ሥጋዌ – የድኅነት ቍልፍ – ክፍል አንድ

በመምህር ፀሐዬ ዳዲማስ

ታኅሣሥ ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጌታችን የሰው ልጆችን የሚያድንበት የማስተማር ሥራው (ወንጌልን መስጠቱን) ሲጀምርም ሲፈጽምም በነገረ ድኅነት ትምህርት ነው። የስብከቱ መነሻ የትምህርተ ድኅነት መዳረሻ የኾነው የመንግሥተ ሰማያትን ነገር ማውሳት ነበር፡፡ ‹‹መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመር፤›› እንዲል (ማቴ. ፬፥፲፯)። ከሰማያት የወረደበትንና ሰው የኾነበትን የድኅነት ሥራውን ፈጽሞ በትንሣኤው የሰው ልጆችን ሕያውነት አረጋግጦና የዘለዓለምን ሕይወት አውጆ ወደ አባቱ ያረገው ‹‹ወደ ዓለም ዅሉ ሒዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ዅሉ ስበኩ። ያመነ የተጠመቀም ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል፤›› በማለት ትምህርተ ድኅነታዊ ትእዛዝን ለሐዋርያት በመስጠት ነበር (ማር. ፲፯፥፲፭-፲፮)።

ቅዱስ ጳውሎስም ትምህርተ ክርስትና ከድኅነት ጋር ያለውን የጠበቀ ቍርኝት፣ የማይነጣጠል አንድነት የሚያመለክቱ ኃይለ ቃላትን በመልእክታቱ አስፍሮ ይገኛል። ‹‹የሰበክሁላችሁን ደግሞም የተቀበላችሁትን በእርሱም ደግሞ የቆማችሁበትን በእርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለሁ›› (፩ቆሮ. ፲፭፥፩) በማለት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ሲያሳስብ፣ ‹‹የእውነትን ቃል፣ ይኸውም የመዳናችሁን ወንጌል፤ ሰምታችሁ ደግሞም በክርስቶስ አምናችሁ፣ በተስፋው መንፈስ በመንፈስ ቅዱስ ታተማችሁ›› (ኤፌ. ፩፥፲፫) በማለት ደግሞ ለጊዜው ኤፌሶናውያንን፤ ለፍጻሜው ዳግም የሰው ልጅን ዅሉ ድኅነት መክሯል፡፡ ወንጌላዊው ማርቆስም ስለ አጠቃላይ የክርስትና ትምህርት ምንነት ሲያስረዳ ‹‹ለዘለዓለም ድኅነት የኾነውን የማይለወጠውን ቅዱስ ወንጌል›› በማለት ነው የሚገልጠው (ማር. ፲፮፥፰)።

የክርስትና ትምህርት የድኅነት ትምህርት ነው። ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው የሰው ልጆችን መዳን ቁልፍ መጠቅለያውና ማጠንጠኛው ነው። አቀራረቡም ‹‹ነገረ ድኅነታዊ›› ነው – የክርስትና ትምህርት። ከጥንት ጀምሮ ሐዋርያትና ሊቃውንት የወንጌላውያኑን እና የሐዋርያትን አሰረ ፍኖት በመከተል የክርስትናን ትምህርት የጠበቁት ነገረ ድኅነትን አምልቶና አስፍቶ በማስተማር ነው።

ኢትዮጵያውያን ሊቃውንትም እንደዚሁ ትምህርታቸውንና ዝማሬአቸውን ዅሉ ነገረ ድኅነታዊ በማድረግ የክርስቶስ ተከታይነታቸውን፣ የሐዋርያትና የሊቃውንት ልጅነታቸውን አስመስክረዋል። በዚህ አጭር ጽሑፍም ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት የጌታችንን ልደት አስመልክተው ያቀረቡአቸውን የነገረ ድኅነት ትምህርቶች በአጭሩ እናቀርባለን፡፡

በክርስትና ትምህርት ከመጀመርያዎቹ የክርስትና ዘመናት ጀምሮ የሊቃውንትን ከፍተኛ ትኩረት የሳበው የእግዚአብሔር ሰው መኾን ነው። ሰው ሊድን የሚችለው በእግዚአብሔር ነው፣ እግዚአብሔር ደግሞ  የወደቀውን ሰው ለማዳን የወደደው ራሱ የሰዎችን ሙሉ (ፍጹም) ማንነት፣ ከኃጢአት በቀር፣ ወስዶ (ተዋሕዶ) ነው። ስለዚህ የድኅነት መነሻ ቍልፉ የእግዚአብሔር ፍጹም ሰው መኾን ነው። ቅዱስ አግናጥዮስ ምጥው ለአንበሳ ‹‹እግዚአብሔር ለሰዎች ሰው እንደ ኾነ መሰላቸው እንጂ እሱ ሰው ሊኾን አይችልም›› በማለት ለሚያስተምሩት ለዶሰቲስቶች (Docetists) መቃወምያ አድርጎ ባቀረበው እና ለትራልዮን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ የሚከተለውን ጽሑፍ አበርክቶልናል፤

‹‹ከእግዚአብሔር የራቁ እምነት የሌላቸው ሰዎች ‹ሰውን መሰለ እንጂ የሰውን ፍጹም ሥጋ ለራሱ አልወሰደም (አልለበሰም)፣ የሞተውም በምስል ነው እንጂ እሱ በትክክል መከራ አልተቀበለም› እንደሚሉት ከኾነ [እጄንና እግሬን] ለምን [በሰንሰለት] እታሰራለሁ ይመስላችኋል? ለምንስ ለተራቡ አናብስት ለመሰጠት ይናፍቀኛል?… ድንግል ማርያም የፀነሰችው ሥግው ቃለ እግዚአብሔርን ነው። እግዚአብሔር ቃልም በእውነት ከድንግል ተወለደ፣ የለበሰውም ሥጋ ለእኛ [ለሰዎች] ያለንን ሁሉ ያለው ነው፤›› (ወደ ትራልዮን ሰዎች ምዕራፍ ፲)።

ይህም የሚያሳየን ለሰዎች መዳን የእግዚአብሔር ቃል ከሰማይ መውረድና ከድንግል መወለድ ብቻ ሳይኾን የክርስቶስ ፍጹም አምላክ ሳለ ፍጹም ሰው መኾን አስፈላጊ ነው። አስቀድመን የጠቀስነው ሊቅ ትምህርቱን ሲያጠናክረውም ‹‹ሕፃናትን በማኅፀን የሚሠራቸው እርሱ በማኅፀን አደረ፣ ከድንግል ሥጋና ነፍስን ነሥቶ ያለ ወንድ ዘር አምላክ ሳለ ሰው ኾነ›› በማለት ክርስቶስ የተዋሐደው ሥጋ ከድንግል የነሣው ፍጹም የሰው ልጆች ሥጋ መኾኑን አረጋግጦልናል። ቅዱስ አግናጥዮስስ በመልእክቱ ላስተማራቸውም ይህ እውነት ባይኾን ኖሮ ራሱን ለተራቡ የበረሃ አናብስት የሚሰጥ ሞኝ እንዳልኾነ በማስረገጥ ያዳነው እና የሚያመልከው ክርስቶስ ፍጹም አምላክ፣ ፍጹም ሰው መኾኑን ያስረዳቸዋል (ዝኒ ከማሁ)፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም የ‹‹ለፌ እማርያም›› የእግዚአብሔር ወልድን ቅድምና በሚያመሠጥርበት እና አስተማሪውን ፎጢኖስን በሚዘልፍበት አንቀጹ የሥጋዌን ምሥጢር እንዲህ በማለት አስቀምጦልናል፤ ‹‹ዳግመኛም ድንግል መልአኩን እንዳልኸኝ ይኹንልኝ አለችው። ያን ጊዜም ቃል ከእርሷ ሥጋን ተዋሐደ [ሥጋን ነሣ] … በዚያ [በሰማይ] በአባቱ ቀኝ አለ፤ በዚህም [በምድር] በእናቱ ማኅፀን ውስጥ አለ። … በዚያ ያለ እናት አባት አለው፤ በዚህም ያለ ምድራዊ አባት እናት አለው። በዚያ ገብርኤል በፍርሃት ይቆማል፣ በዚህም ገብርኤል በሐሴት የምሥራች ይናገራል፤ በዚያ በጽርሐ አርያም የሚደነቅ ከማይታይ አብ የመወለድ ምስጋና፤ በዚህም በቤተ ልሔም የሚደነቅ ከድንግል የመወለድ ምስጋና … በሰው መጠን ጐልማሳ ባይኾን፣ በሰው ልጆችም አካል ባይገለጥ እኛን ስለ ማዳን ማን መከራ በተቀበለ ነበር። እነሆ  ከሰማይ ትጉሃን ይልቅ የሰው ልጅ ከበረ፤ እግዚአብሔር ከሴት (ከእመቤታችን) ተወልዷልና፤›› (መጽሐፈ ምሥጢር፣ የልደት ምንባብ)።

የድኅነት ወይም የሰው ልጆች መክበር እና የሥጋዌን የጠበቀ ቍርኝት ተመለከታችሁ! እነዚህ ቅዱሳን አበው የሚነግሩን እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ሰው ባይኾን የሰው ልጆች ድኅነት ጥያቄ ውስጥ ይገባ እንደ ነበር ነው። አግናጥዮስ ‹‹እግዚአብሔር ፍጹም ሰው ባይኾን ሞቴ ከንቱ በኾነ››፤ አባ ጊዮርጊስም ‹‹እግዚአብሔር በሰው ሥጋ ባይገለጥ ማን ባዳነን?›› በማለት የክርስቶስን ሥጋዌ የድኅነተ ሰብእ ቍልፍ መለኮታዊ ተግባር መኾኑን ያስረዳሉ።

ይቆየን