ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት

ሰኔ ፴ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዝግጅት ክፍሉ

እንደሚታወቀው ሰኔ ፴ ቀን ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት የተወለደበት ዕለት ነው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን የመጥምቁ ዮሐንስን ታሪክ በአጭሩ እናቀርብላችኋለን፤

ቅዱስ ዮሐንስ የካህኑ ዘካርያስና የቅድስት ኤልሳቤጥ ልጅ ሲኾን፣ የልደቱ ታሪክም እንዲህ ነው፤ በቅዱስ ሉቃስ ወንጌል እንደ ተገለጸው ካህኑ ዘካርያስ እና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ኹሉ በመፈጸም ያለ ነቀፋ የሚኖሩ ጻድቃን ነበሩ፡፡ ኤልሳቤጥም መካን ነበረችና ልጅ አልነበራቸውም /ሉቃ.፩፥፭-፯/፡፡

ልጅ ይሰጣቸው ዘንድም እግዚአብሔርን ዘወትር ይማጸኑት ነበር፡፡ ካህኑ ዘካርያስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ ዕጣን በማሳረግ ላይ ሳለም የእግዚአብሔር መልአክ በዕጣኑ መሠዊያ ቀኝ ቆሞ ጸሎቱ እንደ ተሰማና ሚስቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ እንደምትወልድ፤ ስሙንም ዮሐንስ እንደሚለው፤ በመወለዱም ብዙዎች እንደሚደሰቱ፤ ልጁም በእግዚአብሔር ፊት ታላቅ እንደሚኾንና የወይን ጠጅና የሚያሰክር መጠጥ እንደማይጠጣ፤ እንዲሁም ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ እንደሚሞላበት ነገረው /ሉቃ.፩፥፰-፲፯/፡፡

ካህኑ ዘካርያስም *እኔ ሽማግሌ ነኝ፤ ሚስቴም በዕድሜዋ አርጅታለችና ይህን በምን አውቃለሁ?* አለው፡፡ መልአኩም *እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬ ነበር፡፡ እነሆም በጊዜው የሚፈጸመውን ቃሌን ስላላመንህ ይህ ነገር እስከሚኾን ቀን ድረስ ዲዳ ትኾናለህ፤ መናገርም አትችልም፤* አለው፡፡ ከውጪ ቆመው ጸሎት ሲያደርጉ የነበሩት ሕዝብም ዘካርያስን ከቤተ መቅደስ እስኪወጣ ይጠብቁት ነበር፤ በመዘግየቱም ይደነቁ ነበር /ሉቃ.፩፥፲፰-፳፩/፡፡

ከቤተ መቅደስ በወጣም ጊዜ ሊያናግራቸው ባለመቻሉ ይጠቅሳቸው ነበር፡፡ በዚህም በቤተ መቅደስም ራእይ እንዳየ አስተዋሉ፡፡ እርሱም ድዳ ኾኖ ኖረ፡፡ የማገልገሉም ወራት ሲፈጸምም ወደ ቤቱ ሔደ፤ ከሁለት ቀን በኋላም አረጋዊቷ ቅድስት ኤልሳቤጥ ፀነሰች፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም በመካንነቷ ከሰዎች የሚደርስባት ሽሙጥ ተወግዷላታልና *እግዚአብሔር በዚህ ወራት ከሰው ስድቤን ያርቅ ዘንድ እንዲህ አደረገልኝ* ስትል ለአምስት ወራት ተሸሸገች /ሉቃ.፩፥፳፪-፳፭/፡፡

ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችን ጌታችንን በድንግልና እንደምትወልድ ሲያበሥራት *ወንድ ሳላውቅ ይህ እንዴት ሊኾን ይችላል?* ባለችው ጊዜ እግዚአብሔር ኹሉን ማድረግ እንደሚቻለው ለማስረዳት መካኗ ቅድስት ኤልሳቤጥ በስተእርጅና መውለዷን ጠቅሶላታል፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥ በፀነሰች በስድስተኛው ወር እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልትጠይቃት ወደ እርሷ በሔደች ጊዜም ቅዱስ ዮሐንስ በማኅፀን ውስጥ ኾኖ ለቅድስት ድንግል ማርያም እና በማኅፀኗ ላደረው አካላዊ ቃል (ለኢየሱስ ክርስቶስ) ሰግዷል /ሉቃ.፩፥፳፮-፵፩/፡፡

ቅድስት ኤልሳቤጥም ድምጿን ከፍ አድርጋ *አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው፡፡ የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል? እነሆ የሰላምታሽን ድምፅ በሰማሁ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሏልና፡፡ ከጌታ የተነገረላት ቃል እንደሚፈጸምላት ያመነች ብፅዕት ናት፤* በማለት እመቤታችንን አመስግናታለች /ሉቃ.፩፥፵፪-፵፭/፡፡ የመውለጃዋ ቀን ሲደርስም ሰኔ ፴ ቀን ንዑድ፣ ክቡር የኾነው መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ተወለደ። ዘመዶቹ የሕፃኑን ስም በአባቱ መጠሪያ *ዘካርያስ* ሊሉት ቢወዱም እናቱ ግን *ዮሐንስ ይባል* አለች፡፡

የመልአኩን የብሥራት ቃል ባለመቀበሉ አንደበቱ ተይዞ የነበረው ካህኑ ዘካርያም ስሙ *ዮሐንስ* ይባል ብሎ ሲጽፍ አፉ ተከፈተ፤ አንደበቱም ተፈታና በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ *… አንተ ሕፃን ሆይ የልዑል ነቢይ ትባላለህ፤ መንገዱን ልትጠርግ በጌታ ፊት ትሔዳለህና፡፡ የኃጢአታቸው ስርየት የኾነውን የመዳን ዕውቀት ለሕዝቡ ትሰጣለህ፡፡ ይህም ከላይ የመጣ ብርሃን በጐበኘበት በአምላካችን ምሕረትና ርኅራኄ ምክንያት ነው፡፡ ብርሃኑም በጨለማና በሞት ጥላ ተቀምጠው ላሉት ያበራል፤ እግሮቻችንንም በሰላም መንገድ ያቀናል፤* ብሎ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ነቢይነትና አጥማቂነት፣ እንደዚሁም የክርስቶስን የማዳን ትምህርት እንደሚያበሥር አስቀድሞ ትንቢት ተናገረ /ሉቃ.፩፥፶፯-፸፱/፡፡

ዮሐንስ ማለት *እግዚአብሔር ጸጋ ነው* ማለት ነው፡፡ ትርጓሜ ወንጌልም መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን ፍሥሐ ወሐሴት (ተድላና ደስታ) ይለዋል፤ ወላጆቹ በእርሱ መወለድ ተደስተዋልና /ሉቃ.፩፥፲፬/፡፡

በቅዱስ ወንጌል እንደ ተጻፈ ሄሮድስ የመድኀኒታችን የክርስቶስን መወለድ ከሰብአ ሰገል ሲሰማ መንግሥቴን ይወስድብኛል ብሎ ስለ ሰጋ ጌታችንን ያገኘሁ መስሎት የቤተልሔም ሕፃናትን መግደል ጀመረ /ማቴ.፪፥፩-፲፮/፡፡ በዚህ ጊዜ ቅድስት ኤልሳቤጥ ልጇን ከሞት ለማዳን ስትል ሕፃኑ ዮሐንስን ይዛ ወደ በረሃ ተሰደደች። በበረሃም ድንጋይ ቤት ኾኖላቸው፣ እግዚአብሔርም ከብርድ፣ ከፀሐይና ከአራዊቱ አፍ እየጠበቃቸው መኖር ጀመሩ፡፡ ወደ በረሃ ሲገቡ ቅዱስ ዮሐንስ የሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሕፃን ነበር፡፡ ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ለእስራኤል እስከታየበት ቀን ድረስ በምድረ በዳ ኖረ /ሉቃ.፩፥፹/፡፡

የሄሮድስ ጭፍሮችም ዮሐንስን ፈልገው ባጡት ጊዜ ዘካርያስን በቤተ መቅደስ ውስጥ በሰይፍ ገደሉት፤ ካህናቱም በንጹሕ ልብስ ገንዘው በአባቱ በበራክዩ መቃብር ቀበሩት፡፡ ደሙም እስከ ፸ ዓመት ድረስ ሲፈላ ኖረ። ጌታችንም የዘካርያስ ደም እንደሚፋረዳቸው ሲያስረዳ *ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል* በማለት ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ገሥጿቸዋል /ሉቃ.፲፩፥፶፩/፡፡

ቅድስት ኤልሳቤጥ ወደ በረሃ በገባች በአምስተኛ ዓመቷ፤ ቅዱስ ዮሐንስም ሰባት ዓመት ሲሞላው ሕፃኑን ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፈች፡፡ ቅዱስ ዮሐንስም እግዚአብሔር ከአራዊት አፍ እየጠበቀው፤ ሲርበው ሰማያዊ ኅብስትን እየመገበው ሲጠማውም ውኃ እያፈለቀ እያጠጣው፤ አናብስቱና አናምርቱ እንደ ወንድምና እኅት ኾነውለት በበረሃ መኖር ጀመረ፡፡ በበረሃ ሲኖርም የግመል ጠጉር ይለብስ፣ በወገቡም ጠፍር ይታጠቅ፣ አንበጣ (በአቴና ቀምሲስ፣ በኢትዮጵያ ሰበቦት /የጋጃ ማር/) የሚባል /የበረሃ ቅጠል/ እና መዓረ ጸደንያ /ጣዝማ ማር/ ይመገብ ነበር /ኢሳ.፵፥፫-፭/።

፴ ዓመት ሲሞላውም በነቢዩ በኢሳይያስ ቃል *… የጌታን መንገድ አዘጋጁ፤ ጥርጊያውንም አቅኑ፤ እያለ በምድረ በዳ የሚጮኽ ሰው ድምፅ፡፡ ዐዘቅቱ ሁሉ ይሙላ፤ ተራራውና ኮረብታውም ኹሉ ዝቅ ይበል፡፡ ጠማማውም የቀና መንገድ ይኹን፤ ሸካራውም መንገድ ትክክል ይኹን፡፡ ሥጋም የለበሰ ኹሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፤* ተብሎ እንደ ተነገረ ቅዱስ ዮሐንስ *መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!* እያለ እየሰበከ በዮርዳኖስ ዙሪያ ወዳለው አገር ኹሉ ወጣ /ሉቃ.፫፥፫-፮/።

የይሁዳ አገር ሰዎች ኹሉ ኃጢአታቸውንም እየተናዘዙ ከእርሱ ይጠመቁ ነበር። እርሱም፡- *… እናንተ የእፉኝት ልጆች ከሚመጣው ቍጣ እንድትሸሹ ማን አመለከታችሁ? እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ፤ መልካም ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ኹሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል፤* ይላቸው ነበር፡፡ *ምን እናድርግ?* ብለው ሲጠይቁት *ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፤ ምግብም ያለው እንዲሁ ያድርግ፤* ይላቸው ነበር። ቀራጮችን፡- *ከታዘዘላችሁ አብልጣችሁ አትውሰዱ፤* ጭፍሮችንም፡- *በማንም ላይ ግፍ አትሥሩ፤ ማንንም በሐሰት አትክሰሱ፤ ደመወዛችሁም ይብቃችሁ፤* እያለና ሌላም ብዙ ምክር እየመከረ ወንጌልን ይሰብክላቸው ነበር /ሉቃ.፫፥፯-፲፬/፡፡

በተጨማሪም *… እኔ ለንስሐ በውኃ አጠምቃችኋለሁ፤ ነገር ግን የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ፣ ከእኔ በኋላ የሚመጣውና ከእኔ ይልቅ የሚበረታው እርሱ በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃችኋል፤ መንሹም በእጁ ነው፤ አውድማውንም ፈጽሞ ያጠራል፤ ሥንዴውንም በጎተራው ይከታል፤ ገለባውን ግን በማይጠፋ እሳት ያቃጥለዋል* በማለት የክርስቶስን በሥጋ መገለጥ እና አምላክነት ነግሯቸዋል /ማቴ.፫፥፩-፲፪፤ ሐዋ.፲፫፥፳፬-፳፰/።

ቅዱስ ዮሐንስ ከፈሪሳውያን ወገን የኾኑ ካህናትና ሌዋውያን *ስለ ራስህ ምን ትላለህ?* ብለው በጠየቁት ጊዜም እርሱ ክርስቶስ እንዳልኾነና *የጌታን መንገድ አቅኑ* ብሎ በምድረ በዳ የሚጮኽ ቃለ ዐዋዲ (ዐዋጅ ነጋሪ) መኾኑን ተናግሯል /ሉቃ. ፫፥፲፭-፲፰፤ ዮሐ.፩፥፲፱-፳፫/።

ቅድስት ኤልሳቤጥ *የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል?* /ሉቃ.፩፥፵፫/ ስትል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ መኾኗን እንደ መሰከረችው ኹሉ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችን ሊጠመቅ ወደ እርሱ በሔደ ጊዜ *እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል፤ አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ባሪያ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ እንዴት ጌታ ወደ ባሪያው ይመጣል?* በማለት የጌታችንን አምላክነት በትሕትና ተናግሯል /ማቴ.፫፥፲፬/፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ጌታችንን *… ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለሁ፤ አንተንስ በማን ስም ላጥምቅህ?* ሲለው *እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሥልጣንህ ዘለዓለማዊ የኾነ የዓለሙ ካህን፤ የዓለምን ኃጢአት የምታስወግደው የእግዚአብሔር በግ፤ ብርሃንን የምትገልጽ የእግዚአብሔር አብ የባሕርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይቅር በለን?* እያልህ አጥምቀኝ ብሎት እንደታዘዘው አድርጎ አጥምቆታል፡፡ ቅዱስ ጌታችንን ባጠመቀው ጊዜ ከሰማይ *በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት፤* የሚለውን የእግዚአብሔር አብ ቃል መስማቱንና መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱን በመመስከር ምሥጢረ ሥላሴን አስተምሯል /ማቴ.፲፯፥፭፤ ዮሐ.፩፥፴፬/፡፡

ጌታችንም፡- *ምን ልታዩ ወደ ምድረ በዳ ወጣችሁ? … ነቢይን? አዎን ይህ ከነቢይም ይበልጣል። (እነሆ መንገድህን በፊትህ የሚጠርግ መልክተኛዬን በፊትህ እልካለሁ) ተብሎ የተጻፈለት እርሱ ነው፤ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም፤ ልትቀበሉትስ ብትወዱ ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው፤ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ* በማለት የቅዱስ ዮሐንስን ታላቅነት ተናግሯል /ማቴ.፲፩፥፱-፲፩/።

ኤልያስ ፀጉራም እንደ ኾነ ኹሉ ዮሐንስም ልብሱ የግመል ፀጉር መኾኑ፤ ሁለቱም መናንያን፣ ጸዋምያን፣ ተሐራምያን (ፈቃደ ሥጋን የተዉ)፣ ዝጉሐውያን (የሥጋን ስሜት የዘጉ)፣ ባሕታውያን መኾናቸው፤ በተጨማሪም ኤልያስ አክአብና ኤልዛቤልን፣ ዮሐንስ ደግሞ ሄሮድስና ሄሮድያዳን መገሠፃቸው፤ ኤልያስ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ቀድሞ እንደሚመጣ ኹሉ ዮሐንስም ከክርስቶስ ቀዳሚ ምጽአት (በአካለ በሥጋ መገለጥ) ቀድሞ ማስተማሩ ያመሳስላቸዋልና ጌታችን ዮሐንስን ኤልያስ ብሎታል። *እነርሱም ስለ ዮሐንስ እንደ ነገራቸው አስተዋሉ፤* ተብሎ እንደ ተጻፈ /ማቴ.፲፩፥፪-፲፱/።

በአጠቃላይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ከአዲስ ኪዳን አበው አንዱ የኾነ፣ ንጹሓን ነቢያት፣ ቅዱስ ገብርኤልና አባቱ ዘካርያስ ትንቢት የተናገሩለት፣ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ቅኑት እንደ ገበሬ፣ ጽሙድ እንደ በሬ ኾኖ እግዚአብሔርን ያገለገለ፣ በፍጹም ልቡ ዓለምን የናቀ፣ ከተድላዋና ከደስታዋም የተለየ፣ አምላክን ለማጥመቅ የታደለ ሐዋርያ፣ መምህር፣ ሰማዕት፣ ባሕታዊ፣ ነቢይ፣ ጻድቅ ነው፡፡

ሊቁም ከመላእክት፣ ከነቢያት፣ ከካህናት፣ ከሐዋርያት መካከል እንደርሱ መለኮትን ለማጥመቅ የተመረጠ አለመኖሩን በመጥቀስ *ዮሐንስ ከማከ ሶበ ፈተዉ ወጽሕቁ፤ እሳተ ነዳዴ ኢተክህሎሙ ያጥምቁ፤ ራጉኤል በትጋሁ ወኢዮብ በጽድቁ፤ ዮሐንስ ሆይ ራጉኤል በትጋቱ፣ ኢዮብም በጽድቁ ቢመኙም ሆነ ቢጨነቁ እንደ አንተ የሚነድ እሳትን (መለኮትን) ሊያጠምቁ አልተቻላቸውም* ሲል መስክሮለታል /መልክአ ዮሐንስ መጥምቅ፣ ለአዕይንቲከ/፡፡

በመጨረሻም መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ *ድንበር አታፍርሱ፤ ዋርሳ አትውረሱ፤* እያለ ንጉሡ ሄሮድስንና ሄሮድያዳን በመገሠፁ ምክንያት አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የራስ ቅሉ ክንፍ አውጥቶ በዓለም እየተዘዋወረ ፲፭ አምስት ዓመት ወንጌልን አስተምሯል፡፡

ቅዱስ ዮሐንስ ሰኔ ፴ ቀን የተወለደበት፤ መስከረም ፩ ቀን ቃል ኪዳን የተቀበለበት፤ መስከረም ፪ ቀን በሰማዕትነት ያረፈበት፤ ጥር ፲፩ ቀን ጌታችንን ያጠመቀበት፤ የካቲት ፴ ቀን ራሱ የተገኘችበት፤ ሚያዝያ ፲፭ ቀን ራሱ ያረፈችበት (ነፍሱ የወጣችበት)፤ ሰኔ ፪ ቀን ደግሞ ፍልሰተ ዐፅሙ (ዐፅሙ የፈለሰበት) በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡

የቅዱስ ዮሐንስ ሕይወቱና ትምህርቱ፣ ያደረጋቸው ድንቆችና ተአምራት፣ እንዲሁም እግዚአብሔር የሰጠው ቃል ኪዳንና ሰማዕትነቱ በገድሉ በሰፊው ተጽፏል፡፡ እኛም ክብሩን ለማስታወስ ያህል ይህንን አቀረብን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፤ እኛንም በቅዱስ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከቱም ይጠብቀን፡፡

ምንጭ፦ መጽሐፈ ስንክሳር፤

ትርጓሜ ወንጌል (ወንጌለ ሉቃስ)፤

ገድለ ዮሐንስ መጥምቅ፡፡