‹‹ሰው የለኝም››

በመምህር ኃይለሚካኤል ብርሃኑ

መጋቢት ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ኃይለ ቃሉን የተናገረው በደዌ ዳኛ ተይዞ የአልጋ ቁራኛ ኾኖ ይኖር የነበረው መጻጕዕ ነው፡፡ መጻጕዕ ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ መጻጕዕ ይህንን የኀዘን ሲቃ የተሞላበት ተስፋ የመቁረጥ ምልክት የኾነውን ‹‹ሰው የለኝም›› የሚለውን አቤቱታ ያቀረበው ሳይንቅ ለጠየቀው፣ አይቶ በቸልታ ላላለፈው፣ የሰውን ድካሙን ለሚረዳ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ እንደተረከው በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹‹ቤተ ሳይዳ›› የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፡፡ አምስትም መመላለሻ ነበረባት፡፡ ቤተ ሳይዳ ማለት ቤተ ሣህል (የይቅርታ ቤት) ማለት ነው፡፡ አምስት መመላለሻ የሚለውን ትርጓሜ ወንጌል እርከን ወይም መደብ ይለዋል፡፡ በእርከኑ ወይም በመደቡ ብዙ ድውያን ይተኛሉ፡፡ ከእነሱም ውስጥ የታወሩ፣ አንካሾች፣ የሰለሉ፣ ልምሹ የኾኑ፣ የተድበለበሉ በየእርከን እርከኖች ላይ ይተኛሉ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ውኃውን ለመቀደስ በየዓመቱ በሚወርድ ጊዜ ድምፁ እስኪያስተጋባ ድረስ ውኃው ይናወጣል፡፡ ድውያኑም በዚያ ሥፍራ ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቃሉ፡፡ ምክንያቱም በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ውኃው ሲናወጥ ቀድሞ ወደ ውኃው የገባ አንድ ሰው ከደዌው ይፈወስ ነበርና፡፡

ፈውሱ በየጊዜው ከዓመት አንድ ጊዜ ይደረግ የነበረው የእግዚአብሔር ተአምራት በአባቶቻችን ጊዜ ነበር እንጂ አሁንማ የለም ብለው ድውያኑ ከማመን እንዳይዘገዩ ሲኾን፣ የድውያኑ መፈወስ አለመደጋገሙም (በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ መፈጸሙም) በኦሪት ፍጹም ድኅነት እንዳልተደረገ ለማጠየቅ ነው፡፡ በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፡፡ ከአልጋው ላይ ተጣብቆ ይኖር ነበር፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወደዚያ ሰው ቀርቦ አየው፡፡ ጌታችን ክብር ይግባውና ተጨንቀን እያየ ዝም የማይለን፣ ስንቸገርም የሚረዳን ቸር አምላክ ነውና መጻጕዕ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ለብዙ ዓመታት እንደተሰቃየ፣ ደዌው እንደጸናበት መከራውም እንደበረታበት አውቆ በርኅራኄ ቃል ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› አለው፡፡ ፈቃዱን መጠየቁ ነው፡፡

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ፍትሐዊ ነውና ለማዳን የእያንዳንዳችን ፈቃደኝነት ይጠይቃል እንጂ ሥልጣን ስላለው፣ ክንደ ብርቱና ዅሉን ማድረግ የሚቻለው ስለኾነ ብቻ ያለ ፈቃዳችን የሚገዛን አምላክ አይደለም፡፡ በእኛ ላይ የሚያደርገውን የማዳኑን ሥራ ‹‹ልትነጻ ትወዳለህን፣ ምን እንዳደርግልህስ ትሻለህ?›› በማለት ከጠየቀ በኋላ ‹‹እንደእምነትህ ይኹንልህ፤ እንደእምነትሽ ይኹንልሽ›› እያለ በነጻነት እንድንመለላለስ ነጻነታችን ያወጀልን የፍቅር አምላክ ነው፡፡ መጻጕዕንም ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ባለው ጊዜ እሱ ግን የሰጠው ምላሽ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ‹‹ጌታ ሆይ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያው ውስጥ የሚያኖረኝ ‹ሰው የለኝም› ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል›› ብሎ መለሰለት፡፡ መጻጕዕ፣ ሰዎች ባጣ ጊዜ እንደሸሹት፣ በታመመ ጊዜ እንደተጸየፉት፣ ‹‹እንዴት ዋልኽ? እንዴት አደርኽ?›› የሚለው ሰው እንዳጣ፣ ወገን አልባ እንደኾነ እና ተስፋ እንደቆረጠ ለጌታችን ተናገረ፡፡

ጌታችን የልብን የሚያውቅ አምላክ ሲኾን ‹‹ልትድን ትወዳለህን?›› ብሎ የጠየቀበት ምክንያት አላዋቂ ሥጋን እንደተዋሐደ ለማጠየቅ ነው፡፡ አልዓዛር በሞተ ጊዜ ‹‹መቃብሩን አሳዩኝ ወዴት ነው የቀበራችሁት?›› እንዳለው ዅሉ፡፡ መጻጕዕም በምላሹ ‹‹ሰው የለኝም›› ማለቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ሲያየው የሠላሳ ዓመት ጎልማሳ ነውና የውኃውን መናወጥ ተጠባብቆ ያወርደኛል ብሎ በማሰቡ ነው፡፡ አንድም አምስት ገበያ ሰው ይከተለው ነበርና አንዱን ሰው ያዝልኛል ብሎ ነው፡፡

ብዙዎቻችን የሕይወታችን ዋልታ በሰው እጅና በሰው ርዳታ ያለ ይመስለናል፡፡ ሰዎች ካልረዱን፣ ካልደጎሙን፣ አይዟችሁ ካላሉን፣ ከጎናችን ካልኾኑና በሰዎች ካልታጀብን ነገር ዅሉ የማይሳካልን ይመስለናል፡፡ ለዚህም ነው በሰዎች ትከሻ ላይ እንወድቅና ክንዳቸውን ተመርኩዘን እነሱ ሲወድቁ አብረን የምንወድቀው፡፡ ሲጠፉም አብረን ለመጥፋት የምንዳረገው፡፡ እስኪ ከሚደክመው ከሰው ትከሻ፣ ከሚዝለው ከሰው ክንድ እንውረድና በማይዝለውና በማይደክመው በአምላክ ክንድ ላይ እንደገፍ፡፡ እርሱ መታመኛ ነው፤ ያሳርፋል፡፡ የማይደክምም ብርቱ መደገፊያ ነው፡፡

መጻጕዕ ዅሉ ነገሩ በሰዎች እጅ ላይ ነው ብሎ ስላሰበና የሰዎች ርዳታ ስለቀረበት ተስፋ ቆርጦ ነበር፡፡ የተማመነባቸው ሰዎችም ሲርቁት ሕይወቱ ጨልሞበት ነበርና ‹‹ሰው የለኝም›› አለ (ዮሐ.፭፥፯)፡፡ የተቸገረውን ለመርዳት፣ ድሃውን ባዕለ ጸጋ ለማድረግ፣ የተጨነቀችቱን ነፍስ ለማጽናናት አማካሪ የማይሻው አምላክ ግን ወዲያውኑ ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ ሰውዬው (መጻጕዕ) ወዲያውኑ ዳነ፡፡ አልጋውንም ተሸክሞ ሔደ፡፡ ቀነ ቀጠሮ ሳይሰጥ፣ ይህን ያህል ክፈል ሳይል ብቻ መሻቱን ተመልክቶ በአምላካዊ ቃሉ ፈወሰው፡፡

በዮሐንስ ወንጌል ትርጓሜ እንደተገለጸው የእግዚአብሔር መልአክ የቀሳውስት፣ ውኃው የጥምቀት፣ አምስቱ እርከን የአምስቱ አዕማደ ምሥጢር፣ አምስቱ ድውያን የአምስቱ ፆታ ምእመናን ማለትም የአዕሩግ፣ ወራዙት፣ አንስት፣ ካህናት፣ መነኮሳት ምሳሌዎች ናቸው፡፡ እነዚህንም ሰይጣን የሚዋጋበት ለእያንዳንዱ እንደየድካሙ ሊያጠቃው ይሞክራልና ያንን ድል የሚነሱበትን ምሥጢር እንደሚያድላቸው ያጠይቃል፡፡ አዕሩግን በፍቅረ ንዋይ፣ ወራዙትን በዝሙት ጦር፣ አንስትን በትውዝፍት (የምንዝር ጌጥ)፣ ካህናትን በትዕቢት፣ መነኮሳትን በስስት ጦር ሰይጣን ይዋጋቸዋል፡፡ እነርሱም በጥምቀት ባገኙት ኃይል (የልጅነት ሥልጣን) ድል ያደርጉታልና የዚያ ምሳሌ ነው፡፡ ለመጻጕዕ መፈወስ የዘመድ ጋጋታ፣ የሰዎች ርዳታ አላስፈለገውም፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ተፈውሷል፡፡ ለዚህም ነው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፤ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና፤›› (መዝ.፸፪፥፲፪) ሲል የተቀኘው፡፡ ጻድቁ ኢዮብም እንዲሁ ‹‹ረዳት (ኃይል) የሌለውን ምንኛ ረዳኸው፤›› (ኢዮ.፳፮፥፪) በማለት የእግዚአብሔርን አዳኝነት መስክሯል፡፡

የድንግል ማርያም ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወቱ የደረሰለት ሰው እንዲህ ይባረካል፡፡ ስለዚህ ሰው የለኝም፣ ገንዘብ የለኝም፣ ሥልጣን የለኝም፣ ወገን የለኝም፣ ረዳት የለኝም በማለት ተስፋ የቆረጥን ሰዎች እግዚአብሔር ከሰውም፣ ከሥልጣንም፣ ከገንዘብም በላይ ነውና እርሱን ተስፋ አድርገን ዅል ጊዜ በስሙ መጽናናት እና የሚያስጨንቀንን ዅሉ በእርሱ ላይ መጣል እንደሚገባን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹አቤቱ የሚፈልጉህ ዅሉ በአንተ ደስ ይበላቸው፤ ሐሴትም ያድርጉ፡፡ ዅልጊዜ ማዳንህን የሚወዱ ዘወትር እግዚአብሔር ታላቅ ይኹን ይበሉ፤›› (መዝ.፵፥፲፮) እንዳለው ዅሉ ዅል ጊዜም በአምላካችን እግዚአብሔር ደስተኞች እንኹን፡፡

   ወስብሐት ለእግዚአብሔር