ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልም

በአሁኑ ዘመን ዓለማችን በከፍተኛ የአስተሳሰብ፣ የቴክኖሎጂና የማኅበራዊ ለውጥ ሒደት ውስጥ ትገኛለች፡፡ እነዚህን የለውጥ ሒደቶች  የመረዳት አቅም ያጣ ግለሰብም ሆነ ተቋም የሚሻውን በቀላሉ መፈጸምና ማስፈዐም አይችልም፡፡  አላማዎቹ በጎም ይሁኑ ክፉ ከተጨባጭ ሁኔታዎቹ ተነጥሎ ማሳካት አይችልም፡፡ በሀገራችንም ከመንግሥት ጀምሮ በርካታ ድርጅቶች ከሙከራ ትግበራ አንሥቶ ሀገር አቀፍ አፈጻጸም እስኪሆኑ ድረስ እነዚህን ሁኔታዎች ያገናዘቡ የተለያዩ የአሠራር ማሻሻያዎችን ተግባራዊ እያደረጉ ነው፡፡
ቅድስት ቤተክርስቲያናችንም በዚህ ዓለም ያሉ የለውጥ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ለጊዜያችን የሚመጥን፣  የተቀበለችውን የእግዚአብሔርን መንጋ የመጠበቅ ሐላፊነቷን መወጣት የሚያስችላት፣ ከክርስቶስ ፍቅር የማይለይ አሠራርን በአመራርና አስተዳደራዊ ክፍሎቿ ማስገባት ግዴታዋ ሆኗል፡፡ ግዴታውን ያስከተለው ደግሞ ሰው ሳይሆን አጠቃላይ ዓለማዊ ሆኔታው ነው፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ የማይካድ እውነት ነው፡፡ ለዚህ እውነታ መሥራት ደግሞ ተገቢም አስፈላጊም ነው፡፡
ክርስቲያኖች አነሰም በዛም የጊዜውን የአሠራር ለውጥ ሒደት እያፋጠነ ያለው የመረጃ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች እየሆኑ ነው፡፡  የመረጃ ቴክኖሎጂው ደግሞ ክርስቲያኖች ክፉና ደጉን እንዲያውቁ ለማድረግ እገዛ አድርጎላቸዋል፡፡ ከዚያም አልፎ የእነሱ የሆነውን ከሌሎች ጋር ማነጻጸራቸው አይቀሬ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ደግሞ የክርስቲያኖች ነች፡፡ ስለዚህ የእኛ ብለው ላመኑባት ቤተ ክርስቲያን በጎውን እንድትይዝ፣ ከክፉው እንድትሸሽ ይመኛሉ፤ ለሚመለከተው ያሳስቡበታልም፡፡ ለዚያም ይሠራሉ፡፡ ይህም ሌላው እውነታ ነው፡፡

ምእመናን ይህን ወቅታዊ የለውጥ ሒደት ከግምት አስገብተው ቤተክርስቲያናቸውን ከመጠበቅ አንፃር ዛሬ ይዛ እንድትገኘ ከሚፈልጉአቸው ዋና ዋና ጉዳዮች አንዱ የአመራርና አስተዳደራዊ አቅምን የማጠናከር ተግባርን ነው፡፡
የአመራርና አስተዳደር አቅም ማለት ደግሞ የአሠራር፣ የአደረጃጀትና የሰው ኃይል አቅምን ይመለከታል፡፡ ያለን አሠራር ከነቀፋ የሚያድነን፣ ለመተማማት ሰበብ የማይፈጥር /ግልጽ/ ያጠፋ የሚቀጣበት፣ ያለማ የሚከብርበት /ተጠያቂነት የሰፈነበት/ እንዲሆን ነባራዊ ሁኔታው ያስገድዳል፡፡ ለዚህም ከሕገ ቤተክርስቲያኑ ጋር የማይጋጭ፣ በየደረጃው ያሉ የሥራ ክፍሎችን እርምጃ የሚያፋጥን ደንብና መመሪያ አዘጋጅቶ ማጽደቅ ይፈልጋል፡፡  ይህ ደግሞ ያለንን መዋቅርና አደረጃጀት እንድንፈትሽ ይጠይቃል፡፡ አካባቢያዊ ለውጦችን ከግምት አስገብቶ በዘመናዊው የአስተዳደር ዘይቤ የሚመራ የሰው ኃይል በየደረጃው መቀመጥ ይኖርበታል፡፡ እነዚህ ግፊቶች የተወሰኑ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ያመጡት አይደለም፡፡ የአጠቃላዩ የለውጥ ግስጋሴ ያስከተላቸው ናቸው፡፡ ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች በየጊዜው ከሚፈጠሩ ሁኔታዎች ጋር በማስተያየት፣ ነባር፣ ጠቃሚና መንፈሳዊ የሆኑ፤ መቼም መች የሚያስፈልጉንን ኦርቶዶክሳዊ መገለጫዎቻችንን ከመጠበቅ ጋር እያጣጣሙ ማካሔድ ለነገ የማይባል ተግባር ነው፡፡ በፍጥነት ተግባራዊ እንድናደርግ ያስገደደንም ከላይ የጠቀስናቸው ተጨባጭ እውነታዎች ናቸው፡፡ ለዚህ እውነታ ደግሞ ማድረግ ያለብንን እንድናደርግ ያስፈልጋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስም እነዚህን የምእመናንን ትኩረቶች ተረድቶ በቅርቡ የአመራርና አስተዳደራዊ አቅምን ለመገንባት ወይም የተሻሉ ጠቃሚ ለውጦችን ለማምጣት ያሳየው ፍላጎትና ጅምር እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው፡፡  «ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ» ያለውን የሐዋርያውን ምክር ሰምቶ እነዚህን ጅምር እንቅስቃሴዎች መደገፍ ደግሞ የክርስ ቲያኖች ሁሉ ድርሻ ነው፡፡

ይሁን እንጂ እነዚህን ተፈላጊ ለውጦች ለማምጣት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አልጋ በአልጋ ሆነው እንደማይሔዱ በቅርቡ የተከሰተው ውጣ ውረድ አመላካች ነው፡፡ይሁንና የቤተክርስቲያኒቱን አንድነትና የቅዱስ ሲኖዶስን የሥልጣን የበላይነት ከማስጠበቅ ጋር ተገቢ ለውጦችን አቅዶ መተግበርን ጊዜው የማይቀር አድርጎታል፡፡ የአሠራር ማሻሻያዎችን ለማምጣት በሚደረጉ የውይይት ሒደቶች በቅዱስ ሲኖዶስ አባላት  መካከል የተለያዩ አስተያየቶች ቢከሰቱ እንኳን ልዩነቶቹ ሊከበሩ ይገባል፡፡ ለመግባባት የሚያስችሉ፣ በበጎ ሐሳብ የሚፈጸሙ ተከታታይ ውይይቶችን ማድረግ ግን አስፈላጊ ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ አባቶች ሁሉ ፍላጎት ለራስ ሳይሆን ለቤተክርስቲያን እስከሆነ ድረስ የአስተያየት ልዩነቶች ቢንፀባረቁም ከብዙኃኑ ብፁዓን አባቶች ውሳኔ ለመለየት አያበቃም፡፡ የራስ ፍላጎቶች እየገነኑ ከመጡ ግን መለያየትን ይጋብዛሉ፡፡ መጽሐፍም «መለየት የሚወድ ቢኖር ምኞቱን ይከተላል» እንዳለ፡፡

ሁሉም የቅዱስ ሲኖዶስ  አባላት  ለሺሕ ዘመናት ብዙ ውጣ ውረዶችን እያለፈች ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ ጭምር እንደብርሃን የሚታዩ በጎ ተግባራትን ስትፈጽም የኖረችው ቤተክርስቲያን ባለአደራዎች እንደሆኑ እናምናለን፡፡  አባቶች ይህንን ተረደተው በስውርም ይሁን በግልጽ፣ በግልም ይሁን በቡድን የሚፈጸሙ ጣልቃ ገብነቶችን ተቋቁመው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለጊዜያችን የሚያስፈልገውን የአመራርና የአስተዳደር ዓይነትና ደረጃ በቤተክርስቲያን ማስፈን አለባቸው የሚል እምነት አለን፡፡ ለዚህ ደግሞ የተጠሩለትን ሕይወትና ዓላማ ከመረዳት ጀምሮ እውነትን ለማገልገልና ለዚያም መከራ አስከመቀበል ለመትጋት ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ ለሚገባና እውነት ለሆነው ነገር መከራን መቀበል የሚገባ ነውና፡፡

በዓለም ያሉት ለውጦች ደግሞ ተጨባጭ ስለሆኑ ለእነዚህ እውነታዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ረገድ የሚኖረን ቁርጠኝነትም ከመለያየት ይልቅ ያቀራርባል፡፡ ያሉትን የለውጥ ሒደቶች፣ የክርስቲያኖችን በጎ ፍላጎት ካልካድን በስተቀር በእርግጠኝነት የአሠራር ማሻሻያዎችን የተጠየቅንበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ያሉት ሁኔታዎች እውነት ናቸውና ለእው ነት በእውነተኛ መንገድ ማገልገል አለብን፤ ሐዋርያው እንዳለው «በእውነት ላይ ምንም ለማድረግ አንችልምና፡፡» ስለዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ዛሬም ይሁን ነገ በግልና በቡድን በሚፈጸሙ የጨለማ ሥራዎች ሳይደናገጡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም ተገቢውን አሠራር  እውን ለማድረግ በረድኤተ እግዚአብሔር እንደሚንቀሳቀሱ እምነታችን ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው አሉ ብሎ ያስቀመጣቸውን በአመራሩና በአሰተዳደሩ የታዩ ችግሮችን ካልፈታና መፍታት የሚያስችሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነባቸው አሠራሮችን ለመዘርጋት ቁረጠኝነት ካጣ ቤተክርሰቲያን በሒደት ሊገጥማት የሚችለው ፈተና ማኅበረ ቅዱሳንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው በቤተ ክርስቲያኒቱ ተንሰራፍተዋል ያላቸውን የአሠራር ችግሮች ግልጽ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ቤተክርስቲያኒቱ በሁለት ተገቢ ባልሆኑ የአካሔድ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳትወድቅ ማኀበራችን  ስጋት አለው፡፡ አንደኛው ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው ግልጽ ያደረገው የውስጥ አሠራር ችግር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እነዚህን የአሠራር ችግሮች አጋኖ በማራገብ ቤተክርስቲያኒቱን በቅጥረኛነት ለማጥፋት የሚካሔደው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ከዚህ አጣብቂኝ ሌላ በሚኖሩ ኋላቀርና ብልሹ አሠራሮች በመመረር ምእመናን የተለያየ አደረጃጀት ፈጥረው በራሳቸው ማስተዋል በመንቀሳቀስ ለቤተክርስቲያን መከፋፈል ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም የያዝነውን ደካማ አሠራር የጠሉ በመንፈስ ያል ጠነከሩ ምእመናን ይሰናከላሉ፡፡ ሥራዎቻችንን ከሚሠሩበት መሥሪያ ቤት፣ ካላቸው ድርጅት ተሞክሮ፣ ከሌሎች አኀት አብያተ ክርስቲያናት ዕድገትና ግስጋሴ ጋር የሚያስተያዩት ደግሞ የአመራርና የአስተዳደር ዘይቤያችንን በመናቅ ይለዩናል፡፡ ከዚያም አልፎ የቤተክርስቲያኒቱ ቅርስ፣ ሀብትና አስተዳደር በአጽራረ ቤተክርስቲያን እጅ እስከ መያዝ ሊደርስ ይችላልና፡፡ ቤተክርስቲያን የማትሸነፍ ቢሆንም የብዙ ምእመናን ሕይወት መፈተኑ የማይቀር ይሆናል፡፡

ማኀበራችን ደግሞ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቤተክርስቲያን ይህ እንዳይገጥማት ነው፡፡ ስለዚህ ያሉ እውነታዎችን ያገናዘበ ችግር ፈቺ አሠራር እንዲዘረጋ ይፈልጋል፡፡ የምንጊዜም ፍላጎቱ ይህቺን ታሪካዊ፣ ሐዋርያዊና ቅድስት ቤተክርስቲያን ያሉአትን ትውፊት፣ ቅርስና አስተምህሮ ጠብቆ የሚያቆይ የአመራርና የአስተዳደር ሥርዓት እንዲኖራት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአቢዮት ሳይሆን ሓላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት በተገቢ ባለሙያዎች በተጠና መንገድና ከመቼውም ጊዜ በላይ በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡   

በመሆኑም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት አባቶች  ለዚህ ትውልድ የደረሰችው ቤተክርስቲያን ወሳኝ ባላደራነታቸውን ተረድተው ከቀደሙት አባቶቻቸው ቆጥረው ሰፍረው የተረከቡትን የቤተክርስቲያኒቱን መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብት ለተተኪው ትውልድ በአግባቡ ማስረከብ ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ኦርቶዶክሳዊና ዘመናዊ አስተዳደርን የማስፈን ሐላፊነታቸውን በሰከነና አሳማኝ በሆነ አካሔድ እንደሚፈጽሙ እምነታችን ነው፡፡ ይህንንም ስንል ያንን በማድረግ ሒደት የሚኖሩ የተለያዩ አስተያየቶችም አንዱን አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ አደርጎ ከማሳየት ይልቅ በየጊዜው ከሚኖሩ ለውጦች ጋር እየተፈተሹ የሚተገበሩ የአካሔድ ዓይነቶች ተደረገው መወሰድ እንዳለባቸው ከመጠቆም ጋር ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም ሕገ ማኅበሩን አጽድቆ የሥራ ፈቃድ የሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ እነዚህን ተፈላጊ የአሠራር ማሻሻያዎች ለማምጣትና ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሰጠው ሓላፊነት ካለ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ይገልጻል፡፡  

ማኅበራትና ሰንበት ትምህርት ቤቶችም አባቶቻችን የሚያደርጉአቸውን የለውጥ ምክክሮች በበጎ በመመልከት ለጊዜያችን የሚገቡና አላራመድ ላሉን ለቤተክርስቲያናችን ችግሮች መፍትሔ የሚሆኑ የአመራርና የአስተዳደር አቅም ግንባታ እንቅስቃሴዎቹ ተጨባጭ እስኪሆኑ ድረስ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጎን መቆማችን ተገቢ እርምጃ ነው፡፡ የአመለካከት ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን እነዚህን ሁኔታዎች እንደዕድል ተጠቅመው መለያየትና ማሰናከያን የሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖችን ለማስታገስ መረባረብ ይገባናል፡፡
በአጠቃላይ ምእመናን እግዚአብሔር አስቀድሞ የሰበሰባትን፣ ኋላም ከብዙ መከራ ታድጐ እዚህ ያደረሳትን ቤተ ክርስቲያን አሁንም እንዲጠብቅልን በጸሎት መቆም ይገባናል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኒቱን አመራር ለስብከተ ወንጌልና ለልማታዊ ተግባራት በሚመች መልኩ ለመቃኘት የሚያደርገውንም እንቅሰቃሴ እንድንደግፍ፤ ያንንም ለማኮላሸት የሚደረጉ ስውርና ግልፅ የሆኑ ሕገወጥ አካሔዶችን ሥርዓተ ቤተክርስቲያን በሚፈቅደው አግባብ ለማስቆም አንድንጥር ማኅበራችን ይጠይቃል፡፡
 
                                                             ወስብሐት ለእግዚአብሔር