ለገዳሙ ካህናትና ዲያቆናት መሠረታዊ የኮምፒውተር አጠቃቀም ሥልጠና ተሰጣቸው

በይበረሁ ይጥና
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም የተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት ለስምንት ወራት በመሠረታዊ የኮምፒውተር ትምህርት ያሠለጠናቸውን አሥራ አምስት ካህናትና ዲያቆናት ጥር 30 ቀን 2002 ዓ. ም. አስመረቀ፡፡

የገዳሙ አስተዳዳሪ ቆሞስ መልአከ ፀሐይ አባ ገብረ ሥላሴ  በምረቃው መርሐ ግብር እንደተናገሩት፤ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ትምህርት ማስተማር ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል፡፡ ትምህርቱን ያገኙት አባቶችም ሆኑ ዲያቆናት በኮምፒውተር ትምህርት መሠልጠናቸው የመረጃ ሥርዓትና ተዛማጅ ሥራዎች በዘመናዊ መልክ ለማከናወን እንደሚያግዛቸውም ተናግረዋል፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቱ ሥልጠናውን አዘጋጅቶ አባቶች፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤቱ ወጣቶች በአንድነት እንዲሠለጥኑ ማድረጉ ቤተ ክርስቲያንን በልማት ለማሳደግ ያለውን ርእይ እንደሚያሳይ ጠቁመው፤ ወደፊትም ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ቤተ ክርስቲያን ብዙ እንደምትጠብቅ ተናግረዋል፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዲያቆን ደረጀ ነጋሽ በበኩሉ፤ የመጀመሪያውን ዙር መሠረታዊ የኮምፒዩተር ሥልጠና ሠልጥነው ያጠናቀቁት፤ አንድ መነኩሴ፣ አሥራ ሦስት ዲያቆናትና አንዲት የሰንበት ትምህርት ቤት አባል ወጣት እንደሆኑ አስረድቷል፡፡ በሥልጠናው ወቅት ያገኙትም የትምህርት ዓይነት ኤም ኤስ ዊንዶ፣ ወርድ፣ ኤክሴል፣ አክሰስና የኢንተርኔት አጠቃቀም የተመለከቱ መሆናቸውን ሰብሳቢው ጠቁሞ፣ ሥልጠናው አገልግሎታቸውን ለማቀላጠፍ እንደሚረዳ አስታውቋል፡፡

ሥልጠናውን ለስምንት ወራት የሰጡት ቀደም ሲል በሰንበት ትምህርት ቤቱ ተኮትኩተው ያደጉ ወጣቶች ሲሆኑ፤ አሠልጣኞች በአሁኑ ጊዜ በኮምፒዩተር ሳይንስ ሙያ በተለያዩ ተቋማት የሚያስተምሩ አባላት እንደሆኑ ምክትል ሰብሳቢው አስረድቷል፡፡ ለወደፊትም ሥልጠናውን ከገዳሙም በተጨማሪ ወደ ሌሎችም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በመሔድ ለአገልግሎትና ለሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ለመስጠት እቅድ መያዙን ተናግሯል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በተለይ ቀደም ብሎ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባል የነበሩ አባቶች በሰጡት አስተያየት አባትና ልጅ በአንድ ሆነው መማራቸው በሰንበት ትምህርት ቤቱና በገዳሙ አባቶች መካከል ያለውን ፍቅርና አንድነት እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ሥራውም ለሌሎች ሰንበት ት/ቤት አርአያ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡ ሰንበት ት/ቤቱ ከ1950 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ 1993 ዓ. ም. ድረስ «ተምሮ ማስተማር ማኅበር» የሚል ስያሜን ይዞ ቤተ ክርስቲያንን እያገለገለ ነበር፡፡ ከ1993 ዓ. ም. ወዲህ «የተምሮ ማስተማር ሰንበት ት/ቤት» በሚል ስያሜ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡