ልሳነ አርድእት

 ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመ/ር ደሴ ቀለብ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ መምህር

ክፍል ፩

የግእዝ ቋንቋ እድገት ከየት ወዴት?

አንዲት ሀገር የራሷ የሆነው ባህሏ /ሥርዓቷ/ የሚያኮራትና ማንነቷንም የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ልትጠብቀውና ከትወልድ ወደ ትውልድ ልታስተላልፈው የባለቤትነት ግዴታዋ ነው፡፡ በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጵያን ለጥቁር ሕዝቦች መኩሪያ እንድትሆን ያደረጋት የልጆቿ ሀገር ወዳድነትና ጀግንነትን የተመላው ባህሏ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት፤ የሥነ ፊደል ሀገር መሆኗም መጻሕፍተ ታሪክን ባነበቡ ሊቃውንት አንደበት ብቻ ሳይሆን በማዳመጥ ትውፊት /ርክክብ/ ለኅብረተሰቡ ኀቡእ ያልሆነ ነገር መሆኑ ነው ፡፡

በተጨማሪም ሀገራችን ኢትዮጵያ የዘመናት ዑደት ስፍር ቀምራ የራሷን አኀዝ ያደላደለች አፍሪካዊት እመቤት ናት ብንል ጽልመት ሊጋርደው የማይችለው ገሀድ ነው፡፡

ይሁን እንጂ እኛ ልጆቿ የትናንቱን ለዛሬ ማበርከት ያልቻልን ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው ትናንት የኢትዮጵያ መሠረተ ቋንቋ የነበረው የግእዝ ቋንቋ ከነበረበት የብሔራዊና የውል ቋንቋነት ይቅርና ዛሬ ዛሬ የት ገባ ሊባል የሚያሳፍር ሆኗል፡፡ አበው ለብዙ ዘመናት ይህን ቋንቋ በዜማ ቤቱ፣ በቅኔ ቤቱና በመጻሕፍት ቤቱ እንዳልተጠቀሙበት ሁሉ ዛሬ ግን የአበው ያለህ ብንል፤ አይደለም መግባባት ይቅርና ገና ተማሪው እንኳን ከማለዳው “ኦኾ” /እሽ/ በማለት ፈንታ “ኦኬ” ቢል ይቀድመዋል ፡፡ ይህ ግን “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” ሳያሠኝ አይቀርም ፡፡

እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ታሪክ መረጃ ሥነ ሐውልቶች የተሸከሙት የግእዝ ቋንቋ ሥነ ጽሑፍ የሀገራችንን ጥንተ ታሪክ የሚያስረዳ መሆኑን ታሪክ ይመሰክራል፡፡ የግእዝ ተፎካካሪ የነበረው የሳባዊያን ቋንቋም በግእዝ ተልቆ /ተበልጦ/ ግእዝ የኢትዮጵያ ነገሥታት ሊቃውንት ኅብረተሰብ መግባቢያ ከመሆኑም አልፎ ከሀገር ውጭም ኢትዮጵያ ሀገረ ፊደል፣ ሀገረ አሚን መሆኗን ያስመሰከረ ልሳን ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ቀድሞ ከ፯ ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ እየተጠናከረ መሄዱ በሚነገርለት በአማርኛ ቋንቋ መሆኑ ቀርቶ በቤተ ክርስቲያንና በተወሰነው የኅብረተሰብ ክፍል ዘንድ እየተገደበ መጣ፡፡ እንዲያውም በተለይ በዘመነ ዓምደጽዮን / ከ፲፫፻፯-፲፫፻፴፯ ዓ.ም./ የንጉሡ ገድል ሁሉ የሚጻፈው በተሰባበረ አማርኛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የሚከተለውን ማየት ይቻላል፡፡ 

  • ሐርልኛ ዓመደ ጽዮን
  • መላለሸ የወሰን
  • ወሀ እንዳመሰን መላላሽ የወሰን
  • ከወጅ ዜብደናን ከገንዝጠጠን
  • ምንቀረህ በወሠን ከድያ አምኖን

በተጨማሪም በዐፄ ይስሐቅ /ከ፲፬፻፯-፲፬፻፳፪ ዓ.ም./ ጊዜ ለንጉሡ የሚቀርቡት መወድሶች ከአማርኛው ላይ ያተኮሩ ይምስላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-

  • ገጽዥን ይስሐቄ ገጽ
  • አርያም ይመስል አንቀጽ
  • እሳት ይመስል ብቁጽ
  • ከመ መደልው ልጽሉጽ
  • ገጹ እንዲያስደነግጽ
  • እስራኤላዊ መደንግጽ
  • ማን አየህ ገጽ በገጽ

 

እነዚህ ግጥሞች ግን እንደምናያቸው ሙሉ በሙሉ አማርኛ አልነበሩም፡፡ ለዚህም ነው ግዊዲ የተባለው የታሪክ ተመራማሪ “ግእዝ -አማርኛ” ጽሑፎች ብሎ የሚጠራቸው፡፡ በእርግጥ ከአማርኛው ላይ ግእዝ መደመር ለአሁኑ ትውልድም የቋንቋ ጣዕም የሥነ ጽሑፍ ቃና መሆኑ አወንታዊ ምላሽ አለው፡፡

ያም ሆኖ ግን ብዙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የጽሕፈት ሥራቸውን ብራና ዳምጠው ቀለም በጥብጠው ይጠቀሙበት የነበረው በዚህ ቋንቋ መሆኑን አላገደውም፡፡ እንዲያውም በዘመነ ዘርዓያዕቆብ /፲፬፻፳፮-፲፬፻፷ ዓ.ም./ መስፋፋት የነበረበት የሥነ ጽሑፍ እድገት ግእዙን የሙጥኝ ያለ ነበር፡፡ በኋላም ቢሆን በዐፄ ሱስንዮስ / ከ፲፭፻፱፱-፲፮፻፳፬ ዓ.ም./ የሃይማኖት መለወጥ ምክንያት ጋር ተያይዞ ኢየሱሳውያን (Jesuites) ጉልህ ችግር ደርሶባት የነበረችውን የሮማ (ስፔን) ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮችን ቁጥር ለማበርከት ሲሉ በአማርኛ በመጻፍ ወረቀቶችን ለመበተን ቢሞክሩም የአንድ ባሕርይ አማኝ የሆነው ዐፄ ፋሲል / ከ፲፮፻፳፬ -፲፮፻፸፬ ዓ.ም/ በመንገሥ የምእመናኑን ፍጹም ቀናዒነት ብሎም የኢየሱሳውያን ከኢትዮጵያ ምድር መውጣት ለልሳነ ግእዝ እንደገና መወለድ መስፋፋት ሆነለት፡፡ ብዙም መጻሕፍተ ግእዝ ተደረሱ፡፡ የቅኔ እድገትም ታየ፡፡ ከዐፄ ፋሲል በኋላም ነገሥታቱ ታላቅ ተሳትፎአቸውን አበርክተዋል፡፡ ስለሆነም ዐፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ /ከ፲፮፻፸፬ -፲፮፻፱፱ ዓ.ም./ እና ሌሎችም ነገሥታት የማይጠፋ ስማቸውን በልቡናችን ቀረጸው አልፈዋል፡፡

ዳግመኛ የ፲፮ኛው እና የ፲፯ኛው ክፍለ ዘመናት ቁስር አልሽር ብሎ እንደገና በመሳፍንቱ ዘመን /ከ፲፯፻፸፯-፲፰፻፵፭ ዓ.ም/ ሀገሪቱ እርስ በርሷ በፖለቲካና በሃይማኖት ድልቅልቅ ስትዋጥ ሀገርን አንድ ማድረግ ይችል የነበረውን ነገረ-ሃይማኖት ለመረዳትና ለመወሠን ሊቃውንቱ የግእዝን መጻሕፍት ማገላበጥ ግድ ሆነባቸው፡፡ የመነጋገሪያ /የመከራከሪያ/ ምሥጢራቸው የሆነው ቅኔም ለልሳነ ግእዝ መስፋፋት ጠቀመ፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቶችም ተስፋፉ፡፡ ፍጹም የሆነ አንድነትም ታዬ፡፡ ዛሬስ የሃይማኖት ውዝግቡን የሚፈቱት የትኞቹ እውን መጻሕፍት ይሆኑ? በእርግጥ ዛሬ ግእዝ ያወቀው ሁሉ ነገረ ሃይማኖትን ተረዳ ማለት አይደለም፡፡ የሚማረውም ለሕይወት /ለፍቅር/ ወይም ታሪክን ለማወቅ ላይሆን ይችላል፡፡ ነበርኩ ለማለትና ክዶ ለማስካድ እንዲመቸው የሚያስብም አይጠፋምና፡፡ በየዋህነት መማር ግን በአማናውያኑ አበው ቀርቷል፡፡

እንግዲህ ለግእዝ ቋንቋ መዳከም ዐቢይ ምክንያት የአማርኛ መተካት ብቻ ሳይሆን ለቋንቋው የሚሰጠው ትኩረት መላላቱ የማያወላውል ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ ዝም ብሎ ግን ቅርስ ቅርስ ማለት ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ “ባዶ ብራና” ካልተነበበ ምን ሊሠራልን፡፡ በተጨማሪም መንግሥትም ሆነ ማንኛውም አካል ግእዝ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ቅርስ መሆኑን ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ቤተ ክህነትም ብትሆን የእነ ቅዱስ ያሬድ የዜማ መጻሕፍት እነ ድጓ፣ የዚቅ ቀለማት፤ የእነ አባ ጊዮርጊስ መጻሕፍት ፣ እነ ሰዓታት በሌላ ቋንቋ ሊዜሙ “ይቻል” ይመስል ለግእዝ የሚሰጠው እንክብካቤ ያሳዝናል፡፡

ድሮ ድሮ የቆሎ ተማሪ ለምኖ አኮፈዳውን፤ ዳዊቱን አንግቦ የሚነጋገረው በዚህ ቋንቋ ነበር፡፡ እንደዛሬው ግን ለወደፊቱ አይደለም የሚነጋገር አባባሉን የሚያጠና /የሚቀጽል/፣ በደንብ ቅኔ የሚቀኝ ይቅርና ዳዊቱን አጣርቶ መድገሙም ራሱ ያጠራጥራል፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ የገጠር ቦታዎች የሚያስተምሩ ብዙ የሊቃውንት በረከቶች ቢኖሩም፤ ነገ የሚተካው ግን ከግእዝ ይልቅ ጣሊያንኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ ብቻ ቢማር የሚያተርፈው ይመስለዋል፡፡ ይህ ግን “አባቱን አያውቅ አያቱን ይናፍቅ” ያሠኛል፡፡

ምንጭ መጻሕፍቱ በግእዝ የሆነው የሀገራችን ታሪክንስ አንባቢና ተርጓሚ ማን ይሆን? በዚህ እኮ ነው የሀገራችንን ታሪክ ለማወቅ የውጭ መጻሕፍት ላይ ጥገኛ የምንሆነው፡፡ አንባቢውና ተርጓሚው አላዋቂ ከሆነ ደግሞ ታሪከ ሀገር ቅድምና ሀገር በምልዑ ልብ የማይመሰከርበት ይመስላል፡፡ የሚገርመው ግን ብዙዎቹ የግእዝ መጽሐፎቻችን በፈርንጆቹ ላይ የማያልቅ ፍቅርን አሳድረውባቸው ቋንቋውን እስከ ሃምሳ ዓመት ድረስ ሲያጠኑ እኛ ግን “የሞተ ቋንቋ” እንለዋለን፡፡ ቋንቋው ሞተ ከማለት ግን ታሪከ ሀገር ቅድምና ሀገር ሞተ ብንል ሳይሻል አይቀርም፡፡ ቢያንስ ቢያንስ በቤተ ክርስቲያን ለካህናቱ የምስጋናቸው አንደበት ግእዙ ነውና፡፡

እንግዲህ እናጠቃለውና ማንኛውም ክፍል /አካል/ ይህ ቋንቋ በጥንቱም ሆነ በአዲስ መልክ እንዲያድግ ጥረት ቢያደረግ፤ የቅኔ መምህራኑም የግእዝ መምህራኑም ምንም እንኳን የኑሮ ችግር ቢኖርም ለራስ የሚስማማ ቦታን ከመምረጥ ለተማሪዎች የሚስማማ ቦታን መርጦ በገጠርም ቢሆን ማስተማር ይኖርባቸዋል፡፡ የቋንቋ ምሁራንም ለዚህ እድገት አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ላይ የጥንቱ ሰዋስው (Classical Grammar) ይምጣልን፣ ይመለስልን፤ መካከለኛው ክፍለ ዘመን የጨለማ ዘመን ነው እያሉ እንዳማረሩት ሮማውያንና ግሪካውያን እንዳንሆን ያስፈራል፡፡ ስለሆነም ሥርወ ቃላትን ለመመርመር ሰዋስውን ለመለየት ግእዝ ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ታላላቅ ደራሲያን ምስክሮች ናቸው፡፡ በተረፈ ግን ሁላችንም የታሪክ፣ የሀገር፣ የወገን፣ የቅርስ ባለአደራዎች መሆናችንን አንዘንጋ፤ እንቅልፉም ይብቃን፡፡

ይቆየን