በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንዳይሆን

ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እና ከየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት የስብከተ ወንጌል ፍቃድ ሳይኖራቸው በየቤተ ክርስቲያኑ ዐውደ ምሕረት በሕዝበ ክርስቲያኑ መካከል እየተገኙ እንሰብካለን እናስተምራለን በማለት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና መመሪያ በሚጥሱ  ሕገወጥ ሰባክያን፤ ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅናና ፈቃድ ውጪ በጉባኤ ሊቃውንት ያልታዩና ያልተመረመሩ የተለያዩ የኅትመት ውጤቶች፤ መጻሕፍት፣ የስብከት የመዝሙር የምስል ወድምፅ /ኦዲዮ ቪዲዮ/ ካሴቶች እየተሠራጩ፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ እምነት፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚጥሱ ተግባራት ሲፈጸሙ ይታያል፡፡

ይህንኑ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓትና አሠራር ውጪ የሆነ ሕገወጥ ተግባር የተገነዘበው ቅዱስ ሲኖዶስ፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነትና ሥርዓት አካሔድ አቅጣጫውን ሳይስት ተጠብቆ እንደቆየ ሁሉ ወደፊትም መቀጠል ስላለበት፤ የካቲት 12 ቀን 2001 ዓ. ም. ባደረገው ስብሰባ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ በቁጥር ል/ጽ/382/2001 የካቲት 16 ቀን 2001 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ፤

1ኛ. በዚህ ውሳኔ መሠረት፤ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ከየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት የስብከተ ወንጌል ፈቃድ ሳይኖራቸው እንዳይሰብኩ በቅዱስ ሲኖዶስ የተከለከለ ስለሆነ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ከሀገረ ስብከት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በየደረጃው ባለው መዋቅር ተግባራዊ እንዲሆን፤

2ኛ. የእያንዳንዱ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ የተጣለበትን ሓላፊነት ተገንዝቦ የመቆጣጠሩን ተግባር በማጠናከር የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና ከሚፈታተን ተግባር    እንዲጠብቅ፤

3ኛ. በጉባኤ ሊቃውንት ተመርምረው ዕውቅና ሳይሰጣቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰም የሚሠራጩ የኅትመት ውጤቶች፤ መጻሕፍት፣ በምስል ወድምፅ /ኦዲዮ ቪዲዮ/ የተዘጋጁ ስብከቶች መዝሙሮች ጥብቅ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው፤

4ኛ. በስብከተ ወንጌል ትምህርት አሰጣጡና በሥርጭቱ ረገድ በቁጥጥሩ የሥራ ሒደት አፈጻጸም ወቅት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅናና ፈቃድ ውጪ የሆነ ከአቅም በላይ ችግር ሲያጋጥም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጭምር በመግለጽ ችግሩ ሕጋዊ መፍትሔ እንዲያገኝ፤ በማለት መመሪያ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ በአሁኑ ወቅት ጐልተው የሚታዩትን የስብከተ ወንጌል ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ሴሚናር፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ አዘጋጅነት መስከረም 11 እና 12 ቀን 2003 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ መካሔዱም ይታወሳል፡፡

በዚህ ቅዱስ ፓትርያሪኩ በተገኙበትና መመሪያ ባስተላለፉበት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በየአህጉረ ስብከቱ፣ አድባራትና ገዳማቱ ስብከተ ወንጌልን በማሰፋፋት ረገድ ዐቢይ ሚና ያላቸው ሓላፊዎች፣ ሰባክያንና ዘማርያን በተሳተፉበት ውይይት፤ የቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓትና አሠራር ተጠብቆ መንፈሳዊ አገልግሎቷም በአግባቡ እንዲፈጸም የሚረዱ ውሳኔዎችም ተወስነዋል፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና አሠራር ለማስጠበቅ የተላለፉትን መመሪያዎች በማስፈጸም ረገድ በጠቅላይ ቤተክህነት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡

በየአህጉረ ስብከቱ ስምሪት በማድረግ ከሚመለከታቸው ሓላፊዎች፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት አስተባባሪዎችና መምህራነ ወንጌል በአጠቃላይ ከደቀ መዛሙርት አገልጋዮች ጋር በተካሔዱ ተከታታይ ውይይቶች የተደረሰበት የጋራ ግንዛቤ ለአፈጻጸሙ አጋዥ ኃይል ሆኗል፡፡ በመምሪያው ሥር በሚያገለግሉ ሊቃነ ካህናት አማካኝነት በየአህጉረ ስብከቱ በርካታ የስብከተ ወንጌል ጉባኤያት ተካሒደዋል፡፡

ማእከላዊነቱን የጠበቀ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድ ድምፅ ወጥ ለሆነው የስብከተ ወንጌል አገልግሎት መስፋፋት መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ ከቀደሙት አባቶች የተረከብነው የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅራዊ ቅብብሎሽ እንደተጠበቀ ዶግማዋ፣ ቀኖናዋና ትውፊቷ ወደፊትም ለትውልድ እንዲተላለፍ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያው ከፍተኛ እንቅሰቃሴ እያደረገ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያኒቱ መምህራነ ወንጌልም ሥርዓትና መመሪያውን ጠብቀው መንፈሳዊ ተልእኮአቸውን እየፈጸሙ ሲሆን፤ መምሪያው ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት ረገድ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት ጋር አብሮ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

በስብከተ ወንጌሉ አገልግሎት ረገድ አበረታች ጥረት እየተደረገ ቢታይም፤ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት፤ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔና መመሪያ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ በአንዳንድ አህጉረ ስብከት ችግሮች እያጋጠሙ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከጥር 20-22 ቀን 2003 ዓ.ም እንዲካሔድ ለተዘጋጀ ጉባኤ የሲዳማ ጌዲኦ፣ አማሮና ቡርጂ አህጉረ ስብከት ለጠቅላይ ቤተክህነት ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ መምህራነ ወንጌል እንዲላኩለት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የተላኩት ሦስት መምህራን በተከሠተው ችግር ምክንያት የተላኩበትን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ሳይፈጽሙ ለመመለስ ተገደዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቃና መንፈሳዊ አገልግሎት አካሔድ ላይ እንቅፋት የሚፈጥር አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡

ለችግሩ ምክንያት የሆኑትም የራሳቸውን ዓላማና ፍላጐት ለማስፈጸም የሚያስቡና የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዓላማ ያልተረዱ የተወሰኑ አካላት እንደሆኑ ከስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያው እና ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መግለጫ ለመረዳት ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅናና ፈቃድ ውጪ ስለሚሠራጩ የኅትመት ውጤቶች፤ መጻሕፍት፣ የስብከትና መዝሙር የምስል እና ድምፅ ካሴቶች የተላለፈው መመሪያ በአግባቡ ተፈጻሚ አለመሆኑን ከመምሪያው ሓላፊ ገለጻ እንገነዘባለን፡፡

በእርግጥ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ ትኩረቷ በማስተማርና በመምከር ወደ መልካም መንገድ መመለስ እንደመሆኑ ይህንኑ ተግባሯን ትፈጽማለች፡፡ ሆኖም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ልጆች አገልጋዮቿና ምእመናን ሁሉ ትምህርቷን ሰምተው፣ ሥርዓቷን   ጠብቀውና መመሪያዋን አክብረው የሚጠበቅባቸውን ሁሉ በአግባቡ መፈጸም ደግሞ ሃይማኖታዊ ግዴታቸው እንደሆነም የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ቤተክህነት ደረጃ በመምሪያው የተዘጋጀው ሴሚናርና፤ በየአህጉረ ስብከቱ በተደረገው ስምሪት የተካሔደው ውይይት በየደረጃው በሚገኙ ሓላፊዎች፣ ሊቃውንትና ሰባክያነ ወንጌል ዘንድ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር አስችሏል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔና መመሪያዎች እንዲሁም የስብከተ ወንጌሉን አሠራርና ሥርዓቱን የጠበቀ አፈጻጸም በማስተዋወቅ ረገድ ጠቀሜታው እጅግ የጐላ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነቱ በየደረጃው የሚካሔደው ውይይትና ተከታታይነት ያለው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በየአህጉረ ስብከቱ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ አባቶች መምህራነ ወንጌልና አገልጋዮች ዘንድ የጋራ ግንዛቤና የተቀናጀ አሠራር ለማምጣት ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ወደፊትም ይህ ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቷን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማሳካት ሥርዓቷን፣ መዋቅርና አሠራሯን አክብረውና ጠብቀው በየዘርፉ ለተሰማሩ አገልጋዮቿ ሁሉ ስለአገልግሎታቸው ሪፖርት ማቅረብ፤ ያከናወኑትን ተግባር አፈጻጸማቸውንና የአገልግሎታቸውን ውጤት መገምገም፤ በአጋጠሙ ችግሮች ላይ መወያየትና መፍትሔ መፈለግ፤ የወደፊቱን የአገልግሎት አቅጣጫ መተለም እና ማቀድ አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ሲሆን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና መዋቅር ማስጠበቅ፣ መመሪያና አሠራሯ የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ ይቻላል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቷ ሥርዓትና አሠራር ውጪ የሚሆኑትንም በአግባቡ ተከታትሎ በወቅቱ ለማረምና ለማስተካከል አመቺ ይሆናል፡፡

ሁላችንም የምንፈልገው ትክክለኛ አሠራርና መልካም ውጤት እንዲመጣ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና መመሪያ እንዲሁም የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ጥረት ብቻውን በቂ እንደማይሆን እንገነዘባለን፡፡

ለውሳኔዎቹና ለሚተላለፉት መመሪያዎች ተግባራዊ አፈጻጸም መሟላት የሚገባቸው አስፈላጊ ነገሮች ካልተሟሉ ውሳኔውም ሆነ መመሪያው በወረቀት፤ ዕቅዱም በሐሳብ ብቻ ተወስነው ይቀራሉ፡፡

የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና አሠራር አክብሮና ተከትሎ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ሌሎች ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎቷን ማስፈጸምም ሆነ መፈጸም ከጠቅላይ ቤተክህነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ ሓላፊዎች፣ አባቶችና አገልጋዮች ሁሉ ቀዳሚ የሓላፊነት ግዴታቻው መሆኑ ይታወቃል፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት አክብረው የሚሠሩ ለሐዋርያዊ ተልእኮዋ መሳካት የበኩላቸውን ድርሻ የሚያበረክቱ፤ የተለያዩ ኅትመት ውጤቶች መጻሕፍት፣ የስብከተ ወንጌልና መዝሙር አዘጋጆች፣ ሰባክያነ፣ ዘማርያን፣ አሳታሚና አከፋፋዮች የአገልግሎቱ አካላት እንደመሆናቸው፤ የስብከተ ወንጌል መምሪያው በቤተ ክርስቲያን አሠሪርና መመሪያዎች ላይ በማወያየት የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር መሥራት አለበት፡፡ እነሱም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት እንዲጠበቅ የበኩላቸውን ክርስቲያናዊ ሓላፊነት ይወጡ ዘንድ ይገባልና፡፡ ምእመናንም እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታቸው የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና መመሪያ በሚገባ የመፈጸም የልጅነት ድርሻና ሃይማኖታዊ ግዴታ አለባቸው፡፡

እያንዳንዱ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፤ በአጥቢያው የቤተ ክርስቲያኒቷን ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ላይ ያላቸው እምነትና ተስፋ እንዲጠነክር፣ በሰላምና በፍቅር በተረጋጋ ሁኔታ የአገልገሎቷ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑና ለዘለዓለማዊ ሕይወት እንዲበቁ፣ እንዲሁም የልጅነት ድርሻቸውን እንዲወጡ በማድረግ ረገድ፤ በመምራት፣ በማስተባበር፣ በቅርብ ሆኖ በመከታተል የተቃና እንዲሆን የተጣለበት አባታዊና መንፈሳዊ ሓላፊነት እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ይህ ታላቅ መንፈሳዊ ሓላፊነት ከግል አሳብና አመለካከት ይልቅ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዓላማ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲያስፈጽሙ የሚያስገድዳቸው እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡

ስለዚህ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና መመሪያ ላይ እንደተገለጸው፤ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች የተጣለባቸውን ሓላፊነት ተገንዝበው በሚገባ የመምራትና የማስተባበር እንዲሁም የመቆጣጠሩን ተግባር በማጠናከር የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና ከሚፈታተን ተግባር መጠበቅ አለባቸው፡፡

ምእመናንም ትክክለኛውን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመቀበል፣ ሥርዓትና መመሪያዋን በአግባቡ በመፈጸም በሰላምና በፍቅር ሃይማኖታዊ የልጅነት ድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል፡፡

አሁን ባለንበት ዘመን የቴክኖሎጂው እድገትና ተደራሽነት አመቺ በሆነበት እና የሕዝቡም ፍላጐትና ጥያቄ በዚያው መጠን በጨመረበት ወቅት፤ እጅግ በርካታ የኅትመት ውጤቶች፤ መጻሕፍት፣ የስብከትና የመዝሙር የምስል እና የድምፅ ካሴቶች /ኦዲዮ ቪዲዮ/ እየተዘጋጁ መቅረባቸው አስፈላጊነቱ አያጠያይቅም፡፡

ስለዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱን አሠራር ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ፤ ሊቃውንቱንና በሙያው የተዘጋጁ ብቁ ባለሙያ የሰው ኃይል ማሠማራት፣ አስፈላጊውን የአገልግሎት መሣሪያ ማሟላትና በቂ በጀት መመደብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሲሆን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሥርዓት ጠብቀው ለተዘጋጁ የኅትመት ውጤቶች መጻሕፍት፣ የስብከትና መዝሙር ካሴቶች የዕውቅናና ፍቃድ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ይቻላል፡፡

ይህንን ለማስፈጸም የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያው ብቸኛ ጥረት ብቻ በቂ እንደማይሆን ይታመናል፡፡

ስለዚህ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የጠቅላይ ቤተክህነት ሓላፊዎችና በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ትኩረትና ተግባራዊ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ መምሪያው    የተሰጠውን ተግባርና ሓላፊነት በብቃት እንዲያከናውን የቅርብ ክትትል ማድረግ፣ አፈጻጸሙን እየተከታተሉ በመገምገም አስፈላጊውን ሁሉ ማሟላት ይገባል፡፡ ምክንያቱም የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ሥርዓት እና አስተምህሮ እንዲሁም ወጥ የሆነው መዋቅራዊ አሠራሯ     ባልተከበረና በተጣሰ ቁጥር የቤተ ክርስቲያኗ ህልውና አጠያያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ለመናፍቃን ሥውር ተልእኮ ምእመናንን ሊያጋልጣቸው ይችላል፡፡ የግል ፍላጐትና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ግለሰቦችም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የምሕረት ዐደባባይ ያለአግባቡ እንዲጠቀሙበት ዕድል ይሰጣል፡፡ ስለዚህ የመምሪያው ጥረት ብቻውን በአንድ እጅ ማጨብጨብ እንዳይሆን  ትኩረት ሊሰጠው ይገባል እንላለን፡፡

ምንጭ፡ስምዐ ጽድቅ ከየካቲት 1-15/2003 ዓ.ም.

ወስብሐት ለእግዚአብሔር