ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም

ዲ/ን ቀለመወርቅ ሚደቅሳ

በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የረጅም ዘመን ሐዋርያዊ ጉዞ ላይ በጎ ተፅዕኖ ካላቸው የአራተኛው መ/ክ/ዘመን አባቶች መካከል አንዱ ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ነው፡፡ይህ አባት ምንም እንኳን በቋንቋ ውሱንነትና በቦታ ርቀት በርካቶች ሥራዎቹና ጽሑፎቹ የታወቁለት ባይሆንም ሕይወቱን በብሕትውና የመራ የትርጓሜ መጻሕፍትን ፣የቅኔ፣ የግጥምና የወግ ጽሑፍ በማዘጋጀት የኖረ ባለ በጎ ገድል አባት ነው፡፡

የቅዱስ ኤፍሬምን ሥራዎች በማሰባሰብ በመጽሐፍ መልክ ካወጡ ሰዎች አንዱ የሆነው (ዶ/ር ሰባስትያን ብሮክ) ’the Luminous Eye’’ በሚል ርዕስ ካዘጋጀው መጻሕፍ  ውስጥ ጎላ ጎላ ያሉትን ትምህርቶች እየተረጎምን ልናቀርብ ወደድን፡፡ ይህም ክፍል አንድ መግቢያ ሆኖ የቅዱስ ኤፍሬምን ሕይወትና ሥራዎች በአጭሩ የሚቀርብበት ነው፡፡

የቅዱስ ኤፍሬም ሕይወቱ

የቅዱስ ኤፍሬም ሀገረ ውላዱ ከዋክብትን ከሚያመልኩ ሰዎች መካከል ነው፡፡ አባቱም ክርስትናን የሚጠላ ካህነ ጣዖት ነበር፡፡ አንዳንድ ምንጮች ከቅዱስ ኤፍሬም ሕይወት በመነሳት ወላጆቹ ክርስቲያኖች እንደነበሩ ዘግበዋል፡፡ የሐምሌ አስራ አምስት ስንክሳር ግን የአባቱን ካህነ ጣዖትነት ያረጋግጣል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም የተወለደው  በ306 ዓ.ም ገደማ “በሜሶፖታሚያ” ውስጥ በምትገኝ “ንጽቢን” እንደሆነ ይታመናል።(ንጽቢን   በደቡባዊ ቱርክ እና በምዕራባዊ ሶርያ መካከል የምትገኝ ቦታ ናት፡፡) ይህቺም ቦታ ከ318ቱ ሊቃውንት አንዱ የነበረው የቅዱስ ያዕቆብ ሀገረ ሰብከቱ የነበረች ናት፡፡

ይህንን ታላቅ አባታችንን የእግዚአብሔር መንፈስ አመላክቶት ወደ ቅዱስ ያዕቆብ ሄዶ ትምህርተ ክርስትናን ተምሮ የተጠመቀ ሲሆን ከወላጆቹ ጋር የኖረው እስከ አሥር ዓመቱ ብቻ ነው፡፡ በትምህርተ ክርስትና አምኖ ከተጠመቀ በኋላ ግን በቅዱስ ያዕቆብ ዘንድ በብሕትውና ተወስኖ በመማርና በማስተማር በንጽቢን ለሚገኘው መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ሓላፊ እስክመሆን ደርሶ ነበር፡፡

በ393 ዓ.ም የንጽቢን ከተማ  በወራሪዎች እጅ ስትወድቅ ቅዱስ ኤፍሬም ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር በመሆን የሮም ግዛት ወደነበረችው ኤዴሳ (ታናሽ እስያ፣ዑር) ተሰደደ፡፡ ይህቸ ቦታ ቅዱስ ኤፍሬም ከመናፍቃን ጋር የተጋደለባት፣ በቤተክርስቲያን ትምህርት ላይ ያላቸውን አብዛኞቹን የክህደት ትምህርቶች የሞገተባትና  መጻሕፍቱን ያዘጋጀባት ናት፡፡አብዛኛዎቹን ትምህርቶቹንና መጻሕፍቱን ያዘጋጀው በዚች በኤዴሳ በሚገኘው ትምህርት ቤት ነው፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም ከመምህሩ ከቅዱስ ያዕቆብ ጋር በመሆን በአርዮስ ምክንያት በተካሄደው  የኒቅያው ጉባኤ    ( 325 ዓ.ም ) ላይ ተገኝቷል፡፡ በዚህም የአርዮስን ክህደትና ምክንያተ ውግዘት ተገንዝቧል፡፡

ከኒቅያ ጉባኤ መልስ መንፈሰ እግዚአብሔር በራዕይ በገለፀለት መሠረት ቅዱስ ኤፍሬም ከቅዱስ ባስልዮስ (ቁጥሩ ከ318ቱ ሊቃውንት ወገን ነው) ዘንድ ለመገናኘት ወደ ቂሣርያ ሄዷል፡፡ ቅዱስ ባስልዮስም የዲቁና ክህነት ሠጥቶ ከሀገረ ስብከቱ ከፍሎ እንዲያስተምር ወስኖ በእርሱ ዘንድ አኑሮታል፡፤ በዚያም ቦታ ብዙ ተአምራትን አድርጓል( መጻሕፍትንም ጽፏል፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም በትውፊት እንደሚታወቀው ምንኩስናን በገቢር ገለጣት እንጂ ሥርዓተ ምንኩስናን መፈጸሙን በግልጽ የሚመለክት ማስረጃ አልተገኘም፡፡ እንዲያውም በሶርያውያን ክርስቲያኖች የሚዘወተረውን ራስን በአንድ ስፍራ ወስኖ በብሕትውናና በመምህርነት ቤተክርስቲያንን የማገልገል (Proto-monasticism) ሕይወት ይኖር እንደነበር ይታመናል፡፡ በትውፊት ቅዱስ ኤፍሬም ቅዱስ ባስልዮስን ለመጎብኘት ወደ ቀጰዶቅያ እንዲሁም አባ ቢሾይን ለመጎብኘት ወደ ግብጽ እንደተጓዘ የሚነገረውም ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው፡፡

ፍጹም በሆነ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቱ ምሳሌ በሚሆነው ትምህርቱና የምናንኔ ሕይወቱ የሚታወቀው ቅዱስ ኤፍሬም ሐምሌ አስራ አምስት ቀን በ 370 ዓ.ም አርፏል፡፡በዚህ ሁሉ ትጋቱም ሶርያውያን ክርስቲያኖች ‹ጥዑመ ልሳን›፣ ‹መምህረ ዓለም›፣ ‹ዓምደ ቤተ ክርስቲያን› በማለት ይጠሩታል፣ያወድሱታል፣ያመሰግኑታል፡፡የቅዱስ አባታችን ረድኤትና በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን፡፡ አሜን!

የቅዱስ ኤፍሬም ሥራዎች

ቅዱስ ኤፍሬም እንደሌሎች የ4ኛው  መ/ክ/ዘ አበው በርካታ ትምህርቶችንና መጻሕፍትን የጻፈና ያዘጋጃ አባት ነው፡፡ ይህንንም ስንክሳር እንዲህ ይገጸዋል፡፡

እጅግም ብዙ የሆኑ 14 ሺህ ድርሳናትንና ተግሳጻትን ደረሰ፤ ከእርሳቸውም ውስጥ አምላክን የወለደች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ውዳሴዋን ነው፡፡ ‹አቤቱ የጸጋህን ማዕበል ግታልኝ ‘ እስከሚል ድረስ ድርሳናትን ደርሶአል፡፡ (ስንክሳር ዘሐምሌ 15 ተመልከት)

በአሁኑ ዘመን የቅዱስ ኤፍሬም መጻሕፍትና ትምህርቶች እንደሌሎቹ የ4ኛው  መ/ክ/ዘ አበው ሥራዎች ጎልተው የታወቁ አይደሉም፡፡ ለዚህም ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው፡፡

1. ቅዱስ ኤፍሬም አብዛኛዎቹን ትምህርቶችና መጻሕፍትን ያዘጋጀው በዘመኑ ብዙ ተጽእኖ በነበራቸው በግሪክ ወይም በላቲን ቋንቋዎች ሳይሆን በሱርስት በመሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ ሊቃውንት ይህን እውነት እንደ መልካም ነገር ይጠቅሱታል፡፡ ወንጌል በግሪክ ከመጻፏ በፊት የተሰበከችው በሱርስት ነው( ጌታም ያስተማረው በዚሁ ቋንቋ ነው በማለት ይህም የሶርያ ክርስትና በግሪካዊው ፍልስፍና ያልተጠቃ (Little Hellenized) እንዲሆን ያደረገ ነው በማለት እንደመልካም ነገር ይጠቅሱታል። 

2. ቅዱስ ኤፍሬም ትምህርተ ክርስትናን ከሌሎች አበው ለየት ባለ መልኩ በጥበባዊ ስልት (በግጥም፣በቅኔ፣በደብዳቤ፣በጥያቄና መልስ) በማዘጋጀቱና አብዛኞቻችን በዚህ ስልት ጠንከር ያለ ትምህርተ ክርስትና ይገኛል ብለን ስላላመንን ወይም ዝንባሌው ስለሌለን ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ ዘመን በርካታ መጻሕፍት የቅዱስ ኤፍሬም ናቸው እየተባሉ ሲሰራጩ እናስተውላለን። አብዛኛዎች ግን የእርሱ አይደሉም ፤በተለይ የመጀመሪያ ጽሕፈተ ቋንቋቸው ግሪክ የሆኑት።ስለዚህ መጻሕፍቱን ከመጠቀማችን በፊት የቅዱስ ኤፍሬም ድርሰቶች መሆናቸውን ማወቅ ይገባል፡፡

የቅዱስ ኤፍሬም የጽሑፍ ሥራዎች

እነዚህን ጽሑፎች ጠቅለል አድርጎ በአራት መክፈል ይቻላል፦
1. ቀጥተኛ ትርጓሜያት፡- ይህ ክፍል ከመጽሐፍ ቅዱስ አንዱን መጽሐፍ በመውሰድ የተጻፉ ትርጓሜያትን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ምሳሌ – የኦሪት ዘፍጥረት፣ የኦሪት ዘፀአትና የግብረ ሐዋርያት ትርጓሜያትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
2. ጥበበባዊ (Artistic) ትምህርቶች (ትርጓሜያት)፦ በግጥም ወይም በሌላ ጥበባዊ መልክ የተጻፉ ትርጓሜያትን የሚያካትት ነው፡፡ ‹በእንተ ክርስቶስ› (በጥያቄና መልስ የቀረበው) ትምህርት ተጠቃሽ ነው፡፡ እንዲሁም ‹በነገረ ምጽአት ላይ ለፑከሊየስ የተጻፈው ደብዳቤም፡፡›
3. በቁጥር የተደረጉ ስብከቶች (Verse homilies)፦ አንድን ርዕስ በማንሳት የተሰጡ ስብከቶችን የምናገኝበት ክፍል ነው፡፡ ‹በእንተ እምነት› የተሰኘው ስብከቱ ተጠቃሽ ነው፡፡
4. የዜማ ወይም የቅዳሴ ድርሰቶች፡፡

ቅዱስ ኤፍሬምና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያዘጋጀቻቸውን አብዛኛዎችን የትርጓሜ መጻሕፍት ያጠኑ ሊቃውንት መጻሕፍቱ የኤዴሳ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የትርጓሜ ስልትና የምስጢር ፤ የዘይቤ አንድነት እንደሚስተዋልባቸው ያስረዳሉ፡፡ ከዚያ ውጪ በውዳሴ ማርያምና በአንቀፀ ብርሃን መካከል ያለው የአንድነት ጉዳይ ከትርጓሜ መጻሕፍት ወደ ጸሎት መጻሕፍትም ሊራመድ እንደሚችል ያስገነዝባል፡፡ ለዚህ ሃሣብ መቋጫ የስርግው ሐብለ ሥላሴን ንግግር እናቅርብ፡-

‹ኤፍሬም (ሶርያዊ)› የሶርያ ተወላጅ እርሱ የደረሳቸው መጻሕፍት ወደ ግእዝ ብዙዎቹ ተመልሰዋል፡፡ በተለይ ውዳሴ ማርያም በየዕለቱ በሕዝበ ክርስቲያን የሚጸለይ ጸሎት ነው፡፡

በመጽሐፈ አክሱም እርሱና አባ ሕርያቆስ የተባለው ቅዳሴ ማርያም የደረሰው ወደ አክሱም መጥተው ማይ ከርዋህ በሚባል ስፍራ ተገናኝተው ኤፍሬም ያሬድን ውዳሴ ማርያምን ሕርያቆስን ደግሞ ቅዳሴዋን እንዳስተማረው በሰያፍ መንገድ ይገለጻል፡፡ እዚህ ላይ ዋናው ቁም ነገር ቅዱስ ያሬድ በስድ ንባብም ሆነ በግጥም መልክ የደረሳቸው ድርሰቶች የሶሪያ ቤተክርስቲያን ባህል የተከተሉ መሆናቸውና የሶርያ ቤተክርስቲያን ለኢትዮጵያ መንፈሳዊ እድገት ከፍ ያለ አስተዋጽዖ እንዳደረገች የሚያሳይ ነው፡፡ (አማርኛና የቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት ረቂቅ ኤፍሬም የሚለውን ተመልከት)፡፡

ይቆየን !