በማ/ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ።

 
(የአሜሪካ ማዕከል፤ አትላንታ፤ ጆርጂያ)፦ “የቤተ ክርስቲያናችንን ህልውና መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ነው” በሚል መሪ ቃል ግንቦት 20, 21 እና 23/ 2003 ዓ.ም ሲካሔድ የቆየው በማ/ቅዱሳን የአሜሪካ ማዕከል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎችን በማሳለፍ እና የ2004 ዓ.ምሕረትን ዕቅድ በማጽደቅ ተጠናቀቀ።

ለ13ኛ ጊዜ በተካሔደው እና የዲሲ እና አካባቢው ሀ/ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አበው፣ ዲያቆናት ወንድሞች፣ የማኅበሩ አባላት ወንድሞች እና እህቶች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የተካሔደው ጉባኤ የማዕከሉን የ2003 ዓ.ም ዓመታዊ የተግባር ድርጊቶች ሪፖርት ከማዳመጡም በላይ በቀረቡት ሪፖርቶች ላይ ውይይት አድርጓል። “የማዕከላችን የአገልግሎት ተግዳሮቶች እና የመፍትሔ አቅጣጫዎች”፣ “የማኅበሩ አባላት ማሕበራዊ ተሳትፎ” እንዲሁም “የቤተ ክርስቲያን አንድነት” በሚሉ ርእሶች ዙሪያ ትምህርቶች ተሰጥተው ውይይቶች ተደርጎባቸዋል።
 
ወደ ኢትዮጵያ ስለሚተላለፍ ሳምንታዊ የሬዲዮ ፕሮግራም ጉዳይ በሰፊው ተወያይቷል። የተዋሕዶ ድምጽ/ድምፀ ተዋሕዶ/ በመባል ስለተሰየመው እና በሳምንት ሁለት ቀን ወደ ኢትዮጵያ መተላለፍ ስለሚጀምረው የሬዲዮ ጣቢያ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አባላት ያጠኑት ጥልቅ ጥናት ከቀረበ በኋላ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።
ማኅበሩ ከዚህ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል የሬዲዮ ዝግጅት በአጭር ሞገድ ሲያስተላልፍ ቆይቶ በሥርጭቱ የሞገድ ጥራት ማነስ ምክንያት ዝግጅቱን በማቋረጥ ጉዳዩን ሲያጠና ቆይቷል። ከረዥም ጊዜ ጥናት በኋላ በተሻለ የሬዲዮ ሞገስ ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ቴክኒካዊ እና ሌሎች መሰል ዝግጅቶችን ሲያከናውን ቆይቶ አሁን ዝግጅቱን ለመጀመር ከመጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱን ማኅበሩ አረጋግጧል። ለዚህ አገልግሎት ሁነኛ ሚና በመጫወት ላይ የሚገኘው የአሜሪካ ማዕከል አባላትም፥ ስለ ሬዲዮው የተደረገውን ገለጻ በመከታተል ከእነርሱ የሚፈለገውን ነገር በመቀበልና ለተግባራዊነቱ ውሳኔ በማሳለፍ አጀንዳው ተጠናቋል።
የ2004 ዓ.ምሕረትን የአገልግሎት ዕቅድ ያደመጠው የማዕከሉ ጠቅላላ ጉባኤ በመጪው ዓመት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ ለኢትዮጵያ” የሚል ዐውደ ርእይ ይካሔድ ዘንድ የቀረበውን ዕቅድ እንዲሁም ስለ ሕጻናት ትምህርት፣ ስለ ስብከተ ወንጌል፣ ስለ ድረ ገጾች መጠናከር፣ በአሜሪካ የሚገኙትን አህጉረ ስብከት ስለመርዳት፣ ቃለ እግዚአብሔርን በመጻሕፍት፣ በጋዜጦችና በተለያዩ የሕትመት ውጤቶች ስለማሰራጨት፣ ሰንበት ት/ቤቶችን ስለመርዳት ወዘተ በጠቅላላው በየአገልግሎት ክፍሎቹ የቀረቡለት ዕቅዶች ላይ ተወያይቶ አጽድቋቸዋል።
ከማዕከሉ አገልግሎት ክፍሎች በተጨማሪ ማዕከሉ ባሉት 11 “ቀጣና ማዕከላት” የተዘጋጁትን ዕቅዶች ተመልክቶ ማሻሻዎችን በማድረግ አጽድቋቸዋል። የ2003 ዓ/ምሕረት አገልግሎትን በተመለከተ የኦዲት እና ኢንስፔክሽንን ሪፖርት አድምጧል። በዚህም ድክመት በታየባቸው የአገልግሎት ዘርፎች ላይ ችግሮችን ለማቃለል የሚያስችሉ መፍትሔዎችን ጉባኤው ለግሷል።
በእንግድነት ከአዲስ አበባ በመጡት በመልአከ ሰላም ጌታቸው ደጀኔ ትምህርት ከመሰጠቱም በላይ፥ የሰሜን አሜሪካ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መልእክትም በተወካዩዋ አማካይነት በንባብ ተሰምቷል።
ጉባኤውን በታላቅ ንቃት የተከታተሉት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃምም በሰጡት ቃለ ምዕዳን በስጋት እና በፍርሃት መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች ከመሥራት ወደ ኋላ ማለት እንደማይገባ መክረው ማዕከሉ የጀመረውን አገልግሎት አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ሰጥተዋል። ጉባኤው በሚከናወንባቸው ጊዜያት በሙሉ እንደማይለዩ፣ ጉዳዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እስከሆነ ድረስ በተልዕኮው ከማኅበሩ ጎን እንደሚቆሙ በማስረዳት ጉባኤተኛውን አበረታተዋል።
የዚህ ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ ሲጠናቀቅም 14ኛውን ጉባኤ በዴንቨር ለማካሄድ ባለተራው ጽዋውን ሲወስድ የሜኔሶታ ቀ/ማዕከል በበኩሉ 15ኛውን ለማዘጋጀት “ማነህ ባለ ሣምንት” የሚለውን ጥሪ ተቀብሏል። “ያብጽዐነ አመ ከመ ዮም …” በሚለው ተስፋ አዘል መዝሙር በቀነ ቀጠሮ ጉባኤተኛው ስብሰባውን አጠናቆ ወደየመጣበት በሰላም ተመልሷል።