በዓለ ትንሣኤን በትንሣኤ ልቡና እናክብር

በገብረ እግዚአብሔር ኪደ

ሚያዝያ ፲፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

 ፋሲካ ማለት መሻገር ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ወልድ እኛን ከወደቅንበት አንሥቶና ተሸክሞ ከዚኽ ምድር ወደ ሰማያት ተሻግሯልና (ተነሥቶ ዐርጓልና)፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ፡- ‹‹እንግዲኽ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን ሹበላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ ሞታችኋልና ሕይወታችኁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሯልና፡፡ ሕይወታችኁ የኾነ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተ ደግሞ ከእርሱ ጋር በክብር ትገለጣላችኁ፤›› እንዳለን /ቈላ.፫÷፩-፬/፣ በጥምቀት ውኃ ሞቱን በሚመስል ሞት ስንሞት፣ አሮጌው ሰውነታችን እንደ ግብጻውያን ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ አዲሱ ሰውነታችን ግን እስራኤላውያን ባሕሩ ተከፍሎላቸው እንደ ተሻገሩ ተሻግሯል (ተነሥቷል)፡፡

ብልየት ያለበት የቀዳማዊ አዳም ሰውነታችን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተቀብሮ አዲሱ ሰውነታችን ሕይወትን አግኝቶ ተነሥቷል፡፡ መሬታዊው ሰውነታችን ሞቶ ሰማያዊው ሰውነታችንን ለብሰን መንፈሳውያን ኾነን ተነሥተናል፡፡ ወደ ጥንተ ተፈጥሯችን ተመልሰናል፡፡ አኹን ከእኛ የሚጠበቀው ይኽ ተፈጥሯችንን ሳናቆሽሽ መጠበቅ ነው፤ እንደ ተነሣን መዝለቅ፡፡ ይኽን ለማድረግም ተራራ መውጣት፣ ምድርን መቆፈር፣ የእሳት ባሕርን መሻገር አይጠበቅብንም፡፡ ይኽን ጠብቀን እንድንቈይ እግዚአብሔር ከእኛ የሚፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው፤ ፈቃዳችንን፡፡ የሚሠራው እርሱ ራሱ ነውና /ዮሐ.፲፭÷፭/፡፡ መጽንዒ (የሚያጸና) መንፈስ ቅዱስን ያደለንም ስለዚኹ ነው፡፡

የምናመልከውን አምላክ መስለን በሕይወት ሳንሻገር የመሻገርን በዓል (ፋሲካን) የምናከብረው ምን ጥቅም እንዲሰጠን ነው? ከጨለማ ሥራ ወደ ብርሃን ሥራ፣ ከፍቅረ ዓለም ወደ ፍቅረ ክርስቶስ ሳንሻገር ፋሲካን የማክበራችን ትርጕሙ ምንድነው? እኛው ሳንነሣ የመነሣት በዓልን ማክበራችን በፍርድ ላይ ፍርድ በበደል ላይ በደል ከመጨመር ውጪ የሚሰጠን ጥቅም ምንድን ነው? የምንነሣውስ መቼ ነው? በዐይናችን ጉድፍ ብትገባ ስንት ደቂቃ እንታገሣታለን? ታድያ በነፍሳችን ላይ የተጫነውን የኃጢአት ግንድ መቼ ነው የምናስወግደው? መቼ ነው ወደ ላይኛው ቤታችን ቀና የምንለው? ብዙዎቻችን በሕይወታችን ሳንሻገር ነው በዓለ ፋሲካን የምናከብረው፡፡ ክርስቲያን ኾኖ በመብልና በመጠጥ ብቻ ፋሲካን ማክበር ኢ ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡

አዲሱን ሰውነታችን ለብሰን ከተነሣን በኋላ እንደ ቀድሞ ምልልስ የምንጓዝ ከኾነ ግን ተመልሰን ወድቀናል፤ አዲሱ ሰውነታችንን አውልቀን አሮጌውን ሰውነታችንን በድጋሜ ለብሰነዋል፡፡ በእኛነታችን ውስጥ ፍቅረ ንዋይ፣ ፍቅረ ሲመት፣ ፍትወት፣ ይኽንንም የመሰሉ ዅሉ ካለ አዲሱ ሰውነታችን ከእኛ ጋር የለም፤ ቢኖርም ታሟል፡፡ በኃጢአት የመቃጠል ስሜት፣ ርኵሰትና ክፉ ምኞት ከእኛ ዘንድ ካለ አሮጌ ሰው ኾነናል፤ ትንሣኤ ልቡናን ገንዘብ አላደረግንም፡፡ ስለዚኽ ከልቡና ሞት እንነሣና ፋሲካን እናክብር፡፡ እስከ አኹን በኃጢአት ውስጥ ካለን ወደ ብርሃን ክርስቶስ እንምጣ (እንሻገርና) የመሻገርን በዓል እናክብር፡፡ ከክፉ ሥራ ወደ ጽድቅ ሥራ እንሻገርና የእውነት ፋሲካን እናክብር፡፡ ከኃይል ወደ ኃይል እንሻገርና ፋሲካን እናክብር፡፡ ከሞት ሥራ ወደ ሕይወት ሥራ እንነሣና የመነሣትን በዓል እናክብር፡፡

እግዚአብሔር የሚወዳችሁ አንድም እግዚአብሔርን የምትወዱት ሆይ! እኛን የሚያሰነካክል ደግሞም የሚጥለን ፈርዖን (ዲያብሎስ) ተሰነካክሎ ወድቋልና ከግብጽ ሕይወታችን እንውጣ፡፡ ተነሥተንም እንሻገር፡፡ ተሻግረንም ሰማያዊውን ፋሲካ እናክብር፡፡ በግብጽ የነበሩት እስራኤላውያን የበጉን ደም በጉበኑና በኹለቱም መቃን ሲቀቡት አጥፊው ከቤታቸው እንዳለፈ አንብበናል /ዘፀ.፲፪÷፲፫/፡፡ ይኸውም በጉ በራሱ ያንን የማድረግ ኃይል ስለ ነበረው አይደለም፤ ደሙ የክርስቶስ ደም አምሳል ስለ ነበር ነው እንጂ፡፡ እኛ ግን የአማናዊውን በግ /ዮሐ.፩፡፳፱/ ደም በልቡናችን፣ በአስተሳሰባችንና በሰውነታችን ዅሉ እንቀባና (እንቀበልና) እንሻገር፡፡

ይኽን ስናደረግ በእባቡና በጊንጡ ይኸውም በዲያብሎስና በሠራዊቱ ላይ ሥልጣን ይኖረናል /ሉቃ.፲÷፲፱/፡፡ የምንበላው በግ ራሱ ሕይወት ስለ ኾነ ሞት በእኛ ላይ አይነግሥም /ዮሐ.፲፬÷፮/፡፡ በዚኽ ዓለም ሳለን ከዚኽ ደስታ ተካፋዮች ከኾንን (የመዠመሪያውን ትንሣኤ ልቡና በንስሐ ከተነሣን) በሚመጣው ዓለምም በክብር ላይ ክብር፣ በሹመት ላይ ሹመት እንቀበላለን (ኹለተኛውን ትንሣኤ እንነሣለን) /ሉቃ.፳፪÷፲፭-፲፮/፡፡ ብንወድቅ እንኳን መልሰን በመነሣት ከባሕርይ አባቱ ከአብ፣ ከባሕርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር፣ የክብር ክብር፣ ጌትነት የባሕርዩ በሚኾን፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰጭነት በመንግሥተ ሰማያት ጸጋ ክብር እናገኛለንና የጭንቅ ቀን ሳይመጣ በዓለ ትንሣኤን እናክብር፡፡ ለዚህም ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የመከረንን የሚከተለውን ኃይለ ቃል በተግባር ላይ ብናውለው እንጠቀማለን፤

‹‹በምነግራችኁ ነገር እያበሳጨኋችሁና እያሳመምችሁ እንደ ኾነ ይገባኛል? ግን ምን ላድርግ? እኔም እናንተም በምግባር በሃይማኖት የታነጽን እንኾን ዘንድ ብቻ ሳይኾን ከዚያም እናመልጥ ዘንድ ነው፡፡ ነገር ግን በኃጢአት ከመጨማለቃችን የተነሣ እንዴት አድርጌ ላሳምማችኁ እችላለኁ? ብትሰሙኝና ብትለወጡስ እኔም ማረፍ እንኳን በቻልኩ ነበር፡፡ ስለዚኽ እስካልተለወጣችሁ ድረስ እናንተን መገሠንና መምከሬን አላቆምም፡፡ ስለ ገነመ እሳት ተደጋግሞ ሲነገር የሚበሳጭ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እኔ ግን ከዚኽ የበለጠ ያማረ የተወደደ አስደሳች ትምህርት የለም እለዋለኁ፡፡ እንዴት ይኽ አስደሳች ትምህርት ነው ትለናለህ? ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ እኔም ወደዚያ መጣል ከደስታ ዅሉ የራቀ ነውናብዬ እመልስላችኋለሁ፡፡ ስለዚኽ ነፍሳችን ከመታሠሯ በፊት የነቃን የተጋን እንኾን ዘንድ ይኽን ደጋግሜ እነግራችኋለሁ፡፡ ስሐ ይግባ እንጂ ማንም እንደ ተወቀሰ አያስብ፤ በንግግሬም የሚቆጣ አይኑር፡፡ ዅላችንም ወደ ጠባቢቱ መንገድ እንግባ፡፡ እስከ መቼስ በስንፍና አልጋ እንተኛለን? ዛሬ ነገ ማለት አይበቃንም ወይ? ሰማያዊ ቪላችንን ቀና ብለን ብንመለከት እኮ በዚኽ ምድር ይኽንን ለመሥራት ባልደከምን ነበር፡፡ እስቲ ንገሩኝ! ሩጫችንን ስንጨርስ ከሬሳ ሳጥንና ከመግነዝ ጨርቅ ውጪ ይዘነው የምንሔድ ነገር ምን አለ? ታድያ ለምን እንከራከራለን?›› (ሰማዕትነት አያምልጣችሁ እና ሌሎች፣ ገጽ ፻፶፮ – ፻፶፯)፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡