ሰዋሰወ ግእዝ ክፍል ሦስት

ሰኔ 26 ቀን 2005 ዓ.ም.

በመ/ት ኑኀሚን ዋቅጅራ

ባለፈው ሳምንት አምዳችን ከ፳፮ (26)ቱ የግእዝ ፊደላት መካከል የ፲፫(13)ቱን የግእዝ ፊደላት ቅርጽ ከነትርጒማቸው መግለጻችን ይታወቃል፡፡

ዛሬ ደግሞ ተከታዮቹን አሥራ ሦስት (፲፫) ፊደላት እንመልከት

፲፬. ከ ብሂል- ከሃሊ እግዚአብሔር፡፡
      ከማለት – እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው፡፡

፲፭. ወብሂል – ወረደ እም ሰማይ እግዚእነ
      ወ ማለት -ጌታችን ከሰማይ ወረደ፡፡

፲፮. ዐ ብሂል – ዐርገ ሰማያተ እግዚእነ፡፡
      ዐ ማለት – ጌታችን ወደሰማይ ወጣ /ዐረገ/፡፡

፲፯. ዘ ብሂል – ዘኲሎ ይእኅዝ እግዚአብሔር፡፡
      ዘ ማለት -እግዚአብሔር ይይዛል /ሁሉን የሚይዝ ነው/፡፡

፲፰. የ ብሂል – የማነ እግዚአብሔር ገብረት ኀይለ፡፡
      የ ማለት – የእግዚአብሔር ቀኝ ኀይልን አደረገች፡፡

፲፱. ደ ብሂል – ደመረ ሥጋነ ምስለ መለኮቱ፡፡
      ደ ማለት – ሥጋችንን ከመለኮት ጋር አንድ አደረገልን፡፡

፳. ገ ብሂል – ገብረ ሰማያተ በጥበቡ፡፡
     ገ ማለት – ሰማያትን በጥበቡ ሠራ፡፡

፳፩. ጠ ብሂል – ጠዐሙ ወታእምሩ ከመ ኄር እግዚአብሔር፡፡
      ጠ ማለት – የእግዚአብሔርን ቸርነት ታውቁ ዘንድ ቅመሱ፡፡

፳፪. ጰ ብሂል – ጰራቅሊጦስ መንፈሰ ጽድቅ፡፡
      ጰ ማለት – ጰራቅሊጦስ የእውነት መንፈስ ነው፡፡

፳፫. ፀ ብሂል – ፀሐይ ጸልመ በጊዜ ስቅለቱ ለእግዚእነ፡፡
      ፀ ማለት – ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ፀሐይ ጨለመ፡፡

፳፬. ጸ ብሂል – ጸጋ ወክብር ተውህበ ለነ፡፡
      ጸ ማለት – ጸጋ እና ክብር ለእኛ ተሰጠን፡፡

፳፭. ፈ ብሂል – ፈጠረ ሰማየ ወምድረ፡፡
      ፈ ማለት እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ፡፡

፳፮. ፐ ብሂል – ፓፓኤል ሥሙ ለአምላክ፡፡
      ፐ ማለት – ፓፓኤል የአምላክ ስም ነው፡፡ 

ከዚህ በመቀጠል ዝርዋን የግእዝ ፊደላትን /የግእዝ ፊደል ዲቃሎች/ ተብለው የሚጠሩትን ፈደላትና በፊደል ገበታ ላይ በስተመጨረሻ ተጽፈው የምናገኛቸውን ፊደላት እንመለከታለን፡፡

  • በፊደል ገበታ ላይ በስተመጨረሻ ተጽፈው የምናገኛቸው ከዋናው የፊደል የአጻጻፍ ቅርጽ ወጣ ያሉ ሁለት ዓይነት ፊደላትን እናገኛለን፡፡

  • ፩ ዲቃሎች /ዝርዋን/ የግእዝ ፊደላት ፪ ዲቃሎች /ዝርዋን/ የአማርኛ ፊደላት በመባል ይታወቃሉ፡፡

ከግእዝ ፊደላት ዝርዝር ጋር የሚሄዱትን የግእዝ ዝርዋን /ዲቃሎች/ ፊደላትን እንመለከታን፡፡

  • ዝርው ማለት ብትን /ቅደም ተከተልን ያልጠበቀ/ ማለት ነው፡፡

  • ዝርዋን የግእዝ ፊደላት ዝርዋን የሚል ስም የተሰጣቸው ከዋናዎቹ የግእዝ ፊደላት ላይ የተወሰነ ቅጥያ እየተጨመረ የተመሠረቱ ፊደላት በመሆናቸው ነው፡፡

  • ዝርዋን መባላቸው እንደ ዋንኞቹ የግእዝ ፊደላት ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው በሰባቱ የፊደላት ዝርዝር ባለመዘርዘራቸውና አብዛኛውን ጊዜ በግእዝ ፊደል በተጻፉ ጽሑፎች ላይ ብቻ መገኘታቸው ነው፡፡ እነዚህ ፊደላት የተመሠረቱት በዋንኞቹ የግእዝ ፊደላት ላይ የተወሰነ ቅጥያ በማድረግ ነው፡፡

  • ዋንኞቹ የግእዝ ፊደላት የአዘራዘር ሥልት በግእዝ ጀምረው በሳብዕ ቅደም ተከተላቸውን ጠብቀው ይዘረዘራሉ፡፡

ምሳሌ፡- ግእዝ      ካዕብ      ሣልስ         ራብዕ      ኀምስ    ሳድስ      ሳብዕ
       ሀ           ሁ          ሂ          ሃ          ሄ           ህ       ሆ    
       ለ           ሉ          ሊ         ላ          ሌ          ል       ሎ

 

የዝርዋን የግእዝ ፊደላት የአዘራዘር ሥልት ግን ከእነዚህ ይለያል

መነሻ ፊደላት

ግእዝ

ሳድስ

ሣልስ

ራብዕ

ኀምስ

 

የዛሬ አምዳችንን በዚህ እናጠናቅቃለን ሳምንት በአማርኛ ፊደላትና ዝርዋን የአማርኛ ፊደላትን የአጻጻፍና የአዘራዘር ሥልት ይዘንላችሁ እስከምንገናኝ ቸር ይግጠመን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር