ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ

ነሐሴ ፫ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

.jpj

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን

‹‹ወሰላሙ ለክርስቶስ ይጽናዕ በልብክሙ ዘሎቱ ተጸዋዕክሙ በአሐዱ ሥጋ፤ በአንድ አካል የተጠራችሁለት የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይጽና፤›› (ቆላ 3÷15)::

ይህ ቃል ሰው ሁሉ ለሰላም እንደተጠራ፣ ልቡንም ለሰላም ማስገዛት እንዳለበት ያስገነዝበናል፤ በእርግጥም ለሰው ከሰላም የበለጠ አስፈላጊ ነገር የለምና ለሰላም መገዛት ተገቢ ነው፡፡

ሰው ከሰላም ተጠቃሚ እንጂ ተጐጂ የሆነበት ጊዜም፣ ቦታም የለም፤ የሰላም ክፍተት ከተፈጠረ ጣልቃ ገቢው ብዙ ከመሆኑ አንጻር ሕይወት ይጠፋል፤ ሀብት፣ ንብረት ይወድማል፤ ልማት ይቆማል፤ ድህነት ይስፋፋል፤ መጨረሻው እልቂት ይሆናል፡፡

ታዲያ ይህ እንዳይሆን ሰው ሁሉ ለራሱና ለሀገሩ ሲል የሰላም ተገዢ መሆን ይኖርበታል፡፡ ሰላም እንደ ተራ ነገር የምትታይ አይደለችምና በአፋችን ብቻ ሳይሆን በልባችን ውስጥ፣ በጥገኝነት ሳይሆን በገዢነት እንድንቀበላት በጌታችን በአምላካችንና በመድኃታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተሰጥታናለች፤ ከዚያ አኳያ ቤተ ክርስቲያናችን በሰላም ላይ ያላት አቋም የማይናወጥ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በታሪኳ የፈጸመቻቸው፣ እየፈጸመቻቸው ያሉትና ለወደፊትም የምትፈጽማቸው ሁሉ የመጨረሻ ግባቸው ሰላም ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገር መሥራች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እናት፣ እንመሆኗ መጠን የሰላም፣ የፍቅር፣ የሕዝቦች አንድነትና ነጻነት ጠበቃ ሆና የኖረች ቤተ ክርስቲያን እንደሆነች ማንም የማይስተው ሐቅ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን ሃይማኖታዊ፣ ሕዝባዊና ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ስትወጣ ሕገ እግዚአብሔርን ማእከል አድርጋ በምትሠራው ሥራ የአማኙን ቀልብ በከፍተኛ ደረጃ በመሳብ እንደሆነም ይታወቃል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከውጭ የሚመጣ ወራሪ ኃይል ሲያጋጥም በጸሎትና በምህላ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ከመዘርጋት ጋር ታቦቷን፣ መስቀሏንና ሥዕሏን ይዛ፣ ከሕዝቡ ጋር በግንባር ተገኝታ ስለ ሃይማኖት ህልውና፣ ስለ ሕዝብ ክብርና ስለ ሀገር ልዕልና መሥዋዕት ስትከፍል የቆየች አሁንም ያለችና ለወደፊትም የምትኖር ናት፡፡

በአንጻሩ ደግሞ በሀገር ውስጥ አለመግባባት ሲፈጠር አንዱን ካንዱ ሳትለይና ሌላውን ሳታገል ሁሉንም በእኩልነትና በልጅነት መንፈስ በማየት ስትመክር፣ ስታስተምርና ስታስማማ የነበረች፣ አሁንም ያለች፣ ለወደፊትም የምትኖር የቁርጥ ቀን እናት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

የሀገራችን ሕዝቦች በሚያስደንቅ ሁኔታ አንድነታቸውንና ነጻነታቸውን፣ ወንድማማችነታቸውንና ፍቅራቸውን ጠብቀው ለሦስት ሺሕ ዘመናት ሊዘልቁ የቻሉት በቤተ ክርስቲያናችን ሃይማኖታዊ ሰላማዊ አስተምህሮ እንደሆነ የማይካድ ሐቅ ነው፡፡

የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን !!

ከጥንት ጀምሮ ተጠብቆየኖረ የሕዝባችን ተከባብሮ፣ ተስማምቶና ተሳስቦ የመኖር ሃይማኖታዊ ባህላችን በተከበረ ቁጥር፣ ደማቅ የሆነና ዘመናትን ተሻጋሪ የሆነ ታሪክ ለመሥራት የተመቻቸ ዕድል እንደሚፈጥርልን የዘመናችን ልዩ ገጸ በረከት የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እና በዓለም የተመሰከረው ኢኮኖሚያዊ እድገታችን ማስረጃ ነው ፤ በታሪክ እጅግ በጣም ጉልህና ደማቅ ታሪክ ሆኖ የሚመዘገበው የዓባይ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሕዝባችን የሰላምና የወንድማማችነት ፣ የፍቅርና የስምምነት ውጤት መሆኑን ልንዘነጋው አይገባም፡፡

ሀገራችን ጥንታዊትና ታላቅ ብትሆንም በመካከል ባጋጠመን የኢኮኖሚ እጥረት ምክንያት ፣ የድህነት መጣቀሻ እስከመሆን የደረስንበትን ክሥተት ለመለወጥ የሀገራችን ሕዝቦች ዳር እስከ ዳር ደፋ ቀና በሚሉበት በአሁኑ ጊዜ አልፎ አልፎ እየታዩ ያሉ ግጭቶች ቤተ ክርስቲያንን እያሳሰቧት ነው፡፡

ችግሩም እየታየ ያለው በልጆቿ መካከል በተፈጠረው ውዝግብ በመሆኑ ጉዳዩ አላስፈላጊ ከመሆኑም ሌላ የሚፈጥረው ጠባሳም በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

በዚህም ምክንያት በተፈጠረው አለመረጋጋት የልጆቻችን ሕይወት ማለፉን ፤ እንደዚሁም የብዙ ዜጎች ንብረት ፣ ሀብትና ቤት ለውድመት መዳረጉን ቤተ ክርስቲያናችን ስትሰማ ሁኔታው በእጅጉ አሳዝኖአታል፡፡

ችግሩ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በወንድማማችነታቸው ነቅ ታይቶባቸው በማይታወቁ ኢትዮጵያውያን ልጆቿ መካከል በመከሠቱም የቤተ ክርስቲያናችንን ኀዘን ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡

በመሆኑም ይህ ውዝግብ በዚህ ዓይነት ቀጥሎ የልጆቻችን ሕይወት ጥበቃና የዜጎቻችን በሰላም ሠርቶ የመኖር ዋስትና ተቃውሶ ከዚህ የባሰ እክል እንዳያጋጥም፣ እንደዚሁም እየተካሄደ ያለው የልማት መርሐ ግብር እንዳይደናቀፍ በማሰብ ቤተ ክርስቲያናችን ባላት የእናትነት ኃላፊነት የሚከተለውን መግለጫ አውጥታለች፡-

  1. ቤተ ክርስቲያናችን ‹‹ይጥዕመኒ ስማ ለሰላም›› ማለትም ‹‹የሰላም ስሟ ሁልጊዜም ይጥመኛል›› እያለች ስለ ሰላም ጥቅም ብቻ ሳይሆን ስለ ሰላም ስም ተወዳጅነት ጭምር ዘወትር የምትዘምርና የምትጸልይ ናትና አሁን ተከሥቶ ያለው ውዝግብና ተሐውኮ ቆሞ ችግሮች ሁሉ በሕጋዊ መንገድ፣ በወንድማማችነት መንፈስና በውይይት ይፈቱ ዘንድ በዚህ በያዝነው የጾም ሱባኤ በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ጸሎተ ምህላና የሰላም ትምህርት ተጠናክሮ እንዲካሄድ፤
  1. በየአካባቢው የሚገኙ አዛውንቶችና ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና አባወራዎች እንዲሁም እማወራዎች ልጆቻቸውንና የአካባቢው ወጣቶችን በመምከርና በማስተማር የሰው ሕይወትን ከጥፋት፣ የሀገር ሀብትን ከውድመት እንዲታደጉ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤
  1. ሁሉም ወገኖች አለን የሚሉትን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ፣በውይይትና በምክክር እንዲሁም በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ በመጓዝ ችግሩንለመፍታት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ያደርጉ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች፡፡
  1. በተፈጠረው ዉዝግብ ሕይወታቸውንና ሀብት ንብረታቸውን ላጡ ልጆቻችንና ዜጎቻችን ቤተ ክርስቲያናችን ጥልቅ የሆነ ኃዘኗን ትገልጻለች፤ በዚህም ሕይወታቸውን ያጡትን ወገኖች እግዚአብሔር በመንግሥቱ እንዲቀበልልን ቤተሰቦቻቸውንም እንዲያጽናናልን እግዚአብሔርን እንለምነዋለን፤ ለወደፊትም እንደዚህ ዓይነቱ ያለአስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስ ተግተን እንጸልያለን፡፡
  1. ቅዱስ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔርን በመምሰልና በጭምትነት ሁሉ ጸጥ እና ዝግ ብለን እንድንኖር ልመናና ጸሎት ምልጃና ምስጋናም ስለሰዎች ሁሉ፣ ስለ ነገሥታትና ስለ መኳንንትም ሁሉ እንዲደረጉ ከሁሉ በፊት እመክራለሁ፤ ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በመድኃኒታችን በእግዚአብሔር ፊት መልምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው›› (1ጢሞ2፡1-3) ብሎ እንደሚያስተምረን የሀገራችንና የሕዝባችን ሰላምና ፀጥታ ተጠብቆ ይቀጥል ዘንድ በየሀገረ ስብከቱ ያላችሁ ሊቃነ ጳጳሳት፣ በየገዳማቱ የምትገኙ አበው መነኮሳት፣ መምህራንና ሰባክያነ ወንጌል በየዐውደ ምሕረቱ የሰላምና የፍቅር፣ የአንድነትና የስምምነት ትምህርትና መልእክት በማስተላለፍ ሕዝቡን ከጉዳትና ከመቃቃር ትጠብቁ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም ጥሪዋን አደራ ጭምር ታስተላልፋለች፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ 3 ቀን 2008 ዓ.ም

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ