ማኅበረ መነኮሳቱ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ

ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት በሜጫ ወረዳ ቤተ ክህነት በጉታ ቀበሌ ልዩ ስሙ ናዳ በሚባል ቦታ የሚገኘው የፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ገዳም መነኮሳትና አብነት ተማሪዎች ሰኔ ፳፪ እና ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በጣለው ከባድ ዝናም እና በረዶ ምክንያት ያለሙት ፍራፍሬ ሙሉ በሙሉ በመውደሙ፣ መኖርያ ቤታቸውም በመፍረሱ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠየቁ፡፡

ምንኵስናን ከሊቅነት፣ አባትነትን ከሥራ ጋር አስተባብረው የያዙት የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ፣ የትርጓሜ መጻሕፍትና የቅኔ መምህሩ ሊቀ ብርሃናት ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ በቦታው ተገኝተን ቃለ መጠይቅ ባደረግንላቸው ወቅት እንደ ገለጹልን በገዳሙ አካባቢ የሚገኘውን በጎርፍ የተሸረሸረ ሸለቆ በመከባከብ በ፲፱፻፹ ዓ.ም የተጀመረው የልማት ሥራ ገዳሙን በፌዴራል ሁለተኛ፤ በክልል ደግሞ አንደኛ ደረጃ እንዲያገኝና የክብር ሜዳልያ እንዲሸለም አድርጎታል፡፡

ዳሩ ግን ይህ የልማት ውጤት በበረዶው ምክንያት ከጥቅም ውጪ ኾኗል፡፡ ፍራፍሬውና ደኑም ተጨፍጭፏል፡፡ የጠበል መጠመቂያ ቦታዎች ተናውጠዋል፡፡ ንቦችም ከቀፎዎቻቸው ወጥተው ተሰደዋል፡፡ የመነኮሳቱና አብነት ተማሪዎች መኖርያ ቤቶችም ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ከሰባ ሄክታር በላይ የሚገመት ሰብል በበረዶው ናዳ መውደሙን ከገዳሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ ‹‹ወደዚህ ገዳም ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ ዓይነት ክሥተት ደርሶ አይቼ አላውቅም›› ይላሉ ዋና አስተዳዳሪው የጉዳቱን ከፍተኛነት ሲገልጹ፡፡

በበረዶው ምክንያት የረገፈው ፍራፍሬ በከፊል

ከቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል በደረሰን መረጃ ማኅበረ ቅዱሳን ከገዳሙ ድረስ ልዑካንን በመላክ ለጊዜው የዘር መግዣ ይኾን ዘንድ የሃያ ሺሕ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ማኅበሩ ካሁን በፊት አንድ ትራክተር ገዝቶ በስጦታ ለገዳሙ ያበረከተ ሲኾን፣ ለወደፊትም ገዳሙን በቋሚነት ለመደገፍ አቅዷል፡፡

በመጨረሻም ላደረገው የገንዘብ ድጋፍ ማኅበረ ቅዱሳንን፤ በጉልበት ሥራ በመራዳታቸው ደግሞ የአካባቢውን ሕዝበ ክርስቲያን የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ አመስግነው፣ ሌሎች በጎ አድራጊ ምእመናንም ቀለብ በመስጠት፣ ዘር በመግዛት፣ ልብስ በመለገስ፤ ከፍ ሲል ደግሞ መኖርያ ቤት በማደስ በአጠቃላይ በሚቻላቸው አቅም ዅሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ዋና አስተዳዳሪው በገዳሙ ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በረዶው በአትክልቱ ላይ ያደረሰው ጉዳት በከፊል

የፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ገዳም ከ፲፱፻፸፱ ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ የትርጓሜ መጻሕፍት እና የቅኔ ትምህርት የሚሰጥበት ጥንታዊ ገዳም ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ገዳሙ በልማት ሥራ የታወቀ ልዩ ቦታ ነው፡፡ ኾኖም በዘንድሮው ዓመት በወርኃ ሰኔ በአካባቢው በጣለው ከባድ በረዶ የተነሣ ፍራፍሬውና ደኑ በመውደሙ የገዳሙ መነኮሳትና የአብነት ተማሪዎች ኑሯቸው አደጋ ላይ ነው፡፡

ዝግጅት ክፍላችንም የገዳሙን መነኮሳት ከስደት፣ ጉባኤ ቤቱንም ከመዘጋት ለመታደግ፤ እንደዚሁም የልማት ቦታውን ወደ ጥንት ይዘቱ ለመመለስ ይቻል ዘንድ በተቻላችሁ አቅም ዅሉ ድጋፍ በማድረግ ከበረከቱ እንድትሳተፉ ይኹን ሲል መንፈሳዊ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

ማሳሰቢያ

ገዳሙን በገንዘብ ለመደገፍ የምትፈልጉ ምእመናን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መርዓዊ ቅርንጫፍ ሒሳብ ቍጥር፡- 10000 6261 1786 ገቢ ማድረግ የምትችሉ መኾኑን የገዳሙ ጽ/ቤት ያሳስባል፡፡ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘትም በስልክ ቍጥር፡- 09 18 70 81 36 በመደወል የገዳሙን ዋና አስተዳዳሪ ማነጋገር ይቻላል፡፡