ሱባዔና ሥርዓቱ – ክፍል አንድ

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

ነሐሴ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

አሁን ያለንበት ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ጾመ ፍልሰታን የሚጾሙበት፣ ሱባዔ የሚገቡበት ጊዜ ነውና ወቅቱን የሚመለከት ትምህርት ይዘን ቀርበናል፡፡ መልካም ንባብ!

ሱባዔ ምንድን ነው?

‹ሱባዔ› በሰዋስዋዊ ትርጕሙ ‹ሰባት› ማለት ነው፡፡ ሱባዔ በመንፈሳዊ አተረጓጐም አንድ ሰው ‹‹ከዚህ ቀን እስከዚህ ቀን በጸሎት ከፈጣሪዬ ጋር እገናኛለሁ›› ብሎ የሚያቅደው መንፈሳዊ ዕቅድ ነው፡፡ ሰባት ቍጥር በእስራኤላውያን ዘንድ በሥራም በቃልም የሚገለጥ ፍጹም ቍጥር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- ፈጣሬ ዓለማት እግዚአብሔር በሰባተኛው ቀን ሥነ ፍጥረትን ከመፍጠር ማረፉ፣ ለጸሎት የሚተጉ ምእመናን በቀን ለሰባት ጊዜ ማመስገናቸው የሰባት ቍጥርን ፍጹምነት ያመለክታል (ዘፍ. ፪፥፪፤ መዝ. ፻፲፰፥፷፬)፡፡ ከዚህ አንጻር አንድ ሰው ለሰባት ቀናት ቢጾም አንድ ሱባዔ ጾመ ይባላል፡፡ ለዐሥራ አራት ቀን ቢጾም ደግሞ ሁለት ሱባዔ ጾመ እያለ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ሱባዔ መቼ ተጀመረ?

ሱባዔ የተጀመረው ከውድቀት በኋላ በመጀመሪያው ሰው በአዳም ነው፡፡ ቅዱሳን መላእክት አዳምን ጸሎት መጸለይን እንዳስተማሩት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡ መላእክት ለአዳም የጊዜያትን ስሌት አስተምረውት ነበር (ቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ)፡፡ አዳም ጥፋቱን አምኖ ከባሕር ውስጥ ሱባዔ በመግባቱና በመጸለዩ እግዚአብሔር በማይታበል ቃሉ ‹‹ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ሲል ቃል ኪዳን ገብቶለታል (መጽሐፈ ቀሌምጦስ፣ አንቀጽ አራት)፡፡

ሱባዔ ለምን?

የሰው ልጅ ኃጢአት በሚስማማው የሥጋ ሰውነቱ ዘወትር ፈጣሪውን ይበድላል፡፡ በፈጸመው በደል ሕሊናው ይወቅሰዋል፤ ይጸጸታል፡፡ በመጀመሪያ ደፍሮ በሠራው ኃጢአት በኋላ ይደነግጣል፡፡ ይህ በማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሕሊና ውስጥ የሚፈራረቅ ጉዳይ፡፡ በዚህ ጊዜ የፈጣሪውን ይቅርታ ለማግኘት ያስባል፤ ይተክዛል፡፡ ‹‹ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝ ሌላ ሕግ አያለሁ፡፡ እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ? ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?›› እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ (ሮሜ. ፯፥፳፪፥፳፭)፡፡ ሰው በደፋርነቱ የኃያሉን አምላክ ትእዛዝ በተላለፈ ጊዜ የትካዜ ሸክም ሲያስጨንቀው ሸክሙን የሚያቃልልበትና የሚያስወግድበት መንፈሳዊ ጥበብ ከቸሩ ፈጣሪ ተሰጥቶታል፡፡ ይኸውም በጥቂት ድካመ ሥጋ ጸጋ እግዚአብሔር የሚያገኝበት ሥርዓት ሱባዔ ነው፡፡ ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አንድ ሰው በትካዜ ሸክም መንፈሱ ሲታወክ የነፍስና የሥጋ ጸጥታውን ለመመለስና ለማስከበር መጾምና መጸለይ ግድ ይኾንበታል፡፡ በዚህ ጊዜ አመክሮ (ሱባዔ) ይገባል፡፡ ሱባዔ የሚገባውም ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት መሠረታዊ ጉዳዮች ነው፤

፩. እግዚአብሔርን ለመማጸን

ሰው ሱባዔ ከሚገባባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ እግዚአብሔርን ለመማጸን ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሱባዔ ሲገባ በቁርጥ ወደ ፈጣሪው የሚያቀርበው ተማኅጽኖ ሊኖረው ይገባል፡፡ ምንም የምንጠይቀው (የምንማጸነው) ነገር ሳይኖር ሱባዔ ብንገባ የምናገኘው መልስ አይኖርም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ኹኔታና ዝግጅት ሱባዔ የሚገቡ ሰዎች ከሱባዔ በኋላ ምን እንደ ተመለሰላቸው የሚያውቁት ነገር ስለማይኖር ሱባዔ በመግባታቸው የሚያገኙት ጥቅም የለም፡፡ ስለዚህ ሱባዔ ከመግባታችን በፊት ሱባዔ የምገባው ለምንድን ነው? በማለት ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን በግል ሕይወቱ ዙሪያ ስለ አገር ሰላም፣ ስለ ጓደኛው ጤና፣ ወዘተ. ስለ መሳሰሉት ጉዳዮች ፈጣሪውን በጸሎት ይማጸናል፡፡ በዚህ ጊዜ በግል ሕይወቱም ኾነ በአገር ጉዳይ ለገባው ሱባዔ ወዲያውኑ መልስ ሊያገኝ ይችላል፡፡ መልሱ ሊዘገይም ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተሐራሚው ትዕግሥት ይጠበቃል፡፡ ‹‹ለምን ላቀረብኹት ጥያቄ ቶሎ ምላሽ አልተሰጠኝም?›› በማለት ማማረርና እግዚአብሔርን መፈታተን ተገቢ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራበትና ለሚማጸነውም መልስ የሚሰጥበት የራሱ ጊዜ አለውና፡፡

ከዚህ ላይ በጓደኛው ውድቀት ምክንያት ሱባዔ ገብቶ በአንድ ሳምንት ውስጥ መልስ ያገኘ የአንድ ገዳም አገልጋይን ታሪክ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ አኃው (ወንድሞች) ለተልእኮ በወጡበት ወቅት አንዱን ድቀት አግኝቶት ያድሯል፡፡ በነጋታው ‹‹ወንድሜ እኔ ድቀት አግኝቶኛልና እንግዲህ ወዲህ ተመልሼ ከዚያ ገዳም አልሔድም፤ ዓለሙን መስዬ እኖራለሁ›› አለው፡፡ እርሱም ‹‹እኔም እንጂ አግኝቶኛል፤ ይልቁንስ ሔደን ኃጢአታችንን ለመምህረ ንስሐችን ነግረን፤ ቀኖናችንን ተቀብለን እንደ ቀደመው ኾነን እንኖራለን›› ብሎ አጽናንቶ ይዞት ሔደ፡፡ ሔደው ለመምህረ ንስሐቸው ነግረው ቀኖናቸውን ተቀብለው አንድ ሱባዔ፣ ቀኖና እንዳደረሱ ‹‹ሰረይኩ ለከ በእንተ ዘኢገብረ እኁከ፤ ኃጢአት ስላላደረገው ወንድምህ ይቅር ብዬሃለሁ›› የሚል ድምፅ አሰምቶታል (ዜና አበው)፡፡

ከላይ ታሪካቸው የሰፈረው የገዳም አገልጋዮች ለአገልግሎት በተላኩበት አገር አንዱ ድቀት አግኝቶት በዝሙት ሲወድቅ ጓደኛው እንደ እርሱ ድቀት እንዳገኘው አድርጐ ጓደኛውን በማጽናናት ወደ ገዳም በመመለስ አንድነት ኾነው ሱባዔ ይገባሉ፡፡ አንድ ሱባዔ (ሰባት ቀን) እንደ ጨረሱም የወደቀው አገልጋይ ‹‹ኃጢአት ሳይሠራ ለአንተ ብሎ ሱባዔ ስለገባው ወንድምህ ስል ይቅር ብዬሃለሁ›› የሚል ፈጣን ምላሽ ከእግዚአብሔር ዘንድ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ በግል ሕይወትም ኾነ በጓደኛችን ሕይወት ዙርያ ሱባዔ ስንገባ እግዚአብሔር ፈጣን ወይም የዘገየ መልስ ሊሰጠን ስለሚችል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል፡፡

፪. ከቅዱሳን በረከት ለመሳተፍ

ቅዱሳን አባቶች እና ቅዱሳት እናቶች የተጋደሉትን ተጋድሎ በማዘከር ቃል ኪዳን በተሰጣቸው ገዳማትና አድባራት የሚገባ ሱባዔ የቅዱሳኑን በረከት ተካፋይ ያደርጋል፡፡ ቅዱሳን በሚጋደሉበት ቦታ ‹‹ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋ የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ፤›› (ኢሳ. ፶፮፥፮) በማለት እግዚአብሔር ቃል ኪዳን ስለ ገባላቸው ሱባዔ በመግባት ከበረከታቸው መሳተፍ ይቻላል፡፡ በጾመ ነቢያት የነቢያትን፣ በጾመ ሐዋርያት የሐዋርያትን፣ በጾመ ፍልሰታ የእመቤታችንን በረከት ለመሳተፍ ሱባዔ መግባት ከጥንት ጀምሮ የነበረና ወደ ፊትም የሚኖር የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ነው፡፡

ዛሬ ይህን ሥርዓት በመከተል የልዩ ልዩ ቅዱሳንን በረከት ለመቀበል (ለመሳተፍ) የቅዱሳን ዐፅም ካረፈበት ገዳም በጾም፣ በጸሎት፣ በጉልበትም ገዳማትን በማገልገል የቅዱሳንን በረከት ደጅ የሚጠኑ ምእመናንና መናንያን በየገዳማቱ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡ ይኸውም በመጽሐፈ ነገሥት ካልዕ ፪፥፱ ላይ እንደ ተመለከተው ነቢዩ ኤልሳዕ መምህሩን ኤልያስን በማገልገል የኤልያስ በረከት በኤልሳዕ ላይ እጥፍ ኾኖ አድሮበታል፡፡ ይህን አብነት በማድረግ በየገዳማቱ በትሕርምት (ዅሉንም ነገር በመተው) የሚኖሩ መናንያንን ያገለገሉበትን ገዳም አባት በረከት በእጥፍ እየተቀበሉ ለሌሎችም የሚያቀብሉ አባቶች በየገዳማቱ አሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኾኖ በስመ ገዳማዊ የምእመናንን ገንዘብ የሚዘርፉና የእውነተኛ መነኮሳትንና መናንያንን የተቀደሰ ሕይወት የሚያጐድፉ ሰዎች መኖራቸውንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ይቆየን