ሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ ዐረፉ

ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ቴዎድሮስ ኃይሉ

በሕይወት ዘመናቸው ኹሉ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነትና በታማኝነት ሲያገለግሉ የነበሩት ታላቁ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ፣ የትሕትናና የጸሎት አባት ሊቀ ማእምራን ወመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባይነሳኝ ዐረፉ፡፡

0001

ከአቶ ባይነሳኝ ላቀውና ከወ/ሮ በፍታ ተሾመ ሐምሌ ፲፩ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም በላስታ ደብረ ዘመዶ አካባቢ የተወለዱት፤ የአቋቋም፣ የቅኔ፣ የፍትሐ ነገሥትና የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህሩ መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት፣ ልዩ የትርጓሜ ጸጋ የተሰጣቸው፤ ፍቅረ ነዋይ የራቀላቸውና የሚያስተምሩትን ቃለ እግዚአብሔር በሕይወት የኖሩ አባት ነበሩ፡፡

መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ከ፲፱፻፷፭ ዓ.ም ጀምሮ በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለአምስት ዓመታት ያህል በምክትል መምህርነት ያገለገሉ ሲኾን፣ የጉባኤው መምህር የኔታ ክፍሌ ካረፉበት ከ፲፱፻፸ ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው ድረስም ጉባኤ ተክለው፣ ወንበር ዘርግተው በማስተማር በርካታ ሊቃውንትን አፍርተዋል፡፡

ከመካነ ነገሥት ግምጃ ቤተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ቤት ደቀ መዛሙርት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ መጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበት ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ፹ ዓመታቸው ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡

ሥርዓተ ቀብራቸውም ሐምሌ ፪ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት በመካነ ነገሥት ግምጃ ቤት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይፈጸማል፡፡

የሊቁን የመጋቤ ሐዲስ ወልደ ሰንበትን አጠቃላይ አገልግሎትና ሙሉ የሕይወት ታሪክ ወደ ፊት በስፋት ይዘን እንቀርባለን፡፡