በአዲስ ዓመት አዲስ ሕይወት

መስከረም ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

እግዚአብሔር አምላካችን በዕድሜ ላይ ዕድሜን እየጨመረ፣ በየጊዜያቱ ዘመናትን እያፈራረቀ አዲስ ዓመትን ያመጣልናል፡፡ አሁንም በእርሱ ቸርነት ለ፳፻፱ ዓመተ ምሕረት ደርሰናል፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስ በራእዩ ‹‹እነሆ ኹሉን አዲስ አደርጋለሁ … አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፤ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና፡፡ ባሕርም ወደ ፊት የለም›› በማለት እንደ ተናገረው /ራእ.፳፩፥፩-፭/ በየጊዜው ዘመን እያለፈ አዲስ ዘመን ይተካል፡፡ እኛም ዘመን በመጣ ቊጥር ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!›› እንባባላለን፡፡ ስለ ትናንትና እንጂ ስለ ነገ ባናውቅም እስከ ዛሬ ድረስ በመቆየታችን እንደሰታለን፡፡

ነገን በጉጉት ለሚናፍቅ ሰው በእውነትም ዓመት አልፎ ዓመት ሲተካ በጣም ያስደስታል፡፡ ነገር ግን ያለፈውን ዓመት ስንዋሽ፣ ስንሰርቅ፣ ስንዘሙት፣ ስንጣላ፣ ስንተማማ፣ ስንደባደብ፣ ስንሰክር አሳልፈን ከኾነ ‹‹እንኳን አደረሳችሁ!›› የሚለው ቃል ርግማን ይኾንብናል፡፡ በመኾኑም ስለ ተለወጠው ዘመን ሳይኾን ስላልተቀየረው ሰብእናችን፤ ስላልተለወጠው ማንነታችን፤ ስላልታደሰው ሥጋችን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ በኀጢአት እየኖሩ ዐውደ ዓመትን ማክበር ራስን ያለ ለውጥ እንዲቀጥል ማበረታት ነውና ከምንቀበለው ዘመን ይልቅ መጪውን ዘመን ለንስሐ ለማድረግ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ያሳለፍነውን የኀጢአት ጊዜ እያሰብን እስከ ዛሬ ድረስ የጠበቀንን እግዚአብሔርን እያመሰገንን ሕይወታችንን በጽድቅ ልናድስ ይገባናል፡፡ በንስሐ ባልታደሰ ሕይወታችን በዕድሜ ላይ ዕድሜ ቢጨመርልን ለእኛም ለዘመኑም አይበጅምና፡፡ ‹‹ባረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ መጣፊያው ልብሱን ይቦጭቀዋልና፡፡ መቀደዱም የባሰ ይኾናል›› እንዳለ ጌታችን በወንጌል /ማቴ.፱፥፲፯/፡፡

ስለዚህም ያለፈውን ዓመት በምን ኹኔታ አሳለፍሁት? በመጭው ዓመትስ ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል? ልንል ይገባል፡፡ ያለ ክርስቲያናዊ ምግባር እየኖርን ዘመንን ብቻ የምንቈጥር ከኾነ ሕይወታችንን ከሰብኣዊነት ክብር ብሎም ከክርስቲያናዊ ሕይወት በታች እናደርገዋለን፡፡ ራስን ከጊዜ ጋር ማወዳደር መቻል ክርስቲያናዊ ሓላፊነት ነው፡፡ ይኸውም ጊዜ ሳይቀድመኝ ልቅደመው ብሎ ማሰብ መቻል ነው፡፡ በአሮጌ ሕይወት ውስጥ ኾነን ዓመቱን አዲስ ከማለት ይልቅ ከኀጢአት ወደ ጽድቅ በመሸጋገር ራሳችንን በጽድቅ ሥራ ማደስ ይበልጣል፡፡

በመሠረቱ ዘመን ራሱን እየደገመ ይሔዳል እንጂ አዲስ ዓመት የለም፡፡ ሰዓታትም ዕለታትም እየተመላለሱ በድግግሞሽ ይመጣሉ እንጂ ከዚህ በፊት ያልነበረ ሰዓት ወይም ቀን ወይም ደግሞ ወር አለዚያም ዓመት የለም፡፡ ወርኀ መስከረምም ለብዙ ሺሕ ዓመታት ራሱን እየደገመ በየዓመቱ አዲስ ሲባል ይኖራል እንጂ ሌላ መስከረም የለም፡፡ ‹‹የኾነው ነገር እርሱ የሚኾን ነው፤ የተደረገውም ነገር እርሱ የሚደረግ ነው፡፡ ከፀሐይም በታች አዲስ ነገር የለም፡፡ ማንም ‹እነሆ ይህ ነገር አዲስ ነው› ይል ዘንድ ይችላልን? እርሱ ከእኛ በፊት በነበሩት ዘመናት ተደርጎአል›› እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን /መክ.፩፥፱-፲/፡፡

ስለ ኾነም ምንም እንኳን ሕይወታቸውን በሙሉ በጽድቅ የሚያሳልፉ ወይም በንስሐ የሚኖሩ ብዙ ጻድቃን ቢገኙም ሰውነታችንን ጥለን የምንኖር ኀጥኣን ግን በኀጢአት ያሳለፍነውን ዘመን በማሰብ መጭውን ዘመን ለመልካም ሥነ ምግባር ልናውለው፤ አንድም ለንስሐ መግቢያ ልናደርገው ያስፈልጋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ‹‹የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት፤ በመዳራትና በሥጋ ምኞትም፣ በስካርም፣ በዘፈንም፣ ያለ ልክም በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት፣ በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል›› በማለት አስተምሮናልና /፩ኛጴጥ.፬፥፫/፡፡

ስለዚህም በዚህ አዲስ ዓመት ከክፉ ምግባር ኹሉ ተለይተን፣ ከዚህ በፊት በሠራነው ኀጢአታችን ንስሐ ገብተን ለወደፊቱ በጽድቅ ሥራ ኖረን እግዚአብሔርን ልናስደስት ይገባናል፡፡ ‹‹ይደልወነ ከመ ንግበር በዓለ ዐቢየ በኵሉ ንጽሕና እስመ ይእቲ ዕለት ቅድስት ወቡርክት፡፡ ወንርኀቅ እምኵሉ ምግባራት እኩያት፡፡ ወንወጥን ምግባራተ ሠናያተ ወሐዲሳተ በዘቦቶን ይሠምር እግዚአብሔር፤ አሁንም በፍጹም ንጽሕና ታላቅ በዓልን አድርገን ልናከብር ይገባናል፡፡ ይህቺ ዕለት ከሌሎች ዕለታት ተለይታ የተባረከች ናትና፡፡ ከክፉ ሥራዎችም ኹሉ ተለይተን እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝባቸውን አዳዲስ የኾኑ በጎ ሥራዎችን እንሥራ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /መጽሐፈ ስንክሳር፣ መስከረም ፩ ቀን/፡፡

ዘመን አዲስ የሚባለው እኛ ሰዎች (ክርስቲያኖች) ሕይወታችንን በጽድቅ ስናድስ ነው፡፡ ያለ መልካም ሥራ የሚመጣ ዓመት፤ ከክፉ ግብር ጋር የምንቀበለው ዘመን አዲስ ሊባልም፣ ሊኾንም አይችልም፡፡ የሰው ልጅ መንፈሳዊ ሕይወት በመልካም ሥራ ሲዳብር ግን መጭው ዘመን ብቻ ሳይኾን ያለፈውም አዲስ ነው፡፡ ለአዲስ ዓመት አዲስ ሕይወት እንደሚያስፈልግ በመረዳት ራሳችንን በንስሐ ሳሙና አሳጥበን በንጽሕና ልንኖር ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ታጠቡ፤ ሰውነታችሁንም አንጹ፡፡ የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ፡፡ ክፉ ማድረግን ተዉ፡፡ አንጽሑ ነፍሰክሙ ወነጽሩ ነፍስተክሙ፤ ልባችሁን አንጹ፤ ሰውነታችሁንም ንጹሕ አድርጉ›› ተብለን ታዝዘናልና /ኢሳ.፩፥፲፮፤ መጽሐፈ ኪዳን/፡፡

የተወደዳችሁ ምእመናን ‹‹ዐዘቅቱ ኹሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ኹሉ ዝቅ ይበል፡፡ ጠማማውም የቀና መንገድ ይኹን፡፡ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይኹን፡፡ ሥጋም የለበሰ ኹሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ›› ተብሎ እንደ ተነገረው /ሉቃ.፫፥፫-፮/ በኑፋቄ የጎደጎደው ሰውነታችንን በቃለ እግዚአብሔር በመሙላት፤ በትዕቢት የደነደነውን ተራራውን ልቡናችንን በትሕትና በማስገዛት፤ በክፋት የተጣመመው አእምሯችንን በቅንነት በማስጓዝ፤ በኀጢአት የሻከረውን ልቡናችንን በንስሐ በማስተካከል አዲሱን ዓመት የመልካም ምግባር ዘመን እናድርገው፡፡ በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትኾኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ›› በማለት እንዳዘዘን /፩ኛቆሮ.፭፥፯/፣ በኀጢአት እርሾ የተበከለውን ሰውነታችንን በጽድቅ ሕይወት እናድሰው፡፡ በአዲሱ ዓመት በክርስቲያናዊ ምግባር መኖር ከቻልን ከጊዜ ጋር የሚጣጣም አዲስ ሕይወት ይኖረናል ማለት ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡