መጪውን ጊዜ በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” መዋጀት

መስከረም 18 ቀን 2005 ዓ.ም.


ጊዜ ይመጣል ጊዜ ይሄዳል፡፡ ጊዜ መጥቶ ሲሄድ ግን እንደው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ የጊዜውን አሻራ አሳርፎ ነው፡፡ አሻራው ግን አዎንታዊም አሉታዊም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ምርጫው በጊዜ መጠነ ክበብ ውስጥ ያለው የሰው ልጅ ነው፡፡

 

የሰው ልጅ ደግሞ በጊዜያት ውስጥ የረቀቀና የገዘፈ ዓለም ባለቤት ሆኖ የተፈጠረና ጊዜ የማይቆጠሩላቸው የሥሉስ ቅዱስ ፍጡር ነው፡፡ በሕያውነቱ ረቂቁን ዓለም- ዓለመ ነፍስን መስሎና ሆኖ ሲኖር፤ በምድራዊነቱ ግዙፉን ዓለም- ዓለመ ሥጋን በተዋሕዶ ነፍስ መስሎና ሆኖ ይኖራል፡፡ በዚህም የሁለት ዓለም ባለቤት ነው፡፡ የሰማያዊና ምድራዊ ወይም የመንፈሳዊና ዓለማዊ፡፡

 

እንዲህ ሆኖ ሲፈጠር በነጻ ምርጫው እንዲኖር የሚያስችለው ነጻ አእምሮ የተቸረው ብቻ ሳይሆን የምርጫውን ተገቢነትና ትክክለኛነት የሚያረጋግጥበት አእምሮ የተሰጠውም ባለጸጋ ፍጡር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

በረጅሙ የጊዜ ሂደት ውስጥ ከግዙፉ ዓለም- ዓለመ – ሥጋ፤ ግፊት አንጻር መውደቅ መነሣቱ አይቀሬም ነው፡፡ ትልቁ ቁም ነገርም መውደቁ ሳይሆን ወድቆ አለመቅረቱ – መነሣቱ ነው፡፡ ሃይማኖተኛ የሚያሰኘውም ይኼው የመነሣት ጉዞ አካል የሆነው መንፈሳዊነቱ ነው፡፡

 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትገለገለውም የምትጎዳውም በዚሁ ፍጡር ነው፡፡ የመውደቅ መነሣቱም ሰንኮፍ አሐቲ፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊት፣ ኲላዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጥላውን ማሳረፉ አይቀሬ ነው፡፡

 

በዚህ ወቅት በምድር ያለችው ሰማያዊ ቤታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ሰብዓዊ ግፊት በወለዳቸው እኲያት እየተፈተነች ነው፡፡ ከውጪ ከሥጋ በሆኑ በሉላዊነትና የዚህ ውጤት በሆኑት በዘመናዊነት፣ ዓለማዊነት፣ ለዘብተኝነት እየተፈተነች መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

 

በተለይ ከሰሞኑ ከፓትርያርክ አሰያየም ጋር ተያይዞ ለአስቀመጡት የጥፋት ግብ አባቶችን፣ ሊቃውንቱንና ምእመኑን ለመከፋፈል ዓላማ እንዲረዳቸው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ወንዛዊነትን – ጎጣዊነትንና – ዘውገኝነት የቤተ ክህነነቱ ባሕርያዊ ቁመና ለማድረግ ሲውተረተሩ መገንዘብ ችለናል፡፡

 

እነዚህ የክፍፍልና የልዩነት ዐውድማዎች የከፋ ጥፋት ከማድረሳቸው በፊት የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” በወለደው ጥብዓት በቃችሁ ሊባሉ ይገባል፡፡ የሃይማኖት ብሔርተኝነት መነሻው አገራችን በሰማይ፤ ኑሮአችን በዓለመ ነፍስ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ የሃይማኖት ብሔርተኝነት ሲባልም ሃይማኖትን በሃይማኖት እናት፣ አባትና ብሔር አድርጎ መውሰድ ወይም በአጭሩ የሃይማኖት ወገንተኛ ማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ወንዝ- ጎጥና- ዘውግ ዘለል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” በቤተ ክርስቲያናችን የነበረና የቆየ ማእከለ አንድነት እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ለዚህም ትንታኔያችን ማሳያው ሁለት ነው፡፡

 

የመጀመሪያው ምድረ ሙላዱ /መካነ ሙላዱ/ ከኢትዮጵያ ያልሆነው እና ከኢትዮጵያ ተልኮ ሄዶ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ በቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾሞ የመጣው ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ነው፡፡ በአራተኛው መቶ ዓመት “ቅዱስና ያለ ተንኮል የሚኖር ነውርም የሌለበት ከኀጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል” /ዕብ.7፥26/ ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት እንደተናገረው፤ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሾማቸው ከሐዋርያት ሐረገ ክህነት ተያይዞ የመጣ የሐዋርያት ተከታይ የሆነ ሊቀ ካህናት ማግኘት ይገባል ብላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማን ወደ እስክንድርያ ስትልክ በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እንጂ በወንዛዊ- በጎጣዊ- በዘውጋዊ ብሔርተኝነት አይደለም፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያው ፓትርያርክም ራሱኑ /ቅዱስ ፍሬምናጦስን/ ሾሞ የላከው በጎጠኝነት- በዘውገኝነት- በወንዘኝነት ሳይሆን በሃይማኖት ብሔርተኝነት መሆኑን ማስታወስ እንወዳለን፡፡

 

ሁለተኛው ምድረ ሙላዳቸው ከኢትዮጵያ ያልሆኑ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን /479 ዓ.ም. አካባቢ/ የሮማ ግዛት ከነበሩ ልዩ ልዩ አገሮች ዘጠኝ ቅዱሳን ወደ አገራችን መምጣት ነው፡፡ ተሰዐቱ ቅዱሳን በእምነት መሰሎቻቸው የሆኑ ክርስቲያኖች ወደሚኖሩባት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው ሲመጡ ከነትምህርታቸው ቅድስናቸውን የተቀበልነው፤ እነርሱም በስደት በሚኖሩበት አገር ሥርዐተ ምንኩስናን ያስፋፉት፤ ገዳማዊ ሕይወትንና ምናኔን ያስተማሩት፣ ገዳማትን በየቦታው ያቋቋሙትና ያልተተረጎሙትን መጻሕፍት ወደ ግእዝ የተረጎሙት በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እንጂ በወንዛዊ- ጎጣዊና- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት አለመሆኑን ማስታወስ እንፈልጋለን፡፡

 

በዚህ መልኩ የመጣውን ሥርዐተ ሢመት በሥጋዊና በደማዊ ፍላጎት ማጉደፍ ሥርየት የሌለው በደል ነው፡፡ ትናንት አባቶቻችን በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ቤተ ክርስቲያናችን በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ጥገኝነት ተላቃ ራሷን እንድትችልና ከራሷ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እንድትሾም ብርቱ ተጋድሎ ያደረጉት በወንዛዊ- ጎጣዊና- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት እንድንራኮትበት ሳይሆን በሃይማኖት ብሔርተኝነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንድናሸጋግራት ነበር፡፡

 

ትናንት አባቶቻችን በወንዝ- በጎጥ- በዘውግና ቋንቋ ሳይቧደኑና ሳይደራጁ በሃይማኖት ብሔርተኝነት ጳጳሳትን ሾመዋል፤ ሞያና ሞያተኛን አገናኝተው የአገልግሎት ምደባ አድርገዋል፡፡ ከብሔርና ነገድ በላይ ለሃይማኖት ብሔርተኝነት ተገቢውን ዋጋና ክብር ሰጥተው ቤተ ክርስቲያናቸውንና መንጋቸውን በጥብዓት በመንኖ ጥሪትና በትግሃ ሌሊት አገልግለው ላያልፉ አልፈዋል፡፡

 

አስቀድመን ለመግለጽ እንደሞከርነው ዛሬ ከሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ይልቅ ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ ብሔርተኝነቱ ገንኖ ወጥቷል፡፡ ብርቱ የተባሉትን ሁሉ እየቆረጠ ሲጥል እያስተዋልንም ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ሢመት የሚታጩ አበው መንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ ሞያዊ ብቃታቸው፣ የአመራር ክሂሎታቸው፣ ዐቃቤ ሃይማኖተኝነታቸው ሳይሆን ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ ተክለ ቁመናቸው መስፈርት እስኪመስል አባቶችን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን አቧድኖ ለማፋጀት የተዘጋጁ ወገኖች ብቅ ብቅ ማለት መጀመራቸውንም እንገነዘባለን፡፡

 

የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ደፍቀው ወንዛዊ- ጎጣዊና- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት የሚያቀነቅኑ እነዚህ ወገኖች ለቤተ ክርስቲያናችን ልዕልና፣ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ለምእመናን መብዛትና መጽናናት የሚያስቡ አለመሆናቸውን ከዚሁ ድርጊታቸው መረዳት ችለናል፡፡ ይልቁንስ ለእነርሱ ቀኝ እጅ ሆኖ፤ የእነርሱን ፍላጎት የሚያስፈጽም “የተረኞች” አባት ፍለግ ውስጥ የገቡ ሰዎች ቁመናን ገንዘብ ያደረጉ መሆናቸውንም ተረድተናል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኒቱ በቀኖናዋ የ”ተረኞች ፓትርያርክ” ሥርዐተ ሢመት የላትም፤ እንዲኖራትም አልተፈቀደም፡፡ ፕትርክና በወንዛዊ- ጎጣዊና- ዘውጋዊ ተረኝነት የሚገኝ ሳይሆን እግዚአብሔር ባወቀው በግብረ መንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ሢመት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አንዱ እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ ሁለተኛውም እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናችሁ፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደሰጣቸው ያገለግላሉ፡፡ እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፡፡ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም፡፡ የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል” 1ኛ ቆሮ.3፥4-81 ያለውን በዕዝነ ልቡና መያዝናም ተገቢ ነው፡፡

 

ከዚህ አኳያ የ”ተረኝነት ሥርዐተ ፕትርክና” አስተሳሰብ ፍጹም ሥጋዊ ከመሆኑም በላይ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ አዋራጅና ጎጂ ነው፡፡ የዚህ ፍጹም ሥጋዊ አስተሳሰብ አቀንቃኞች ከወዲሁ ራሳቸውን ተረኛ ጥቅመኛ አድርገው የሰየሙ ናቸው፡፡ መቼ ነው እኛ ደግሞ አስወጪ አስገቢ የምንሆነው? ተረኛ አሿሚ፣ አሻሪ ሆነን ቤት የምንሠራው፤ መኪና የምንገዛው ባዮች መሆናቸውንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

እንዲህ ዐይነቱ ፍጹም ሥጋዊ ቅኝት የሚያመለክተው አንድ ነገር ነው፡፡ የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እያጸጸ መምጣቱንና ውስጡ ጥቅመኝነት ሆኖ ሽፋኑ ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ የሆነ ብሔርተኝነት መሠረት እየያዘ መሆኑን ነው፡፡

 

እናም መጪውን ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን የተሻለና በጎ ከማድረግ አኳያ የጊዜውን አበው፣ ሊቃውንትና ምእመን በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ዋጅቶ ከወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት ደዌ መፈወስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡

 

የመጪውን ጊዜ ፓትርያርክ አሰያየምም በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” መዋጀት በመንፈሳዊነታቸው እና በአመራር ክሂሎታቸው እንጂ በጎጣዊ- ወንዛዊ- ዘውጋዊ ማንነታቸው መሆን የለበትም እንላለን፡፡ አባቶቻችን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ሢመት መብቃት ያለባቸው በአባትነታቸው እንጂ መልክዐ ምድራዊ ብሔርተኝነት በወለደው ወንዛዊነት- ጎጣዊነት- ዘውገኝነት አይደለም፡፡

 

ለተግባራዊነቱ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽና የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል የሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ አለባቸው እንላለን፡፡

 

“አባ እገሌ “እገሌ ፓትርያርክ ይሁን” ሲል ሌላኛው ደግሞ ሞቼ እገኛለሁ አለ” እያሉ የሚያናፍሱትን ክፉ ወሬ አሉባልታ የሚያደርግ ቁርጠኝነት ከአባቶቻችን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከራስ ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ እየሰጡ በሥልጣን የሚጣሉ አባቶች ሳይሆኑ ለአንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ኲላዊት ቤተ ክርስቲያን ዓላማ በጋራ የሚሠሩ አባቶች እንደአሉን እንደሚያረጋግጡ ጽኑ እምነታችን ነው፡፡

 

ብፁዓን አበው ለሢመተ ፕትርክና ዕጩ ሆነው የሚቀርቡት አባቶቻችን መንፈሳዊ፣ ለመምራት ብቃት ያላቸውና ዐቃቤ ሃይማኖት እስከ አሁኑ ድረስ ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ ማንነታቸው ከየትም ሊሆን ይችላል የሚል ተጨባጭ መልእክት እንደሚያስተላልፉም ባለሙሉ ተስፋ ነን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ ከባድ ግን ልትወጣው የምትችለው ፈተና አለባት፡፡ በቃላት የሚፈታና የሚነገር ሳይሆን በተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚፈተነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቀጣዩ ጉዞ በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እጅ ለእጅ መያያዝንና ጠንካራ አንድነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለምን አልተጣሉም? ለምን አልተከፋፈሉም? የሚሉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን አርፈው የሚቀመጡበትም ሁኔታ እንደሌለ መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

ይህን የጥፋት ሕልማቸውን እውን ለማድረግ አባቶችን ለመከፋፈል፣ በምእመናን መካከል ልዩነትን ለመፍጠር፣ ሊቃውንቱን ለማጥላላትና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማዳከም ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉም ይታመናል፡፡ ብፁዓን አበውም፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ምእመናንም ይህን አውቀው በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ጠንክሮ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል እንላለን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 1 2005 ዓ.ም.