ሰሙነ ሕማማት (ከዕለተ ሰኑይ እስከ ቀዳሚት ሰንበት)

በመምህር ቸርነት አበበ

መጋቢት ፳፬ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

መግቢያ

ከአባታችን አዳም በደል ወይም ስሕተት በኋላ በሕማማት፣ በደዌያት፣ በመቅሠፍታት፣ ወዘተ በብዙ መከራ የሰው ልጅ ሊኖርባቸው ግድ የኾነባቸው ዘመናት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡ የሰው ልጅ ቢያጠፋ፣ ቢበድል፣ ከሕገ እግዚአብሔር ቢወጣ እንኳን የዋህ፣ ታጋሽ፣ ቸር፣ አዛኝ የኾነው አምላክ የጠፋውን ሊፈልግ፣ የተራበውን ሊያጠግብ የታረዘውን ሊያለብስ፣ ፍቅር ላጣው ፍጹም ፍቅር ሊለግስ፣ ሰላም ለሌለው ፍጹም ሰላም ሊሰጥ፣ ተስፋ ለሌለው ተስፋ ሊያጐናጽፍ ከሰማይ ወረደ፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፤ በገዳመ ቆሮንቶስ ዐርባ ቀንና ሌሊት ጾመ፡፡ በጾሙም የኀጢአት ሥሮች ወይም ራሶች የተባሉትን ስስትን፣ ትዕቢትንና ፍቅረ ንዋይን ድል አደረገልን፡፡ እኛ እርሱ የጾመውን ጾም እንድናከብር እንድንጾም ምሳሌ ኾነን፡፡ ዲያብሎስን ድል አድርጐ ድል እንድንነሣው ኃይልና ምሳሌ ኾነን፡፡

ሰሙነ ሕማማት ምንድን ነው?

‹ሰሙን› – ‹‹ሰመነ ስምንት (ሳምንት) አደረገ›› ማለት ነው፡፡ ይኸውም ከዕለተ ሆሣዕና ሠርክ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ጊዜ ወይም ቀናት የሚያመለክት ነው፡፡ ‹ሕማም (ሕማማት)› – ‹ሐመ ታመመ› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን ይህም የሰውን ዘር ዂሉ ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ለማውጣት ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈቃዱ የተቀበላቸውን ጸዋትወ መከራዎች የሚያሳስብ ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኵነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኀጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን አደባባይ ለካህኑ የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት ነው፡፡

በዚህ ሳምንት ብዙ አዝማደ መባልዕት አይበሉም፤ ይልቁን በመራብ በመጠማት በመውጣት በመውረድ በመስገድ በመጸለይ በመጾም በየሰዓቱ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራዎች በማሰብ አብዝቶ ይሰገዳል፡፡ መከራውን፣ ሕማሙን፣ ድካሙን የሚያስታውሱ ከቅዱሳት መጻሕፍት ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ መዝሙረ ዳዊት፣ ግብረ ሕማማት ወዘተ በየሰዓቱ ይነበባል፡፡ መስቀል መሳለም የለም፡፡ ካህናትም ‹‹እግዚአብሔር ይፍታህ›› አይሉም፡፡ ሥርዓተ ፍትሐት አይፈጸምም፡፡ ይኸውም ይህ ሳምንት ከሞት ወደ ሕይወት የተሸጋገርንበት ከጨለማ ወደ ብርሃን የተጓዝንበት የመሸጋገሪያ ወቅት ምሳሌ በመኾኑ ነው፡፡ በዕለተ ምጽአት መላእክት የመለከት ድምፅ በማሰማት የዳግም ምጽአትን ዕለት ለማሳሰብ ምእመናን ጥሪውን ሰምተው ለዚህም አስቀድመው ተዘጋጅተው የበዓሉ ታዳሚዎች መኾናቸውን በማጠየቅ በዚህ ሳምንት ዲያቆኑ ቃጭል እየመታ በየሰዓቱ ምእመናኑን ያሳስባል፡፡

በሰሙነ ሕማማት የሚገኙ ዕለታትና ስያሜዎቻቸው

ዕለተ ሰኑይ (ሰኞ)

ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ (የቤተ መቅደስ መንጻት) እና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት ነው (ማቴ. ፳፩፥፲፰-፳፪፤ ማር. ፲፩፥፲፩፤ ሉቃ. ፲፫፥፮-፱)፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ «ወመሰለ ሎሙ ወይቤሎሙ አሐዱ ብእሲ በለሰ ቦቱ ውስተ ዐፀደ ወይኑ ወየሐውር ይንሣእ ፍሬሃ ወኢይረክብ …፤ ይህንም ምሳሌ አለ፤ ለአንድ ሰው በወይኑ አትክልት የተተከለች በለስ ነበረችው፡፡ ፍሬም ሊፈልግባት ወጥቶ ምንም አላገኘም …›› በማለት እንደ ጠቀሰው በበለስ ስለ ተመሰለ የሰው ልጅ ሕይወት በማሰብ እንዲመለስ ንስሐ እንዲገባ በሕይወትም እንዲኖር እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ማሳሰቡን ያጠይቃል፡፡ ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደ ጠወለገችና እንደ ተቈረጠች ዂሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቈረጡ እንደዚሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስረዳል፡፡ በለስ የተባለች ቤተ እስራኤል ፍሬ የተባለ ደግሞ ሃይማኖትና ምግባር ነው፡፡ ዂላችን ቤተ እስራኤላውያን ፍሬ ሃይማኖት ወምግባር አስተባብረን ይዘን መገኘት ይገባናል፡፡ ፍሬ አልባ እንዳንኾን ጌታ ሲመጣም እንዳናፍር የመጽሐፉን ቃል ልንጠብቅና ልንፈጽም ይገባናል፡፡ በዚህ የሕማማት የመጀመሪያ ቀን ዕለተ ሰኑይ የምናስበው የምንዘክረው የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ በቸልተኝነት እንዳይደክም፣ እንዳይጠወለግ፣ እንዳይደርቅ፣ ወደ እሳትም እንዳይጣል ማድረግ ይገባናል፡፡

ዕለተ ሠሉስ (ማክሰኞ)

ይህ ዕለት ጌታችን ሰኞ በተናገረውና ባደረገው ተአምር ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹የጥያቄ እና የትምህርት ቀን›› በመባል ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ ገበያ መፍታትን ‹‹በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?›› የሚል ነበር (ማቴ. ፳፩፥፳፫-፳፯)፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ እንደ ተናገረው ጌታችንም ‹‹እውነት እላችኋለሁ፤ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአችኋል›› በማለት አይሁድ በሚከተሉት ልማድ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ እንደማይችሉ አስተምሯል (ማቴ. ፳፩፥፳፰)፡፡

ዕለተ ረቡዕ

ይህ ዕለት ደግሞ የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዕለቱ ‹‹የምክር ቀን›› በመባል ይጠራል፡፡

ዕለተ ሐሙስ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዕለት ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ መኾኑን ለመግለጥ እና ለአርአያነት ጸሐፍት ፈሪሳውያን የአይሁድ ካህናት መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ በማደሩ ምክንያት ጸሎተ ሐሙስ በመባል ይታወቃል፡፡ ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳትና ለማስገንዘብ የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስም ‹‹እግራቸውንም አጥቦ ልብሱንም አንሥቶ ዳግመኛ ተቀመጠ፡፡ እንዲህም አላቸው፤ ያደረግሁላችሁን ታስተውሉታላችሁን? … እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስኾን እግራችሁን ካጠብሁ እናንተ ደግሞ እርስ በእርሳችሁ ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል›› ሲል ተናግሯል (ዮሐ. ፲፫፥፲፪-፳)፡፡

‹‹ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቈረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ›› በማለት ምሥጢረ ቍርባንን የመሠረተበት ወይም ራሱ ምስጢረ ቍርባንን የጀመረበት ቀን በመኾኑ ‹‹የምሥጢር ቀን›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ይኸውም የሰው ልጆች ሥጋውንና ደሙን ተቀብለን ከእርሱ ጋር አንድነትና ኅብረት እንዲኖረን ጥንተ ጠላት ዲለብሎስንም ፍጹም ድል ነሥተን ሰማያዊት ርስት መንግሥተ ሰማያትን እንድንወርስ ለማስቻል ነው (ማቴ. ፳፮፥፳፮-፳፱)፡፡ አይሁድ ጌታችንን ለመያዝ በእነርሱ ጥበብና ፍላጐት ቀስ ብለው መጥተው የያዙበት ቀን ስለ ኾነ በዚህ ዕለት በለሆሳስ (ብዙ የድምፅ ጩኸት ሳይሰማ) የቅዳሴ ሥርዓት ይፈጸማል፡፡ ስለ ኾነም መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዚህ የኅፅበት፣ የምሥጢር፣ የጸሎት ቀን በተባለው በዚህ ዕለት በንስሓ ታጥበው ሥጋ ወደሙ እንዲቀበሉ ቤተ ክርስቲያን በአጽንዖት ታስተምራለች፡፡

ዕለተ ዐርብ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ ‹‹አውቀውስ ቢኾን የክብርን ጌታ ባልሰቀሉት›› (፩ኛ ቆሮ. ፩፥፲፰)፡፡ እንዳለ ይህ ዕለት የአይሁድ ካህናት ያለ በደል ያለ ጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የኾነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ ዕለቱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ዂሉ መድኀኒት ለአዳምና ለልጆቹ ሲል በመልዕልተ መስቀል በቀራንዮ አደባባይ ተሰቅሎ መዋሉን የምናስብበት ታላቅ ቀን ነው (ማቴ. ፳፯፥፴፭-፸፭)፡፡ የሰው ልጆች በዘር ኀጢአት (ቁራኝነት) ይኖሩበት የነበረው የጨለማ ሕይወት ያከተመበት ፍጹም ድኅነት ያገኙባት ታላቅ ዕለት ናት፡፡ ክርስቲያኖች ዂልጊዜም ዕለተ ዓርብ ሲመጣ ሕማሙን ስቅለቱን ሞቱን የምናስብበት ጊዜ ነው፡፡ በሮማውያን ሕግና ሥርዓት መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የሕይወት መቅጫ ዓርማ ኾኖ ሳለ ለእኛ የዲያብሎስ ድል መንሻ ስላደረገው በስቅለቱና በሞቱም ሕይወትን አገኘን፡፡ በዚህም ምክንያት ‹‹መልካሙ ዓርብ›› በመባል እንደሚታወቅ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያትታሉ፡፡

ዕለተ ቀዳሚት ሥዑር

ዕለተ ቀዳሚት እግዚአብሔር የሚታዩትንና የማይታዩትን፣ በእግር የሚሔዱትን እና በክንፍ የሚበሩትን በባሕር የሚዋኙትን እንስሳትን በመጨረሻም ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮ ያረፈባት ዕለት ናት፡፡ ይህች የመጀመሪያው ቅዳሜ ለእግዚአብሔር የዕረፍት ዕለት ናት፡፡ እግዚአብሔርን ሥነ ፍጥረት ፈጥሮ ስላረፈባት ‹‹ሰንበት ዐባይ›› (ታላቋ ሰንበት) ትባላለች፡፡ ታላቋን ሰንበት እስራኤላውያን እንዲያከብሯት ታዟል (ዘፍ. ፩፥፫)፡፡ ዕለተ ቀዳሚት በዘመነ ሐዲስም የተለየ የደኅነት ሥራ ተከናውኖባታል፡፡ ጥንት ሥነ ፈጥረትን በመፍጠር ዕረፍት እንደ ተደረገባት ዂሉ የፍጥረት ቁንጮ የኾነውን አዳምን ለማዳን ሕማምና ሞት የተቀበለው ቸሩ አምላክ በመቃብር አርፎባታል (ማቴ. ፳፯፥፷፩)፡፡

በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ ‹‹ቀዳሚት ሥዑር›› ትሰኛለች፡፡ ‹‹ቀዳሚት ሥዑር›› የተባለችበት ምክንያትም በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ይኸውም ቅድስት ድንግል ማርያም እና ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታችን ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንሥተው ብርሃነ ትንሣኤዉን እስኪያዩ ድረስ እኽል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደርጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት በቅብብሎሽ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን፣ በመጾምና በመጸለይ ዕለቷን እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆችም የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው ያከፍላሉ (ይጾማሉ)፤ ለሁለት ቀን እኽል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ፡፡ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ በልተው ቅዳሜን በመጾም በዓለ ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡

በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቀዳሚት በቅፅረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ ‹‹ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፤ በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ›› እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ያድላሉ፡፡ ይኸውም የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ምሥጢሩም በኖኅ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ኾነው እጅግ የሚያሳዝን ኀጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀዋል፡፡ በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጕደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመልሳለች (ዘፍ. ፱፥፩-፳፱)፡፡

ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡ ቄጠማ፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች መንገሪያ እንደ ኾነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የኾነዉን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡ የክርስቶስ ተከታዮች ዂሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከሚያቃጥለው ዋዕየ ሲኦል (የሲኦል ቃጠሎ) ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማኅደራቸው መመለሳቸውን በዚህ አኳኋን እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡ ከበዓሉ ረድኤት፣ በረከት ያሳትፈን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር