የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም

ቅዱስ ሲኖዶስ ጠንካራ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል

ግንቦት 10/2003 ዓ.ም.

በቤተክርስቲያኒቱ አጠቃላይ ሁኔታ ላይ የሚመክረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በቀጣይ በቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎት መጠናከርና በገጠሟት ችግሮች ላይ መፍትሔን የሚሰጥ ጠንካራ ውሳኔ ያሳልፋል ብሎ እንደሚያምን ማኅበረ ቅዱሳን አስታወቀ፡፡ የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም እንዳስታወቁት፤ ዘንድሮ ከግንቦት 10 ቀን ጀምሮ የሚካሔደው ዓመታዊ መደበኛ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በእግዚአብሔር አጋዥነት እና በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ በመሆኑ ጠቃሚ ሀሳቦች የሚነሡበት፤ ለቅድስትቤተክርስቲያን የሚበጁ ጠንካራ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን ማኅበረ ቅዱሳን በፅኑ ያምናል፡፡
 
«በቅድስት ቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለው ቦታና ልዕልና ከፍተኛ ነው፤ ስለዚህም የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና ከማስጠበቅ፣ በየጊዜው የሚያጋጥሟትን ችግሮችና ፈተናዎች ላይየማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም ውሳኔዎችን ከማሳለፍ አንፃር የጉባኤው ውጤት በጉጉት ይጠበቃል» ያሉት ሰብሳቢው፤ ይህ ይሆን ዘንድ ማኅበሩ ምኞቱን ይገልጣል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የቤተክርስቲያኒቱን ሥርዓት፣ዶግማ እና ቀኖናዋን እንዲሁም ማንነቷን የሚሸረሽር ትልቅ የተሐድሶ እንቅስቃሴ መኖሩን የጠቆሙት ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ፤ በዚህ ላይ የሲኖዶሱ ውሳኔ ወቅታዊነት ያለው ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
በፀረ ቤተክርስቲያን ኃይሎች መንፈሳዊ ተቋማትና ገዳማትን የመበረዝ፣ ውስጧንም የመቀየርና ማንነቷን የማጥፋት ሰፊ ሥራ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰው በእነዚህና በመሳሰሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ እንቅፋቶች ላይ ጉባኤው መክሮ የሚያሳልፈው ውሳኔ ጠቃሚ እና ተስፋ ሰጪ  እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልጠዋል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎ ለማስፈፀሚያነት የሚወጡ መመሪያዎችንና ደንቦችን በአግባቡ የመከታተልና የመቆጣር ሓላፊነትም የቅዱስ ሲኖዶስ መሆኑን ጠቅሰው፤ አፈጻጸሙ ላይ ማኅበሩ የቤተክርስቲያኒቱ አካል እንደመሆኑ መጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል፡፡

እንደ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩም ገለጻ፤ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውሳኔዎችን እንደ ቅድስት ቤተክርስቲያን አካልነቱ ከመፈጸም እና ከማስፈጸም በተጨማሪ ማኅበሩ ባለው የኅትመት ውጤቶች ማለትም በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ በሐመር መጽሔት እና በሌሎች የኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ለምእመናን የማድረስ ሓላፊነቱን ይወጣል፡፡ ማኅበሩ በቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያና ደንብ መሠረት የተዋቀረ በመሆኑ ለቤተክርስቲያኒቱ ያለውን አጋዥነት አሁንም በተግባር ማረጋገጡን እንደሚቀጥል የጠቀሱት ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ በአባቶች ምክር፣ ምርቃትና ቡራኬ የሚመራ መሆኑ አገልግሎቱን እንዳገዘው ተናግረዋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎችን የማኅበሩ አባላትም ሆኑ ምእመናን አክብረው ተግባራዊ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡