በገና እንደርድር

 በመ/ር መንግስተአብ አበጋዝ
ለግማሽ ምእተ ዓመት ያህል በገና ለደረደሩት መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ እሑድ የካቲት 14 ቀን 2002 ዓ.ም ልዩ ነበር፡፡ ስለዚህ በገናቸውን አንሥተው መጋቤ ስብሐት «ማን ይመራመር ማን ይመራመር ያንተን ሥራ ያንተን ግብር ማን ይመራመር …» እያሉ ያመሰግናሉ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለስድስት ወር ያሠለጠናቸው አርባ ስድስት የበገና ደርዳሪዎችን በሩሲያ ባሕል ማእከል የፑሽኪን አዳራሽ ተመልክተዋልና፡፡

«ለረዥም ዘመን ብቸኝነት ይሰማኝ  ነበር» ያሉት መጋቤ ስብሐት ዓለሙ፡፡ «አሁን በዝተናል» በማለት የበገና ማሠልጠኛዎችም ሆኑ ተማሪዎቹ እየጨመሩ መምጣታቸው ሀገራዊ እሴቱንም ሆነ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ለማየቆት ጠቃሚ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መመሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የተቋቋመው የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤት በአብነት ትምህርትና በዜማ መሣሪያዎች እያሠለጠነ ማስመረቅ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ እንደ ት/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ ተፈራ ገለጻ የዛሬውን ጨምሮ አሥራ አራት ዙር አሠልጥኖ አስመርቋል፡፡

ሥራ አስኪያጁ የአብነት ትምህርትና የዜማ መሣሪያዎች ሥልጠና እሴቶቹን ከመጠበቅ ባሻገር የሚያስገኙትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታዎች ሲዘረዝሩ «ለምስጋና፣ ለተመስጦ፣ ጭንቀትንና ርኩስ መንፈስን ለማራቅ፣ ለትምህርት፣ እንዲሁም የሀገርን ቅርስ ከነሙሉ ታሪኩና ጥቅሙ ለማስተዋወቅ፣ ትውፊትን ለትውልድ ለማውረስና በገና ከነበረው ጥቅም አንጻር ቀጣይ አገልግሎት እንዲኖረው ማድረግ ይቆይ የማይባል አገልግሎት ነው፡፡» ይላሉ፡፡

ወጣት ሚልካ ሐጎስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአምስት ኪሎ ኢንጂነሪንግ የ4ኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ከትምህርቷ በተጓዳኝ ትምህርተ ቤተ ክርስቲያን የምትከታተል የግቢ ጉባኤ ተማሪ ናት፡፡ በዚህ ሁሉ የጊዜ ጥበት ግን በአቡነ ጎርጎርዮስ ት/ቤት የሚሰጠውን የዜማ መሣሪያ ሥልጠና ወስዳ በበገና መደርደር ተመርቃለች፡፡ ሚልካ ጊዜዋን አጣጥማ በሳምንት ሁለት ቀን ለሁለት ሰዓት ተከታትላ በስድስት ወር ያጠናቀቀችውን ሥልጠና እንዴት ትገልጠዋለች)

«ጊዜአችንን በአግባቡ የምንጠቀም ከሆነ ሕልምን እውን ማድረግ እንችላለን፡፡ ጊዜዬን ተጠቅሜ በገና ተምሬአለው፡፡ ይህ ለእኔ መንፈሳዊ ሕይወት እጅግ አጋዤ ነው፡፡ ጊዜ መድቤ ደግሞ የአብነት ትምህርቱንና ተጨማሪ የዜማ መሣሪያዎችን ለመማር አስባለሁ፡፡ እድሜዬን ሁሉ አገልጋይ ሆንኩ ማለት አይደል፡፡ በእውነት በገና መደርደር መታደል ነው፡፡» ብላለች፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ትምህርት ቤቱን ከፍቶ ኑና በገና እንደርድር ይላል፡፡