Semera_Kidus_Yohanes_Church.jpg

በአፋር ሰመራ ከተማ የመጥምቁ ዮሐንስ ገዳም ቅዳሴ ቤት ተከበረ

ሎጊያ ወረዳ ማዕከል
    Semera_Kidus_Yohanes_Church.jpg
 
 
 
 
 
 
 
በሰመራ ከተማ የተሰራዉ የቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን

በአፋር ሀገረ ስብከት ሰመራ ከተማ በሀገረ ስብከቱና በአካባቢው ማኅበረሰብ ከፍተኛ ጥረት የተሠራው የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ገዳም መቃኞ ተጠናቆ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ግንባታው የተጀመረው ይኸው መቃኞ ቤተ ክርስቲያን፤ ቤተልሔም፣ የግብር ቤት፣ የዕቃ ቤት እና የውኃ ማጠራቀሚያ ገንዳ እንዲሁም የካህናት ማረፊያ ቤቶችም ጭምር እንደተሠሩለት ታውቋል፡፡

ጥር 30 ቀን 2002 ዓ.ም በርካታ የአካባቢው ምእመናን፤ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች፣ ካህናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ቅዳሴ ቤቱ ሲከበር ከቀረበው መግለጫ ለመረዳት እንደተቻለው፤ 2001 ዓ.ም በሰመራ ከተማ የተቋቋመው ዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ሲቀበል የክርስቲያኖች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ይሁንና በከተማው በወቅቱ ምንም ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ ማስቀደስ፣ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት እንዲሁም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶችን ማግኘት አልተቻለም ነበር፡፡

በዕለቱ ቡራኬ የሰጡት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮናስ እንደገለጹት፤ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የአምልኮ ቦታ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው በአፋር ክልላዊ መንግሥት መልካም ፈቃድ 29 ሺሕ 830 ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ቦታው የመንበረ ጵጵስና፣ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት እና የሕንፃ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያን ያካተተ ማስተር ፕላን /የይዞታ ማረጋገጫ/ የተሠራለት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

«ይህ ቦታ በረሃማ ስለሆነ፤ በበረሃ የገደመው ዘ ንብረቱ ገዳም በተባለለት በቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ስም፤ ቅሩበ ሳሌም ዮሐንስ መጥምቅ ገዳም ተብሎ እንዲጠራ ይሁን» ያሉት ብፁዕነታቸው፤ ቅሩበ ሳሌም የሚለው ሥያሜ ዮሐንስ መጥምቅ የንስሐ ጥምቀት ያጠምቅበት የነበረው አካባቢ እንዲታወስ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የገዳሙ ሕንፃ ቤተክርስቲያን /መቃኞ/ መሠራት እጅግ ያስደሰታቸው መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው ለሥራው የተባበሩትን ሁሉ በማመስገን ምእመናኑን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡

ከሁለት ዓመት  በኋላ  ዋናውን ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ዕቅድ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

በሰመራ ከተማ ምንም ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች የእምነት ሥርዓታቸውን ማከናወን ይቸገሩ እንደ ነበር የጠቀሰው የግቢ ጉባኤው ሰብሳቢ ዲ/ን ደጀን፤ ያም ሆኖ ተማሪው ከዩኒቨርስቲው መደበኛ ትምህርት ጎን ለጎን መንፈሳዊ ትምህርት የመቀበል ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለነበረ ግቢ ጉባኤ ተቋቁሞ ትምህርቱ ይሰጥ እንደነበር አስረድቷል፡፡

«ቦታው ምድረ በዳ ከመሆኑ አንፃር በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው እጅ ተሠራ ለማለት አያስደፍርም» ያለው ሥራውን በሓላፊነት ሲከታተል የነበረው ዲ/ን ናሁሠናይ ደስታ በበኩሉ፤ «የሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ከጀምሩ አንሥቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ ያደረጉ የሰመራ ዩኒቨርስቲ መምህራንና ሠራተኞች፣ የዱብቲ ውኃ ሥራዎች ድርጅት ሠራተኞች፣ የእመቤታችን ጽዋ ማኅበር፣ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችና የአካባቢው ምእመናን ምስጋና ይገባቸዋል» ብሏል፡፡

በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮናስ ከተለያዩ ምእመናን ያገኙዋቸውን ንዋያተ ቅድሳት ለቤተ ክርስቲያኑ መገልገያ ማስረከባቸውንም ከማኅበረ ቅዱሳን የሎግያ ወረዳ ማእከል የተላከልን ዘገባ ያስረዳል፡፡