንዲህ ነበረች›› ብለው የበረቲቱ መብት ተቆርቋሪዎች ሆኑ፡፡ ይባስ ብለው ድሮ በረቷ የፍየሎች መንጋ እንደነበረች ፣ የምትተዳደረውም በፍየሎች ሕግ እንደነበረ ፤ ከጥቂት ምዕተ ዓመታት ወዲህ በተነሡ በጎች በረቲቱ እንደተበላሸች መወትወት ጀመሩ፡፡ ምንም የማያውቁት በጎች ደነገጡ፡፡ ‹‹ወይኔ በረታችን! ለካ በችግር ላይ ነሽ?›› ብለው በረቲቱን የፍየል በረት ለማድረግ ቆርጠው ተነሡ፡፡ ስለበግነት የሚያነሣን በግ ባገኙት መንገድ ማንቋሸሽም ጀመሩ፡፡
በዚህ መካከል ሌላ ክስተት ተፈጠረ ፤ አንዳንድ ከበጎች ጋር ተቀላቅለው የነበሩ ፍየሎች በይፋ በረቱን ለቅቀው እንደወጡ ተሰማ፡፡ ከወጡ በኋላ ‹‹እውነቱን ተረድተን በግ ከመሆን ፍየል መሆን ይሻላል ብለን ተፀፅተናል ፤ ይህንን እውነት ካወቅን ትንሽ ቆይተናል›› ብለው በአደባባይ ተንሰቅስቀው አለቀሱ፡፡ ሁሉን አይተነዋል ፤ ከእኛ ወዲያ በግነት ለኀሣር አሉ፡፡ በረቱ ውስጥም እያሉ ወሳኝ በጎች እንደነበሩና የበረቱን ጓዳ ጠንቅቀው የሚያውቁ ሊቃውንት እንደሆኑም በዘዴ ጠቆሙ፡፡ አንዳንዶቹም ‹‹የበረቱ ጓዳ›› የሚል መጽሐፍ አዘጋጅተው በተኑ፡፡ ተረባርበው የገዙት በጎቹ ሲሆኑ መልስ ከመስጠት ይልቅ ብዙዎቹ በጎች ተሸማቅቀው ‹‹ጉድ ፣ ጉድ ለካ ይሄ ሁሉ ጉድ አለ?›› ብለው ተንሾካሾኩ፡፡
በዚህ ጊዜ በጎች አሁንም ለሁለት ተከፈሉ፡፡ አስቀድመው ሲቃወሙአቸው የነበሩት በጎች ብዙም ሳይደነቁ ‹‹ከመጀመሪያውስ መች በጎች ነበሩና ነው ፍየል ሆንን የሚሉት ፤ በጎች አለመሆናቸው ይታወቅ ዘንድ ከእኛ ዘንድ ወጡ ፤ በጎች ቢሆኑ ኖሮ ከእኛ ዘንድ ጸንተው በኖሩ ነበር፡፡›› ብለው አስረዱ፡፡ አንዳንድ የዋሃን በጎች ግን ‹‹በግ እገሌ ፍየል ከሆነማ ምን ተረፈን? እንደርሱ ያለ በግ ከየት ይገኛል? ፍየሎችን ያሳፈራቸው እርሱ አልነበረም እንዴ! አይ ይህቺ በረት ምን ቀራት ከእንግዲህ…›› እያሉ ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡ ‹‹ከእንግዲህ ትልቅ ነው ብዬ በግ አልከተልም!›› የሚሉም አልጠፉም ይህን ሲሰሙ አስተዋዮቹ በጎች ‹‹አስቀድሞስ በግ በእረኛ እንጂ በግ በበግ ሲመራ የት አይታችኋል ፤ በሉ ይኼ ትምህርት ይሁናችሁ›› አሏቸው፡፡ከዚህ በተጨማሪ “በግ መስለው የሚኖሩ ፍየሎች አሉ” የሚለው የበጎች አቤቱታ አዝማሚያው ያሰጋቸው አንዳንድ በግ መሰል ፍየሎች የበጎችን ልቅሶ ቀምተው ‘ኧረ ፍየሎች በዙ!’ እያሉ ማስመሰል ጀመሩ።
 
ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ ደግሞ ትክክለኛው የበጎች በረት የት እንደሆነ ባለማወቅ በጎች ሆነው ሳለ ከፍየሎች መንጋ ጋር የሚንከራተቱ በጎች ጉዳይ ነው፡፡ ወደ ትክክለኛው በረት እንዳይመጡ በበጎቹ በረት አካባቢ የሚታየው ትርምስ የበጎች በረት መሆኑን ስለሸፈነባቸው ተቸገሩ ፣ የብዙዎቹ በጎች ሕይወት ደግሞ የበግ ስለማይመስል የበረቱን በጎ ምስል እንዳይታይ አድርጎታል፡፡ ከፍየል ሌላ የጅብ ፣ የዕባብ ፣ የውሻ ወዘተ ጠባይ የሚያሳዩ በጎች ቁጥር መብዛቱም እነዚህሰ የጠፉ በጎች እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆነባቸው፡፡ እረኛው ደግሞ ‹‹ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች ብዙ በጎች አሉኝ›› ብሏል፡፡ ከዚህ በረት ውስጥ ያሉ ፍየሎች እንዳሉ ሁሉ ከበረቱ ውጪ ያሉ በጎችም ብዙዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ የጠፉ በጎች በፍየሎች መካከል ቢሆኑም የበጎች በረት ነገር ሲነሣ ግን በቀላሉ የሚነኩ ፣ልባቸው በቶሎ የሚሰበር ፣ ዕንባ የሚቀድማቸው ናቸው፡፡ የእነዚህ በጎች ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ሆነ፡፡ ‹‹ኸረ ብዙ በጎች እየወጡ ነው!›› እያሉ የሚጮኹም አልታጡም፡፡ አንዳንድ በጎች ደግሞ ለበረቱ የተቆረቆሩ መስሎአቸው ‹‹ይውጡ ፤ ኖረውም አይጠቅሙም! ይላሉ›› እረኛው ግን በጎቹን በበረቱ ለመሰብሰብ ብዙ እንደተሰቃየ ታላላቅ በጎች ታሪክ ጠቅሰው ይናገራሉ፡፡
 
በዚህ ሁሉ መካከል በረቱ እየፈረሰ ነው፡፡ በጎችም እየኮበለሉ ነው፡፡ ፍየሎችም ሌት ተቀን በረቱን የፍየል መንጋ መስፈሪያ ለማድረግ እየተጉ ነው፡፡ ተስፋ የሚጣልባቸው በጎችም ግማሾቹ ወጣ ብለው ሣር ሲግጡ ውኃ ሲጠጡ ፣ ግማሾቹም በዋዛ በተራ እሰጥ አገባ ተጠምደው ፣ ግማሾቹ በፍየሎች ላለመጠመድ ሲሉ የበረቱን ነገር ወደ ጎን ተዉት፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እንኳን በረቱን ገብተው ሊታደጉ ሌሎች ትንሽ ሲፍጨረጨሩ ሲያዩ ‹‹አዬ የዚህ በረት ነገር በቀላሉ የሚፈታ እንዳይመስላችሁ… ለማንኛውም መፍጨርጨር ጥሩ ነው!›› ‹‹ይኼን ሠራን ብላችሁ ነው? ወይ አለመብሰል!›› ይሏቸው ጀመር፡፡ ነገር ግን በጎቹ ምንም ባያውቁ በበረቱ ማደጋቸው በራሱ ከመብሰል አልፎ ካልተጠቀሙበት ለማረርም የሚበቃ ጊዜ ነበር፡፡ ይሁንና የጥቂቶቹ በጎች ጥረት ውጤቱ ቶሎ እንዳይታይ ደግሞ ምንም እንኳን ፍየሎች ባይሆኑም እንደ በግ ግን መኖር ያቃታቸው ደካሞች በመሆናቸው አቅም አጠራቸው፡፡ በጎችም ሆነው ፍየሎችን እንዴት እናጥቃ በሚለው ጉዳይ መስማማት አቅቷቸው ሥራውን ሳይጀምሩ የጨረሱ ታካቾችም አሉ፡፡ አንዳንድ በጎች መፍትሔ ለማግኘት “ወደ አንበሳ ሔደን አቤት እንበል” ይላሉ። ሌሎች ብጎች ደግሞ ‘አንበሳ ብዙ አንበሳዊ ጉዳዮች አሉበት ደግሞም አንበሳ የሚፈርደው በጎችንና ፍየሎችን በእኩል ዓይን ተመልክቶ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።
 
የበረቱ ችግር እየከፋ ፣ የፍየሎቹ አካሔድም እየተስፋፋ ቢመጣም አሁንም ግን ዝምታው ሰፍኗል፡፡ ስለ ፍየሎች ጉዳይ እንዲነሣባቸው የማይፈልጉ በጎችም ተፈጥረዋል፡፡ ‹‹ኸረ ፍየሎች እንዲህ እያደረጉ ነው›› የሚል በግ ሲገኝም ‹‹መዓት አታውራ!›› ተብሎ ይገሠፅ ጀመር፡፡ በዕድሜ የገፉ በጎች ደግሞ ‹‹ይህንን ሳላይ በሞትኩ!›› ብለው ያዝኑ ጀመር፡፡ በእርግጥም በዕድሜ የገፉት በጎች ከመቼውም በላይ የተናቁት አሁን ነው፡፡
 
ፍየሎችን ‹ፍየሎች ናቸው› ብሎ መጥራትም በበጎች ዘንድ ጥላቻን የሚያተርፍ ሆነ፡፡ አንዳንድ በጎች ደግሞ መፍትሔ ያመጡ መስሎአቸው ቢንቀሳቀሱም ፍየልን ፍየል ከማለት ውጪ የበግነትንና የፍየልነትን ልዩነት በሚገባ ማስረዳት ተሳናቸው፡፡ በረቱ የፍየል እንጂ የበግ አልመስል አለ፡፡ አንዳንድ በጎች ጆሮአቸውን ማመን እስኪያቅታቸው የፍየሎች ድምፅ ከበረቱ መሰማቱ እየተለመደ እየተለመደ መጣ፡፡ የሚያስፈራው አዲስ የሚወለዱ ግልገሎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲሰሙ የሚያድጉት የፍየሎችን ድምፅ በመሆኑ ስለ በግነት እና የበግ ድምፅ ምንም ሳያውቁ የሚያድጉ መሆናቸው ነው፡፡ አንዳንድ በበረቱ ያደጉ በጎች ጭንቀቱን አልቻሉትም፡፡ ‹‹ጆሮዬ ነው ወይስ … እውነት የበረታችን አኗኗር እንደዚህ ነበረ ፤ እውነት ይህቺ በረት ከፍየሎች ጋር አንድ ነበረች? የተሳሳትኩት እኔ ነኝ ወይስ ሌላው?››የሚሉም ነበሩ፡፡ ለማን አቤት እንደሚሉ ጨነቃቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ለእረኛው አመለከቱ፡፡ በጎ ስላደረጉ በጎች መነገሩ ነውር ሆነ፡፡ ፍየሎቹ ስለ እረኛው ብቻ ነው መነገር ያለበት ባዮች ሆኑ፡፡ ስለ እረኛም ግን ስሙን እየጠሩ ከመፎከር በቀር ፍሬ ያለው ነገር አይወጣቸውም፡፡ በዚህ ከቀጠለ ቀስ በቀስ በግ የመሆንና ፍየል የመሆን ልዩነት ጠፍቶ በረቱ መፍረሱ እንደማይቀር አንዳንድ በጎች ይናገራሉ፡፡ 
 

በምንባቡ መሠረት የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልሱ

1.    ለበረቱ መበጥበጥ ምክንያት የሆኑት እነማን ነበሩ?
2.    በግ መስለው የተቀላቀሉት ፍየሎች በምን ይታወቃሉ? (መለያ ጠባያቸው)
3.    አንዳንድ የዋሃን በጎች የተሳሳቱት በምን በምን ነበር?
4.    በግ ነበርን ብለው የወጡት ፍየሎች መውጣት የማያስደንቀው ለምንድን ነው?
5.    ጥሩ ጥሩ በጎች ለምን የበረቱን ችግር ለመፍታት አልቻሉም?
6.    ፍየሎችን ‹ፍየሎች› ብሎ መጥራት ለምን ነውር ሆነ?
7.    ለበረቱ መልካም ነገርን የሚመኙ በጎች ለምን ተባብረው መሥራት አልቻሉም?
8.    ከበረቱ ውጪ ያሉት በጎች ለምን ወደ በረቱ ለመመለስ አልቻሉም?
9.    በጎች መመራት ያለባቸው በሌላ በጎች ነው ወይስ በእረኛ?
10.     የበረቱን ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት (ከጓደኞቻችሁ ጋር ተወያዩበት)

ማሳሰቢያ ፡- ተማሪዎች ይህን ፈተና ከተፈተናችሁ በኋላ የበጎቹንና የፍየሎቹን ገጸባሕርያት እያነሣችሁ አንዳችሁ ለአንዳችሁ ስም እየሰጣችሁ እርስ በእርስ እንድትነቃቀፉ አልተፈቀደላችሁም! የጎበዝ ተማሪ መለያ በረቱ ሰላም የሚሆንበትን መፍትሔ መጠቆም ነው፡፡
                                             መልካም ፈተና
ምንጭ፡ሐመር የካቲት 2003 ዓ.ም.